በቆጂ የድንቅ ኦሊምፒያኖች መፍለቂያ በመሆን ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም ገናና ስም አላት። በቆጂ በዓለም አትሌቲክስ ትልቅ ስምና ዝና ያተረፉ ካተረፉና ታሪካዊ አትሌቶች ደራርቱ ቱሉ፣ቀነኒሳ በቀለን፣ እና ጥሩነሽ ዲባባን የመሰሉ እንቁ አትሌቶችን ማበርከት ችላለች። ከዚህ ስፍራ የተገኙት እነዚህ ብርቅዬ አትሌቶች በተለያዩ የዓለም መድረኮች የሚያስመዘግቡት ሜዳለያ ብቻውን አንዳንድ ሀገራት ከሚያስመዘግቡት ሜዳለያ የላቀ መሆኑ በቆጂን የበለጠ ስመ ጥር አድርጓታል።
በቆጂ ምንም እንኳን ስሟ በኢትዮጵያና በዓለም ዘንድ ትልቅ ቢሆንም ለስፖርቱ ካበረከተችው አስተዋፅዖ አንጻር የሚገባትን ጥቅም አግኝታለች ማለት አይቻልም። ትንሿ የታላላቅ አትሌቶች መፍለቂያ የሆነች ከተማ በቀጣይ ውጤታማ አትሌቶችን ለማፍራት እንዲቻላት ትልልቅ ስፖርታዊ ውድድሮችን በማዘጋጀት የበለጠ መነቃቃት መፈጠር እንዳለበት ሲነገር ቆይቷል።
ከተማዋ በስም ብቻ ሳይሆን በተግባርም አድጋና የአትሌቶች መፍለቂያ ሆና እንድትቀጥል ያለመ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ለሁለተኛ ጊዜ ለማዘጋጀት ሽርጉድ በማለት ላይ ትገኛለች። ውድድሩን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጁት ሲሆን፣ “ልወቅሽ ኢትዮጵያ“ በሚል መሪ ቃል የፊታችን እሁድ ግንቦት 6 ቀን 2015 ዓ.ም በበቆጂ ከተማ ይካሄዳል።
የውድድሩ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ባላት ስምና ዝና ተጠቅማ የስፖርት ቱሪዝሙን በማሳደግ ከጽዋው ተቋዳሽ እንድትሆን የተወጠነ ሃሳብ
ነው። በተለይም በስፖርት ዘርፉ ያልተጠቀምንበትን እምቅ ሃብት እና የእውቅ ዓለም አቀፍ አትሌቶች መፍለቂያ የሆነችውን በቆጂን ለማስተዋወቅና ከተማዋ እንድትነቃቃ ለማድረግ መሆኑን የኢፌዲሪ ቱሪዝም ሚኒስትር እና የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቁመዋል። ውድድሩ ለአዳጊ አትሌቶች የመወዳደርያ መድረክ በመፍጠርና የስፖርት ቱሪዝምን በተለይም የአትሌቲክስን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማረጋገጥ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት የሚደረግ ጥረት አካል ተደርጎ ይወሰዳል።
የዘንድሮ ሩጫ የ2015 ዓ.ም ኢትዮቴሌኮም ታላቁ ሩጫ በበቆጂ የሚል ስያሜ ይዞ የሚደረግ ይሆናል። በአርሲ ሰንሰለታማ ተራራን የመውጣት፣ የካምፒንግ እና በስመ ጥሯ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የተሰየመውን እና እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ አዳጊ አትሌቶችን የሚያሳትፍ “ጥሩነሽ ዲባባ ሻምፒዮን ሺፒ” በበቆጂ ከሚደረጉ ውድድሮች ዋነኞቹ ናቸው።
ውድድሩ መነሻውንና መድረሻውን በቆጂ ስታዲየም በማድረግ 12 ኪሎ ሜትር የጤና ሯጮች፣ 1 ኪሎ ሜትር የልጆች ሩጫ እና 2000 ሜትር ከ15 ዓመት በታች ጥሩነሽ ዲባባ ወጣቶች ሻምፒዮናን በማካተት ይካሄዳል። ታዋቂ አትሌቶች፣ የበቆጂና የአካባቢውን ኗሪ እና ከአዲስ አበባ የሚጓዙ የጤና ሯጮችን ጨምሮ በውድድሩ 1200 ሰዎች ይሳተፋሉ።
በውድድሩ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች ልክ እንደ በቆጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤት እያስመዘገቡ ያሉ የረጅም ርቀት አትሌቶችን በማፍራት የምትታወቀው የኬንያዋ ኤልዶሬት ከተማ በሚካሄደው ውድድር ተጋባዥ ተወዳዳሪ ሆኖ ይሳተፋል። በተመሳሳይ የበቆጂ ውድድር ላይ ከኤልዶሬት ከተማ 2 ተጋባዥ አትሌቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑም ተጠቁሟል። ይህ እድል ለታዳጊ አትሌቶች የተሻለ ተሞክሮ እንዲቀስሙ ከመርዳቱም በላይ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች የመወዳደር ልምድ እንዲያካብቱ ይረዳል ተብሎ ታምኖበታል። የሁለቱንም ከተሞች እህትማማችነትን በማጠናከር የስፖርት ቱሪዝምን ፍሰት ይጨምራል ተብሎም ይጠበቃል። ወደፊትም ከሁለቱ ከተሞች የተወጣጡ አትሌቶች የሚሳተፉበትን ዉድድር ለማዘጋጀት እቅድ ተይዟል።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዳግማዊት አማረ፤ ውድድሩ መካሄዱ ታዳጊ አትሌቶች ልምድ እንዲቀስሙና በዓለም አቀፍ ውድድሮች የመካፈል ዕድሉን እንዲያካብቱ ይረዳል በማለት በመግለጫው ላይ ተናግረዋል። የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው፣ ውድድሩ መካሄዱ የእውቅ ዓለም አቀፍ አትሌቶች መፍለቂያ የሆነችውን በቆጂ ከተማን ከማስተዋወቅ ባለፍ የቱሪዝም መስህቦች እንዲጎበኙ እድልን ይፈጥራል ብለዋል። “በቆጂ የወሰደን ታሪክ ነው” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ በቆጂ በጣም በርካታ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ያስተዋወቁ ጀግኖች አትሌቶችን ያፈራች ከተማ መሆኗን አስታውሰዋል። በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ ስፍራውን ሲጎበኙ ይሄን ሁሉ ታሪክ ያላት ከተማ ትኩረት መሳብ አለመቻሏ አስገርሟቸው እንደነበር ተናግሯል። ይህም ስፖርት ቱሪዝሙን ለማሳደግ በትኩረት እንዲሠራ ማድረጉን አክለዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ በቆጂ በአትሌቲክስ ውጤታማ የመሆኗ ምስጢር ከፍታ ቦታ ላይ መገኘቷ መሆኑን ጠቁሟል።
የበቆጂ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ተፈሪ ቶላ በበኩላቸው፣ በቆጂ ላይ ሩጫን ማካሄድ ማለት ነገ ደራርቱን፣ ቀነኒሳን መፍጠር በመሆኑ ያለው ጠቀሜታ ትልቅ ነው ሲሉ ገልፀዋል። በ2014 ዓ.ም በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በበቆጂ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው ሩጫ ”ኢትዮጵያ ትሮጣለች“ በሚል መሪ ቃል መካሄዱ ይታወሳል። በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅትም ከበቆጂ የፈለቁትን እንቁ ኦሊምፒያን ከመነሻቸው በማሰልጠን የሚታወቁት አሰልጣኝ ስንታየሁ እሸቱ የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ግንቦት 3/2015