13ኛው የኢትዮ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት በቅርቡ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ተካሂዷል:: በዚህ ‹‹የኢትዮጵያን ይግዙ›› በሚል መሪ ሀሳብ ለአምስት ቀናት በተካሄደው ንግድ ትርዒት ላይ በርካታ የአገር ውስጥ አምራቾች ተሳትፈውበታል:: የንግድ ትርዒቱ ዓላማ የኢትዮጵያን ምርቶችና አገልግሎቶች ለማስተዋወቅና የአገር ውስጥ ምርቶች ገበያ እንዲያገኙ ማድረግ ነው:: ሌላው ዓለምም በምርቶቹ ተጠቃሚ እንዲሆን፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ የአገር ውስጥ አምራቾች እንዲበረታቱ ማስቻልና የአገሪቷም ኢኮኖሚ ከፍ እንዲል ማድረግ ሌሎች አላማዎቹ ናቸው::
በንግድ ትርዒቱ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ አገር አምራቾች፣ ግብዓት አቅራቢዎችና ሌሎችም ተገኝተው ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ የገበያ ትስስርና የልምድ ልውውጥ ማድረጋቸውን መረዳት ተችሏል:: ምርቶቻቸውን ይዘው ከቀረቡት አምራቾች መካከል በሀብቴ ጋርመንት ውስጥ የሚገኘው ኩርታ የልጆች አልባሳት ድርጅት አንዱ ነው፤ ድርጅቱ ከአራስ ጀምሮ እስከ 13 ዓመት ላሉ ልጆች የተለያዩ አልባሳትን እንደሚያመርት የዚህ የኩርታ የልጆች አልባሳት ድርጅት ማርኬቲንግ ባለሙያ ትዕግሥት ግርማ ትገልጻለች::
እንደ ማርኬቲንግ ባለሙያዋ ገለጻ፤ አልባሳቱን ለማምረት የሚውለው ጥጥ (ኮተን) የተባለው ጥሬ ዕቃ ወይንም ብትን ጨርቅ ከውጭ አገር በግዥ በማስገባት ነው ጥቅም ላይ የሚውለው:: አልባሳቱ በተለያየ ዲዛይንና ህትመት ተሰፍተው ለገበያ የሚውሉ ሲሆን፣ አልባሳቱ ለሕፃናቱ ቆዳ ምቹና ለስላሳም ናቸው:: ወላጆች ልጆቻቸውን ቀለል ያለና ምቹ አልባሳት ለማልበስ የሚቸገሩባቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውን ከደንበኞች መገንዘቧን የምትገልጸው ትዕግሥት፤ ድርጅቱ ወደ ምርቱ ሲገባም ይህንኑ ክፍተት በመረዳት እንደሆነ ነው የተናገረችው::
እርሷ እንዳለችው፤ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ምርቶቹን ብዙዎች ዘንድ ተደራሽ በማድረግ የተጠቃሚውን ፍላጎት እያሟላ ይገኛል:: ብዛት ያለው ደንበኛም ማፍራት ችሏል:: በደንበኞቹ ፍላጎትም ድርጅቱ የምርቱን ተፈላጊነት ማረጋገጥ ችሏል:: ምርቶቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ እንዲቀርቡ ጥረት አድርጓል:: በአሁኑ ጊዜም ድርጅቱ የሚያቀርበው የአልባሳት ዋጋ ከፍተኛው 700 ብር ነው:: በአብዛኛው ተመጣጣኝ እንደሆነም ታስረዳለች::
‹‹የኢትዮጵያን ይግዙ›› በሚለው መሪ ሀሳብ የተዘጋጀውን የንግድ ትርዒትም ድርጅቷ እንደሚሠራበት ጠቅሳ፣ የአገር ውስ ጥ አምራች ድርጅቶችን የሚ ያበረታታ እንደሆነም ገልጻለች:: የአገር ውስጥ ምርትን በመጠቀም አምራቾችን በማበረታታት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍ እንዲል በማድረግ ረገድ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንደሚጠበቅ ጠቁማለች::
እንዲህ ዓይነት መድረኮች የኢትዮጵያን ምርት ይበልጥ ለማስተዋወቅ ያግዛሉ ያለችው ትዕግሥት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉ አስር ሱቆች ኩርታ የሕፃናት አልባሳት በስፋት እንደሚታወቅም ነው የተናገረችው:: ድርጅቱ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ለ13ኛ ጊዜ ባዘጋጀው ኢትዮ ቻምበር መሳተፉ ደግሞ ይበልጥ ሊያስተዋውቀው እንደሚችል ነው የገለጸችው:: በተለይም ከሸማቹ ጋር የመተዋወቅና የአቻ ለአቻ የልምድ ልውውጥ እንዲሁም የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጭምር የንግድ ትርዒቱ ጠቃሜታ የጎላ እንደሆነ አስታውቃለች::
ሌላው በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ የተሳተፈው ጭላሎ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ነው:: የፋብሪካው ሴልስ ማናጀር አቶ ፉአድ ዋበላ እንዳለው፤ ይህ መድረክም ጭላሎ የምግብ ማቀነባበሪያ ምርቶችን ለማስተዋወቅና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጠቃሜታው የጎላ ነው::
ፋብሪካው ከሚያመርታቸው ከአስር በላይ የብስኩት ዓይነቶች በንግድ ትርዒቱ ላይ ዋፈር ብስኩቶችን፣ ኦኬ ፓስታ፣ የአትክልትና የዶሮ ጣዕም ያላቸው ምርቶችን ይዞ ቀርቧል:: እንዲህ ዓይነት መድረክ ለሸማቹም ሆነ ለአምራቹ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥርም ጠቅሶ፣ ምርቶቹን ከማስተዋወቅ ባሻገር በፋብሪካ ዋጋ ለሸማቹ ማቅረብ መቻሉንም አቶ ፉአድ ተናግሯል::
ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድም ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው የጠቀሰው አቶ ፉአድ፤ አቻ ከሆኑ ፋብሪካዎች ጋርም የልምድ ልውውጥ ማድረግ ያስቻላቸው መሆኑንም አመላክቷል:: በተለይም ግብዓት አቅራቢዎችና ሌሎች አካላትም በመድረኩ በመገኘታቸው የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ጭምር የአገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታትና ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል የሚሰጥ መድረክ ሆኖ እንዳገኘው ነው ያስረዳው::
ፓች ፉድስ የሚያመርታቸውን የተለያዩ የቸኮሌት ምርቶችን ስታስተዋውቅ ያገኘናት የፓች ፉድስ የሽያጭ ባለሙያ ኪሚያ ሀሰን በበኩሏ፤ ፓች ፉድስ አጠቃላይ የቸኮሌት ምርቶችን በማምረት የሚታወቅ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት መሆኑን ገልጻለች:: ድርጅቱ ከአገር ውስጥና ከውጭ የሚገቡ የተለያዩ ግብዓቶችን በመጠቀም ቸኮሌቶችን እንደሚያመርትም ትናገራለች:: እንደ ቅቤ፣ ወተትና ካካዎ ፓውደር የመሳሰሉትን ጥሬ ዕቃዎች ከውጭ አገር በማስመጣት የተቀሩትን ግብአቶች ደግሞ ከአገር ውስጥ በመጠቀም ቸኮሌቶቹን እንደሚያመርትም ነው ያብራራችው::
ኪሚያ እንደገለጸችልን፤ ድርጅቱ እነዚህን ግብዓቶች በመጠቀም ቸኮሌቶችን በማምረት ምርቱን በዋናነት ለኬክ ቤቶችና ለዳቦ ቤቶች ያቀርባል:: ከዚህ በተጨማሪም ዳቦ ላይ የሚቀቡና ለሕፃናት ምግብነት የሚውሉ በተለይም በቁርስና በመክሰስ ሰዓት ላይ የሚቀርቡ ቅቤዎችንም ያመርታል:: ይህም በአገር ውስጥ ያሉትን አምራቾች የሚያበረታታ ከመሆኑም በላይ ከውጭ የሚመጣውን ምርት በአገር ውስጥ መተካት ያስቻለ ነው::
መንግሥት ከውጭ በሚገቡ የቅንጦት ዕቃዎች ላይ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ቸኮሌት ላልተወሰነ ጊዜ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ መደረጉን አስታውሳ፣ ይህ ሁኔታ ለፓች ፉድስ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩንም ነው የጠቆመችው:: እርምጃውን ተከትሎ ድርጅቱ ቸኮሌቶች ገበያው ላይ ያላቸው ተፈላጊነት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሆኑን ኪሚያ ጠቅሳለች::
ይህም በአገር ውስጥ ያሉትን አምራቾች የሚያበረታታ ከመሆኑም በላይ ከውጭ የሚመጣውን ምርት በአገር ውስጥ ምርት መተካት ያስቻለ ነው ብላለች:: ስለዚህ በአገር ውስጥ የማይገኙ ግብዓቶችን ብቻ ከውጭ በማስመጣት ቸኮሌትን በአገር ውስጥ ለማምረት ሰፊ ዕድል መፈጠሩን ጠቁማለች:: ምርቱን ከውጭ ለማስገባት ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት ረገድም ትልቅ ድርሻ እንዳለው ኪሚያ ገልጻለች::
ፓች ፉድስ ከተመሠረተ ከስድስት ዓመት በላይ እንደሆነው የገለጸችው ኪሚያ፤ ድርጅቱን ቱርኮች፣ ጀርመንና ሶርያውያን በጋራ እንደሚመሩት ጠቅሳ፣ ይህም ተመሳሳይ ለሆኑ አምራች ድርጅቶች የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማስቀረት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው አስረድታለች::
እንደ ኪሚያ ማብራሪያ፤ የንግድ ትርዒቱ የገበያ ትስስርና ሌሎች ተያያዥ ጥቅሞች የሚገኙበት ሲሆን፣ በተለይም ድርጅቱ አሁን ካሉት አከፋፋዮች በተጨማሪ ምርቶቹን በመላው የአገሪቷ አካባቢዎች ተደራሽ ማድረግ የሚችሉ የተሻሉና አቅም ያላቸው አከፋፋዮችን ለማግኘት ያስችለዋል::
እነዚህ አከፋፋዮችም ፓች ፉድስ የሚያመርታቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማኅበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ ምርቶቹ እንዲታወቁ ያደርጋሉ:: ቸኮሌት በአገር ውስጥ እየተመረተ ስለመሆኑም ለማወቅ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል:: ከዚህ በተጨማሪም በዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቱ የሚሳተፉ ጥሬ ዕቃ የሚያቀርቡ በርካታ የማኑፋክቸሪንግ ካምፓኒዎች በመኖራቸው ከእነዚህ ካምፓኒዎች ጋርም ትስስር በመፍጠር የአገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል::
ይህ ከኢትዮጵያ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በትብብር የተዘጋጀ የንግድ ትርዒት የኢትዮጵያ ምርቶች፣ አገልግሎቶችና ግብአቶችን በማስተዋወቅ ለኢንዱስትሪ ልማት እድገት ለሥራ ፈጠራ፣ የገበያ ትስስር ላይ ሚና እንደሚኖረው ታምኖበታል:: በተለይም የውጭ ኩባንያዎች መሳተፋቸው ለአገር ውስጥ ምርቶችና አገልግሎቶች የሚሆኑ ግብአቶች ቴክኖሎጂዎች የሚተዋወቁበትና የአገሪቱን የኢንዱስትሪ ደረጃ በማስተዋወቅ ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ታምኖበታል::
ይህን መሰል የንግድ ትርዒቶች ፋይዳ ምንድን ነው? ስንል ለኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ውቤ መንግሥቱ ላነሳንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንዳሉት፤ ይህ የንግድ ትርዒት በዋናነት የኢትዮጵያን ምርቶችና አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅ የተዘጋጀ ነው፤ ምርትና አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ሥራ መሥራት ያስችላል::
ለአብነትም የኢትዮጵያ ምርቶች ገበያ እንዲያገኙ ማድረግና የኢትዮጵያን አገልግሎቶች ሌላው ዓለም እንዲጠቀም ማድረግ ይጠቀሳል:: ከዚህ በተጨማሪም ኢንዱስትሪዎች የተሻለ አቅም እንዲኖራቸውና የውጭ ባለሀብቶችም የኢንዱስትሪዎቹን አቅም በማየት ግብዓት እንዲሰጡ፣ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉና በጋራ መሥራት የሚችሉበትን መንገድ የማሳየት፣ የማስተማርና የማነቃቃት ሥራ የሚሠራበት እንደሆነ አስረድተዋል::
የንግድ ትርዒቱ ዋና መልዕክት ‹‹የኢትዮጵያን ይግዙ›› የሚል መሆኑን ያስታወሱት አቶ ውቤ፤ የኢትዮጵያን ይግዙ ማለት ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ምርት እያመረቱና በራሳቸው ምርት እየተጠቀሙ የራሳቸውን ቴክኖሎጂ በማሳደግ የተሻለ አገር መፍጠር የሚቻልበት ዕድል ነው ይላሉ:: እንደ ቻይናና ኮርያ የመሳሰሉት አገራት ያደጉት በዚሁ መንገድ መሆኑን ጠቅሰው፣ አገሮቹ በራሳቸው ምርት ማደግ እንደቻሉ ነው አቶ ውቤ ያስታወቁት፤ ኢትዮጵያውያንም በኢትዮጵያ ምርት በመጠቀም አገሪቷን የማሳደግና የማስተዋወቅ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን አስረድተዋል::
በንግድ ትርዒቱ 250 የሚደርሱ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ተገምቶ እንደነበር የጠቀሱት አቶ ውቤ፤ የውጭ አገራትና የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት የንግድ ትርዒት እንደመሆኑ በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች መሳተፋቸውን ተናግረዋል::
እሳቸው እንዳሉት፤ የንግድ ትርዒቱ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን ይግዙ የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍ፣ ለማስተዋወቅና ለማስፋት ነው:: ይህን ለማሳካትም የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የተለያዩ ድጋፍና ክትትሎችን በማድረግ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የማበረታታት ሥራ እየሠራ ይገኛል:: ለአብነትም በንግድ ትርዒቱ ሴት አምራቾች በነፃ መሳተፍ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል:: ይህም ከማበረታቻዎቹ መካከል የሚጠቀስ ነው::
የንግድ ትርዒቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ከ52 አገራት ከመጡ ኩባንያዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟን አቶ ውቤ አስታውቀዋል:: ኢትዮጵያ ከእነዚህ አገራት ጋር መረጃ በመለዋወጥ እንደዚህ ዓይነት ዓለም አቀፍ የሆኑ የንግድ ትርዒቶች ሲዘጋጁ የተለያዩ የውጭ አገራት ኩባንያዎች እንዲሳተፉ፤ ኢትዮጵያውያንም በውጭው ዓለም የንግድ ትርዒት መሳተፍ የሚችሉበት የአሠራር ሥርዓት ስለመኖሩም ተናግረዋል:: ኢትዮጵያ ከአብዛኞቹ አገራት ጋር ጥሩ የሚባል የንግድ ትስስር የፈጠረች በመሆኑ የኢትዮጵያ አምራቾች በተለያዩ አገራት በሚያደርጉት የንግድ ትርዒት ተሳትፎ የተሻለ ገበያ ማግኘት እንደቻሉና የንግድ ትስስሩን ማሳለጥ እንደተቻለም ተናግረዋል::
ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ከስሙ መረዳት እንደሚቻለው ማሳያ ነው:: የሚሉት አቶ ውቤ፤ ኤግዚቢሽኑ የኢትዮጵያን ምርቶች በስፋት ያሳያል እንጂ ሸማቹ መግዛት እንዲችል ብዙም ዕድል አይሰጥም:: ይሁንና አልፎ አልፎ ሽያጭ ሊኖር እንደሚችል ገልጸው ምርቶቻቸውን እያስተዋወቁ ጎን ለጎን ለሸማቹ መሸጥ እንዲችሉ የተፈጠረ ዕድል ስለመኖሩም ተናግረዋል::
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ሊያስተዋውቁ በሚችሉ ማንኛቸውም ተግባራት ሚዲያው ትልቅ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ በተለየ መንገድ ሊሠራበት ይገባል ብለዋል:: የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ በጋራ መሥራት እንደሚገባ ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያን ምርቶች ለማስተዋወቅ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ከሚዲያው ጋር ተናብበው መሥራት እንዳለባቸውና ይህን ተግባራዊ ማድረግ ሲቻል ትርጉም ያለው ውጤት ማምጣት እንደሚቻልም አስገንዝበዋል::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2015