በልግ የዝናብ ወቅታቸው የነበሩ በርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎች በቀደሙት አራት አመታት የዝናብ ጠብታ ጠፍቶ በእጅጉ በድርቅ ተጎድተው እንደነበር ይታወሳል። በእነዚህ አመታት ከፊል አርሶ አደሮች መሬታቸው ጦም አድሮ፣ አርብቶ አደሮችም ለከብቶቻቸው የሚያጠጡት ውሃ አጥተው አይናቸው እያየ ከብቶቻቻውን አጥተዋል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችንም ለተረጂነት ዳርጓል። ለአራት ተከታታይ አመታት ያጋጠመው የዝናብ እጥረት በተለይም የኦሮሚያ ክልል ቦረና አካባቢ በእጅጉ ለጉዳት መዳረጉን የመገናኛ ብዙኃንም በተከታታይ ሲዘግቡ ቆይቷል።
የበልግ ወቅት በመጣ ቁጥርም የአካባቢው ህዝብ ዝናብ ሲጥል ጠብታ ውሃን እንዲይዝ ለማድረግ ምክረ ሀሳቦች ሲሰጡ ቆይተዋል። ውሃን ለመያዝ የሚያስችሉ የአነስተኛ ግድቦች ግንባታ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸው አይዘነጋም። የተያዘው የበልግ ወቅትም ከመግባቱ በፊት ጀምሮ በተመሳሳይ ሥራዎች ሲሠሩ ነበር።
በተያዘው የበልግ ወቅት የዝናብ ስርጭቱ የአራቱን አመታት ጉዳት የሚያካክስ በሚመስል መልኩ ሀገሪቱን እያዳረሰ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። የዝናቡ መጠን በዝቷል የሚሉ ወገኖችም ይሰማሉ። አንዳንዶች ስጋታቸውን እንዲህ የሚገልጹት ዝናቡ የሚፈለገውን ያህል ከመጠን ሲያልፍም ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑ ነው። የመኸሩ እርሻ በስፋት የሚካሄድበት ወቅትም እየተቃረበ ነው፤ ከሦስት ወራት የክረምት ወቅት በኋላ ደግሞ ሁለተኛ የበልግ ወቅታቸው የሆኑ አካባቢዎች በድጋሚ ይጠብቃሉ።
በዚህ የበልግ ወቅት ስላለው የዝናብ ስርጭትና ለበልጉ የግብርና ሥራ ስላበረከተው አስተዋጽኦ በተለይም ጠብታ ውሃ ሳይቀር እንዲያዝ ይስጥ የነበረው ምክረሃሳብ ምን ያህል ተግባራዊ እንደሆነ፣ውሃውን ለመያዝ የሚያስችሉ አነስተኛ ግድቦችን ለመሥራት የተደረገውን ጥረትና ተግባራዊነቱን፣እንዲሁም የዝናብ ስርጭቱን ቀጣይነት በተመለከተ ዳሰሳ አድርገናል። ትኩረት ያደረግነውም በልግ ተጠቃሚ በሆኑ በኦሮሚያ ክልል የተከናወኑት ሥራዎች ላይ ሲሆን፣ ምክረሃሳብና ወቅታዊውን የአየር ሁኔታ ትንተና መረጃ እየሰጠ ያለውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚትዮሮሎጂ ኤጀንሲ መረጃም አካተናል።
በቅድሚያም የኦሮሚያ ክልል መስኖና አርብቶ አደሮች ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ግርማ ረጋሣ በልግ አብቃይ በሆኑ የክልሉ አካባቢዎች ስላለው የዝናብ ስርጭት ሲያብራሩ እንዳሉት፤ ዝናብ አጠር በሆኑ የክልሉ አካባቢዎች አሁን እየጣለ ያለው ዝናብ ስርጭት ከተጠበቀው በላይ ነው። ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል። በተሠሩት አነስተኛ ግድቦችም ውሃ በመያዝ የሚጠበቀውን ግብም ማሳካት ተችሏል።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በልግ ወቅታቸው ለሆኑ አካባቢዎች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ለአነስተኛ ግድብ ሥራ ግንባታ የሚውል በቂ በጀት መድቧል። በዚሁ መሠረትም በክልሉ ቦረናን ጨምሮ ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ከ72 በላይ አነስተኛ ግድቦችን ለመገንባት በእቅድ ተይዞ እየተሠራ ቆይቷል። ከፀጥታ መደፍረስና በተለያዩ ምክንያቶች ሥራቸው ከተስተጓጎለው በአራቱ የወለጋ አካባቢዎች ውስጥ ሊከናወኑ የታቀዱ ስምንት ፕሮጀክቶች እንዲሁም ከምዕራብ ሸዋ፣ደቡብ ምዕራብ ሸዋና ጉጂ አካባቢዎች በስተቀር በአጠቃላይ በክልሉ ሊከናወኑ ከታቀዱት አነስተኛ የግድብ ሥራ ፕሮጀክቶች ውስጥ ወደ 56 ፕሮጀክቶች ተተግብረዋል።
ከነዚህ ውስጥ ወደ 32 የሚሆኑት ፕሮጀክቶች በበልጉ የጣለውን ውሃ ይዘዋል። ከተከናወኑት ፕሮጀክቶች 14ቱ በቦረና ዞን የተሠሩ ሲሆኑ፣ ቀደም ሲል ከነበሩት ግድቦች ጋር ተደምረው በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ወደ 18 ግድቦች ይገኛሉ። በግድቦቹ የተያዘው ውሃም ከ20 ሚሊዮን ሜትር ኪዩቢክ በላይ ይገመታል። ውሃው ከአንድ ነጥብ አምስት ኪሎሜትር በላይ የሚተኛ እንደሆነም ኢንጂነር ግርማ ጠቁመዋል።
ግድቦቹ በሀገር በቀል ግብአት በራስ አቅም የተከናወኑ መሆናቸውን የጠቀሱት ኢንጂነር ግርማ ፣ግድቦቹም በዝናብ ወቅት ሊፈጠር የሚችል ጎርፍን ለመያዝ ተብለው የተሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። በግድቦቹ የተያዘውን ውሃ ለእርሻና ለእንስሳት ብቻ ሳይሆን ሰዎችም አክመው ለመጠጥ ሊያውሉት እንደሚችሉም አስታውቀዋል።
የዝናብ ስርጭቱ የቀጠለ በመሆኑ የአካባቢው ማህበረሰብ በአሁኑ ጊዜ እየተጠቀመ ያለው የዝናብ ውሃ ነው። በተለይም አርብቶ አደሩ እንስሳቱን ይዞ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወር በመሆኑ አካባቢው ላይ የማይቆይባቸው አጋጣሚዎች ናቸው ያሉት። ወደ ሌላ አካባቢ ሲሄዱም ወደ ቦታቸው ሲመለሱ ከግድቡ ውሃ ለመጠቀም የሚችሉበት እድል ስለተፈጠረላቸው ስጋቱ ተቃልሏል።
የዝናብ ውሃን ለመያዝ ተብሎ ግድብ መገንባቱ ለተጨማሪ የገቢ ማስገኛ ልማትም እንዲውል እየተሠራ መሆኑን የጠቀሱት ኢንጂነር ግርማ፣ ለዓሣ እርባታ ልማት እንደሚውልም ነው የገለጹት። በአርብቶ አደሩ አካባቢ በግድብ የተያዘው ውሃ ከመጠን በላይ ሆኖ ሲገኝም በማስተንፈስ አካባቢው ላይ የእርሻ ሥራ የሚከናወንበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑም አስረድተዋል።
አሁን እየጣለ ያለው የዝናብ ስርጭት ቀጣይነትና የዝናቡን ውሃ ጥቅም ላይ ለማዋል የተሠሩት ሥራዎች ስላሳደሩት ተስፋና እቅድ በተመለከተም ኢንጂነር ግርማ እንዲህ ሲገልጹ ‹‹አርብቶ አደሮች ወደ ግድቡ እንዲሰበሰቡና ወደ ግብርና ሥራውም እንዲገቡ እንዲሁም ተያያዥ የሆኑ ገቢ የሚያስገኙ ሥራዎችን እንዲሠሩ ያነሳሳሉ። ›› ሲሉ ሥራዎቹ የኢኮኖሚ ለውጥ ያመጣሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
የግድብ ፕሮጀክት ሥራ ዓላማው ውሃ መያዝ ብቻ አይደለም፤ ማህበረሰቡን የሚጠቅም ገቢ እንዲያስገኝ መደረግም ይኖርበታል። ከዚህ አንፃር ባለፉት ተከታታይ አራት አመታት ካጋጠመው የዝናብ እጥረት ተሞክሮ በመውሰድና አሁን ያለውን መልካም አጋጣሚ ማዕከል በማድረግ በተለይም በዝናብ እጥረቱ የደረሰውን ጉዳት ለማካካስ የአካባቢው ማህበረሰብን በማነቃቃት እየተሠራ ስላለው ሥራም ኢንጂነር ግርማ ላነሳንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ‹‹በቆላማ አካባቢ አንዱ ከሌላው ይለያል። ለአብነትም ሐረርጌና ባሌ አካባቢዎች ከፊል አርሶአደር አካባቢ በመሆናቸው የግብርና ሥራ ለመሥራት ፍላጎቱም ተሞክሮውም አላቸው። በሌላኛው ክፍል ደግሞ የእርሻ ሥራ ልምድ የለም። ›› ሲሉ ይገልጻሉ። ‹‹በመሆኑም የንቅናቄ ሥራ ይጠበቃል። ለምሳሌ ቦረና አካባቢ የእርሻ ሥራ ለማከናወን ተስፋ ሰጪ ጀምሮች አሉ። ስልጠናዎችን ለመስጠትና የውይይት መድረኮችንም ለማዘጋጀት ሥራዎች ተጀምረዋል። ማህበረሰቡ ከደረሰበት የከፋ ችግር ትምህርት በማግኘቱ ግንዛቤው ተቀይሯል ሲሉም ነው ያብራሩት።
እንደ ኢንጂነር ግርማ ማብራሪያ፤ በክልሉ በአራት አመታት ውስጥ ወደ 255 ግድቦች ለመሥራት እቅድ ተይዞ ተያያዥ የሆኑ ተጨማሪ ሥራዎችን በመሥራት አካባቢዎቹ ላይ ለውጥ ለማምጣት እየተሠራ መሆኑን ነው። የበልጉ ወቅት እስከ ግንቦት 30 የሚቀጥል በመሆኑ ስርጭቱ ከመጠን በላይ ይሆናል የሚለው ጉዳይ ስጋት አይደለም፤ ግድቡ 20 ሜትር ከፍታ አለው። ይህ እስኪሞላ ድረስ መጠበቅ የሚቻልበት እድል አለ። ቢሞላም ማስተንፈሻ የተሠራለት በመሆኑ በዚህም መንገድም ማስተንፈስ ይቻላል።
ዝናቡ የሚቋረጥበት ሁኔታ ቢያጋጥም በግድቡ የተያዘውን ውሃ ለተወሰነ አመት ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑም አመልክተዋል። ውሃ በባህሪው በትነትና በአጠቃቀም ጥንቃቄ ጉድለት የሚቀንስ መሆኑን ግምት ውስጥ መግባት አለበት ብለዋል።
ከመስከረም ወር በኋላ የሚከተለው ሁለተኛው የበልግ ወቅት ተስፋ የተጣለበት መሆኑን በመጥቀስ በዚያን ጊዜም በተመሳሳይ የዝናብ ስርጭቱ ጥሩ ከሆነ ስጋቶች እንደሚቀንሱም ተናግረዋል። መስሪያ ቤታቸው ከኢትዮጵያ ሚትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ጋርም ጥሩ ግንኙነት እንዳለው ጠቅሰው፣ ኢንስቲትዩቱ በሚሰጠው የመረጃ ትንተና መሠረት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
በዚህ የበልግ ወቅት ስለተከናወኑት ተግባራትና ወቅታዊውን የዝናብ ስርጭት በተመለከተ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ሚትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ሚትዮሮሎጂ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሳምነው ተሾመ እንዳሉት፤ በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች በተለይም በድርቅ ተጽእኖ ሥር በነበሩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለአብነትም ሶማሌ፣ ጉጂ፣ቦረና፣ የተወሰኑ የሲዳማ ክልል፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ የደቡብ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ህዝቦች አካባቢዎች ከየካቲት 30ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለበልግ አመቺ የሆኑ የአየር ሁኔታ ክስተቶች ተፈጥረዋል። በአብዛኞቹ አካባቢዎችም የዝናብ ስርጭት መኖሩን ከተሰበሰቡ የሚትዮሮሎጂ መረጃዎች ማረጋገጥ ተችሏል።
በ24 ሰዓት ውስጥ በአንድ የሜትዮሮሎጂ ጣቢያ ላይ ከአንድ ሚሊ ሊትር እስከ አስር ሚሊ ሊትር መጠን ያለው ዝናብ በሚጥልበት ጊዜ ዝናቡ ቀላል የዝናብ መጠን ያለው ተብሎ ሊጠራ ይችላል፤ በ24 ሰዓት ውስጥ ከ11 ሚሊ ሊትር እስከ 29 ሚሊ ሊትር መጠን ያለው ዝናብ ከጣለ ደግሞ ዝናቡ መካከለኛ፣በ24 ሰዓት ውስጥ ከ30 ሚሊ ሊትር በላይ ያለው መጠን ዝናብ ከጣለ ደግሞ ዝናቡ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ተብሎ ይጠራል።
ከየካቲት 17 ቀን 2015ዓ.ም ጀምሮ በልግ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆነው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከመካከለኛ፣ በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ስለመጣሉ በሚትዮሮሎጂ ጣቢያዎች መመዝገቡን አስረድተዋል።
በአጠቃላይ ከየካቲት 17 እስከ ሚያዝያ 23 ቀን 2015 ዓ.ም 77 በሚደርሱ የሚትዮሮሎጂ ጣቢያዎች ከባድ መጠን ያለው (ከ30 እስከ 160 ሚሊ ሊትር) ዝናብ ተመዝግቧል ያሉት ዶክተር አሳምነው፣ በአጠቃላይ በተጠቀሱት ቀናት በልግ ዋነኛና ሁለተኛ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተስፋፋና የተጠናከረ የዝናብ ሁኔታ ነበራቸው ብለዋል። በዚህም ግብርና ሥራን ከማሳለጥ፣ ልምላሜን በመጨመር፣ ድርቁን ከማስታገስ፣ እንዲሁም ግድቦች በቂ ውሃ እንዲይዙ በማስቻል፣ በተፋሰሶችና በወንዞች ለነበረው የውሃ አቅርቦትም ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አስታውቀዋል።
የኢንስቲትዩቱን የትንበያ መረጃና ምክረሀሳብ መሠረት በማድረግ በዝናብ የተገኘውን ውሃም በመሰብሰብ ረገድ በማህበረሰቡ በኩል እየተደረገ ያለውን ጥረት ኢንስቲትዩቱ በተለያየ መንገድ ከሚያገኘው መረጃ በመገንዘብ እንዲህ ያሉ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ታምኖባቸዋል።
ዝናቡ በዝቷል ተብሎ እንደ ስጋት ለሚነሳውም ስጋቱ አንጻራዊ ሊሆን እንደሚችል በመጠቆም ስጋቱ የመጣው ቀደም ባሉት አምስት የበልግ ተከታታይ ወቅቶች ከመደበኛ በታች ከነበረው ዝናብ ጋር ተያይዞ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል። ከአመታዊ የዝናብ መጠን እስከ 55 በመቶ የሚሆነው የዝናብ መጠን የሚገኘው በበልግ ወቅት እንደሆነም አመልክተዋል።
በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆነው ሶማሌ፣ ደቡብ ኦሮሚያ ቆላማ ስፍራዎች፣ ጉጂ፣ ቦረና፣ሲዳማ፣ የደቡብ ብሔርና ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ መደበኛ የሆነ ዝናብ እንደሚኖራቸውና የዝናቡም አገባብ ሊዘገይ እንደሚችል ቀደም ሲል ትንበያ መስጠቱ ይታወሳል።
የበልግ ዝናብ ሁለተኛ ወቅታቸው የሆኑ ደቡብ ትግራይ፣ ምሥራቅ አማራ፣ አፋር፤ ሐረርና ድሬዳዋን ጨምሮ መካከለኛ የሀገሪቱ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ እንደሚኖራቸውና መዘግየትም እንደሚኖር ኢንስቲትዩቱ በተጨማሪ ትንበያ ሰጥቶ ነበር። በቅድመ ትንበያው መሠረትም የበልግ ዝናብ ከየካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በተለያየ መጠን በመጣል ላይ ይገኛል። በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎችም የደመና ሽፋኑ ጨምሯል። አካባቢዎቹ ከቀላል እስከ ከባድ የዝናብ መጠን አግኝተዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች የጣለው ከባድ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች፣ እንስሳትና በሰው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል።
ኢንስቲትዩቱ ባለፈው ጥር ወር 2015 በጀት አመት ላይ በበጀት አመቱ ስለሚኖረው የአየር ትንበያ ሁኔታ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ መድረክ አዘጋጅቶ የሚጠበቀውን የአየር ሁኔታ ይፋ ማድረጉም ይታወሳል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2015