በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ለሦስት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው የሠራተኛው የስፖርት ውድድር ባለፈው ጥር 07/2015 በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በበጋ ወራት ፉክክሮች ተመልሷል። ባለፉት በርካታ ሳምንታት በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ፉክክሮችን ሲያስተናግድ ቆይቶም ወደ መገባደጃው ተቃርቧል።
ለስድስት ወራት የሚቆየው የሠራተኞች ስፖርት ውድድር ከመጪው እሁድ ጀምሮ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚሸጋገር ሲሆን በተለይም በሁለት ዲቪዚዮን ተከፍሎ የሚካሄደው ውድድር የግማሽ ፍፃሜ ፉክክር ተጠባቂ ነው። የውድድሩ አዘጋጅ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን(ኢሠማኮ) የስፖርት ክፍል ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ካሳ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፣ በሁለት ዲቪዚዮን በርካታ ቡድኖችን ሲያፎካክር የቆየው የእግር ኳስ ውድድር በመጪው እሁድ የፍፃሜ ተፋላሚዎች ይለዩበታል።
በአንደኛ ዲቪዚዮን እግር ኳስ ውድድር በበርካታ የዙር ጨዋታዎች በሰበሰቡት ነጥብ መሠረት ከሁለቱ ምድቦች የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ የሆኑ አራት ክለቦች ተለይተዋል። በዚህም መሠረት በመጀመሪያው ምድብ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ቀዳሚ ሆኖ ያጠናቀቀ ቡድን ሲሆን፣ ዮሐንስ ቢፍ ኢንወተር ሁለተኛ መሆን ችሏል። በምድብ ሁለት አንበሳ የከተማ አውቶብስ አገልግሎት ኢትዮ ቴሌኮምን በማስከተል የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ ሆኗል። በዚህም መሠረት የምድብ አንድ አንደኛው አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ የምድብ ሁለት ሁለተኛውን ኢትዮ ቴሌኮም በግማሽ ፍፃሜው ፍልሚያ ይገጥማል። በተመሳሳይ የምድብ ሁለት አንደኛው አንበሳ አውቶብስ አገልግሎት የምድብ አንድ ሁለተኛውን ዮሐንስ ቢፍ ኢንወተር ጋር የሚያደርጉት ጠንካራ ፉክክር እንደሚጠበቅ አቶ ዮሴፍ አብራርተዋል።
በተመሳሳይ የእግር ኳስ ውድድር ሁለተኛ ዲቪዚዮን ፉክክር የመጀመሪያውን ምድብ ቀዳሚ ሆኖ የጨረሰው መከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ በምድብ ሁለት ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኮካኮላን በግማሽ ፍፃሜ ይገጥማል። የምድብ ሁለት አንደኛው ሆራይዘን አዲስ ጎማ ደግሞ የምድብ አንድ ሁለተኛውን የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የዋንጫ ተፋላሚ ለመሆን ይገጥማል። በሁለቱም ዲቪዚዮኖች የሚካሄዱ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች በመጪው እሁድ እንደሚከናወኑ ከአቶ ዮሴፍ መረዳት ተችሏል።
የስፖርት ክፍል ኃላፊው አያይዘውም በሠራተኛው ስፖርት በተለያዩ ዲቪዚየኖች በሁለቱም ፆታ የሚካሄደው የቮሊቦል ውድድርም በጠንካራ ፉክክር መቀጠሉን ጠቁመዋል። በወንዶች አንደኛ ዲቪዚዮን የቮሊቦል ውድድር ባለፉት በርካታ ሳምንታት በተካሄዱ የዙር ጨዋታዎች ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ በነጥብ እየመራ ይገኛል። ተስተካካይ አንድ ጨዋታ የሚቀረው አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ በሰበሰበው ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን አንበሳ የከተማ አውቶብስ ሁለተኛ ላይ ይገኛል።
በተመሳሳይ ፆታ የሁለተኛ ዲቪዚዮን ፉክክር ሆራይዘን አዲስ ጎማ እየመራ ሲሆን መከላከያ ኮንስትራክሽንና የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በነጥብ ተከታዩን ደረጃ ይዘው ወደ ወሳኝ የጥሎ ማለፉ ጨዋታ ለማለፍ እየተፎካከሩ ነው። የሴቶች ቮሊቦል ፉክክርን አንበሳ የከተማ አውቶብስ በነጥብ እየመራ የሚገኝ ሲሆን፣ መከላከያ ኮንስትራክሽንና አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ይከተላሉ።
የሠራተኛው ስፖርት ድምቀት የሆኑ የቤት ውስጥ ውድድሮችም በተመሳሳይ ጠንካራ ፉክክር እያስተናገዱ ይገኛሉ። በአንደኛ ዲቪዚዮን የወንዶች ጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር ኢትዮ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የነጥብ መሪነቱን ሲይዝ፣ ኢትዮ ቴሌኮምና አንበሳ የከተማ አውቶብስ ይከተሉታል። በሁለተኛው ዲቪዚዮን ደግሞ ብራና ማተሚያ ድርጅት፣መከላከያ ኮንስትራክሽንና ፋፋ ምግብ አክሲዮን ማኅበር በቅደም ተከተል በሰበሰቡት ነጥብ ተከታትለው እየመሩ ይገኛሉ። አንበሳ የከተማ አውቶብስ፣ኢትዮ ቴሌኮምና ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ በሴቶች ጠረጴዛ ቴኒስ የነጥብ ፉክክሩን እየመሩ የሚገኙ ቡድኖች ናቸው።
ሌላው የዳርት ውድድር ሲሆን በወንዶች ጂኦ ሴንቴቲክ ኢንደስትሪያል አንበሳ የከተማ አውቶብስና መከላከያ ኮንስትራክሽንን አስከትሎ የነጥብ መሪነቱን ይዞ ይገኛል። በተመሳሳይ በሴቶች መካከል የሚካሄደው የዳርት ውድድር በአንበሳ የከተማ አውቶብስ የነጥብ መሪነት የቀጠለ ሲሆን ጂኦ ሴንቴቲክ ኢንደስትሪያልና ኢትዮ ቴሌኮም ቀጣዮቹን ደረጃዎች ይዘው እየተፎካከሩ እንደሚገኙ አቶ ዮሴፍ አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 4/2015