ከአገራችን የእደ ጥበብ ውጤቶች አንዱ ሆኖ የቆየው የሹራብ ሥራ አብዛኛውን ጊዜ በሴቶች ሲከወን እንደኖረም ይታወቃል። ይህ የሹራብ ሥራ ከቴክኖሎጂ ጋር እየተዋደደ መጥቷል፤ በእጅም ሆነ በማሽን በተለያየ ዲዛይን እየተመረተ ይገኛል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ የሹራብን ዲዛይን ዘመኑን በሚመጥን መልኩ በዲጂታል መሣሪያ ዲዛይን አድርጎ መሥራት እየታቸለ ነው። ሹራብን በእጅ ከመሥራት ይልቅ በዲጅታል ማሽን ተጠቅሞ መሥራት ውስጥም ተገብቷል። በዚህም በሹራብ ሥራ ላይ የበለጠ ለውጦች እየታዩ መጥተዋል።
አሁን ላይ ሹራቦች ቀደም ሲል ከነበረው የተለመደ አሠራርና ዲዛይን ወጣ ባለመልኩ ጥራታቸውን ጠብቀው የትም ቦታ ላይ ሊለበሱ በሚችሉበት ሁኔታ ዲዛይን ተደርገው ተመርተው ለገበያ እየቀረቡ ናቸው። ዘመናዊ ፋሽንን በተከተለ መልኩ የሚሠሩ እነዚህ ውብና ማራኪ የሹራብ አልባሳት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተወዳጅነታቸው እየጨመረና እየተለመዱ መምጣታቸውን የዘርፉ ባለሙያዎችም ይመስክራሉ።
የሹራብ ሥራ ለመሥራት ንድፍ ከማውጣት ጀምሮ ብዙ ጊዜ የሚወስድና ልፋትን የሚጠይቅ መሆኑን ባለሙያዎቹ ጠቅሰው፣ ተሠርተው ሲለበሱ ግን የሚያምሩና ረጅም ጊዜ ሊቆዩ የሚችሉ እንደሆኑም ይናገራሉ።
የሰላማዊት ሹራብ ማምረቻ ድርጅት ባለቤት የሆነችው ወይዘሮ ሰላማዊት ሁሴን በሹራብ ሥራ ላይ ቆይታለች። እሷ እንደምትለው፤ በሹራብ የሚሠሩ ለወንዶች፣ ለሴቶችና ለሕፃናት የሚሆኑ ዩኒፎርሞችን ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት የሹራብ ሥራዎች ድርጅቷ ይሠራል። ወይዘሮ ሰላማዊት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ትኩረቷን በሹራብ በሚሠሩ የሴቶች ካባዎች ላይ አድርጋለች። እነዚህ ከሹራብ የሚሠሩ የሴቶች ካባዎች እንደ ባህል አልባሳት ሁሉ ጥለት እንዲኖራቸው ተደርጓል።
ካባዎቹ ቀደም ሲል ያልተለመዱ ከሹራቡ ዳር ዳር ላይ የባህል ጥለት ያላቸው ለየት ያሉ ናቸው የምትለው ወይዘሮ ሰላማዊት፣ የሹራብ ካባው ለወጣቶችም ሆነ ለአዋቂ በሚሆን መልኩ እንደሚዘጋጁም ትናገራለች። ካባውን ወጣቶች በቀበቶ አድርገው ከታይት ጋር ይለብሱታል፤ እናቶች ደግሞ እንደ ካባ ይደርቡታል ነው የምትለው።
ካባዎቹ ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም ባይለመዱም አሁን ላይ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መምጣቱን የምትጠቆመው ሰላማዊት፤ የሹራብ ካባ ምርቶቿን ፖስታ ቤት፣ ሽሮሜዳ፣ ኮልፌና መርካቶ አካባቢ ለሚገኙ የአገር ውስጥ ተረካቢዎች ታቀርባለች። አብዛኛዎቹን ካባዎች ፖስታ ቤት አካባቢ የሚገኙ መደብሮች ከሷ ተረክበው ወደ ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ ለዲያስፖራው እንደሚሸጡት ገልጻለች።
«በቅርቡ በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው ኤግዚቢሽን ላይ ያገኘኋቸው ውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ኒውዮርክ ላይ እኔ ዲዛይን የማደርገውን የሹራብ ካባ በኦንላይን መግዛታቸውን አውግተውኛል›› የምትለው ሰላማዊት፤ ካባው እንደተመቻቸውና ደስተኛ መሆናቸውን በመግለጽ በድጋሜ ገዝተው መሄዳቸውንም ትናገራለች። ሰላማዊት የሹራባ ካባው ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ የሚላከው በአንዲት ግለሰብ መሆኑን ጠቅሳ፣ ግለሰቧ በኦንላየን እየሸጠች መሆኑን ነው የምትናገረው፤ ካባውን በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በእጅጉ እንደሚፈልጉት ትጠቁማለች።
የምዕራባውያንን ተፅእኖ ለመከላከል በኢትዮጵያውያን ተካሂዶ በነበረው “የ#በቃ” (#NOMORE) እንቅስቃሴ ላይ የምትታወቀው ጋዜጠኛ ሐርሜላ አረጋዊ ለብሳው እንደነበር አስታወሳ፤ ሐርሜላ ካባውን በፖስታ ቤት በኩል እንዳገኘችው ማወቋን ትገልጻለች።
‹‹የካባ ሥራዎችን ከመጀመሬ በፊት ከባለቤቴ ጋር በመሆን ብዙ የሹራብ ሥራዎችን እንስራ ነበር›› የምትለው ሰላማዊት፤ ቀደም ሲል በሁለት መልክ ከሹራብ ካባ መሥራት የተለመደ እንደነበር ታስታውሳለች። ከዚህ በተሻለ መልኩ ባህላዊ ይዘት እንዲላበስ አድርገን ብንስራው የሚለውን ሀሳብ በማፍለቅ ባለቤቷ ዲዛይኑን እንደሠራው ገልጻ፤ ውጤቱ ሲታይ በጣም ቆንጆ እንደነበርና ወደ ገበያ ሲያወጡት በቶሎ ተቀባይነት እንዳገኘም ነው የተናገረችው። ካባው ለሕፃናት፣ ለወጣቶች እና ለአዋቂም በሚሆን መልኩ እንደሚመረት ትገልጻለች።
ሰላማዊት እንዳለችው፤ የሹራብ ካባውን ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። በ2014 ዓ.ም ከግንቦት 1 እስከ 5 በልማት ባንክ የተሰጠውን ሥልጠና በመወሰድ አምስት ተጨማሪ ማሽን ለመግዛት የሚያስችል ፕሮፖዛል አቅርባለች፤ ማሽኖቹን ስታገኝ ደግሞ ካባውን በጥራት በማምረት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ሀሳብ አላት። ይህ ሀሳብ እውን ሆኖ ሲሳካ ደግሞ የሹራብ ካባው ተደራሽነት እየሰፋ ይመጣል።
ሰላማዊት እንደምትለው፤ ሹራብ በማሽን የሚሠራ ቢሆንም፣ ብዙ የሰው ኃይል ያስፈልገዋል። አሁን ላይ ሰባት ቋሚ ሠራተኞችና ከ15 በላይ ጊዜያው ሠራተኞች አሏት። ካባውን ለመስራት የምትጠቀምበት ዲጅታል ማሽን ኮምፒዩተራይዘድ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሁሉም ሰው የሚያወቀው አይደለም። ስለዚህ ማሽኑን ለመጠቀም እንዲቻል የሰለጠነ የሰው ኃይል ያስፈልጋል። አሁን ላይ ሦስት ሰዎች ስልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ ነው።
ዲጅታል ማሽኑ ላይ መሥራት ያለበት ሰው የተማረና ሥልጠና የወሰደ ማሽኑን በሚገባ በማወቅ አስፈላጊውንም የመፍትሔ አቅጣጫ እያስቀመጠ የሚመጣ መሆን አለበት የምትለው ሰላማዊት፤ ዲጅታል ማሽኑ እንከን ሲያጋጥመው ድምጽ ያሰማል፤ ከዚያም ያጋጠመውን ችግር ስለሚፅፍ ያንን አንብቦ መረዳት የሚችል የሰለጠነ ሰው ያስፈልጋል ትላለች። ተጨማሪ ዲጅታል ማሽኖች ወደ ሥራ ሲገቡ ደግሞ በዚያው ልክ የሰው ኃይል ማሰልጠንና ብቁ ባለሙያ ማፍራት እንደሚቻል ትገልፃለች።
‹‹የሹራብ ሥራውን አሃዱ ብለን ስንጀምር ቀደም ሲል ለሥራው የሚያገለግለው በጣሊያን ጊዜ የነበረ ማሽን በዲጅታል ማሽን እንዲተካ በማድረግ የተሻለ ነገር ለመፍጠር አንድ እርምጃ ከፍ ያለ ነገር ማበርከት ብንችል ብለን አስበን ነው›› የምትለው ሰላማዊት፤ ልጆቻችንን ደግሞ ከእኛ በተሻለ መልኩ ከፍ ካደረጉት የአገራችንን የሹራብ ሥራ አንድ ደረጃ ማሳደግ እንችላለን ስትል ትገልጻለች።
«የሹራብ ካባን ለመሥራት በመሠረታዊነት የሚያስፈልገው ጥሬ ዕቃ የሱፍ ክር ነው» የምትለው ሰላማዊት፤ የሱፍ ክሩን በቋሚነት ከውጭ የሚያስመጡ እንዳሉ ጠቅሳለች። እስካሁን ባለው ሂደት የጥሬ ዕቃ የዋጋ ጭማሪ እንጂ የጥሬ ዕቃ የአቅርቦት እጥረት እምብዛም እንዳላጋጠማት አስረድታለች።
ሙያው በትምህርት ሳይሆን በልምድ ያገኘችው እንደሆነ የምትናገረው ሰላማዊት፤ የሹራብ ሥራ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ሙያውን በተለያየ መልኩ ዲዛይን በማድረግ እያሳደገችው መጥታለች። ሙያው በትምህርትም የተደገፈ ቢሆን ደግሞ የተሻለ መሥራት እንደሚቻል ነው የተናገረችው። እርሱን ለማሳካት ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ ትገልጻለች። የሹራብ ሥራውን የጥራት ደረጃ በመጨመር ወደ ውጭ አገር ኤክስፖርት ለማድረግ ሙከራ እያደረገች መሆኗን ገልፃም ሀሳቧ ታጠቃልላለች።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 30/2015