ባለሀብቶች በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ እንዳለባቸው ተጠቆመ

ቢሾፍቱ፡ባለሀብቶች በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲሰማሩ መንግሥት የፈጠራቸውን እድሎች በመጠቀም በዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያሳድጉ ተጠየቀ።በ ‹‹ፍቃዱ ፀጋዬ ቢዝነስ ግሩፕ›› በቢሾፍቱ ከተማ የተገነቡ ፋብሪካዎች ተመርቀዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፣ መንግሥት የአምራች ዘርፉን በማበረታታት በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖረውን ድርሻ ለማሳደግ የሚያስችሉ ርምጃዎችን እየወሰደ በመሆኑ ባለሀብቶችም እነዚህን እድሎች በመጠቀም በዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት፣ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ መሰማራት ዘርፉን ከማሳደግ ባሻገር የባለሀብቶችን ምርታማነትና ትርፋማነት የሚያሳድግ ነው።በዘርፉ ላይ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ኢንቨስትመንታቸውን በማስፋት ተጨማሪ የሥራ እድሎችን መፍጠር እና የወጪ ንግድን ማሳደግ ይገባቸዋል።

መንግሥት አምራች ኢንዱስትሪውን በማነቃቃት የዘርፉን የኢኮኖሚ ድርሻ ለማሳደግ እየሠራ ይገኛል። በዚህም የወጭ ንግድን ለማበረታታት፣ ገቢ ምርቶችን ለመተካት፣ የሥራ እድል ለመፍጠር፣ የምርት አቅም አጠቃቀምን ለማሳደግ እና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ትኩረት ተሰጥቷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ባለሀብቶችን ለመደገፍ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ካውንስል ተቋቁሞ የዘርፉን ችግሮች የመለየትና የመፍታት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡

ባለሀብቶች የወሰዱትን መሬት በፍጥነት ወደ ሥራ በማስገባት ምርቶችን እሴት በመጨመር ለገበያ ማቅረብ እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት መተካት እንዳለባቸውም ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

አቶ መላኩ ቢሾፍቱ ከተማ የአምራች ኢንዱስትሪውን በማነቃቃት አበረታች አፈፃፀም እንዳላት ጠቁመው፣ ከተማዋና አካባቢው ለአምራች ዘርፍ ኢንቨስትመንት ትልቅ አቅም ያላቸው በመሆኑ መፍትሄ ያላገኙ ችግሮችን በመፍታት የባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል።

የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ፣ ቢሾፍቱ የኢንዱስትሪና የቱሪዝም መናኸሪያ መሆኗን ጠቁመው፣ በከተማዋ የሚገኙ 1968 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግርና ለወጪ ንግድ ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ በርካታ የከተማዋ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የነበሩባቸው ችግሮቻቸው እንዲቃለሉ ማስቻሉን የጠቆሙት አቶ አለማየሁ፣ ንቅናቄው ሲጀመር ከ40 በመቶ በታች የነበረው የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አሁን ወደ 67 በመቶ ማደጉን ተናግረዋል።

እንደ አቶ አለማየሁ ገለፃ፣ በከተማዋ በ2017 የበጀት ዓመት በአስር ወራት ለ60ሺ ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል።የመሬት አስተዳደር ችግሮችንና የጥሬ እቃ አቅርቦት እጥረትን በማቃለል ሀገር በቀል ባለሀብቶችን ለማበረታታት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው።

የ‹‹ፍቃዱ ፀጋዬ ቢዝነስ ግሩፕ›› መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፍቃዱ ፀጋዬ በበኩላቸው፣ ድርጅታቸው በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ መሰማራቱን ተናግረዋል።ድርጅቱ በቤት ውስጥ እቃዎች፣ በጨርቃ ጨርቅና በዱቄት ምርት እንዲሁም በመኪና መገጣጠም እና በሆቴል ዘርፎች ተሰማርቶ ለዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡

በቀጣይም ከውጭ ገብተው የሚገጣጠሙ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የማስፋፊያ ግንባታዎችን እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You