ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚያጠናክሩ ቅርስ እና ባህላዊ ዕሴቶች

ኢትዮጵያ በርካታ ባህላዊ እሴቶች ያሏት ሀገር ነች። እነዚህ ባህላዊ ዕሴቶች ለመላው ኢትዮጵያውያን የማንነት፣ የኩራት እና ራስን ለመግለጥ የሚያስችሉ ሀብቶች ናቸው። ከትውልድ ትውልድ በቅብብል የመጡ የእያንዳንዱን የማኅበረሰብ ክፍል እና ግለሰብ ስብዕና አጉልተው የሚያንፀባርቁ እንደዚሁም የማንነት ግብር መገለጫዎች ናቸው። እነዚህን ሀብቶቻችንን ሁሉ ዘርዝሮ መናገር አይቻልምና ለዛሬው ‹‹ሀገርኛ ዓምዳችን›› እንደ ሀገር ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ መስተጋብራችንን የሚያጠናክሩ በሰሜን ሸዋ ዞን የሀገራችን ክፍል የሚገኙ ባህላዊ እሴቶች እንድንቃኝ እንሆናለን፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ሰፋ ያሉ ሃሳቦችን ከሰጡን መካከል ደግሞ በሰሜን ሸዋ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ተዋበች ጌታቸው ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ባህላዊ እሴቶቻችን ማኅበራዊ መስተጋብሮቻችን የምናጠናክርባቸው እና ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸው ናቸው። ባህላዊ ዕሴቶች ከቦታ ቦታ፤ ከአካባቢ አካባቢ ቢለያዩም የእርስ በርስ ማኅበራዊ መስተጋብራችንን በማጠናከር ብርቱ ሀገራዊ አበርክቶ አላቸውም። ከዚህ አንጻርም እንደ ሰሜን ሸዋ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ቀደምት ዕሴቶችን በለውጡ መንግሥት ሰላም፤ ዴሞክራሲን እና አንድነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ እየተሠራባቸው ካሉ ዕሴቶች ጋር በማስተሳሰር እንዲጎለብቱ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ ነው።

ክንውኑ ከፍቅር፤ ይቅርታ እና መደመር ጋር ተሰናስለው እየተሠራባቸው ካሉ ሀገራዊ እሴቶች ጋር በማስተሳሰር በሀገር ውስጥ ያሉ የአስተሳሰብ እና የአመለካከት ልዩነቶችን ለማስታረቅ እንዲሁም ሁሉንም ማኅበረሰብ ወደ አዲሱ የለውጥ መንገድ ማዝለቅን ታሳቢ ያደረገ ስለመሆኑም ኃላፊዋ ያብራራሉ፡፡

‹‹ባህል የሰዎች ማንነትና የግብር መገለጫ ነው። መገለጫዎችም በብዙ ዓይነት የባህል ጥበቦች ሕያው ባህላዊ ዕሴቶች ሊወከሉ ይችላሉ›› ሲሉ በባህላዊ እሴቶች ዙሪያ በዞኑ እየተከናወነ ያለውን ተግባርም ያስረዳሉ። አክለውም የባህል ዕሴቱን በተግባር የመተርጎሙ ሁኔታ የሚመጣው በሚሠራው ሥራ ልክ ነው። የውክልናቸው መግዘፍና መኮሰስም የሚወሰነው የባህል ምኅዳሩ በሚፈጥረው ምቹ ሁኔታ ነው ይላሉ፡፡

ባህላችንን ማግዘፍ ማንነታችንን የመቀበልና የማስቀጠል ዕድልን የሚያሰፋ ነው። በተቃራኒው የሚታዩ ድርጊቶች ዕድልም በብርቱ የሚያጠብበት ኃይል ነው። የሌሎች ሀገሮች ልምድ እንደሚያሳየው ማኅበራዊ መስተጋብሮቻቸውን የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶች ለማብዛት የፈጠራ ክህሎታቸውን በመጠቀም ሳይቀር ጥረት የሚያደርጉበት ሁኔታ ስለመኖሩ መረጃዎች ያሳያሉ። እኛ ግን የብዙ ባህላዊ እሴቶች ባለቤቶች ብንሆንም እንደነሱ ባለማስተዋወቃችን ከባህላዊ እሴቶቻችን ማግኘት የሚገባንን ጥቅም እንዳናገኝ እንደሆንን ያብራራሉ።

አሁንም ባህላዊ እሴቶቻችንን በማስተዋወቅ የማኅበራዊ አንድነታችንና መስተጋብራችንን ዋጋ መቀበል ተገቢ በመሆኑ ተግተን እየሠራን ነው የሚሉት ኃላፊዋ፣ በዞኑ እንደ ጠራ ወረዳ ባሉት ስፍራዎች የባህል ዕሴቶች ለዘመናት ሳይተዋወቁ ቆይተዋል። በመሆኑም በወረዳው ያሉትን የባህል ዕሴቶች መለየት በማስፈለጉ በየዘርፋቸው መለየታቸውን ያነሳሉ፡፡

‹‹ባህላዊ ዕሴቶቻችንን መጠቀም በሀገራችን ሁለንተናዊ የለውጥ እና የመደመር ሂደት ውስጥ ደማቅ ዐሻራ ያሳርፋሉ›› የሚሉት ኃላፊዋ፤ ከተለዩት ውስጥ የጋራ መግባቢያችን የሆነው ቋንቋ፤ እንግዳ ተቀባይነታችን፤ በጦርነት ወይም በአንድ ሕዝባዊ ተሳትፎ የሚሻ ተግባር ወቅት የመሪን ትዕዛዝ የመቀበል እና የመተግበር ባህላዊ እሴት እንደሚገኙበትም ያብራራሉ።

‹‹ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት›› ሲሉ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ባወጁበት በዓድዋ ጦርነት ወቅት የታየው ነፋስ ያልገባበት እና የጠላት የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ያልፈታው ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን የተንፀባረቀበት ሕዝባዊ ምላሽ ከተለዩት ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዝ ነውም ይላሉ።

በዚህ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያውያን በወቅቱ ጥሪውን ላቀረቡላቸው ለሀገሪቱ መሪ ለነበሩት ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በሰጡት ታላቅ ምላሽ አንድነት እና ትብብር ገዝፎ ታይቷል። ያኔ በየግዛቱ ያሉ መሪዎች የእርስ በርስ ጦርነት ሊያስነሳ በሚችል ሁኔታ ውስጥ ቅራኔ ገብተው የሚገኙ ቢሆኑም ሀገር ግን ከሁሉም እንደምትቀድም ተገንዝበው ነገሩን ትተውታል። የጋራ ጠላትን ለመመከትም በኅብረት ዘምተዋል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድ መሆንንም መርጧል። ይህ ደግሞ ለመላው ዓለም ሕዝብ ትምህርትን የሰጠ ባህል ሆኖ አልፏል ሲሉም ማኅበራዊ መስተጋብሩ በባህል ዕሴቶቻችን ሲቃኝ ምን ያህል የድል ብስራትን እንደሚያቀዳጅ ያነሳሉ።

እንደ ዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ይሄን የአብሮነትና የትብብር መንፈስ የሚያጎለብተው ባህላዊ ዕሴት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው። በዚህም ሁሉም በዞኑ የሚከናወኑ ሥራዎች ከታች እስከ ላይ በዚህ ባህላዊ ዕሴት አግባብ የሚከናወኑበት ናቸውም ብለውናል።

ወይዘሮ ተዋበች እንደሚናገሩት፤ በዞኑ ከተለዩትና በትኩረት እየተሠራባቸው ካሉ ባህላዊ ዕሴቶች ውስጥ ሌላኛው ቋንቋ ነው። ቋንቋ የድምፅ፤ የምልክት ወይም የምስል ቅንብር ሆኖ ለማሰብ ወይም ደግሞ የታሰበን ሃሳብ ለሌላ ለማስተላለፍ የሚረዳ መሣሪያ ነው። ከዚህ አንጻርም በእነዚህ ሁሉ ባሕርያቱ ባህላዊ ዕሴቶቻችንን ከማስፋት አንጻር የማይተካ ሚና አለው። መስተጋብሮቻችንንም ያጎለብትልናል። እናም ማኅበራዊ ዕሴቶቻችንን በማጠናከሩ፤ አብሮነታችንን በማጉላቱና የሰው ልጅ ሃሳቡን፤ ፍላጎቱን እና ምኞቱን እንዲሁም አመለካከቱን የሚገልጽበት መግባቢያ በመሆኑ ረገድ ያለውን አበርክቶ በመመልከት በስፋት እንዲሠራበትም ተመርጧል። በርካታ ሥራዎችም እየተሠሩበት ይገኛል።

ሌላው እና ሦስተኛው በዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የእርስ በርስ ማኅበራዊ መስተጋብራችንን የማጠናከር ፋይዳ አላቸው ተብለው ከተለዩት ውስጥ የተካተተው እንግዳ ተቀባይነት ነው። እንግዳ በፍቅር መቀበል በኢትዮጵያ የተለመደ ነው። ይሄ የትኛውም ዓይነት ብሔር ያለው ኢትዮጵያዊ ትውውቅን ግምት ውስጥ ሳያስገባ የሚያከናወነው በጎ ተግባር ነው። አብሮ መብላት እና መጠጣትን ጨምሮ በርካታ ማኅበራዊ መስተጋብሮቻችንን የሚያጠናክሩ ተግባራት ይከወኑበታል። ራሱን የቻለ ኢትዮጵያዊነት መሠረት የሚጥል እና ወንድማማችነትን ለመፍጠር የሚያስችልም ነው። በትብብር ለሚከናወን ተግባርም ቢሆን መሠረት ይሆናል። ስለዚህም እንግዳ ተቀባይነት እና ወንድማማችነት የኢትዮጵያውያን የተፈጥሮ መዋቅራዊ ስሪት በመሆኑ እንደ ዞኑ ባህልና ቱሪዝም ይሄንንም በመለየት ትኩረት ያደረገ ሥራ እየተከወነበት ስለመሆኑ ወይዘሮ ተዋበች ያነሳሉ።

በዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የተለየው ለስብዕና ግንባታ ይጠቅማል የተባለው እና የኢትዮጵያውያኖች የአንድነት ዐሻራ በጉልህ ተንፀባርቆ ያረፈበት የካራ ምሽግ ካብ ሌላኛው በባህላዊ እሴት ውስጥ ተለይቶ እየተሠራበት ያለው ስለመሆኑ ኃላፊዋ ይናገራሉ።

በዞኑ ባህል እና ቱሪዝም መምሪያ የባህል ዕሴት ልማት ባለሙያ እየሩስ ጌታቸው እንደሚሉት፤ “ካራ ምሽግ” የሚባለው ቃል የሁለት ቃላት ጥምረት ነው። “ካራ” ማለት ቢላዋ ወይም ጐራዴ ማለት ነው። ምሽግ ማለት ደግሞ ለጠላት የማይመች ድብቅ እና የተለየ ቦታ ማለት ነው። በመሆኑም ሁለቱን ቃላት በማጣመር ቦታው “ካራምሽግ” ተሰኘ። ቦታው በጦር፣ በጎራዴ፣ በጋሻ በወረዳው ጦርነት በሚካሄድበት በድሮ ጊዜ በምሽግነት ያገለግል የነበረ ነው።

የካራ ምሽግ የጦር ካምፕ በሰሜን ሸዋ ዞን በሚዳ ወረሞ ወረዳ ርዕሰ ከተማ በስተሰሜን አቅጣጫ 22 ኪሎ ሜትር ከአዲስ አበባ ከተማ 247 ኪ.ሜትር ርቀት በበኸራ ቀበሌ ውስጥ የሚገኝም ነው። የደቡብ ወሎንና የሰሜን ሸዋ ዞኖችን የሚያገናኝ አንድ በር ብቻ ያለው ስትራቴጂካል የጦርነት ቦታ ነው። ይህ የጦርነት ካምፕ በዮዲት ጉዲት ዘመነ መንግሥት ጊዜ እንደተቆረቆረ የሚነገርለትም ነው። ምሽጉ ታላቅ የጦር አውድማ በሀገራችን የተከናወኑ አራት ታላላቅ ጦርነቶች ማለትም የዮዲት ጉዲትን፣ የአሕመድ ግራኝን፣ የጣሊያንንና የኢሕአዴግንና የደርግ ጦርነቶች የተካሄዱበት ታላቅ የጦርነት አውድማ ነው። ለዚህ ተግባር የተመረጠበት ምክንያት ቦታው ከግራና ከቀኝ በረጃጅም ገደሎች ወይም ዙሪያውን ገደላማ ሆኖ ያለው አንድ በር (መንገድ) ብቻ በመሆኑም ነው። ከመንዝ የተለያዩ ቦታዎች፣ ከደብረ ብርሃን፣ ከሞረትና ጅሩ፣ ከመርሐቤቴና አጎራባች ወረዳዎች የዮዲት ጉዲትን ጦርነት ለመከላከል በማሰብ በሰው ጉልበትና በጋማ ከብት እየተጋዘ በኅብረት እንደተካበና ሥራውም ከመክበዱ የተነሳ በየቀኑ የበርካታ ሰዎች ጣቶች እየተቆረጠና በቁና ይለቀም እንደነበር የባህል ዕሴት ልማት ባለሙያዋ እየሩስ ይናገራሉ።

የካራምሽግ ካብ የተካበበት ቦታ ከሰሜን ደቡብ ወሎ አቅጣጫ የጃማ ወረዳን በማለፍ ወደ መሐል ሀገር ለመሄድ ካራምሽግ ሲደረስ ዙሪያውን ገደላማ ሆኖ አንድ በር ብቻ ያለው ለጦርነት ስትራቴጂካል የሆነ ቦታ ነው። የካራምሽግን የጦር ካምፕ የሚያዋስኑት ከሰሜን የደቡብ ወሎ ዞን ጃማ ወረዳ ሊባኖስ ቀበሌ ከምስራቅ የድማ ማርያም ጎጥ መካከል ላይ የሚገኝ ቦታ ነው። እናም እነዚህ አካባቢዎች በሙሉ ባህላቸውን፣ ዕሴታቸውን እንዲጋሩበት ዕድል የሚፈጥር ነው ይላሉም።

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በዚሁ ቦታ አካባቢ በአራት ትላልቅ ጎራዎች የሚከፈል ካምፕ አለ። እነዚህ ተራራዎች (ካምፕ) ከታች ከደቡብ አቅጣጫ ሱንቢት መጨረሻ አካባቢ አሪሮ ጎጆ ካምፕ፣ በዚሁ በኩል አንቦ ውሃ በኩል ያለው የጦር ካምፕ ሰገነት ፤ ከሰሜን ከጭራሮ በኩል የፈሩ ካምፕ፣ ከደቡብ ወሎ ሊባኖስ ቀበሌ በኩል ያለው ካምፕ ደግሞ ዘውያ ካምፕ እየተባሉ ይጠራሉ። ይህም እንደ ላይኛው ማኅበረሰቡን በባህልና ዕሴት እንዲተሳሰር ያደርገዋል። ከዚያም ባሻገር ወደ ድማ ማርያም የሚፈሰው ውሃ ከወንጭት ጋር ይገናኛል፤ ወደ መንቀሎና መተላ አቅጣጫ የሚፈሰው ውሃ ጃራ ወንዝ ጋር ይቀላቀላል። መልሰው ታች ከወረዱ በኋላ ዋስ ላይ ወንጭት ላይ ይገናኛሉ። ይህም የውሃ ሀብታቸውን ሳይቀር በአንድ እንዲጠቀሙ የሚያስችላቸው እንደሆነ ያብራራሉ።

የካራምሽግ ካምፕ የተካበው የዮዲት ጉዲትን ጦርነት ለመከላከል ይቻል ዘንድ በወቅቱ በነበረው ምስለኔ ኤርሚያስ የተሰኘ የመርሐቤቴ ተወላጅ ነው። በወቅቱ የሚዳና 70 የመርሐቤቴ ነዋሪዎች በሙሉ ካቡን ሲክቡ በሥራው ክብደት የተነሳ የደከሙበትና ያለቁበት እንደነበረም ከመምሪያው የባህል ዕሴት ልማት ባለሙያ እየሩስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። እንደ መረጃው ከሆነ ከመንዝ፣ የጅሩን ሰው እዘዙና አምጡ ተብሎ የመንዝና የሞረት ሰዎች መጥተው ካቡት። ሰዎቹ አንድ ጊዜ አምጥተው የጣሉትና የካቡት ድንጋይ በግምት 100 ቤት ለመሥራት ይበቃ ነበር። እናም ዛሬ ድረስ ‹‹የሞረቶች ካብ›› እየተባለ የሚጠራው ይህ ካብ በወቅቱ የነበረውን የትብብር መንፈስን የሚያንፀባርቅ በመሆኑ እንዲህ አይነት ትብብሮች ይኑሩን ብሎ ለማስተማር ይጠቅማልና መምሪያው በትኩረት የሚሠራበት ባህላዊ እሴት አድርጎት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ አንስተዋል።

ባለሙያው እንደሚሉት፤ እነዚህ ቅርሶች እና ባህላዊ ዕሴቶች በማኅበረሰቡ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ፣ ክብር፣ ግምት እና ተቀባይነት አላቸው። ይህን አክብሮና ለይቶ መሥራት ደግሞ ቀጣዩን ትውልድ ማኅበራዊ መስተጋብሩን እንዲያጠናክር ማስተማር ነው። ጥበባዊ ሥራዎቹን እያየም ከማድነቅ ባሻገር የራሱ የሆነ ዐሻራ እንዲያሳርፍ ዕድል መስጠትም ነው። ትውልዱ ዘመን ተሻጋሪ ሥራን መሥራት እንዲችልም ማበረታታት ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሕዝቦች አንድነት እና የእርስ በርስ ትስስር ልዩ ዋጋ እንዲሰጠው ማስቻል ነው።

በኅብረት መንቀሳቀስ ሲቻል ማኅበራዊ መስተጋብርን ማጠናከር ብቻ ሳይሆን አይቻልም የተባሉ ነገሮችን ችሎ ማሳየትም ጭምር እንደሆነ ያስረዳልም። እናም ይህ ሀብት ያለው ክልል ሁሉ በዚህ መልኩ እየሠራና እየሰነደ ለቀጣዩ ትውልድ አስተማሪ ነገርን መተው ይገበዋል ሲሉም በማሳረጊያቸው አንስተዋል። መልካም ሳምንት!

በሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You