በውድድር ውጤታማነት ብቻ ስኬታማ መባል እንደማይቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለዚህም ማሳያ የሚሆነውም በአንድ ስፖርት ቋሚና ቀጣይነት ያለው ውጤት አለመገኘቱ ነው። ለአብነት ያህልም ኢትዮጵያ ውጤታማ በሆነችበት አትሌቲክስ፤ በአንድ ዓመት ልዩነት በተካሄዱት የቶኪዮ ኦሊምፒክ እና የኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የተመዘገበውን ውጤት ሰፊ ልዩነት ማንሳት ይቻላል። በአህጉር አቀፍ ውድድሮች በዓመታት ልዩነት የሚገኝ የእግር ኳስ ስፖርት ተሳትፎንም ለአብነት ማንሳት ይቻላል።
ቀጣይነት ያለው ውጤት በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ አለመመዝገባቸው በኢትዮጵያ ስፖርት ከሚታዩ ክፍተቶች መካከል አንዱ ነው። በመሆኑም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር በዚህ ላይ የሚያተኩርና የመፍትሄ ሃሳቦችን የሚያመላክት ጥናት በማዘጋጀት ላይ ይገኛል። ጥናቱም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስፖርት ሳይንስ መምህራን፣ ከስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት፣ ከመገናኛ ብዙኃን እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ 17 ባለሙያዎችን ባካተተ ቡድን እየተከናወነ ይገኛል።
በዚህም በስፖርቱ ወጥ የሆነ ውጤታማነት ላለመመዝገቡ ምክንያቱ ምን ምንድነው በሚል፤ ለስኬታማነትስ ተግዳሮት የሆነው የዝግጅት፣ የስልጠና ግብዓቶች፣ ድጋፍ አለመኖር፣… የሚለውን ለይቶ ለማውጣት እንደሚቻል በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ በቀለ አመላክተዋል። ከጥናቱ
ከሚገኘው ግብረመልስ ባለፈም ባለድርሻ አካላትን በመጋበዝና ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን በማካተትም ስትራቴጂክ እቅድ ይዘጋጃል።
በተጨማሪም ጥናቱ ተለይተው በተመረጡ ስፖርቶች እንዴት ውጤታማ ለመሆን ይቻላል የሚለውንም ያካተተ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል። እነዚህ ስፖርቶችም አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ቮሊቦል፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ እና ብስክሌት ናቸው። በእነዚህ ስፖርቶችም እንደ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎ ማድረግ ብቻም ሳይሆን ውጤት ማስመዝገብ እንዲቻል ታስቦ ነው ጥናቱ የሚካሄደው።
በዓለም አቀፍ ውድድሮች ውጤታማ ለመሆን ከጥናቱ ባሻገር በቅድሚያ የሚከናወኑ በርካታ ተግባራት ይኖራሉ። ዋነኛው ተግባር ተመጋጋቢነት ያለው ሥልጠና ሲሆን፤ የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክት ደግሞ ለሁሉም መሠረት ነው። በመሆኑም ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በተያዘው ዓመት በአዲስ መልክ በ1ሺ269 የሥልጠና ጣቢያዎች ላይ 31 ሺ የሚሆኑ ታዳጊዎችን በ11 የስፖርት ዓይነቶች ለማሠልጠን አቅዶ ነበር። ይሁንና እስካሁን 96 በሚሆኑ ጣቢያዎች ላይ 18ሺ የሚሆኑ ታዳጊዎች ናቸው ወደ ሥልጠና የገቡት።
ይህንንም በመመልከት የሚገመግም በሦስት የተከፈለ ልዑክ በቅርቡ ወደየአካባቢው የሚጓዝ ይሆናል። ይህን በማድረግም ከዚህ ቀደም እንዳጋጠመው ውድቀትን በመጨረሻ ከማመላከት ይልቅ ሂደቱ ምን ይመስላል የሚለውን ለመመዘን እንደሚያስችልም ሥራ አስፈጻሚው ይጠቁማሉ። በሌላ በኩል በመላው አገሪቷ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚና የጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከልን ጨምሮ በጠቅላላው 19 የማበልጸጊያ ማዕከላት ያሉ ሲሆን፤ ግማሽ በሚሆኑት ላይ በባለሙያዎች ምልከታ ተደርጓል። በዚህም ሥልጠናው ምን ይመስላል፣ በምን መልክ ይሰጣል፣ በእርግጥም በሪፖርት ከሚቀርበው ጋር ተመሳሳይ ነው የሚለውን መገምገም እንዲሁም ችግሮቻቸውን ነቅሶ ማውጣት ተችሏል።
በዚህ ግምገማም የተደረሰበት በማበልጸጊያ ማዕከላቱ የሚሰጠው ሥልጠና ተመሳሳይ አለመሆኑ ነው። የሥልጠና አሰጣጡ፣ ሥልጠናው የሚሰጥበት ጊዜ ቆይታ፣ የማሠልጠን ብቃት፣ ወደ ማዕከላቱ ተመርጠው የሚገቡ ሠልጣኞች ያላቸው ተክለ ቁመና፣ … የተለያየ መሆኑ ተረጋግጧል። በተለይ በክልል ያሉ ማዕከላት የተለያየ የገቢ ምንጭ ያላቸውና የብቃታቸውም ልክ የማይገናኝ ነው። በመሆኑም የተገኘውን መረጃ በመተንተንና የአማራጭ ሃሳቦችን በመያዝ የግንዛቤ መስጫ መድረክ ለማዘጋጀት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። ከዚህ ጎን ለጎን መልካም ልምድ ያላቸው ማዕከላት ተሞክሯቸውን ለሌሎች እንዲያካፍሉ ለማድረግ መታቀዱንም ሥራ አስፈጻሚው ጨምረው ገልጸዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2015