የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ቁንጮ የሆነው የአክሱም ሐውልት በጣሊያን ወረራ ወቅት ከኢትዮጵያ ምድር ከነበረበት ተነስቶ ወደ ጣሊያን ተወስዶ እንደነበር ይታወሳል። ይህን ታሪካዊ ቅርስ ለማስመለስ ከብዙ ዓመታት በኋላ በ80ዎቹ መጨረሻ እና በ90ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ስኬታማ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመፍጠር ሐውልቱ ዳግም ወደ አገሩ እንዲመለስ ተደርጓል።
ስለዚህ ጉዳይ በአዲስ ዘመን ምን ዓይነት ዘገባዎች ወጥተው ነበር፤ ከእነዚህ ዘገባዎች መሃልም አንዱን ለትውስታ በዚያው በ90ዎቹ መጀመሪያ ላይ የአገር ዋርካ የሆነው አንድ ግዙፍ ፋብሪካ በኪሳራ ሳቢያ ለመዘጋት ቋፍ ላይ ከደረሰበት በድጋሚ ነፍስ ዘርቶ ለትርፋማ ስኬት በቅቷል። በትግራይ ክልል ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል ተገልጾ ነበር። ጫት አደንዛዥ እጽ ነው? ምሁራኑን እርስ በእርስ ያከራከረ ጥያቄ…እነዚህንና ሌሎችንም ከአዲስ ዘመን ድሮ ልናስታውስ ወደናል።
የአክሱም ሐውልት አስመላሽ የቴክኒክ ቡድን ወደ ሮም ይሄዳል
የአክሱም ሐውልት ብሔራዊ ኮሚቴ የቴክኒክ ቡድን ሐውልቱ ወደ አገሩ የሚመለስበትን ሁኔታ ለማጥናት ሰሞኑን ወደ ሮም እንደሚንቀሳቀስ በቅርስና ጥናት ድርጅት የአርኪዮሎጂ እና አንትሮፖሎጂ መምሪያ ትናንት አስታወቀ።
የአክሱም ሐውልት አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ የቴክኒክ ቡድን አባልና የአርኪዮሎጂና አንትሮፖሎጂ መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ዮናስ በየነ በማስታወቂያና ባህል ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ የቡድን አባላቱ በሚያደርጉት ጉዞ የአክሱም ሐውልት ወደ አገሩ ተመልሶ ጥንት በነበረበት ሁኔታ የሚተከልበትና የአሠራር ስልት ያጠናል።
የጣሊያን ወገን የአክሱም ሐውልት ወደ አገሩ ባለበት ሁኔታ እንዲመለስ ኃላፊነቱን ኢክሮም ለሚባለው ዓለም አቀፍ የቅርሶች ጥገናና እንክብካቤ ጥናት ማዕከል የሰጠ መሆኑን ማዕከሉም ተገቢውን በመጀመር ሐውልቱ በሚመለስበት ሁኔታ የቅድመ ተግባራት ክንዋኔ ሰነዶችን አዘጋጅቶ ወደ ኢትዮጵያ መላኩን ዶ/ር ዮናስ አስረድተዋል። (አዲስ ዘመን ነሐሴ 23 ቀን 1990ዓ ም)
በደረሰበት ኪሣራ ሊዘጋ የነበረው ፋብሪካ አትራፊ ሆነ
ከአራት አመት በፊት ለሁለት ተከታታይ የበጀት ዓመት በደረሰበት ኪሳራ ሊዘጋ የነበረው የቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት የ41 ሚሊዮን ብር ካፒታል ባለቤትና አትራፊ ለመሆን በቅቷል ሲሉ የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።
ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ማቴዎስ አሰሌ እንደተናገሩት በ1984 እና 85ዓ.ም . የ3 ሚሊዮን 700 ሺ ብር ኪሳራ ደርሶበት እንደነበር አስታውሰው፣ ባለው ሕግ መሠረት መዘጋት ከነበረበት ሁኔታ በመነሳት በየዓመቱ መሻሻል በማሳየት ትርፋማነቱን አጠናክሮአል።(አዲስ ዘመን ጥቅምት 14 ቀን 1990ዓ/ም)
ጫት ከአደገኛ መድኃኒቶችና ዕጾች ይመደባል?
ጉዳዩ የጤና ባለሙያዎችን እያከራከረ ነው
ጫት አነቃቂ ከሆኑት ከሻይ፣ ከቡናና ከአልኮል እንጂ ከአደገኛ መድኃኒቶችና ዕጾች ጋራ አይመደብም ሲሉ በመስኩ ጥናት ያደረጉ ምሁር አስታወቁ። አንድ የጤና ጥበቃ ኤክስፐርት ደግሞ ጫት ከአደገኛ መድኃኒቶችና ዕጾች እንደሚመደብ ገለጹ።
ዶ/ር መኮንን ሀጎስ፣ በመመኮ የተባለው የግል ድርጅት አማካሪ ሰሞኑን ለጋዜጣዊ ሪፖርተር በሰጡት መግለጫ ጫትን ጨምሮ በአንድ ሺ አምስት መቶ ዕጽዋት ላይ ጥናት ሲያደርጉ መቆየታቸውንና በጥናታቸውም ጫት ከአደገኛ መድኃኒቶችና ዕጾች ሊመደብ እንደማይችል ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
ማንኛውም ነገር ከመጠን በላይ ከተወሰደ ጎጂነት እንዳለው የገለጹት ዶ/ር መኮንን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የአደገኛ መድኃኒቶችና ዕጾች መቆጣጠሪያ፣ መከላከያ ቡድን ከፍተኛ ኤክስፐርት የሆኑት አቶ አብርሃም ገብረጊዮርጊስ ጫትን ከካናቢስና ኮኬይን ጋር ይመደባል በማለት ለመገናኛ ብዙኃን በቅርቡ የሰጡት መግለጫ የተሳሳተ ነው ብለዋል። ጫትን ከአደንዛዥ ዕጾች መመደብም ፍጹም ኢሳይንሳዊ መሆኑንም አስምረውበታል። (አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 29 ቀን 1990ዓ/ም)
በትግራይ የምግብ እጥረት ይከሰታል ተባለ
መቀሌ(ዋኢማ)፡- በትግራይ ክልል በሚገኙ ሁለት ዞኖች የበልግ ምርት በመቀነሱ የምግብ እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችል ተገለፀ።
ማህበረ ረድኤት ትግራይ (ማረት) ባለፈው ሐሙስ ባሰራጨው የእርዳታ ጥሪ እንደገለፀው የተሻለ የዝናብ መጠን በሚታይባቸው ዓመታት እንኳን ሳይቀር አጥጋቢ ምርት የማይመዘገብበት ምሥራቃዊ ዞንን ጨምሮ በምርታማነቱ በሚጠቀሰው ደቡባዊ ዞን ሦስት ወረዳዎችና ሌሎች ጣቢያዎች በድርቅ በመመታታቸው የምግብ እህል እጥረት ሊያጋጥም ችሏል። እንደማህበሩ ገለጻ በራያና አዘቦ፣ በአላማጣ፣ በሳምራ ዝቅተኛ ቦታዎች፣ በእንዳመሆኒና በህንጣሎ ዋጅራት ጣቢያዎች እንዲሁም በማዕከላዊ ዞን በሚገኙ በአበርጋሌ፣ በወሬይሌህና በመረብሌህ ወረዳዎች የሚገኙ አርሶአደሮች ባጋጠማቸው የግጦሽና የውሃ እጥረት በሺ የሚቆጠሩ ከብቶቻቸው በመሞታቸው ለስደት እየተጋለጡ ይገኛሉ። (አዲስ ዘመን መስከረም 10 ቀን 1990 ዓ/ም)
ዥንጉርጉር ጥገና
በድሬዳዋ ከተማ በቤቶች አስተዳደር ስር የሚገኙ የቤቶች እድሳት በሰፊው ቀጥሏል። አሠራራቸው በአንድ ጣሪያ ስር ሆኖ በመንግሥት ስር የሆነው ኪራይ ቤቶች ሲጠገን በቀበሌ ስር ያሉትን ግን መለስ ብሎ የሚያያቸው ባለመኖሩ የአንድ አካል ሁለት መልክ ማለትም እድሳትና እርጅና ተጣምሮ ይታይባቸዋል።
ስለሆነም በአንድ ጣሪያና ግርግዳ ስር ያሉ ቀደም ሲል የአንድ ግለሰብ የነበሩ ቤቶች በመንግሥትና ቀበሌ ከሚያዙ ይልቅ የገቢያቸው መጠን ተዳምሮ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ውለው ተገቢውን ጥገናና እድሳት ቢደረግላቸው ወይም ቀበሌዎች የጥገናውን ሥራ ከመንግሥት ጋር በማራመድ የቤቶች እንክብካቤ መጠበቅ አለባቸው እንጂ ውሎ አድሮ ችግርን እንደሚያስከትል አያጠራጥርምና ይታሰብበት።
ከድሬዳዋ ታዛቢ
(አዲስ ዘመን ኅዳር 7 ቀን 1988ዓ/ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2015