የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እጩ ኮከቦች

የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሳምንት በፊት አዲስ ቻምፒዮን ማግኘቱ ቢረጋገጥም ላለመውረድ የሚደረገው ትግል እስከመጨረሻ ሳምንት መርሃግብር ዘልቋል። ከሊጉ ቀደም ብለው መውረዳቸውን ያረጋገጡ ክለቦች ቢኖሩም በውድድር ዓመቱ አራት ክለቦች ለመውረድ በመገደዳቸው ፉክክሩና ሽኩቻው ይበልጥ ጦፏል።

ከሦስት ዓመት በፊት ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀለው ኢትዮጵያ መድን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉ ቻምፒዮን መሆኑን ቀድሞ ማረጋገጡ ይታወሳል። ከጅማ አባጂፋርና ከመቀለ 70 እንደርታ ጋር የሊጉን ዋንጫ ያሳኩት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከተለያዩ ክለቦች ጋር የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ የማንሳት ቁልፍ ያገኙ ናቸው። አሰልጣኝ ገብረመድህን መድንን ለቻምፒዮንነት በማብቃት በተለያዩ ሦስት ክለቦች የተሳካላቸው የመጀመሪያው አሰልጣኝ ሆነዋል።

የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ36ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የመጨረሻውን የመዝጊያ ጨዋታ በተለየ ሁኔታ ለማድረግ ፣ የቀጥታ ስርጭት ተደራሽነትን ፣ የክለቦችን ውጤት እና የመጫወቻ ሜዳዎች ያሉበትን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ማሻሻያ ተደርጎበታል። በዚህም መሠረት 36ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ከእሁድ ሰኔ 15/2017 እስከ ሐሙስ ሰኔ 19/2017 ለአምስት ተከታታይ ቀናት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል።

ፕሪሚየር ሊጉ በዚህ ሁኔታ ሊገባደድ ጫፍ በደረሰበት በዚህ ወቅት የውድድር ዓመቱን የኮከብነት ክብር ማን ይጎናፀፋል የሚለውም ጉዳይ አጓጊ ነው። የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ አክሲዮን ማህበር የውድድር ዓመቱን ኮከብ እጩዎች ከቀናት በፊት ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ የእግር ኳስ ቤተሰቡ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች የሚሰጣቸው ድምፅ ዛሬ ይዘጋል። የሊግ ካምፓኒው እጩ አድርጎ ካቀረባቸው ኮከቦች መካከል የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች ማን ሊሆን ይችላል የሚለው ጉዳይ በጉጉት ይጠበቃል።

በኮከብ ተጫዋች በኩል ሰባት ተጫዋቾች እጩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ቡናዎቹ ዲቫይን ዋቹንካና ራምኬል ጀምስ ተካተዋል። የቻምፒዮኑ መድን ተጫዋቾች ሀይደር ሸረፋ፣ መሐመድ አበራና ዳዊት ተፈራም ከአንድ ክለብ የታጩ ሦስት ኮከቦች ናቸው። የመቻሉ ሽመልስ በቀለ ሌላኛው እጩ ሲሆን፣ የሃዋሳ ከተማው የግብ ማሽን አሊ ሱሌይማንም መካተት ችሏል። ኤርትራዊው አሊ ሱሌማን ሃዋሳ ከተማን ከተቀላቀለ በኋላ ባለፈው ሳምንት 99ኛ የነጥብ ጨዋታውን አድርጓል። በዓመቱ ያያቸው የቢጫ ካርዶች ቁጥር 5 መድረሳቸውን ተከትሎ 100ኛ ጨዋታውን ከአዳማ ከተማ ጋር ማድረግ የሚችልበት ዕድል ግን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በ99ኙ ጨዋታዎች 92 ግቦችን በሊግ ጨዋታዎች ሰባት ደግሞ በኢትዮጵያ ዋንጫ ለክለቡ ማስቆጠር ችሏል። ዘንድሮም በሊጉ 21 ግቦችን በማስቆጠር ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ የማጠናቀቅ ትልቅ እድል አለው። እሱን ተከትለው የፋሲል ከነማው ጌታነህ ከበደና የኢትዮጵያ ቡናው አህመድ ሁሴን በእኩል 13 ግብ ተፎካካሪ ናቸው።

በተስፈኛ ተጫዋች በኮከብነት እጩ መሆን የቻሉት የመድኑ በረከት ካሌብ፣ የኢትዮጵያ ቡናው ይታገሱ ታሪኩ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ሔኖክ ዮሐንስ፣ የባህር ዳር ከተማው ሔኖክ ይበልጣልና የመቀለ 70 እንደርታው ዘረሰናይ ብረሃነ ናቸው። ዘንድሮ ሊጉ ላይ አንድ ወጣት ክስተት እንደነበር ብዙዎች ይስማማሉ። ይህ ወጣት የኢትዮጵያ መድን ተጫዋች ሲሆን ሙሉ ስሙ ወገኔ ገዛኸኝ ይባላል። ተስፈኛው ተጫዋች ሜዳ ላይ ታጋይ ነው፣ ኳስ ሲገፋ የተካነበት ነው፣ አንድ ለአንድ ከተቃራኒ ተጫዋች ጋር ኳስ ይዞ ሲገናኝ አሸናፊ ነው፣ ከኳስ ጋር እና ያለ ኳስ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች እጅግ ማራኪ ሲሆን ቡድኑ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ እጅግ ወሳኝ ጎሎችንም በተደጋጋሚ ጊዜ አስቆጥሯል። ዘንድሮ ድንቅ ዓመት ያሳለፈው መድን ቻምፒዮን ሲሆን ይሄ ወጣት 98 በመቶ ጨዋታዎች ላይ ቋሚ ተሰላፊ ነበር። በብሔራዊ ቡድንም የላቀ ግልጋሎት ሰጥቷል። ይሁን እንጂ በተስፈኛ ወጣት ኮከቦች እጩ ውስጥ አለመካተቱ አስገራሚና በብዙዎት ዘንድ ጥያቄ ያስነሳ ሆኗል።

በኮከብ ግብ ጠባቂነት የመድኑ አቡበከር ኑራ እጩ መሆን የቻለ ሲሆን፣ በውድድር ዓመቱ በሊጉ በ20 ጨዋታ መረቡን ሳያስደፍር ወጥቷል። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ዳንላንድ ኢብራሂም በ20 ጨዋታ ግብ አላስተናገደም። የባህርዳር ከተማው ግብ ጠባቂ ፔፔ ሰዒዶ በ15 ጨዋታ ግብ ያልተቆጠረበት ሆኖ በእጩነት ቀርቧል።

በቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You