እ.አ.አ 1999 የስፔኗ ሴቪሌ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተካሄደ። በወቅቱ ኢትዮጰያን በወከለው ብሄራዊ ቡድንም በ10ሺ ሜትር ጀግናዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ በወሊድ ምክንያት አልተካተተችም ነበር። ነገር ግን ደራርቱ ስትጠራ ከጎኗ የማትለየው ኮማንደር ጌጤ ዋሚ ሀገሯን ወክላ አደራዋን ተቀብላ ነበር ወደ ስፔን ያመራችው። ከደራርቱ ጋር በመሆን በሚያሳዩት የቡድን ስራ እንዲሁም ከራሷ አሸናፊነት ይልቅ ለሀገሯ ቅድሚያ በመስጠት የምትታወቀው አትሌት ጌጤ ዋሚ በውድድሩ ዕለት ሀገሯን ወክላ ተሰለፈች።
በሩጫው የርቀቱን አብዛኛውን ዙር ስትመራ የቆየችው እንግሊዛዊቷ አትሌት ፓውላ ራድክሊፍ ውድድሩን የምታሸንፍ ትመስል ነበር፤ ሆኖም አራት ዙሮች ሲቀሯት መዳከሟን ያዩት ሁለቱ አትሌቶች ቀድመዋት ሮጡ። በእርግጥ ከሁለቱ አትሌቶች መሪነቱን የተረከበችው ኬንያዊቷ አትሌት ቴግላ ሎሩፔ አሯሯጥም አሸናፊነቱን ለራሷ የምታስቀረው ዓይነት ነበረ። የመጨረሻው ዙር ላይ ግን የተዳከመች የመሰለችው ራድክሊፍ ፍጥነት ጨምራ ወደፊት በመውጣቷ በድጋሚ ሌላ ልብ አንጠልጣይ ክስተት ተስተዋለ። በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ግን በአስደናቂ እርጋታ ትሮጥ የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት የሩጫውን ፍጥነት በመቆጣጠር በተመሳሳይ ብቃት ላይ ነበረች። ጥቂት መቶ ርቀቶች ሲቀሯት ግን በሚያስደምም ፍጥነት ማርሿን ቀይራ ወደፊት ተስፈነጠረች።
በተለመደው ኢትዮጵያዊ የአሯሯጥ ስልት ወደፊት የምትምዘገዘገዋ ጌጤን ለተመለከተ ሊያቆማት የሚችል ምድራዊ ኃይል ስለመኖሩ ያጠራጥራል። በፍጹም የአሸናፊነት ብቃት የርቀቱን የመጨረሻ መስመር ስትረግጥም ነጯን አትሌት በሜትሮች ልዩነት አስከትላ ዓለምን ባስደነቀ ፍጥነት ነበር። አንዱን ጀግና በሌላ ጀግና እግር በመተካት የምትታወቀው ኢትዮጵያ በወቅቱ ታዋቂ በሆነችበት በዚህ ርቀት በሴቶች አጠራጣሪ የነበረውን ድልም ጌጤ 30:24.56 የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ ሀገሯ የለመደችውን ስኬት ማስገባት ችላለች። የገባችበት ሰዓት ደግሞ የአፍሪካ እና የውድድሩ ክብረወሰን በመሆኑም የድርብ ክብር ባለቤት እንድትሆን አስችላታል። ጌጤ በዚያው ዓመት በተካሄደው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ላይም በተመሳሳይ ርቀት የድል ባለቤት በመሆኗ ዓመቱን በብቃትና በስኬት ነበር ያሳለፈችው።
ጌጤ ቀጣዩ ዓመት የኦሊምፒክ ዓመት በመሆኑ ብቃቷን ይበልጥ አጠናክራ እንደለመደችው ሃገሯን ለማኩራት በሲድኒ ተካፍላለች። በመገናኛ ብዙሃን በብዛት የማትታየው የአስደናቂ እርጋታ እመቤቷ ጌጤ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት ወርቃማ ዘመን በሚባልበት ወቅት ከነበሩት አትሌቶች መካከል ተጠቃሽ ናት። በ1966ዓ.ም በደብረብርሃን ጫጫ ከአባቷ አቶ ዋሚ ደግፌ እና ከእናቷ ወይዘሮ ዘነበች ወንድሙ የተወለደችው የኢትዮጵያ ጌጥ የአትሌቲክስ ህይወትን ክለብ በመግባት የጀመረችው በ1982 ዓ.ም ነበር። የያኔዋን ወጣት አትሌት ተስፋ በመመልከት የተረከባት ደግሞ የኦሜድላ (የፌዴራል ፖሊስ) ስፖርት ክለብ ነበር።
ብርቱዋ አትሌት በ1ሺ500 ሜትር ተሳትፎዋ በሀገር አቀፍ ውድድሮች ብቃቷን ከማስመስከር አልፋ፤ እአአ በ1992 የዓለም ወጣቶች ቻምፒዮና እንዲሁም በ1995 የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ሀገሯን ለማኩራት በቃች።
በዚህም ዋናውን ብሄራዊ ቡድን በመቀላቀል እአአ በ1996 የአትላንታ ኦሊምፒክ ተሳታፊ ልትሆን ቻለች። ከአራት ዓመት በፊት የባርሴሎና ኦሊምፒክ አሸናፊዋ የሀገሯ ልጅ ደራርቱ ቱሉ በርቀቱ ዳግም የድል ባለቤት ትሆናለች በሚል ብትጠበቅም አልሆነላትም ነበር። በወቅቱ ይህንን የኢትዮጵያውያን ድንጋጤ የነሃስ ሜዳሊያ በማጥለቅ የመለሰችው ጌጤ ነበረች። ሀገር ወዳዷ አትሌት በሜዳሊያ ብዛት እስካሁን አቻ ባልተገኘለት ቀጣዩ የሲድኒ ኦሊምፒክም በ10ሺ ሜትር ብር በ5ሺ ሜትር ደግሞ ነሃስ በማግኘት የሁለት ሜዳሊያዎች ባለቤት መሆን ችላለች።
እአአ የ1996 እና 2001 የዓለም ሀገር አቋራጭ ቻምፒዮና አትሌት ከመም ውድድሮች ባሻገር በጎዳና ላይ ሩጫዎችም አስደናቂ ድሎችን የግሏ ማድረግ ችላለች። እአአ ከ2000 ወዲህ ወደ ማራቶን የገባችው ጌጤ በአምስተርዳም፣ በርሊን(ሁለት ጊዜ)፣ ኒውዮርክ፣ ሳንዲያጎ ማራቶኖችን ጨምሮ በበርካታ ውድድሮች አሸናፊነትን ተቀዳጅታለች። ጌጤ ከስፖርቱ ዓለም ከራቀች በኋላ ለዓመታት ከስፖርት ቤተሰቡ እይታ ጠፍታ ከቆየች በኋላ በድጋሚ በተለያዩ ስራዎች ዳግም አትሌቲክስን ተቀላቅላለች። በዚህ ወቅትም የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበርን በማገልገል ላይ ያለች ሲሆን፤ ከትናንት በስቲያ ደግሞ ‹‹የኢትዮጵያ ጌጥ›› በሚል ርዕስ የህይወት ታሪኳን የሚተርክ መጽሐፍ አስመርቃለች። ከመጽሐፉ የሚገኘውን ገቢ ሙሉ ለሙሉ ለበጎ አድራጎት ዓላማ በማዋልም ለበርካቶች አርዓያ እና ምሳሌ በመሆንም ቀጥላለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2015