የሳይበር ጥቃት መሠረት የሚያደርገው ቴክኖሎጂን በመሆኑ ቴክኖሎጂ እያደገ በመጣ ቁጥር የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትም እያየለ ይመጣል። አገሮች ይህን ጥቃት ለመከላከል እየሠሩ ቢሆንም፣ ጥቃቱ የሚያደርሰው ጉዳትና እያስከተለ ያለው ስጋትም እየጨመረ መሆኑ ይገለጻል። የሳይበር ጥቃት በተለያየ መልኩ የሚካሄድ ነው። ይህን ጥቃት ለመከላከል ዘመኑ የሚፈልገውን ቴክኖሎጂ መታጠቅን ይጠይቃል፤ ይህን ቴክኖሎጂ መታጠቅ እስካልተቻለ ድረስ ጥቃቱ በዚያው ልክ እየጨመረ እንደሚመጣ መረጃዎች ያመላክታሉ።
አገራችን ኢትዮጵያም የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል ብዙ እየሠራች ትገኛለች። በአገራችን በ2015 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ውስጥ የተከናወነው የሳይበር መከላከል አስመልክቶ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ አስተዳደሩ በ2015 በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ውስጥ የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት ስጋትና አደጋ ለመከላከል በሦስት ደረጃ (በስትራቴጂ፣ በታክቲካልና በኦፕሬሽን) የዳሰሳ ጥናቶችን ሠርቷል።
በዚህ መሠረት የተሠሩት ሥራዎችና የዳሰሳ ጥናቶች በሦስት መሠረታዊ እይታዎች የተቃኙ ናቸው። እነዚህም የመጀመሪያ እይታ የሰው ኃይል (ተቋማት ሥራቸውን ለመሥራት የሰው ኃይል፣ ከአመራር እስከ በታች ሠራተኛው ድረስ) ፣ ሁለተኛው ተቋማት በታጠቁት ቴክኖሎጂ ላይ የሚፈጸም ክፍተት ወይም ተጋላጭነት ( የሳይበር ጥቃት)፣ ሦስተኛው ተቋማቱ የአሠራር ሥርዓታቸውንና ያላቸውን ሀብት ከመጠበቅ አንጻር ምን ያህል የተጠበቁ ናቸው የሚሉት የተካተተበት ሥራ ነው የተሠራው።
የዳሰሳ ጥናቱ የተለያዩ መንገዶችን በመከተል የተከናወነ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ መደበኛ፣ ታቅዶ በየጊዜው የሚሠራ ሥርዓትን በመከተል፣ ድንገተኛ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ እና ከደንበኞች በሚመጡ ጥያቄዎች በተመለሱ ምላሾች መሠረት የዳሰሳ ጥናት መደረጉን ነው ያብራሩት። የዳሰሳ ጥናቱ ትኩረት ያደረገው የሳይበር ደህንነት ስጋት/Threat/፡- የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት/Vulnerabilities/ እና የሳይበር ደህንነት አደጋ/Risk/ ላይ ነው።
በሳይበር ደህንነት ስጋት/Cyber Security Threat/በዘጠኝ ወራት ውስጥ ዳሰሳ የተደረገባቸው የአደጋው ሰለባ ሊሆኑ የሚችሉት ወይም የሆኑት ተቋማትና ዘርፎች በአጠቃላይ ሲታይ ቁልፍ መሠረተ ልማቶችና መሠረተ ልማቶችን የሚያስተዳደሩ ተቋማት፣ ቁልፍ የመንግሥት ተቋማትና የሚኒስትር መስሪያ ቤቶችና የክልል ቢሮዎች እንዲሁም ባንኮችና የፋይናንስ ተቋማት፣ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት፣ የሚዲያ እንዲሁም የሕክምና ተቋማትና የከፍተኛ የመንግሥት ትምህርት ተቋማት ናቸው።
የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት/ Cyber Security Vulnerabilities/ በዘጠኝ ወር ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ 80 የመንግሥትና የግል ተቋማት የኦዲትና የግምገማ (ኢቫይሌሽን ) ሥራ የተሠራ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 34ቱ የመንግሥትና 46ቱ የግል ተቋማት ናቸው።
የሳይበር የተጋላጭነት ዳሰሳው በሰው ኃይላቸው፣ በታጠቋቸው ቴክኖሎጂዎችና የአሠራር ሂደታቸው ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። ከተደረገው ኦዲት አንጻር 486 የሳይበር ተጋላጭነት ክፍተቶች ተገኝተዋል ሲሉም ተናግረዋል። ከተገኙት ክፍተቶች መካከል 129 የሚሆኑ የሳይበር ወንጀለኞች ይህንን ክፍተት አግኝተው ቢሆን ኖሮ በጣም ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ተጋላጭነቶች ነበሩ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ 217 መካከለኛ የሚሆኑ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ተጋላጭነቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፤ 140 የሚሆኑ ዝቅተኛ ደረጃ ያላቸው ተጋላጭነቶች ተገኝተዋል ብለዋል።
እነዚህ ከፍተቶች ከፍተኛ የሙያ ክህሎት በመጠቀም የተገኙ መሆናቸውንም ጠቅሰው፣ ተቋማቱ በተመሳሳይ ክፍተቶች በሕገወጦች ወይም በሳይበር ወንጀሎች እጅ እንዳይወድቁና ወዲያውኑ ክፍተቶቹ እንዲሞሉ ይደረጋል ብለዋል። በዚህ መሠረት የተለያዩ እርምት እርምጃዎች ተቋማቱ እንዲወሰዱ ተደርጎ ሊደርስ የሚችለውን ከፍተኛ ጉዳት ማስቀረት ተችሏል ሲሉም አስታውቀዋል።
የሳይበር ደህንነት ስጋት/cyber security Threat/፡-
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 4ሺ422 የሳይበር ጥቃቶች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ ውስጥ 4ሺ272 የመከኑ ጥቃቶች ሲሆኑ፤ በዚህም የሳይበር ወንጀለኞቹ ያቀዱት ሳይፈጸም ቀርቷል። 150 የተሳካ የሳይበር ጥቃቶች ተፈጸመዋል። የሳይበር ደህንነት ስጋትን ከመከላከል አንጻር 94 ነጥብ86 በመቶ ጥቃቱን መከላከል ተችሏል።
የደረሱት የጥቃት ዓይነቶችና የተሳካ ሙከራ፣ ያልተሳካና የመከነ ሙከራን ስንመለከት በዘጠኝ ወር ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የተመዘገበው የሳይበር ጥቃት የድህረ ገጽ ጥቃት ነው ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። በድህረ ገጽ ጥቃት 19 የተሳኩ ሙከራዎች ፣ 1ሺ665 የመከኑ ሙከራዎች መደረጋቸውን ጠቅሰው፣ በአጠቃላይ 1684 የጽረገጾች ጥቃት ተፈጽሟል ብለዋል።
በሁለተኛ ደረጃ የደረሰው የማልዌር ጥቃት መሆኑን አመልክተው፣ በዚህም 24 የተሳካ ጥቃት፣ 845 የመከኑ ጥቃቶች፣ በድምሩ 869 ጥቃቶች ደርሰዋል ሲሉ ተናግረዋል። ይህም በአጠቃላይ በአገሪቱ ላይ ከተቃጡ የሳይበር ጥቃቶች አንጻር ስታይ 24ነጥብ 27 በመቶኛ እንደሚይዝ አስታውቀዋል።
የመሠረተ ልማት ማቋረጥ የጥቃት ዓይነት ሲታይ፤ አንድ የተሳካ ጥቃት ተፈጽሟል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ 265 የመከኑ ጥቃቶች መሰንዘራቸው መመዝገቡንም ገልጸዋል። በሰርጎ መግባት ሙከራ ምንም የተሳካ ጥቃት እንዳልተመዘገበም ጠቅሰው፣ 422 የተመከቱ ጥቃቶች መፈጸማቸውንም ተናግረዋል።
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ሌሎች የተለያዩ ጥቃቶችን ( የኢሜልና በማህበራዊ ሚዲያ የሚደረጉ ጥቃቶች) ስንመለከት 106 የተሳኩ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። በዚህ ረገድ የመከነ ጥቃት የለም። ይህም ጥቃት የተፈጸመው ከሳይበር ጥቃት ግንዛቤ እጥረት፣ የንቃት ህሊና ጉድለት እና በሰዎች የአጠቃቀም ክፍተት ነው።
በአጠቃላይ በእነዚህ ሳይበር ጥቃቶች ምክንያት ከደረሱት ጉዳቶች ውስጥ ጥቃቶች ኢላማ ያደረጓቸው ተቋማትና ሀብቶች የማጨበርበር ድርጊቶች፣ በማህበራዊ ሚዲያ ስም የማጥፋት፣ አካውንት የመንጠቅና ገንዘብ የመሰብሰብ፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሰበሰቧቸው ዳታ ቤዞች በመያዛቸው ምክንያት የተስተጓጎሉ ዜጎች፣ የሥራ ሂደቶች መራዘም ፣ የዜጎች መንገላታት በዚህ ምክንያት ሥራ ላይ ያልዋለ ጊዜ እና የመሳሰሉት ጉዳቶች በአገሪቱ ተመዝግበዋል።
የሳይበር ጥቃቱ የሚያደርሰው ጉዳት ከመከነው አንጻር ሲታይ ጥቂት ቢሆንም፣ የተወሰነ በገንዘብ የሚገመት ኪሳራ መድረሱም ተገልጿል። በጥቂት ሚሊዮኖች የሚገመት ጉዳት ሊያደርስ መቻሉ ተጠቁሟል።
በዚህ በጀት ዓመት በሳይበር ጥቃት የተፈጸሙ ጥቃቶች ከክብደት አንጻር ሲታዩ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ሩብ ዓመት ያሉትን ስንመለከት በሦስቱ ሩብ ዓመቶች የደረሱት ጥቃቶች ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲታዩ ቁጥሩ በተወሰነ መልኩ መቀነስ ቢያሳይም፣ የጥቃት ዓይነቶችና ኢላማ ካደረጓቸው ተቋማት አንጻር ሲታይ ግን ከፍተኛ ለውጥ አሳይቷል ሲሉ አስታውቀዋል።
የጥቃቱን ክብደት በሚያደርሱት ጉዳት ስንመዝናቸው 38 በመቶ በጣም ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶች ተመዝግበዋል ሲሉ ገልጸው፣ 38 በመቶ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶች መስተናገዳቸውንም ነው የጠቀሱት። 24 በመቶ መካከለኛ የሳይበር ጥቃቶች መስተናገዳቸውን ተናግረው፣ ዝቅተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ጥቃቶች እንዳልተፈጸሙም ጠቁመዋል። የጥቃቶቹ ብዛት ሳይሆን ሊያደርሱት የሚችሉት ጉዳት በጣም ከፍተኛ እንደነበር ጠቅሰዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ እነዚህ ጥቃቶች ቢደርሱ ኖሮ መሠረተ ልማቶች ማቋረጥ ይችሉ ነበር። ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ለተወሰነ ጊዜያት የማቋረጥ ወይም የማስተጓጎል ሥራዎች በማድረስ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተፅእኖ በማሳደር ገቢን ማስተጓጎል ይችሉ ነበር። የዳታዎች መሰረቅና መጥፋት ያስከትል ነበር፣ ዳታዎች በመመስጠር የቤዛ ክፍያን ይጠይቅ ነበር። እንዲሁም የግንኙነት መንገዶችን በመጥለፍና የክፍያን መንገድ በመጠቀም ገንዘብ በማጨበርበር መውሰድ ይቻልም ነበር።
የመረጃ እና የመገናኛ ቴክኖሎጂ ቁጥጥር
የኢንፎርሜሽንና መረጃ ደህንነት አስተዳደር ወደአገር ውስጥ በሚገቡና ከአገር በሚወጡ የመረጃ እና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች ላይ ቁጥጥሮችን ያደርጋል። በተለያየ መልኩ በአገሪቱ በሚገኙ ኬላዎች ላይ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ይሠራል። የተለያዩ ጥቆማዎችንና መረጃዎችን መሠረት በማድረግ ድንገተኛ ምልከታ፣ ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል።
እነዚህ የመገናኛና የኮሙኒኬሽን (የመረጃ) ቴክኖሎጂ በግለሰቦች ወይንም ባልተገባቸው ሰዎች እጅ ቢገቡ አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የደህንነት አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ። እነዚህን ከመከታተልና ከመመከት አንጻር ከፍተኛ የሆነ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ ሲሠራ ቆይቷል።
በዚህ መሠረት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ፍቃድ ከተጠየቀባቸው 3 ሺ 123 የተለያዩ ዓይነት ቴክኖሎጂዎች ውስጥ 453 የሚሆኑት የደህንነት ስጋት የሚያስከትሉ በመሆናቸው አደገኛ ተብለው ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ተደርጓል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሰለሞን አስታውቀዋል። በከፊል ውል ፈርመው የተፈቀደላቸው 16 መሆናቸውንና ፍቃድ ያገኙት ደግሞ 2691 መሆናቸው ተጠቁሟል።
የሳይበር ደህንነት አደጋ/cyber security Risk/
በአገር አቀፍ ደረጃ የሳይበር ጥቃት ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ደረጃ ምን ሊሆን ይቻላል የሚለው ተተንትኗል። ይህም አገር አቀፍ የሳይበር አደጋ ስጋት በተመረጡ አራት ዘርፎች ተመላክቷል። በሚዲያ፣ ጤና፣ የጸጥታና ደህንነት እንዲሁም ቁልፍ መሠረተ ልማት አካባቢ ያሉ ተቋማት ላይ ትኩረት በማድረግ የሳይበር ደህንነት ስጋትና ተጋላጭነትን በማጣመር ብሔራዊ የሳይበር ደህንነት አደጋ ያመላከተ ትንተና ተሠርቷል።
ለአብነት ያህል የሚዲያ ተቋማትን ብንመለከት በስምንት ተቋማት ላይ የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል፤ በዚህም ከሰው ኃይል፣ ከቴክኖሎጂና ከአሠራር ሥርዓት አንጻር በተደረገ ምልክታ ሲታይ ሊደርስ የነበረው የአደጋ ደረጃ ከፍተኛ ነው። አደጋው ሊያደርስ ከሚችለው ተፅእኖ አንጻር ሲታይ በተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ላይ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ሕጋዊ ኪሳራዎች ሊያደርሱ የሚችሉ ናቸው። በእነዚህ የሚዲያ ተቋማት ላይ የስጋት ምንጮች (ተዋናይ) የሚባሉት አንቂዎች (አክቲቪስቶች) ፣ ሁለተኛ በመንግሥታት የሚደገፉ አካላት እና ያኮረፉ ወይም አጀንዳ ያነገቡ ሠራተኞች ናቸው። እነዚህ ተዋንያን ይዘውት የተነሱት አላማ ፖለቲካዊ አንድምታና የገንዘብ ፍላጎትም ያለው መሆኑና ዝናን በመሻት የሚመለከት አላማን አንግበው እንደተንቀሳቀሱ የዳሰሳ ጥናቱ ያሳይል።
በጤናው ዘርፍ በስድስት ተቋማት ላይ ዳሰሳ ተደርጓል። የአደጋ ደረጃቸውም እንዲሁ ከፍተኛ ነው። የደረሰባቸውን ተፅእኖ ስንመለከት የኢኮኖሚ፣ ፖሊቲካ፣ ማህበራዊና ሕጋዊ ነው። ከጤናው ዘርፍ አንጸር የሚታዩት የስጋት ተዋንያን አንቂዎች (አክቲቪስቶች) ፣ በመንግሥታት የሚደገፉ አካላት እና ያኮረፉ ወይም አጀንዳ ያነገቡ ሠራተኞች የተሳተፉበት ሲሆን፣ አንግበው የተነሱት አላማ የፖለቲካ ትርፍ፣ ገንዘብና ዝና ማበላሸት ናቸው።
በፀጥታና ደህንነት አምስት ተቋማት ላይም የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል። የአደጋ ደረጃቸው በሰውና በአሠራር ሥርዓት ሲታይ ከፍተኛ ሲሆን፣ ይሁንና ግን ቴክኖሎጂ ላይ የተሻለ አቅም ስላላቸው መካከለኛ አደጋ መሆኑ ታይቷል። በሚደርሰባቸው ጥቃት የሚኖረው ተፅእኖ ከፍተኛ ሲሆን፣ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካ ተጽዕኖ ይደርስባቸዋል። እንደ ኤጀንት የሚሳተፉት የስጋት ምንጮች ወንጀለኞች፣ አንቂ(ሀክቲቪስቶች)፣ አሸባሪዎች፣ በመንግሥታት የሚደገፉ አካላት፣ ያኮረፉና አጀንዳ ያነገቡ ሠራተኞችም ሚናቸውን የተጫወቱ ሲሆን ፣ ወታደራዊ፣ ፖሊቲካዊ ፣ ማህበራዊ እና ዝናን መሻት አላማ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ናቸው።
መሠረተ ልማት በሚያስተዳደሩ ሁለት ተቋማት ላይ የዳሰሳ ጥናት መደረጉን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ የእነዚህ ተቋማት የአደጋ ደረጃ በሰውና በአሠራር ሥርዓት ሲታይ ከፍተኛ ሲሆን ቴክኖሎጂ ላይ የተሻለ አቅም ስላላቸው መካከለኛ አደጋ የታየባቸው ናቸው። የተፅእኖው ደረጃ ከፍተኛ ሲሆን የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ማህበራዊና ሕጋዊ ተፅእኖ ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል። የስጋት ኤጀንት ወንጀለኞች፣ አንቂ (አክቲቪስቶች)፣ አሸባሪዎች፣ በመንግሥታት የሚደገፉ አካላት፣ ያኮረፉና አጀንዳ ያነገቡ ሠራተኞችም እና ዝና ፈላጊዎች እንዳሉበት ተመላክቷል።
እንደ መውጫ
በአጠቃላይ በሳይበር ጥቃት ከንቃተ ህሊና ጉድለት የተነሳ የተከሰቱ የሳይበር ጥቃቶች መኖራቸውን አቶ ሰለሞን ጠቅሰዋል። እንደ አስተዳደሩ በማህበራዊ ሚዲያዎች በሳይበር የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ሬዲዮ እና የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም በየወቅቱ ንቃተ ህሊና የሚጨምሩ ዜናዎች የሚለቀቁ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እነዚህን መከታተልና ራስን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ተቋማትም እንዲሁ ትኩረት ሰጥተው በየወቅቱ መውሰድ ያለባቸው እርምጃዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
የሳይበር ጥቃት የዲጂታል ሉአላዊነትን የሚጥስ ጉዳይ በመሆኑ የአገር ሀብት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና የተለያዩ ጉዳዮችን የሚያናጋ ዘመኑ የወለደው /መራሽ / ጦርነት በየሴኮንዱ የሚከናወንበት አውድ ነው። ስለዚህ በጥንቃቄና በንቃት መራመድ እንዲቻል እያንዳንዱ ሰው ንቃተ ህሊና ከፍ እንዲል ያስፈልጋል ብለዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል ከጥቃት ሊከላከሉ የሚችሉ የሳይበር ደህንነት ቴክኖሎጂዎችን መታጠቅ ያስፈልጋል። የሳይበር ንቃተ ሕሊና ስልጠናዎችንም መውሰድ ይገባል። እያንዳንዱ ሰው በየስድስት ወሩ የሳይበር ጥቃት ንቃተ ህሊና ስልጠና ካልወሰደ የማህበራዊ ምህንድስና ተጋላጭነቱ እያደገ ነው የሚሄደው። የሳይበር ወንጀለኞች የተለያዩ ቴክኒኮች ስለሚጠቀሙ ዜጎች የንቃተ ህሊና ስልጠና መውሰድ አለባቸው። ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞችና ባለድርሻ አካላትም እንዲሁ ስልጠናውን መውሰድ ይኖርባቸዋል።
የሳይበር ጥቃት ስልጠና በአግባቡ በመወሰድ የሳይበር ጥቃትን መከላከል ካልተቻል ሳይበር የመከላከል አቅማችን እየተዳከመ እንደሚሄድ የሚገልጹት አቶ ሰለሞን፤ ተጋላጭነትን በየጊዜው በመፈተሽና መድፈን ያስፈልጋል ብለዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2015