በኢትዮጵያ አትሌቲክስ አንጋፋውና ትልቁ የውድድር መድረክ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና በመጪው ሳምንት መጀመሪያ ይካሄዳል። በውድድሩ ላይ ታዋቂ አትሌቶች የሚካፈሉ ሲሆን፤ ለዓለም አቀፍ ውድድሮች መዘጋጃና ማጣሪያ እንደሚሆንም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
ከ1963 ዓ.ም አንስቶ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ፌዴሬሽኑ ከሚያዘጋጃቸው ዓመታዊ ቻምፒዮናዎች መካከል ትልቁ ነው። ሃገራቸውን በዓለም አቀፍ መድረክ ያስጠሩ በርካታ አትሌቶች የፈሩበት ይህ ውድድር ዘንድሮ ለ52ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ይካሄዳል። በሩጫ እና በሜዳ ተግባራት ውድድሮች የሚካሄደው ይህ ቻምፒዮና ከግንቦት 08-13 ይካሄዳል። ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ክለቦች እና የማሰልጠኛ ማዕከሎችም ምርጥ አትሌቶቻቸውን የሚያሳትፉ ይሆናል።
ቻምፒዮናው የውድድር ዕድል ከመፍጠርና ተተኪ አትሌቶች ከማፍራት ባለፈ ለዓለም አቀፍ ውድድሮች መዘጋጃ እና ማጣሪያ እንደሚሆንም ፌዴሬሽኑ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። በርካታ ታዋቂ አትሌቶች የሚካፈሉበት ይህ ውድድር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚሳተፉባቸው የግል ውድድሮቻቸው አቋማቸውን የሚለኩበት መድረክም ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ባለፈ ከወራት በኋላ በሃንጋሪ ቡዳፔስት ለሚከናውነው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሃገራቸውን በ10ሺ ሜትር የሚወክሉ አትሌቶች የሰዓት ማጣሪያ ለማድረግ የሚመረጡበት ቅድመ ውድድር እንደሚሆንም ታውቋል። በዚህም በሰረት በርቀቱ በሁለቱም ጾታዎች ከ1-8 የሚወጡ አትሌቶች ብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ ለመካተት በሚከናወነው የሰዓት ማጣሪያ ውስጥ የሚገቡበትን እድልም ያመቻቻል።
11ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም 30 ክለቦችና የማሰልጠኛ ተቋማት የሚካፈሉበት ቻምፒዮናው፤ በወንድ 743 እንዲሁም በሴት 527 በጥቅሉ 1ሺ270 አትሌቶች ይፎካከሩበታል። ለስድስት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው በዚህ ቻምፒዮናም ቀድሞ የሚካሄድበት የአዲስ አበባ ስታዲየም በእድሳት ላይ በመሆኑ ወደ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሊዘዋወር ችሏል። ይሁንና አካዳሚው ለሜዳ ተግባራት ውድድሮች ምቹ ባለመሆኑ ፌዴሬሽኑ ለማስተካከል መሞከሩን እንዲሁም የውርወራ ውድድሮችን በሌሎች አማራጭ ሜዳዎች የሚያደርግ መሆኑንም አስታውቋል። በሌላ በኩል በሴቶች የምርኩዝ ዝላይ ውድድር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚካሄድም ተገልጿል።
በሃገር ውስጥ በሚካሄዱ ቻምፒዮናዎች ታዋቂ አትሌቶችን ማየት እምብዛም የተለመደ ባለመሆኑ ከበርካቶች ቅሬታ ሲቀርብ ተስተውሏል። በዚህ ውድድር ግን ከ20 በላይ ዝነኛ አትሌቶች ተካፋይ እንደሚሆኑ ክለቦቻቸው አስታውቀዋል። ከእነዚህም መካከል በወንድ የፌዴራል ማረሚያ ስፖርት ክለብ አትሌቶቹ ሰለሞን ባረጋ፣ ኋይለማርያም አማረ፣ ጥላሁን ኋይሌ፣ ከመቻል ሙክታር እድሪስ እና ሳሙኤል አባተ፣ ሲዳማ ቡና ጌትነት ዋለ፣ ኤርሚያስ ግርማ፣ ከኦሮሚያ ፖሊስ ለሜቻ ግርማ እና ቦኪ ድሪባ፣ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በሪሁ አረጋዊ፣ ታደሰ ወርቁ፣ ሃጎስ ገብረህይወት እና ሞገስ ጥኡማይን የመሳሰሉ አትሌቶች ይጠቀሳሉ።
በሴቶች ደግሞ ከትራንስ ለተሰንበት ግደይ፣ ከፌዴራል ማረሚያ አክሱማዊት እምባዬ፣ ሰንበሬ ተፈሪ፣ ሲዳማ ቡና ዘርፌ ወንድም አገኝ፣ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ሃብታም አለሙ፣ ሂሩት መሸሻ፣ ጽጌ ገብረሰለማ፣ ግርማዊት ገብረእግዚአብሄር፣ ያለምዘርፍ የኋላው፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብርቄ ኃየሎም፣ ከአማራ ማረሚያ መቅደስ አበበ፣ ቦሰና ሙላቴ፣ ዳዊት ስዩም እና ወርቅውሃ ጌታቸው በቻምፒዮናው ተካፋይ እንደሚሆኑ ተረጋግጧል። በዚህም ተተኪ አትሌቶች ልምድ በማግኘት እንዲሁም ትልቅ ብቃት ላይ ከደረሱት አትሌቶች ጋር የመፎካከር እድልን ያገኛሉ።
በቻምፒዮናው የተለያዩ ስራዎች የሚያከናውኑ ባለሙያዎች የተዘጋጁ ሲሆን፤ የዓለም አትሌቲክስ የዳኝነት ምስክር ወረቀት ያላቸው 80 ዳኞች ውድድሩን ይመራሉ። በውድድሩ ወቅትም በአትሌቶች ላይ የአበረታች ንጥረ ነገር ናሙና መውሰድ እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብሮች የሚኖርም ይሆናል። በግል ከ1-3 ለሚወጡ እንዲሁም በቡድን አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶችም የሜዳሊያ፣ የዋንጫ እና የገንዘብ ሽልማት የሚበረከትላቸው ይሆናል። በአጠቃላይ በዚህ ቻምፒዮና ከ2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የተመደበ መሆኑም ታውቋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2015