ተሰማ መንግሥቴ፣ ዘውዴ መታፈሪያ እና ገብረየስ ገብረማሪያም ከተገናኙ ሰነባብተዋል:: አጠር ቀጠን ብሎ ፊቱ የገረጣው ተሰማ፣ ፊቱ ሞላ ብሎ ወፍሮ ሲያዩት፤ ዘውዴ እና ገብረየስ ፊታቸው በፈገግታ ፈካ:: መካከለኛ ቁመት ያለው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፊቱ ላይ ማዲያት መታየት የጀመረው ገብረየስ፣ የጓደኛው ተሰማ ደንቦሽቦሽ ማለት ደስታ ፈጥሮለታል:: እርሱ አንድ ሰሞን እንዲህ አምሮበት እንደነበር አስታውሶ፤ ወዲያው ግንባሩን ቋጥሮ ያለፈውን ለመርሳት ሲሞክር ደስታው ደበዘዘ::
ከልጅነቱ ጀምሮ ውፍረት አብሮት የኖረው ዘውዴ፣ ለተሰማ ‹‹ ሰሞኑን ሹመት አገኘህ እንዴ ? እንዴት ነው? ›› ብሎ ተሰማን በመጠየቅ ጨዋታውን አስጀመረ:: ተሰማ ፈገግ ብሎ፤ ‹‹ የምን ሹመት ነው?›› ሲል ጥያቄውን በጥያቄ መለሰ:: ገብረየስ እነዘውዴ እና ተሰማ መጠጥ ሲያዙ፤ እርሱ ግን ያዘዘው ውሃ ነበር:: ዘውዴ ለተሰማ ‹‹ ይሔ ሁሉ ውበት ፈሶብህ የምን ሹመት ነው? ብለህ መሾምህን እንዳትደብቅ፤ ደግሞ ያው መቼም በአጋጣሚም ሆነ በዕድል ዋናው ቀድሞ መሾምህ ነው:: ከታች ያለው መጥቶ የሚያልፍበት ዕድል የለ፤ በሹመት ላይ ሹመት የሚደራረበው ከላይ ላለው ነው:: ›› ሲለው ገብረየስ በዘውዴ ንግግር ከት ብሎ ሳቀ::
ተሰማ ግራ ተጋባ፤ ‹‹ መጠጥ እየጠጣን ያለነው እኛ ውሃ እየጠጣህ ምን እንደዚህ አሳቀህ?›› ሲል ጠየቀ:: ገብረየስ ‹‹ እኔ ከሹመት ወደ ባለሙያነት ተምዘግዝጌ አይደል እንዴ? ነገሩ ያሳቀኝ የእኛ የኢትዮጵያውያን ነገር አስገራሚ ሆኖብኝ ነው:: ሹመት ለሕዝብ በጎ አኗኗር ጉልበትን እና እውቀትን መስዋዕት ማድረግ ሳይሆን፤ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ እንደሚባለው የራስን ጥቅም ለማስቀደም መሞከር፤ መስገብገብን የመሳሰሉ መጥፎ ባሕሪያት መገለጫችን ሊሆኑ ምንም አልቀራቸውም:: ሥልጣን ቅድሚያ ለግል ሳይሆን ለሕዝብ ጥቅም መቆም መሆን እያለበት፤ የእኛ ነገር ተቃራኒ ነው:: ስትሾም ምቾት ይቅርብኝ፤ ዕውቀቴን እና ሙሉ አቅሜን ለሕዝብ ላውለው ካልክ ትወርዳለህ፤ መውረድ ብቻ ሳይሆን ትዋረዳለህ::
እኛም አንድ ሰሞን ተሹመን ውለን ሳናድር፤ የፈለግነውን እየበላን የፈለግነውን እየጠጣን ከሃሳብ ነፃ ሆነን አምሮብን ታይተን ነበር:: ይህ ለእኔ አናዳጅ መሆኑ ቀርቶ አዝናኝ ሆኗል:: እየሳቅኩ ያለሁት ለዚሁ ነው:: በእርግጥ ለራስ ጥላ ለእግር ከለላ መኖር እንዳለበት እስማማለሁ:: ነገር ግን የፖለቲካ ድንቁርና ወይም መሐይምነት፣ ቦዘኔነት፣ ያልደከሙበትን ጥቅም መፈለግ፤ ጥቅም አሳዳጅነት፤ ሕዝብን ከተዘዋዋሪ የባርነት ቀንበር ነፃ አለማውጣት፤ ድህነትን በሚቀንሱ ከተቻለ ደግሞ ድህነትን በሚያጠፉ ሥራዎች ላይ ከመጠመድ ይልቅ፤ አዲስ ሃሳብ እና አዲስ ሥራ ለመፍጠር ጠቢብ ለመሆን ከመጣር ይልቅ ብዙም ፋይዳ የማይሰጡ ቁሶችን መሰብሰብ፤ ለራስ የተደላደለ ኑሮ በማሰብ የሥልጣን ጊዜን ማሳለፍ ተጠያቂ የሚያደርግ ነገር ሲመጣ ደግሞ ብሔር ስር ተሸጉጦ ኔትወርክ መዘርጋት ከማናደድ አልፎ ብስጭት ውስጥ ከመክተት ይልቅ አሁን አሁን እያዝናናኝ ነው፤ እንዲህ እንደአሁኑ እያሳቀኝ ነው:: ›› አለ::
ተሰማም በበኩሉ ፈገግ አለ:: ‹‹ቅድሚያ የሚሰጠውን ጉዳይ ለመፈፀም የማይቻል ሆኖ እያለ ተፈላጊ ላልሆነ ነገር በከንቱ መቸገር ትክክል አይመስለኝም:: ለራሱ አያውቅ አዋይ ቅቤ ለመነ ላዋይ ይባላል:: ሕዝብን ከድህነት ከማውጣት በፊት ራስህ ከድህነት መውጣት አለብህ:: ›› በማለት ሹመት ቀድሞ ተሿሚውን ማበልፀግ አለበት የሚል እምነት እንዳለው ሲናገር ዘውዴ በትዝብት አተኩሮ አይን ዓይኑን እያየ ነበር::
ዘውዴ፤‹‹ ፖለቲከኛው እና ባለስልጣኑ ያየውን ልብላ እያለ መስገብገብ ካበዛ ቁንጣን ይይዘዋል:: ቁንጣን ደግሞ በሽታ ላይ ይጥላል:: የኔነው ሲሉት ቁርጠት ሆኖ እንደሚገድለው ሁሉ ፅንፈኝነትም በተመሳሳይ መልኩ ገዳይ ነው:: የብሔርም ሆነ የሃይማኖት ጉዳይ ሲያነሳ መጠን ያስፈልጋል:: የአንድ ብሔርን ወይም ሃይማኖትን በደል መግለፅ ፅንፈኝነት አይደለም:: ግን ደግሞ አንዱ ብሔር ሌላውን ብሔር በድሏል በሚል ሌላው ብሔር ላይ ቅስቀሳ ማድረግ፤ አንድ ማኅበረሰብ በሌላ ማኅበረሰብ እንዲጎዳ ማነሳሳት ፅንፈኝነት ነው:: ፅንፈኝነት ሰዎች ላይ ትልቅ በደል መፈፀም ነው:: ›› አለ::
ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹ እኔ ቀድሞም ያልኩት ግባችን የዜጎች እኩልነት እንጂ ሀገር ማፍረስ መሆን የለበትም በማለቴ የሞቀ ኑሮዬ በረዶ እንዲሆን ተፈርዶብኛል:: ለዓመታት ስታገል ኖሬ አመራር ስሆን ማመዛዘን አለብን፤ ሚናችንን እንለይ፤ የያዝነው የሕዝብ አደራ ነው፤ በበቂ ሁኔታ ለሀገራችን ጠብ የሚል ነገር እንሥራ፤ ሁሉንም ከሃይማኖት እና ከብሔር መነፅር በፀዳ መልኩ እንይ፤ በቀናነት እናገልግል፤ ይህን አስተሳሰብ በሁሉም ውስጥ እናስርፅ ባልኩኝ፤ ይህ ሁሉ መጣብኝ::
በረሃ ስገባ ዓላማዬ ጭቆናን ማስወገድ ነበር፤ ወንበር ስንይዝ ዓላማችንን በትክክል ለይተን ማወቅ ይኖርብናል:: ሰፊው ሕዝብ የሚፈልገው ዴሞክራሲያዊ ሰላም ነው:: ዋነኛው ዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሰላም ቢሆንም፤ ይህንን በቀላሉ ማምጣት ሲያዳግት የሆነ ብሔር ወይም ሃይማኖት ውስጥ መሸጎጥ ይመጣል:: ይህ ደግሞ መፍትሔ አይሆንም:: በብሔር ወይም በሃይማኖት ስር ሳይሸጎጡ ፖለቲከኛ፣ አክቲቪስትም ሆነ ባለሥልጣን ለመሆን የሐቀኝነት ፍላጎት ብቻ በቂ አይደለም:: ብዙ ማወቅ፤ ብዙ መማር እና መመራመር ይጠይቃል:: በብቃት በመምራት ዴሞክራሲያዊ ሰላም ለማምጣት ምሑራንን ማማከር እና በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ማበጀት የግድ ነው:: ያለበለዚያ በብሔር እና በሹመት ስር እየተሸጎጡ የሚልመጠመጡ ሀገርን አደጋ ላይ ይጥላሉ:: ›› አለ::
ተሰማም በሃሳቡ እንደሚስማማ ጭንቅላቱን እየወዘወዘ አመለከተ:: ቀጥሎም ‹‹ትክክል ነው፤ ፅንፈኛ መሆን አይገባም:: ፅንፈኛ በመሆን በድል አድራጊነት ራሱ ላይ እባብ የሚጠመጥም ነው:: በደል ተበዳዩን ብቻ ሳይሆን በዳዩንም የሚጎዳ ነው:: በዳይ ለጊዜው እርካታ ሊኖረው ይችላል:: ቆይቶ ግን በደሉ ወደ እርሱ መገልበጡ አይቀርም:: በትክክል እንዳልከው የሚያዋጣው መሥራት ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አንድ ሰው ሲሾም የትምህርት ደረጃው ሲሻር ግን ሃይማኖት እና ብሔሩ እየተጠቀሰ መነገር የለበትም:: ሁሉም የማንም መብት ሳይጣስ ሁሉም እኩል እየታየ የሚገለገልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እናደርጋለን:: ›› ሲል እየኖረበት ያለውንም ባይሆን ያሰበውን ተናገረ::
ዘውዴ ብድግ ብሎ አጨበጨበ:: ‹‹ፅንፈኝነትን ይዞ ሙጭጭ ማለት ያፈርሳል እንጂ አይገነባም፤ ፅንፈኝነት ሲበረታ ዘላቂ በሆነ መልኩ ያከስራል እንጂ አያተርፍም:: የማኅበረሰብ ድጋፍ አስፈላጊ ነው:: ድጋፉ ግን የአሸዋ ላይ ቤት መሆን የለበትም:: ድጋፍ መገኘት ያለበት በአሻጋሪ ሃሳብ የበላይነት ነው:: ለመከራ ያለው መነኩሴ ዳዊቱን ሽጦ አህያ ይገዛል፤ እንደሚባለው ዋነኛውን ለመላው የአገሪቱ ዜጎች የሚጠቅም፣ አገር የሚያሳድግ የበላይ መሆን የሚችል ሃሳብ ይዞ፣ መጠለያ ጥግ መፈለግ ሲገባ ምንም ዓይነት ሀገራዊ ጥቅም የሌለውን ይልቁንም ሀገርን ወደ ኋላ የሚጎትተውን አንሸራታች ጥግን ይዞ መንከላወስ ብዙ አያስጉዝም:: ምንም እክል ቢያጋጥም ዓላማ አይዘነጋም:: አደራህን ተሰማ በምንም መልኩ በኃላፊነት ቦታ ላይ ስትቀመጥ ፅንፈኝነትን ተጠየፍ፤ አታዳላ፤ ፅንፈኝነትን ይዘህ ጀግና ከምትባል፤ እንደገብረየስ የሁሉንም ሕዝብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትም ሆነ የሁሉንም ተሰሚነት እያስተጋባህ ከሥልጣንህ ብትገለል ይሻልሃል:: ›› አለው::
ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹ኢትዮጵያውያን ብዙ ጠላት አለን፤ ከነቃን በጋራ ጠላቶቻችንን ማስወገድ እንችላለን:: ለማኝ ቢያብድ ስልቻውን አይጥልም እንደሚባለው የፈለገ ብናብድ ሀገራችንን አሳልፈን አንሰጥም:: ዓላማችን ኢትዮጵያ ናት:: ኢትዮጵያን ለማሳደግ ፍላጎት ካለ የሚፈለገውን ተግባር ማከናወን ይቻላል:: በዓለም ፖለቲካ ውስጥ ግን ለላም የሣር ለምለም የሚባል ነገር የለም:: ዓለም ለድሃ አገር ጥቅም የሚሰጥን ነገር ከመንከባከብ ይልቅ፤ በተቃራኒው ለሚጎዳቸው ነገር ትኩረት ይሰጣል:: መዋጋት ስትፈልግ መሣሪያ ይቀርብልሃል፤ በተቃራኒው የትኛውንም ሀገር የሚለውጥ ፕሮጀክት አቅደህ ድጋፍ ብድር ይነፈግሃል:: ለመንግሥት ኢኮኖሚውን ለመደገፍ እጃቸውን የሚያጥፉ በብሔር ፅንፈኝነት ሀገር እንድትፈርስ ድጋፍ ያደርጋሉ::
ትጉህ አመለ ጨዋ እና ለሀገርህ ታማኝ ከሆንክ በአፍሪካ ምድር የዓለምን ፖለቲካ ተቆጣጥረህ ሀገርን መምራት አትችልም:: ጠልፎ ሊጥልህ የሚታትር የዓለም ቀማኛ ይፈትንሃል:: አንተ የዜጎችን የኑሮ ሸክም ለማቃለል ስትዳክር በተቃራኒው ዜጎች እንዲጠሉህ፤ ፅንፈኞች እንዲያሰቃዩህ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ:: ይሄኔ ትሽመደመዳለህ::
ለዚህ መፍትሔው አመራሩም ሆነ ፖለቲከኛው እንዲሁም የተማረው ሰው አጠቃላይ ሕዝቡ መንፈሰ ጠንካራ፤ ለተወሰነ ብሔር እና ለተወሰነ ሃይማኖት ሳይሆን ለመላው ሕዝብ እኩልነት እና ዴሞክራሲ ቆራጥ መሆን ይጠበቅባቸዋል:: በሁሉም ውስጥ ፀጥታ እና የመንፈስ እርጋታ ያስፈልጋል:: ብሩህ እና ጀግና አመራር ቢኖርም ሕዝብ በአስተውሎት ለመመራት ካልተዘጋጀ ጉዳዩ ተወሳስቦ ወዳልታሰበ ጎዳና ሊወስድ ይችላል::
በየትኛውም ብሔር ውስጥ ያለ ሰው ወይም በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ ያለ ሰው፤ በጭቃ ቤት ውስጥ ይኖራል:: ሁሉም በድህነት እየኖረ፤ ማንም በኢኮኖሚ የተለየ ታላቅነት ሊኖረው አይችልም:: የየትኛው ብሔር ሰው አኗኗር ከሌላኛው የተሻለ ሆኖ አያውቅም:: ሕዝብ አፍቃሪ ጥያቄው ስለሕዝብ ነው:: የመሬት ከበርቴ እና ንጉሥ እያሉ አፈር ስለሚገፋ ገበሬ እየጠቃቀሱ ከማላዘን ይልቅ፤ ቴክኖሎጂን መጠቀሚያ መንገድን ማመቻቸት ተማርን ከሚሉ ወገኖች ይጠበቃል:: አርሶ ለሚያበላ አርሶ አደር የሚጠቅመው ፅንፈኝነት ሳይሆን ትልቅ ጥበብ ነው::
ፅንፈኛ ሆኖ ተወዳጅነትን መጨመር እና በዓለም ታዋቂነትን ማትረፍ ይቻላል:: ነገር ግን የሕዝብን አኗኗር ባሕል እና ወግ የእርስ በእርስ ትስስርን መበጣጠስ የታሪክ ተጠያቂነትን ያስከትላል:: ተጠያቂነት ደግሞ ምንም እንኳ ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ ነው የሚባለው መንግሥት ብቻ ሳይሆን የአሁኑ ትውልድ በሙሉ ተጠያቂ ይሆናል::
ትንሹዋን ነገር እንደምክንያት በመጠቀም ብዙ ነገር ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይቻላል:: የአዕምሮ ድሃ፣ ክፉ እና ተንኮለኛ ሆኖ መዝረፍ፤ በፅንፈኝነት ብዙዎችን ማሰናከል ላያዳግት ይችላል:: መጨረሻ ላይ ጉዳቱ ለሁሉም መሆኑ አይቀርም:: ፖለቲከኛ ሁሉ ቀጣፊና አታላይ ነው ማለት ያስቸግራል:: ለሰው ደግ የሚያስብ እና ለጥሩ ነገር የሚተጋ እንዳለ መረሳት የለበትም::
ፖለቲከኞችም ሆኑ ምሑራን አንዱን ብሔር እንደአዋቂ፣ እንደተለየ ንጉሥ፣ የተለየ አቅም እንዳለው ጀግና ሌላውን እንደደካማ፣ መሐይም፣ ባሪያ፣ ማየት ነበር ቢሉም ይህ ያለፈ ታሪክ ነው:: አሁን ለየትኛውም ብሔር የበላይነት ሳይሆን ለሁሉም እኩልነት መሮጥ ያስፈልጋል:: የውጪ ጠላትን ተመርኩዞ ፅንፍ ይዞ የሚበጠብጠውን ገለል ማድረግ ከእኛም ሆነ ከአጠቃላይ ከሕዝቡ የሚጠበቅ ነው:: ›› ሲል ተሰማ፤ ዘውዴ በንግግሩ ተደስቶ ቆሞ አጨበጨበ::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3/2015