አዲስ ዘመን ድሮ

በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ አምዳችን በአንጋፋው ጋዜጣ በ1960ዎቹ አጋማሽ ለንባብ የበቁ የተለያዩ ዘገባዎችን መርጠናል፡፡ ለማስታወስ የመረጥናቸው ርዕሰ ጉዳዮች በዚያ ዘመን መሠረታዊ የነበሩና ዛሬ ላይ ሆነን ያንን ጊዜ የሚያሳዩን ናቸው፡፡

የቅድመ ታሪክ አጥኚ ጓድ በ3 ጠ/ግዛቶች ይሰማራል

አዲስ አበባ፣ (ኢ•ዜ•አ•) ከልዩ ልዩ የባህር ማዶ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ አርኪዎሎጂስቶችና ሳይንቲስቶች የሚገኙበት አንድ የቅድመ ታሪክ አጥኚ ጓድ በሀረርጌ፣ በአሩሲና በሸዋ ጠቅላይ ግዛቶች እየተዘዋወረ የጥናት ስራ በቅርቡ የሚጀምር መሆኑ ትናንት ተገለጠ።

የጥንታዊያን ታሪኮች ቅርስ አስተዳደር የአርኪዎሎጂ መምሪያ በሰጠው መግለጫ ከልዩ ልዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡት ምሁራን የቅድመ ታሪክ ጥናት ለማድረግ አዲስ አበባ መግባታቸውን ገልጦ፤ ጥናቱም ለሶስት ወሮች የሚካሄድ መሆኑን አስረድቷል።

የጥናት ጓዱም “የአፍሪካ ቀንድ ባህላዊ ቅድመ ታሪክ” የተሰኘውን መጽሐፍ በደረሱት በፕሮፌሰር ጄ• ዴሞንድ ክላርክ የሚመራ ሲሆን፣ እኚሁ ምሁር በተለያዩ የአፍሪካ ክፍሎች የሰሩና በርከት ያሉ የጥናት ጽሑፎችን ያዘጋጁ ታዋቂ ሰው እንደ ሆኑ መግለጫው አስረድቷል።

አርኪዎሎጂስቶቹና ሳይንቲስቶቹ የሚመጡት ከካሊፎርኒያ፣ ከኬምብሪጅ፣ በአውስትራሊያ ከሚገኘው ከማክኳሪ ዩኒቨርሲቲዎች ሲሆን፤ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲም ሚስተር ኢስማኤል ሁሴን ከጓዱ ጋር አብረው በጥናቱ ስራ ተካፋዮች እንደሚሆኑ ተገልጧል።

ጥናቱ የሚካሄድባቸው በደቡባዊው የአፋርና የአዋሽ ግዛት፣ በአዋሽ ብሄራዊ ክልል፣ በድሬዳዋና በገዋኔ፤ እንዲሁም በሀረርጌና በአሩሲ መካከል በሚገኘው ጎብታማ ግዛት መሆኑን በመግለጫው አመልክቷል።

ጥናቱ የሚካሄድባቸው እነዚሁ ስፍራዎች የኢትዮጵያን ረባዳ ሸለቆንና ከፍታ ያላቸውን መሬቶች የሚይዙ ቀበሌዎች መሆናቸውንና ጥናቱም በቀበሌዎቹ በቅድመ ታሪክ ለዘመናት ሰዎች ሰፍረውበት የነበረውን ስፍራ ለይቶ ለማወቅ የሚረዳ በመሆኑ በዚያን ጊዜ የኖሩት ሰዎች ምን አይነት ህይወትና የአኗኗር ዘዴ ይመሩ እንደ ነበር ማረጋገጫን ሊሰጥ እንደሚያስችል አረጋግጧል።

ከዚህም በቀር በእነዚሁ ስፍራዎች የሚኖሩት ሰዎች፣ ለምግቦቻቸው ያውሏቸው የነበሩትን እፅዋትና እንስሳት አፅም ፈልጎ ለማግኘት ጥናቱ እንደሚረዳ ከመግለጫው የተገኘው ዜና አመልክቷል።

ከዚህም ሌላ ጥናት ጓዱ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ከጊዜው ጋር ያሳየውን ለውጥ፣ በተለይም ከአደንና እፅዋትን ከመሰብሰብ አንስቶ ለምግብ የሚሆኑ እህሎችን በእርሻ ማብቀል እስከ ተጀመረበት ድረስ ያሉትን ሁሉ ለውጦች ለይቶ ለማወቅ ምርመራና ጥናት እንደሚያካሂዱ ተገልጧል። (ጽሑፉ ይቀጥላል • • •)

(አዲስ ዘመን፣ ታህሳስ 26 ቀን 1966 ዓ•ም)

ብርሀንና ሠላምና ሠራተኞቹ የኅብረት ውል ተፈራረሙ

የብርሀንና ሠላም ማተሚያ ቤት የአሰሪው ወገንና የሠራተኞች ማህበር ለሶስት አመት የሚቆይ የህብረት ስምምነት በትናንትናው እለት በህዝባዊ ኑሮ እድገትና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በተደረገው ሥነሥርአት ተፈራርመዋል።

በህዝባዊ ኑሮ እድገት ሚኒስቴር በተደረገው የጋራ ስምምንት መፈራረም ሥነሥርዓት ላይ የአሰሪና የሠ ራተኞች ጉዳይ የቦርድ ሊቀ መንበር ክቡር ፊታውራሪ ደምሴ ተፈራና ሌሎችም ከፍተኛ ባለ ስልጣኖች ተገኝተዋል። ከጥቅምት 1 ቀን ጀምሮ በስራ ላይ የሚውለውን ይህንን ስምምነት የፈረሙት በማተሚያ ቤቱ ስም አቶ አባተ ልመንህ የብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ሲሆኑ፣ ከሠራተኞቹ ወገን ደግሞ የማተሚያ ቤት ሠራተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ክፍሌ ተስፋጽዮን ናቸው።

ክቡር ፊታውራሪ ደምሴ ተፈራ ሁለቱ ወገኖች ስምምነቱን በተፈራረሙበት ወቅት በተናገሩት ቃል፤ በመካከላችሁ ሶስተኛ ቡድን ሳይገባና አስማሚ ሳያስፈልጋችሁ በመግባባት የህብረት ስምምነቱን እዚህ ደረጃ ስላደረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ካሉ በኋላ፣ ይህ ድርጊት ሌሎች ሊከተሉት የሚገባ መልካም አርአያ ነው በማለት ወደፊትም በመካከላቸው ሊፈጠር የሚችል ውዝግብ ቢኖር እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ በቅን መንፈስ በመወያየት ተስማምተው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሠራተኞች ማህበር የተቋቋመው በ1959 ዓ/ም ሲሆን፣ ከአሰሪው ጋር የህብረት ስምምነት ሲፈራረም የአሁኑ የመጀመሪያ ጊዜው ነው። በመካከሉ በተፈጠሩት አንዳንድ ምክንያቶች ማህበሩ ከፈረሰ በኋላ ከአንድ አመት በፊት እንደገና የተቋቋመ መሆኑን የማህበሩ ፕሬዚዳንት አስረድተዋል።

ማህበሩ ባዘጋጀው የህብረት ስምምነት ረቂቅ መሰረት፣ በሳምንት ሁለትና ሶስት ቀን በመደራደር ያለ ብዙ ጭቅጭቅ ሁለቱ ወገኖች ስምምነት ላይ ለመድረስ ሁለት ወር ብቻ የፈጀባቸው መሆኑን አቶ ክፍሌ ገልጠዋል። በተጨማሪ ማህበሩ በአሁኑ ጊዜ ሶስት መቶ የሚደርሱ አባል ማህበርተኞች እንዳሉት አስረድተዋል።

(አዲስ ዘመን፣ ታህሳስ 4 ቀን 1966 ዓ•ም)

አንድ ጥያቄ አለኝ

ስለሺ መኮንን፣ ከጎንደር:-

በጎንደር ከተማ አዲስ ጋዜጣ ተቋቁሟል። በወር አንድ ጊዜ ይታተማል። እንዳይቋረጥ አበርታልን። ጋዜጣውንም አብሬ ልኬልሀለሁ።

*አየሁት። እደግ ተመንደግ የሚያሰኝ ነው። ጋዜጣውን እንዳነበብኩት ይህን ያህል አጥጋቢ ወሬ ባይኖረውም ጀማሪ ነውና አጀማመሩም ቢሆን የሚያስደስት ነው። አንድ ይልቅ ደስ ያላለኝ ነገር አለ። “ጋዜጣው በ10 ሳንቲም ተሸጦ ራሱን እንደሚችል ተስፋ አለን” ይላል። በዚህ አይነት ሁኔታ ማለት እራሱን እናስችላለን በሚል ሁኔታ የተቋቁሞ እንደ ሆነ እድሜው የሚረዝም አይመስለኝም። በየትም አገር ቢሆን በራሱ ሽያጭ ብቻ ራሱን የሚችል ጋዜጣ የለም። ብዙ ማስታወቂያዎች እንዲወጡበት ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ማስታወቂያ በጎንደር በብዛት የሚገኝ አይመስለኝም። ስለዚህ ጋዜጣውን የጎንደር ማዘጋጃ ቤት ለጋዜጣው ነዋሪ የሆነ በጀት ሊቆርጥለት ይገባል። ገቢም ቢገኝ ለራሱ እየወሰደ ሲሆን ለስራው ማስፋፊያ እየተወለት ቢሄድ መልካም ይመስለኛል። እንዲህ በየጠቅላይ ግዛቱ አንዳንድ ጋዜጦች ብቅ ሲሉ የመሻሻል ምልክት ከመሆኑም ሌላ እጅግ የሚያስደስት ነውና ሌሎቹስ ጠቅላይ ግዛቶች እንዴት ናቸው? በማተሚያ ቤት ማሳበብ መቼም አይቻልም። አሳቡ ካለ አዲስ አበባ እየታተመ ሊደርስ ይችላልና ነው። ጎንደሮች፣ ጋዜጣችሁን ሁሉንም የሚያስንቅ አድርጉት።

ፓውሎስ ኞኞ:-

(አዲስ ዘመን፣ ታህሳስ 6 ቀን 1966 ዓ•ም)

የአዳጊ አገሮች የሲኒማ በአል አልጀርስ ተጀመረ

አልጀርስ፤ አንድ ሳምንት የሚቆየው የአዳጊ አገሮች የሲኒማ በአል አልጀርስ ከተማ ውስጥ የተጀመረ መሆኑ ተገለጠ። በአሉን በሊቀመንበርነት እንዲመሩ የተመረጡት የአልጄሪያ ፊልም ሰሪ የሆኑት ላሚኒ መርባህ ሲሆኑ፣ የሴኔጋሉ ሴሚባ ኡስሜነረና የኩባንያው ሴኞር ሳንቲያጎ አልሻሬዝ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል።

የአዳጊ አገሮች ፊልም ሰሪዎች፣ አቅራቢዎች፤ በዚህ በአል ላይ የተገኙ የፊልም ስራዎቻቸውን የሚመለከቱ ጉዳዮችን እንደሚመረምሩ ታውቋል። ከሚመረምሯቸው ጉዳዮች መካከል ስለ ፊልም ማከፋፈል ችግር ጉዳይ እንደሚነጋገሩ ታውቋል። ብዛታቸው ከፍ ያሉ በአዳጊ አገሮች የተሰሩ ፊልሞች በበአሉ ላይ እንደ ታዩ ታውቋል።

(አዲስ ዘመን፣ ታህሳስ 4 ቀን 1966 ዓ•ም)

ግርማ መንግሥቴ

 

አዲስ ዘመን ህዳር 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You