ኢትዮጵያ ካሏት የማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ አንዱ የሲዳማ የዘመን መለወጫ በዓል የሆነው ፍቼ ጫምባላላ ነው። ይህ በዓል በየዓመቱ በሚያዚያ ወር መግቢያ ላይ በሲዳማ ብሔረሰብ ዘንድ በደማቅ ሥነሥርዓት ይከበራል። ‹‹ፍቼ›› የዋዜማው በዓል ሲሆን፣ ‹‹ጫምባላላ›› ደግሞ አሮጌው ዓመት ተሸኝቶ አዲሱ ዓመት የሚገባበት ቀን ነው። በዓሉ በሲዳማ ክልል በሁሉም አካባቢዎች በተለያዩ ዝግጅቶች ባሕላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ይከበራል፤ በሃዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ጉዱማሌ ደግሞ በተለየ ሁናቴ በርካታ የሲዳማ ክልል ሕዝብ፣ የፌዴራልና የተለያዩ ክልሎች መሪዎችና ተወካዮች፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች በተገኙበት በደማቅ ሥነሥርዓት ይከበራል።
ይህ ክብረ በዓል የዘመን መለወጫ እንደመሆኑ የሲዳማዎች የዘመን አቆጣጠር ውጤት ተደርጎ ይቆጠራል። የሲዳማ ብሔር የራሱ የሆነ የጊዜ ቀመርና ሰዓት እንዳለውም ይጠቁማል። ብሔረሰቡ ሰከንዶችን ወደ ደቂቃዎች ብሎም ወደ ሰዓታት ለውጦ፤ ሰዓታትን ደምሮ፣ ቀናትን ፈጥሮ፣ የቀናትን ጥምረት ደግሞ ወደ ሳምንታት ቀይሮ ዓመታትና ዘመናትን ሁሉም በሚግባባበት ሁኔታ የሚቀምርበት ጥበብ እንደሆነም ይነገራል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ጨምሮ ጥቂት ሀገራት ብቻ የዚህ የጊዜ ቀመር ሥርዓት ባለቤቶች መሆናቸውን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። አብዛኛዎቹ ሀገራትም ከእነዚህ የዘመን ቀመሮች ወስደው እንደሚጠቀሙ ታሪክ ያመለክታል። የሲዳማ አዋቂዎች /ጠበብቶች/ የሰማይ አካላትና እንቅስቃሴያቸውን በማጥናት ማንም ሳይስተምራቸው የሳይንስ ግኝት እምብዛም ባልተስፋፋበት በጥንት ዘመን ራሳቸውን በራሳቸው አስተምረው፣ አጥንተውና ተፈላስፈው የጊዜ ቀመር አበጅተው ሕዝባቸውን በተደራጀ ሁኔታ እንዲንቀሳቀስ አስችለውታል።
በሲዳማ ብሔረሰብ የጊዜ ቀመር መሠረት አንድ ቀን በሰዓታት የተከፋፈለ ነው፤ አራት ቀናት አንድ ሳምንት፣ ሰባት ሳምንታት አንድ ወር እያለ አስራ ሁለት ወራትን ፈጥሮ ሦስት መቶ ሀምሳ አራት ቀናትን ወይም በአራት ዓመታት አንድ ጊዜ ሦስት መቶ ሃምሳ አምስት ቀናትን በድምሩ አንድ ዓመትን ይፈጥራል። መቶ ዓመት ‹‹ሰኔ›› ይባላል። ሺ ዓመት ወይም ሚሊኒየም ደግሞ ‹‹ቱንሶ›› ተብሎ ይጠራል። ይህ የጊዜ አቆጣጠር በድንቅ ብቃት የተቀመረና ከጥንት ጀምሮ የሲዳማ ብሔረሰብ ሲገለገልበት የቆየ፣ አሁንም እየተጠቀመበት ያለ የብሔረሰቡን ሥልጣኔ የሚያሳያም ጭምር ነው።
ፍቼ ጫምባላላ ከድንቅ የዘመን አቆጣጠር ቀመርነቱ በዘለለ ለሲዳማ ብሔረሰብ መልካም ማንነት መሠረት የሆኑ በርካታ እሴቶችን በውስጡ ይዟል። የሲዳማ ሕዝብ ኅዘን፣ ቂም፣ ቁርሾና ክፋትን ይዞ ወደ አዲሱ ዓመት አይሻገርም። በዚህ ፋንታ እርቅ፣ ይቅርታ፣ ሰላምና ደስታ የሚፈጥሩ ሥራዎችን በሁሉም ቤተሰብና በማኅበረሰብ ደረጃ ይፈጽማል። ግጭቶች ይወገዳሉ፣ የልዩነት እድሎች ይጠባሉ። ሰላምና ፍቅር ይሰፍናሉ። በዚህ በዓል ወቅት የመረዳዳት ባሕል ይጎለብታል፤ ዘመድ አዝማድ ተጠራርቶ በጋራ ይመገባል። ያለው ለሌለው ያካፍላል። ትንሽ፣ ትልቅ፣ ቤተሰብ ባዳ ሳይባል ሁሉም ከሻፌታው /የሲዳማ ባሕላዊ ምግብ ከሚቀርብበት ቁስ/ በጋራ ይቋደሳል። የሲዳማን አንድነትና ኅብረት ማኅበረሰቡ ጠብቆ እንዲዘልቅ ካስቻሉ እሴቶች ውስጥም አንዱ ይኸው የፍቼ ጫምባላላ እሴት ነው።
ይህ ድንቅ የዘመን መለወጫ ቀመርና የብሔረሰቡን በርካታ መልካም እሴቶችን ያቀፈው የፍቼ ጫምባላላ በዓል በ2008 ዓ.ም በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ተርታ ተመዝግቦ ከሀገር ቅርስነት ባለፈ የዓለም ቅርስ ሆኗል። በዚህ ቅርስነቱ ደግሞ ለሲዳማ ክልል በአጠቃላይም ለኢትዮጵያ ጎብኚዎችን በመሳብና በመሳሰሉት ሌላ ቱሩፋት ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል። ለመሆኑ በዓሉ የጎብኚዎችን ቀልብ እንዲስብና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅዖ እንዲያበረክት ምን እየተሠራ ነው? አቶ መሐመድ ሌንጂሼ በሲዳማ ክልል የሸበዲኖ ወረዳ ጣርቤሳ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። የፍቼ ጫምባላላ በዓል ለሲዳማ ሕዝብ ትልቅ በዓል መሆኑንና የብሔረሰቡ ትልቁ የማንነት መገለጫው እንደሆነ ይናገራሉ። በፍቼ ጫምባላላ በዓል የተጣላ የሚታረቅበት፣ ተለያይቶ የቆየ የሚገናኝበትና አንድነት የሚጎለብትበት እንደሆነም ይገልጻሉ። ከዚህ ባለፈ በዓሉ ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት፣ እርስ በርስ የመረዳዳት ባሕል የሚጠናከርበት፣ ርህራሄና እዝነት ከፍ የሚልበት እንደሆነም ነው አቶ መሐመድ የሚያብራሩት።
በፍቼ ጫምባላላ ወቅት እንኳን ለሰው ለእንስሳትና ለዕፀዋትም ጭምር ርህራሄ እንደሚኖር የሚገልፁት አቶ መሐመድ፤ በዚሁ በዓል ወቅት አንድም የእንስሳት እርድ እንደማይፈፀምና ዕፅዋትም እንደማይቆረጡ ይናገራሉ። ከዚህ ይልቅ የቤት እንስሳዎች ከታሰሩበት በረት ወጥተው ለግጦሽ እንደልብ የሚሠማሩበት፤ አንድም ዕፅዋት የማይቆረጥበት የሲዳማ ሕዝቦች የነፃነት በዓል መሆኑን ያስረዳሉ። በዓሉን ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦችን ሕዝቦች ያለልዩነት የሚያከብሩት መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
የፍቼ ጫምባላላ በዓል ከሲዳማ ብሔረሰብ ሕዝቦች በዓልነት አልፎ የኢትዮጵያና የዓለም በዓል መሆኑንንም ነው አቶ መሐመድ የሚገልጹት፤ በዓሉ የውጪ ሀገር ጎብኚዎችን ቀልብ እንዲስብ ሁሌም በድምቀትና ሰላማዊ መንገድ ማክበር እንደሚገባ ያመለክታሉ። እርስ በርስ ከመጋጨትና ከመጠላላት ይልቅ የበዓሉ ዋነኛ እሴት የሆኑትን ፍቅር፣ አብሮነትና መተሳሰብን ማንባረቅ እንደሚያስፈልግም ይጠቁማሉ።እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ሽማግሌዎች በዓሉ የሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን የውጪ ሀገር ጎብኚዎችንም እንዲስብ የማስተዋወቅና በተለይ ደግሞ ወጣቱ ለበዓሉ መከበር የሰላም ዘብ ሆኖ እንዲቆም ምክርና ተግሳፅ በመስጠት ኃላፍነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ያስገነዝባሉ። ከዚህ ባለፈ በሀገሪቱ ሰላም እና እርቅ እንዲፀና ሁሉም የሲዳማ ሽማግሌዎች ጉዱማሌ ወጥተው በጋራ ሊመክሩና መፍትሔ ሊያበጁ እንደሚገባም አቶ መሐመድ ይገልጻሉ።
የሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፍ አቶ ጃጎ አገኘሁ እንደሚሉት፤ የፍቼ ጫምባላላ በዓል ከዘመን መለወጫ በዓልነቱ ባሻገር በውስጡ በርካታ እሴቶችን ይዟል። ምንም እንኳን ግጭቶች ተፈጥሯዊ ቢሆኑም በዚህ በዓል በግጭትና በጥላቻ በሕዝቦች ዘንድ የተበላሹ ግንኙነቶች ይታደሳሉ። ግጭቶቹ እንዲፈቱ ሕዝቦችን በማስታረቅና ወደሰላም በመመለስ ረገድ ደግሞ የሀገር ሽማግሌዎች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው። ያለ እርቅ ፍቼ ጫምባላላን ማክበር አይቻልም። ግጭትንና ጥላቻን ይዞ ወደ አዲሱ ዓመት መሸጋገር አይቻልም። ከዚህ እንፃር በዓሉ የእርቅ፣ የመቻቻልና የሰላም በዓል ነው ማለት ይቻላል። የተጋጩ ማኅበረሰቦችንም ሽማግሌዎች በ‹‹አፍኔ›› ሥርዓት ያስታርቃሉ። እርቅን ያወርዳሉ፤ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋሉ። ከዚህ አኳያ በዓሉ በውስጡ የያዛቸውን እሴቶችን በአግባቡ መጠቀም የሚቻልባቸው እድሎች አሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ በፍቼ ጫምባላላ በዓል ወቅት አንድም ዕፅዋት የማይቆረጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለአካባቢ ጥበቃ የሚሰጠው ትኩረትም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይህ ትኩረት ለአረንጓዴ አሻራም የራሱ አስተዋፅዖ አለው። ከዚህ ባሻገር በፍቼ ጫምባላላ ውስጥ ያሉ ሀገር በቀል ባሕላዊ እውቀቶችና ጥበቦች ለሳይንሳዊ ጥበብ መነሻ ሆነው ያገለግላሉ።እንደ ኃላፍው ገለፃ፤ የሕዝቦችን ትስስር በማጠናከር ረገድም በዓሉ ትልቅ አስተዋፅዖ አለው። በኦሮሞ የኢሬቻ፣ በሃዲያ የያሆዴ፣ በሃላባ የሴራ፣ በወላይታ የጊፋታ፣ በጋሞ ዮዮ መስቀላ፣ በጌዲዮ ደራሮ እና ሌሎች መሰል በዓሎች በኢትዮጵያ ሲከበሩ ሕዝቦችን እንደሚያቀራርቡና በተመሳሳይ የፍቼ ጨምባላላ በዓልንም በርካታ ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው የሚያከብሩት በመሆኑ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ከመጨመር አኳያ የራሱን ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ይህ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
በዓሉ በዩኔስኮ በማይዳሰሱ የዓለም ቅርስነት ተመዝግቧልና በውስጡ የያዛቸው እሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ ለማድረግ በዓሉን በልዩ ልዩ መልኩ የማስተዋወቅ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል። ሌሎች በሳይንስና ምርምር እንዲደገፉ የማድረግ ሥራዎችም ጎን ለጎን እየተከናወኑ ናቸው። ስለዚህ ከሃዋሳ ዩኒቨርስቲና ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የዘመን አቆጣጠሩ ወደ ሳይንሳዊ መንገድ እንዲመጣ የማድረጉ ሥራ እየተካሄደ ይገኛል። ይህም በዓሉ ባሕላዊውንም ሆነ ሳይንሳዊውን መንገድ ሳያዛንፍ እንዲጠበቅ ያስችለዋል። በተመሳሳይ በጥበቡም በኩል እንዲተዋወቅ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
ለአብነትም በቤቶች ድራማ፣ በዘጋቢ ፍልሞች የማስተዋወቅና ፍቼ ጫምባላላን በተመለከተ ዳጎስ ያለ ሰነድ ተዘጋጅቶ እንደመረጃ በዩቲዩብ የሚለቀቀብት ሥራም እየተሠራ ነው። እነዚህ ሥራዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ። ትውልዱም በዓሉን በሚጠብቅ መልኩ መረጃዎችን የሚያገኝበት ሁኔታ እየተመቻቸ ይገኛል። የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ እንደሚገልፁት፤ የሲዳማ ብሔረሰብ ለኢትዮጵያ ካበረከታቸው ሥልጣኔዎች ውስጥ አንዱና ትልቁ የፍቼ ጫምባላላ የዘመን መለወጫ በዓል ነው። የኢትዮጵያን ሥልጣኔ እንደ ምሶሶ ይዘው ያሉት ፍቼ ጫምባላላን የመሳሰሉና በሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ውስጥ ያሉ ባሕላዊ እሴቶች፣ታሪኮችና ቅርሶች ናቸው። በዩኔስኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተመዘገቡት የማይዳሰሱ የኢትዮጵያ ቅርሶች ውስጥ አንዱ የፍቼ ጫምባላላ በዓል እንደመሆኑ ይህ የዘመን መለወጫ በዓል ከሲዳማ ሃብትነት ተሻግሮ የኢትዮጵያ ብሎም የዓለም ሀብት ሆኗል። ፍቼ ጫምባላላን የመሳሰሉ በርካታ የብሔር ብሔረሰቦች የማይዳሰሱ ቅርሶች ለምሳሌ እንደ ሀዲያው ያሆዴ፣እንደ ወላይታው ዮዮ ጊፋታና ሌሎችም ቅርሶች የሕዝቦቹ ወይም የሀገሪቱ ትልቅ እውቀት ናቸው።
የሲዳማ የዘመን አቆጣጠርም ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው። ስነ ከዋክብትን መቁጠር፣ የተለያዩ ከዋክብትንና ጨረቃን አገናኝቶ ቀናትን፣ ሳምንታትን፣ ወራትንና ዓመታትን መቁጠርም ቀላል አይደለም። ከዚህ አኳያ ይህ ትልቅ እውቀትና ሥልጣኔ እንደመሆኑና ሀገር በቀል እሴት እንደመሆኑ መጠበቅና ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ያስፈልጋል። የዓለም ቅርስ እንደመሆኑ መጠን ደግሞ የጎብኚዎችን ቀልብ እንዲስብ ይህን ቅርስ በስፋት የማስተዋወቅ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር በኩልም የተጀመሩ አንዳንድ ሥራዎች አሉ። የሲዳማ ሕዝብ ትልቅ ሥነ ሥርዓትና ሥነ ምግባር ብሎም ትልቅ ታሪክ ያለው ሕዝብ ነው። በኢትዮጵያ እንደ ሲዳማ ያሉ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችም ተመሳሳይና የጋራ እሴቶች አላቸው። እነዚህን እሴቶች መጠበቅና መንከባከብ ብሎም ልክ እንደ ፍቼ ጨምባላላ የዘመን መለወጫ በዓል በዩኔስኮ በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች ተርታ እንዲመዘገቡ ሁሉም ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል። የሕዝቦች ማኅበራዊ ትስስር፣ አንድነት፣ ባሕል፣ እሴት ከሚሳኤል የበለጠ ኃይል አለውና እነዚህን እሴቶች ማበልፀግና ማጠናከር ብሎም መጠቀም ያስፈልጋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም