ፅንፈኝነት በብሔር፣ በሃይማኖት ወይም በቡድን ላይ ተመሥርቶ የሚነሳ ፤ የአመፅ እና የሽብር መንስኤ እንደሚሆን የዓለም የፖለቲካ ጸሐፍት ይገልጹታል። አንድን ሀገር እስከመፍረስ ከሚያደርሱ ምክንያቶች መካከል አንደኛው እንደሆነም እንዲሁ ።
ፅንፈኝነት ማለት ምን ማለት ነው ከሚለው ጀምሮ በትክክል ፅንፈኝነት በኢትዮጵያ አለ? ካለ መታየት የጀመረው መቼ እና በምን ምክንያት ነው? አደጋው እስከምን ይዘልቃል? በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ በአማራ ክልል የተፎካካሪ ፓርቲዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ ጋር ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- ፅንፈኝነት ማለት ምን ማለት ነው ከሚለው ብንጀምር ?
አቶ ተስፋሁን፡- ፅንፈኝነት የተለያየ ትርጉም አለው። ነገር ግን በዋናነት የሚጠቀሰው መለያየትን፣ በደልን፣ በቀልንም የሚያጠነጥን የጥላቻ ጥግ ማለት ነው። ፅንፈኝነት ካለ መነጋገር፣ መደራደር እና መስማማት የሚባል ነገር የለም። ፅንፈኝነት ሕግ ደንብ መመሪያ አያውቅም። ሕጉ የራሱ ፍላጎት ብቻ ነው። በከፍተኛ ጥላቻ ላይ በማውጠንጠን የራስን ፍላጎት ብቻ መሠረት ያደረገ ነው። አንዳንዱ የራሱን ፍላጎት መሬት ለማስነካት የትኛውንም ዓይነት እርምጃ ይወስዳል።
አክራሪነት ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ነው፤ ወደ ፖለቲካው የሚያዘነብል እጅግ በጣም ሰፊ የሆነ ጉዳይ ነው። በዋናነት ግን አንድ ሰው ፅንፈኝ የሚያሰኘው ትኩረት የሚያደርገው በደል፣ ጥላቻ፣ በቀል እና መለያየት ላይ ሲሆን ነው። ፅንፈኝነት ሲኖር የሠላም ድርድር የለም። አንዱ ሌላውን ማጥፋት አለበት። ፅንፈኝነት ደም በማፍሰስም ቢሆን አሸናፊ መሆን የሚፈልግ ነው፤ ይህን ለማድረግ ግብረገብነት፣ መቻቻል እና መከባበር የመሳሰሉትን ጉዳዮች ረግጦ የሚሔድ ነው። በዋናነት ግን ከበደል፣ ከቂምም ሆነ ከሌላው በመነጨ በወሰን አልባ ጥላቻ የራስን ፍላጎት ማስፈፀም መፈለግ ነው።
ሕጋዊ ውክልና ሳይኖራቸው ውክልና እንዳላቸው በማስመሰል ቅቡልነት ለማግኘት የሚጥር ነው። በኢትዮጵያ ፅንፈኝነት አለ። የተበደልኩት እኔ ብቻ ነኝ የሚል አለ። የኔ ሃሳብ ብቻ ነው ትክክል የሚል አለ። ከእኔ ሃሳብ ውጪ የሚራመድ አካል መኖር የለበትም የሚሉ አሉ። ይሄ ማለት ያለምንም ጥያቄ ፅንፈኝነት እና ፅንፈኞች አሉ ማለት ነው። ይህ ማለት ግን ፅንፈኛ ሕዝብ አለ ማለት አይደለም። ሕዝብ እንደሕዝብ ፅንፈኛ ሊባል፤ ሊሆን አይችልም። በአንድ ብሔር ውስጥ የተወሰኑ ቡድኖች ፅንፈኛ ሊሆኑ ይችላሉ።
አዲስ ዘመን፡- ፅንፈኝነት አለ ካሉ፤ በኢትዮጵያ መታየት የጀመረው መቼ ነው?
አቶ ተስፋሁን፡- ደርግ ከመውደቁም በፊት ሆነ ደርግ ከወደቀ በኋላ ተበድያለሁ የሚል አለ። የፖለቲካ ጥያቄ አለ። ጥያቄዬ አልተመለሰልኝም የሚሉ አሉ። የኔ ማኅበረሰብ ተጨቁኗል የሚሉ ማቀንቀኖች ነበሩ። ነገር ግን እነኚህ የፖለቲካ ጥያቄዎች አሁን ላይ ጫፍ እየወጡ፤ ጥግ ድረስ እየሄዱ ናቸው።
እኩልነት የለም፤ እኔ በደል አለብኝ የሚሉ ጥያቄዎች ልካቸውን አልፈው የመጨረሻ ጥላቻ ላይ ደርሰዋል። ጥላቻ ካለ ደግሞ በተቃራኒው ያለውን በጠላትነት የመፈራረጅ ሁኔታ አለ። በሌላ በኩል ደግሞ ለዛሬም ሆነ ለነገ፤ ትክክል እኔ ያልኩት ብቻ ነው፤ የሚል ነገር አለ። ይህ አስተሳሰብ ከፖለቲካ ፓርቲዎች መመሥረት ጋር ተያይዞ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ጫፍ ይዘው መጥቷል ።
ፅንፈኝነት የብሔር ፓርቲ እየተመሠረተ ሲሔድ እጅ እግር ኖሮት ሥርዓት እና ቅርፅ ይዞ የመጣው ከደርግ ጊዜ ጀምሮ ነው። አሁን እዚህ እና እዛ ተበድያለሁ የሚሉ ጥያቄዎች ከልክ በላይ ተለጥጠው ወሰን አልፈው ለመቻቻል፣ ለመነጋገር እና ለድርድር ምንም ዓይነት ቦታ ሳይኖራቸው አንዱ ሌላውን በማጥፋት ላይ፤ አንዱ ሌላውን በመደምሰስ ላይ ሙሉ አሸናፊ ለመሆን ሲባል ወደ ፅንፈኝነት ተደርሷል ።
የፖለቲካ አሸናፊነት የአንድ አካል ብቻ ሳይሆን ሰጥቶ በመቀበል የሁለቱም አካል አሸናፊነት፣ አብሮ መኖር እና መቻቻልን የያዘ ቢሆንም እነዚህን ነገሮች የሆነ ሳጥን ውስጥ ቀብረው ‹‹እኔ ብቻ አሸናፊ መሆን አለብኝ፤ ካላሸነፍኩ አልቀመጥም›› በሚል፤ በደም የመመለስ ፍላጎት እየታየ መጣ። አሁን ደግሞ እንደሚታየው እየሆነ ነው።
ሶሻሊዝምም ሆነ ሌላ፤ ወይም ግራ ዘመምም ይሁን ቀኝ ዘመም፤ እዚህች አገር ውስጥ የኔ የፖለቲካ ርዕዮት ዓለም እንጂ ከዛ ውጪ መኖር የለበትም የሚል ካለ፤ በንግግር እና በውይይት ርዕዮተ ዓለሙ እንደሚጠቅም መናገር ካልቻለ እና ከእርሱ ውጪ ሌላ መኖር የለበትም ብሎ ካመነ ወደ ፅንፈኝነት ሄደ ማለት ነው። ይሄ ደግሞ እየታየ ነው። መገዳደል ላይ ተደርሶ አይተናል።
እኔ የማራምደውን ሃሳብ አላራመደም፤ የኔን ፍላጎት አያሟላም እና የኔን ሃሳብ አይቀበልም ስለዚህ መኖር የለበትም፤ የሚል ከፋፋይ ሃሳብ ሲመጣ ፅንፈኝነት መጣ ማለት ነው።
የእኛን ቅዱስ ቅዱስ እያልን፤ የእነርሱ እርኩስ እርኩስ ካልን የእኛ እና የእነርሱ እያልን ከተናጨን ፅንፈኝነት አለ። ይህ ከኋላ ታሪክ ጀምሮ በፖለቲካ ርዕዮት ዓለምም ሆነ በብሔር መልክ ሲታይ ነበር። አሁን ደግሞ የብሔር መልክ የያዘ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ፅንፈኝነት አደገኛ አስተሳሰብ ከመሆኑ አንጻር በኢትዮጵያ ለምን ተከሰተ?
አቶ ተስፋሁን፡- ኢትዮጵያ አምባገነን መንግሥት አስተናግዳለች። አምባገነን መንግሥት ካለ በደል ሊኖር እንደሚችል ምንም የሚያጠያይቅ አይደለም። ነገር ግን የፖለቲካ በደል ካለ በፖለቲካ ይመለሳል። እኔ ብዙዎች እንደሚሉት የምጋራው የፅንፈኝነት መነሻ ምክንያት የፖለቲከኞች አቅም ማነስ ነው። አቅም ሲያንሳቸው ድጋፍ ለማሰባሰብ ወደ ፅንፈኝነት ያዘነብላሉ።
በተጨማሪ ፅንፈኝነት ታሪክን በአግባቡ ካለማወቅ ብቻ ሳይሆን አሸናፊ ለመሆን ብቻ በማሰብም ምክንያት የመጣ ነው። በኢትዮጵያ መሸነፍ እና ማሸነፍ ፖለቲካ አይደለም። ከተሸነፍኩ ምን አጣላሁ ካሸነፍኩ ምን አገኛለሁ? የሚል ዕሳቤን ብቻ ስናራምድ ስለነበረ ፅንፈኝነት እየተስተዋለ ነው።
በሌላ በኩል ፖለቲከኞች እንወክለዋለን የሚሉትን ያንን ፍላጎታቸውን ለማሳካት ስስ የሆኑ ነገሮችን መፈለግ እና በዛ ሂደት ውስጥ የራስን ፍላጎት ለማስፈፀም መጣር ነው። ስለዚህ እኔ የማምነው ፅንፈኝነት የፖለቲከኞች እና የመሪዎች የብቃት ማነስ ነው። እናም የፖለቲካ ሥልጣንን ለመቆጣጠር አቋራጭ መስመር መጠቀም ነው።
የራስን አስተሳሰብ የሚቀበል ሰይጣንም ቢሆን ቅዱስ ነው። የሚቃወም ካለ ደግሞ እርኩስ ነው። ይህ ከምክንያታዊነት መውጣት ነው። ሰው እንዲህ ነው መባል ያለበት በብቃቱ ተመዝኖ ሊሆን ሲገባ፤ በተቃራኒው የራስ ወገን የሆነውን ብቻ ማስጠጋት ነው። ሌላው የተቃራኒ ወገን እንደሆነ ስለሚታሰብ ነው።
ፅንፈኝነት መደቡ እኔ ወይም እኛ የሚለው ነው። እውነቱ ያለው እኔ ጋር ብቻ ነው፤ እኔ ብቻ ያልኩት ትክክል ነው፤ ፍትሕ ያለው እኔ ጋር ብቻ ነው ማለት ነው። አንደኛው እኔ ተበድያለሁ፤ በሌላ በኩል ደግሞ እኔ ካልሆንኩ ሞቼ እገኛለሁ የሚል ነው።
የፖለቲካ ሜዳ ውስጥ አሸንፎ ለመገኘት የትኛውንም መጫወቻ ካርታ መምዘዝ ማለት ነው። ከሀገር ይልቅ የሆነ ሰፈር ወይም ጎጥን ማስቀደም ነው። በሀገር ወይም በሕዝብ ደረጃ ፅንፈኝነት አይኖርም።
ፅንፈኝነት በባህሪው ደካማ በመሆኑ ሥርዓተ መንግሥትን የመቆጣጠር አቅም የለውም።
ምክንያቱም ፅንፈኝነት ሙሉ ተቀባይነት ሊያገኝ አይችልም። ከፅንፈኝነት የሚወለደው ሽብርተኝነት ነው። በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት፣ በመነጋገር በመቻቻል ሊሳካ የማይችል ፍላጎት ሲሆን ሽብር ወደ ማምጣት ይገባል። ይህ ሰፋ ያለ ፅንሰሃሳብ ሲሆን መንግሥታዊ ሥልጣንን ለመቆጣጠር ያለው ዕድል አናሳ ነው። ምክንያቱም የሚራመደው በሕዝብ ሳይሆን በተወሰነ ቡድን ነው። ይህ የብሔር ወይም የርዕዮተ ዓለም ስም ሊኖረው ይችላል።
የሚቀነቀነው ግን በተወሰነ ቡድን ነው። ነገር ግን በዓለም እንደታየው ፅንፈኝነት ከጋራ አሸናፊነት ይልቅ ለብቻዬ አሸናፊ ልሁን የሚል ሲሆን፤ ጥፋት እና ውድመት የሚያስከትል ነው። አለመረጋጋት ያስከትላል። የሕዝብን አንድነት እና አብሮ የመኖር ባሕልን ይሸረሽራል። ምክንያቱም ፅንፈኞች አብሮነትን ብቻ ሳይሆን ማስተዋልን ይነጠቃሉ። የሆነ የሠፈር ሳጥን ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ከዛ በዛች ሰፈር ታጥረው የሚያቀነቅኑት ሃሳብ ውስን ቢሆንም ብዙዎችን የሚያጠፋ መርዝ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- የፅንፈኝነትን ምክንያት፤ ወይም ፅንፈኛ የምንለው ፖለቲከኛውን ብቻ ነው። ፖለቲከኛው የፅንፈኝነት ሃሳብን ይዞ ሲመጣ፤ ለምን ተከታይ ሕዝብ ያገኛል? እዚህ ላይ የሕዝብስ ንቃተ ሕሊና መታየት የለበትም?
አቶ ተስፋሁን፡– ሕዝብ ትክክል ነው ተብሎ ስለሚታመን ሕዝብ አይተችም። ነገር ግን ፖለቲካ
ደግሞ የማኅበረሰብ ንቃተ ሕሊና ድምር ነው። ስለዚህ የነቃ እና የበቃ ማኅበረሰብ ፅንፈኝነትን አያስተናግድም። አንዳንዴ ከፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን ፅንፈኝነት ከማኅበረሰብም ሲመጣ ይታያል። ነገር ግን የነቃ ማኅበረሰብ ፅንፈኝነት ቢታይ እንኳ የሚገስፅበት፣ የሚያርምበት እና የሚያስተካክልበት መንገድ ሠፊ ነው።
ፖለቲካ የንቃተ ሕሊና ደረጃ ነው። የነቃ የበቃ ማኅበረሰብ ጥሩ የሆነ የፖለቲካ ባሕል ይኖረዋል። ስለዚህ የፖለቲካ ባሕላችን በጊዜ ሂደት እያረመው ስለመጣ እንጂ በኢትዮጵያ ፅንፈኝነቶች እንደመታየታቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ የንቃተ ሕሊና ከፍ ባይል ኖሮ ኢትዮጵያ እንደሀገር አትቀጥልም ነበር።
በሀገሪቱ ያልተቀነቀኑ የጥላቻ ጥጎች የሉም፤ ፅንፈኝነት ከማቆጥቆጥ አልፎ በተግባር ታይቷል። እንደፅንፈኞች ሃሳብ ቢሆን ኖሮ ሀገራችን ሀገር ሆና አትቀጥልም ነበር። ብዙ ቦታ በተከፋፈለች ነበር። ይህ እንዳይሆን ያስቻለው የሕዝብ ንቃተ ሕሊና ጥሩ በመሆኑ ነው። ጉዳቱን መቀነስ ተችሏል፡፤
አዲስ ዘመን፡- በእርግጥ የፅንፈኝነትን ጉዳት መቀነስ ተችሏል? በእርሶ እምነት አሁን በኢትዮጵያ ፅንፈኝነት በምን ደረጃ ላይ ነው ማለት እንችላለን?
አቶ ተስፋሁን፡- እኔ ፅንፈኝነት የሀገረ መንግሥቱ ስጋት ነው የሚል እምነት የለኝም። ነገር ግን በትንሹ ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዳይገቡ እያደረገ ነው የሚለው የሚካድ አይደለም። ምክንያቱም ዜጎች በማንነታቸው ሲፈናቀሉ እየታየ ነው። ይሔ የኔ ብቻ ነው የሚል እና ሌላውን አግላይ የማድረግ ሁኔታ አለ። ከእኛ ወይም ከእኔ ውጪ ለምን ሌላ ሃሳብ ታራምዳለህ በሚል መገዳደሎችም ነበሩ። ቢሆንም ግን ተስፈኞች ስለሆንን ወደፊት ነገሮች ይስተካከላሉ ብለን ስለምናምን አያስጨንቅም።
ነገር ግን አንድ ሃሳብ ምንም ሆነ ምን ተቀባይነት ሊያገኝ እና ረዥም እድሜ ሊኖረው የሚችለው ዘላቂ ተቀባይነት ሲያገኝ የበላይ ይሆናል። መለያየትን እና ጥላቻን ማቀንቀን የትም እንደማያደርስ እያየን ነው። ከመነጣጠል ይልቅ አብሮ መኖር እኔ ብቻ ላሸንፍ ከማለት ይልቅ የሁለቱም ወገን አሸናፊነት (ዊን ዊን)ን መቀበል ይገባል። መንግሥትም የሚቀበለው መቻቻልን ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ መንግሥታዊ ኃላፊነት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በፅንፈኝነት ምክንያት ኢትዮጵያ እስከ አሁን ምን አጣች?
አቶ ተስፋሁን፡– የኢኮኖሚ እድገት ሰላም እና ደህንነት ይፈልጋል። የሥራ ዕድል እና የተስተካከለ ኢኮኖሚ ሳይኖር ሰላም አይኖርም። የተስተካከለ ኢኮኖሚ እንዲኖር ፖለቲካው መስተካከል አለበት።
ሰላም እና ደህንነት ከሌለ ኢኮኖሚው አያድግም፣ ኢኮኖሚው ካላደገ ፖለቲካው አይስተካከልም፤ እነኚህ ነገሮች በአብዛኛው የሕዝብ እና የመንግሥት ትኩረት ልማት ላይ እንዳይሆን ያደርጋሉ። ለምሳሌ ዜጎች ጠዋት ወጥተው በሰላም ስለሥራቸው ከሚያስቡ ይልቅ ዛሬ ማን ተገደለ፤ የትኛው መንገድ ተዘጋ በሚሉ ሃሳቦች አዕምሮቸው እንዲያዝ ይሆናል። ይህ ደግሞ ያለምንም ጥያቄ ኢኮኖሚውን ይጎዳል። ያለምንም ጥያቄ አምራች ኃይሉ ባልሆነ ሃሳብ ተጠልፎ ምርታማ እንዳይሆን ያደርገዋል።
ከዛ ባለፈ ከምንም በላይ ሰላም ነው። አሁን በግልጽ ዜጎች በማንነታቸው ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ተቸግረዋል፤ አልፎ ተርፈው ሲሞቱ እየታየ ነው። ይህ ጉዳት ነው። ይሄ በጊዜ አደብ እንዲይዝ እና እንዲስተካከል ካልተደረገ በተራዘመ ሂደት ውስጥ የኢኮኖሚ ቀውስ ያመጣል።
ጽንፈኝነት አሁንም ብዙ ችግሮችን እያስከተለ ነው። ሀገር እንደሀገር የምትቀጥለው የተጠናከረ ሥርዓተ መንግሥት ሲኖራት ነው። የዜጎች ሰላም እና ደህንነት ተጠብቆ በመቻቻል እና ሰጥቶ በመቀበል አብሮ መኖር ሲቻል ነው ። በተቃራኒው አንዱ ሌላውን ማጥፋት ከሆነ ሀገር እንደሀገር መቀጠል አትችልም። ከዚህ አንጻር ለችግሩ ፈጣን መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል፤ ዘላቂ መፍትሔ ልናገኝለት ካልቻልን ሊያሳጣን የሚችላቸው ነገሮች ብዙ ይሆናሉ የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ፅንፈኝነት ማኅበራዊ ትስስርን እና አጠቃላይ ግንኙነትን እንደሚጎዳ ይገለፃል። ይህ ምን ያህል አደገኛ ነው?
አቶ ተስፋሁን፡- ፅንፈኝነት ማኅበራዊ ግንኙነትን በሰፊው የሚጎዳ ነው። ኦሮሞ ከአማራ፣ አማራው ከሶማሌ፣ ከትግሬ ሁሉም የተጋባ እና የተጋመደ መሆኑ የታወቀ ነው። ጫፍ ሲደርስ ይህንንም ይሸረሽራል፤ ይንዳል። ሀገር ይበትናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለሆነ እንጂ፤ ሕዝቡ ብዛት ባላቸው እሴቶቹ የተጋመደ በመሆኑ እና ዝም ብሎ በውስን ፅንፈኞች ባለመመራት እንጂ የተሠራው እኮ ማኅበረሰብን በሚንድ መልኩ ነው።
ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔሮች አሏት። ስለዚህ ከእኛ በላይ ማንም የለም የሚሉ የብሔር ፅንፈኞች ከመጡ ሀገር ይንዳሉ። ይህ መታወቅ አለበት። ፅንፈኝነት እንዲጠበቅ እና እንዲጠብቅ የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት እንዳይቀጥል፤ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንዳይቀጥል፤ እኔ ብቻ የሚል ካለ፤ በየትኛውም አገር ውስጥ አንዱ በዳይ ሌላው ተበዳይ አንዱ ጨቋኝ ሌላው ተጨቋኝ ከሆነ እና ፍትሕ ካልሰፈነ ሀገር እንደሀገር አይቀጥልም። ይህ ስጋት ነው።
እኔ ብቻ ተበድያለሁ በሚል በቀል ካለ፤ ትናንትን በማሰብ ቅራኔን በማጮህ ቅራኔን ከተገቢው በላይ በማክረር እና በመለጠጥ ቅራኔ ፅንፈኝነትን በማዋለድ፤ ፅንፈኝነት ደግሞ ከላይ በገለፅኩት መሠረት ሀገር ሰላም እንዳይኖራት፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዳይኖር እና ማኅበራዊ እሴቷ እንዲበጠስ የሚያደርግ ነው። ስለዚህ ለአገር ጠንቅ ነው። ደግነቱ እነኚህ ሃሳቦች በኢትዮጵያ ውስጥ እንብዛም ተቀባይነት ስለማይኖራቸው ለተወሰነ ጊዜ ሰላምን ከማስተጓጎል እና የኢኮኖሚ ዕድገትን ከማጎሳቆል ያለፈ ሚና አይኖራቸውም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመለያየት ይልቅ አብሮ መኖርን የሚፈልግ ነው። በዛ አግባብ መታየት ያለበት ነው። የፖለቲካ ገበያው ደግሞ አሁን ላይ የሚፈልጋቸው አይደሉም። አሁን አንዱ የበላይ አንዱ የበታች ብሎ ነገር የለም። አሁን የእኩል ተጠቃሚነት እና የፍትሐዊነት ጉዳይ ብቻ ነው። ትናንት እንዲህ ነበር በሚል ታሪክ ላይ ተመርኩዘን የጦርነት አውድማ አንፈጥርም።
ኢትዮጵያ ዓለም የደረሰችበት ላይ እንድትደርስ እንጂ እኔ ብቻ የሚል ሃሳብ ይዞ መንቀሳቀስ ብዙ ርቀት አያስኬድም። የዓለም አገራት እንኳ ከመለያየት ይልቅ አብሮ መኖርን በመረጡበት ዘመን፤ የመፍትሔ ሃሳቦችም የሚገኙት አብሮ ከመኖር እንጂ ከመነጠል አለመሆኑ መታወቅ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ፅንፈኝነት እያቆጠቆጠም ሆነ እያደገ በየትኛውም መንገድ የሀገር አጥፊ በመሆኑ መገታት አለበት። እንዲገታ ማን ምን ማድረግ አለበት?
አቶ ተስፋሁን፡- መንግሥት እንደመንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት መቻል አለበት። ፅንፈኝነት በባሕሪው ደም አፋሳሽ ነው። ስለዚህ ደም እንዳይፈስ መንግሥት ግዴታዎችን መወጣት አለበት። የፖለቲካ ምሑራን የተባልን ነገን ማሰብ መቻል አለብን። የግል ፍላጎትን ከሀገር ጥቅም እና ከሀገር አንድነት ጋር ማወዳደር ውርደት እና ውድቀት ነው።
ስለዚህ ውድድራችንን ሃሳብ ላይ ማድረግ አለብን። ሰጥቶ መቀበል መነጋገር መቻቻል የሚባሉትን መርሐችን እናድርጋቸው። በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የጋራ አቋም ይኑረን። ኢትዮጵያ እንደሀገር እንድትቀጥል ሁላችንም አስተዋፅዖ እናድርግ። በሌሎች ጫማ ውስጥ ሆነን ሌሎችን እንረዳ። ከእኛ በተቃራኒው ያሉ ካሉ ችግራቸው ምን እንደሆነ እናዳምጥ፤ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን ከበቀል ይልቅ ይቅር ባይነትን አድርገን ትልቋ ስዕላችን ኢትዮጵያን ማድረግ አለብን። ሶሻሊስትም ሆንን ካፒታሊስት፣ ግራ ዘመምም ሆንን ቀኝ ዘመም ዓለም በዘመነበት መንገድ መሔድ መቻል አለብን።
የታሪክን ጠባሳና ቁርሾ ለታሪክ እንተወው፤ ይገባናል ፖለቲካ ከታሪክ ይቀዳል፤ ነገር ግን ትናንትን እያሰብን ወደ ኋላ ሳይሆን ወደ ፊት መራመድ መቻል አለብን። የእኛ የምንላት የሁላችን ሀገር ለወደፊት ተስፋ ልንሰንቅላት ይገባል። እንታገልለታለን የምንለው ማኅበረሰብ በደም ውስጥ ሳይሆን በመቻቻል አሸናፊነትን ማምጣት ይቻላል። አሸናፊነትን በጋራ ማምጣት ይቻላል። ይህንን ካደረግን መስተካከል እና መታረም ይቻላል። መንግሥት ግን መንግሥታዊ ተግባሩን መፈፀም አለበት።
የመንግሥት የመጀመሪያ ተግባር መንግሥታዊ ደህንነትን ማስጠበቅ ነው። እርሱን ለማድረግ መቻቻል የግድ ነው። ከዛ ባለፈ እኩልነት እና መቻቻል ካለ ነገሮች ይስተካከላሉ። በሀገራችን ወደ ፊት የምንፈልገውም እና በኢኮኖሚ የታፈረች የተከበረች ዳር ድንበሯን ያስጠበቀች፤ ታሪኳን ያከበረች፣ የዜጎች አንድነት የተጠበቀባት ሀገር ትሆናለች የሚል እምነት አለን። ይህ ከተደረገ ሀገራችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላሟን አስጠብቃ ወደ ልማት ፊታችንን እናዞራለን። እነኚህን ነገሮች በሚገባ መሬት ላይ አውርደን ከሠራን ኢትዮጵያ የምትፈልገው ግብ ላይ ትደርሳለች።
አዲስ ዘመን፡- ያለፈውን ለታሪክ እንተወው ብለዋል። እዚህ ላይ አንዳንድ ሰዎች ተቃውሞ አላቸው። በተጨባጭ ጥናት ላይ ተመርኩዞ ያጠፋም ካለ ወይም ሳያጠፋ እንደአጥፊ እየታሰበ ያለ ካለ እንዲሁም እውነተኛ የተበደለው ተረጋግጦ ይቅርታ መጠየቅ ያለበትም ሆነ ይቅርታ ሊጠየቅ የሚገባው ካለ ታውቆ ይቅር መባባል ያስፈልጋል እንጂ እንዲሁ ለታሪክ እንተወው ብሎ ማዳፈን ተገቢ አይደለም የሚሉ አሉ። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ተስፋሁን፡- ታሪክን ለታሪክ እንተወው ስንል አንወቀው ማለት አይደለም። የትኛውም ታሪክ መልካምም ሆነ መጥፎ ታሪክ አሁን ላለው ትውልድ ቁርሾ እና የጦርነት መነሻ መሆን የለበትም። ወቀሳውንም ውዳሴውንም እዛው ለባለታሪኩ መተው አለብን። እኛ የባለታሪኮቹ ወራሾች ነን። መጥፎም ሆነ መልካም ታሪክ ተምረንበት እናልፋለን እንጂ ትናንት በተደረገ ታሪክ ላይ ተመሥርተን መገዳደል ትርጉም የለውም። ስለዚህ ታሪክን ለታሪክ እንተወው ማለት እንተወው፤ ትምህርት እንውሰድበት ማለት ነው።
አሁን እንደተፈጠረ አድርገን በምክንያትነት ተጠቅመነው አንጋጭበት። ታሪክ እንዳለ አምነን እይታችንን የሃሳብ ግጭት እና ፍጭት እንጂ ደም ልንፋሰስበት አይገባም። ታሪክ ምንም ሆነ ምን አሁን አብረን እየኖርን ነው። ቢያንስ አብረን መኖራችንን አንክድም። ስለዚህ ታሪክን መዘን ቁርሾ አንፍጠርበት፤ ታሪክን መዘን ግጭት አናምጣበት፤ ታሪክን መዘን የሕዝብን አንድነት አንሸርሽርበት፣ ታሪክን መዘን የግል ፍላጎታችንን ለማስፈፀም የፅንፍ ሳጥን ውስጥ አንክተተው ።
ጥሩውን መጥፎውን ከታሪክ እንማር ነገር ግን በታሪክ ላይ ተመሥርተን በቀል፣ ቂም፣ ጥላቻ እና መለያየትን አምጥተን ተግባራዊ እናደርጋለን ማለት ስህተት ነው። እንጂ ታሪክ ያስፈልጋል። መጠናትም አለበት። በዓለም በርካታ መጥፎ ታሪኮች አሉ ተቀምጠዋል። የኛም መጥፎውም ሆነ ጥሩ ታሪክ በጥናት ተመርኩዞ መቀመጡ ክፋት የለውም። መቀመጥም አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ።
አቶ ተስፋሁን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2015