
አዲስአበባ፡- የሸገር ከተማን የሚያካልለውና 155 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የቀለበት መንገድ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ አፈጻጸም 20 በመቶ መድረሱን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ጉግሳ ደጀኔ አስታወቁ። በከተማዋ ኢንቨስት ለሚያደርጉ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎች መፍጠሩንም አመልክተዋል።
የሸገር ከተማ ምክትል ከንቲባና የአስተዳደርና አገልግሎት ክላስተር አስተባባሪ አቶ ጉግሳ ደጀኔ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ የሸገር ከተማን የሚያካልለውና ለአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ መጨናነቅ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ ታሳቢ ተደርጎ እየተገነባ ካለው 155 ኪሎ ሜትር ውስጥ የመጀመሪያው ምዕራፍ 38 ኪሎ ሜትር የሚሆነው መንገድ አፈጻጸም 20 በመቶ ደርሷል።
የቀለበት መንገዱ የከተማውን ዙሪያ የሚያገናኝ 250 ሜትር ስፋት ያለው መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ከንቲባው፤ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ የትራፊክ ፍሰቱን ከማቃለል ባሻገር እንደሀገር ያለውን የመንገድ ደረጃም ከፍ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።
የከተማ አስተዳደር ለመንገዱ ግንባታ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መበጀቱን አስታውቀው፤ አጠቃላይ የመንገድ ግንባታውን በአምስት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። ይሁንና መንገዱ በሚያካልላቸው እንደ እንጦጦ ተራራ ያሉ አካባቢዎች ላይ ከመልክዓ ምድሩ አቀማመጥ አኳያ የግንባታ ጊዜውን ከፍ ሊያደርጉት እንደሚችሉ አስረድተዋል።
ከእዚሁ ጎን ለጎንም በከተማዋ የሚገኙ መንገዶችን ደረጃ የማሻሻልና ተጨማሪ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች የማስፋፋት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ከግንባታ ቆይታቸው አንፃር የተበላሹና አስቸጋሪ መንገዶችን መልሶ የመገንባት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ “አሁን ላይ ወደ 80 ኪሎ ሜትር አካባቢ የሚጠጋ መንገድ ከፊሉ እየተሠራ ነው” ብለዋል።
ከእነዚህ መንገዶች መካከልም ከሎክ 18 እስከ ኬላ ወይም ታጠቅ አካባቢ መልካኞኞ ክፍለ ከተማ እስከ ኬላ ድረስ ወደ 16 ነጥብ 5 የሚሆን ኪሎ ሜትር ግንባታ ተጠቃሽ እንደሆነ አብራርተዋል። በተጨማሪም ወደ 50 ሜትር ስፋት ያለው መንገድ እየተገነባ መሆኑን፤ እንዲሁም እስከ ሰበታ የሚደርሰው መንገድ ኮንትራት ተሰጥቶ ሥራ የመጀመር ሂደት ውስጥ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ከእዚህም ባሻገር ከኬላ እስከ ሱሉልታ፣ ከአዲስ አበባ ድንበር ጣፎ የሚሄዱ መንገዶች ፕላን ተሠርቶ መጠናቀቁን ምክትል ከንቲባው አመልክተዋል። “በአጠቃላይ መሠረተ ልማቶቹ ለከተማ አስፈላጊ ስለሆኑ ወደ መሬት የማውረድ፤ ውስጥ ለውስጥ ደግሞ ገባርና ብሎክን ከብሎክ ወይም መንደርን ከመንደር የሚያገናኝ መንገዶችን በተለያዩ ግብዓቶች የሚሠራ ወደ 380 ኪሎ ሜትር ግንባታ በአብዛኛው ተጠናቋል” በማለትም አብራርተዋል።
አያይዘውም ሸገር የወደፊቷ ስማርት ከተማ እንደ መሆንዋ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን መታቀዱን ጠቁመው፤ አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት ያንን የሚመጥኑ የሕግ ማሕቀፎችን ማዘጋጀቱን፤ እንዲሁም የአሠራር ሥርዓቶችን የማዘመን ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል። በተለይም ደግሞ አገልግሎቱን ወደ ኤሌክትሮኒክስ መንገድ (ኢ-ሰርቪስ) የመቀየር ሥራ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል። “የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ለማስጀመርም ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ፣ ከኢንሳና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ተቀናጅተን እየሠራን ነው” ብለዋል።
በእዚህም በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የኢንቨስትመንት ጥያቄ የሚስተናገድበትን ሥርዓት በኦንላይን እንዲሆን መደረጉን አመልክተው፤ ይህም ከእዚህ በፊት ይታይ የነበረው የሰው መጨናነቅና እንግልት ማስቀረት እንዳስቻለ አስረድተዋል።
“አሁን ላይ ኢንቨስተሩ የትም ቦታ ሆኖ በቀላሉ በኤሌክትሮኒክስ መንገድ ማመልከትና መስፈርቶቹን ካሟላ በቀጥታ ተቀባይነት የሚያገኝበት ሁኔታ ተፈጥሯል” በማለት አብራርተዋል።
በሌላ በኩል ሸገር ከተማ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አቅራቢያ የሚገኝ፣ ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚደረጉ የንግድ መስመሮች በሙሉ የሚያልፉበት፣ የባቡር መስመርና መሰል መሠረተ ልማቶቹ ያሉበት መሆኑ፤ እንዲሁም በርካታ ሕዝብ የሚኖሩበት መሆኑ ማንኛውም ኢንቨስትመንት ምቹ መሆኑን አብራርተዋል። በተጨማሪም ሰፊና ለልማት ምቹ የሆነ መሬት ያለበት አካባቢ መሆኑን አስታውሰው፤ “በከተማዋ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ መሠማራት የሚፈልግ ማንኛውም ባለሀብት ወደ ከተማችን እንዲመጣ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም