ጦርነት ጀግና የለውም

የሰፈራችን እድር ለፋፊ ጋሽ ቢራራ ትላንት ማለዳ ለአባቴ እንድነግረው መልዕክት ልከውኝ ነበር። ዛሬ ጠዋት መንገድ አግኝተውኝ ‹ለአባትህ ነገርከው እንዴ ቢሉኝ ነው ስበር ቤት የመጣሁት።

ቤት ስገባ አባቴ ዜና እያደመጠ ነበር። በእኛ ቤት ሕግ ውስጥ አባቴ ዜና እያደመጠ ማውራት አይፈቀድም። ጉዳይ ያለው ሰው አባቴን ለማግኘት ዜናውን እስኪጨርስ የመጠበቅ ግዴታ አለበት። እኔም በገዛ አባቴ ላይ መብት ተነፍጌ የገዛ አባቴን መጠበቅ ጀመርኩ።

ከተለያየ ሰው የተላኩት ለአባቴ ያልነገርኩት አንድ መዓት መልዕክት ልቤ ውስጥ አለ። ጊዜያቸው ያለፈ፣ ሰሚ ያጡ መልእክቶች። ይሄኛውን ግን ጠብቄም ቢሆን መናገር አለብኝ ያለዛ ጋሽ ቢራራ መታወቂያ ለማውጣትም ሆነ ለማደስ እዛች ቀበሌ ቤት ድርሽ አያደርጉኝም..ሲበዛ ቂመኛ ናቸው። የዛሬ ዓመት የጠፋ የቀበሌ መታወቂያዬን ላወጣ ሄጄ የሆንኩትን አረሳውም..ሁለት ጊዜ ለአባቴ መልዕክት ልከውኝ ረስቼው ሳላደርስ ቀርቼ ነበር ያን እንደ ቂም ቆጥረው ሳምንት ሙሉ ደጅ አስጠንተውኛል።

አሁን..አሁን አድገን ገባን እንጂ በፊት ቀበሌ ቤቱ የእሳቸው ይመስለን ነበር። ፊት እያዩ፣ ውለታ እየቆጠሩ ነበር ሲያስተናግዱ የነበሩት። ይሄ ብቻ አይደለም የመንደሩ እድር ለፋፊ ስለሆኑ ቂም የያዙባቸው ሰው ቤት ሀዘን ሲኖር ከልባቸው ጡሩንባ አይነፉም፣ ድንኳንና፣ የለቅሶ ቤት እቃ ሲሰጡ እንኳን ያዳላሉ ይባላል። በዛ ላይ መታወቂያዬ ጊዜው አልፏል መታደስ አለበት..ታዲያ የጋሽ ቢራራን መልዕክት ይዤ ወደ አባቴ ብሮጥ ምን ይገርማል ትላላችሁ?

ቤት ስደርስ አባቴ ሪሞቱን በእጁ እንደጨበጠ ዐይኑን ቴሌቪዥኑ ላይ ተክሏል። ያ ሪሞት መቼ ከአባቴ እጅ እንደሚወጣ አላውቅም። ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ ከነሪሞቱ እዛች ዘወትር የሚቀመጥባት ለወገቤ ትመቸኛለች የሚላት ባለመደገፊያ ሶፋ ላይ አየዋለው። ከሰዐትም ማታም እንዲህ እንደ አሁኑ ተንጠልጥዬ ቤት ስመጣ ከነሪሞቱ እዛችው ጠዋት የተቀመጠባት ሶፋ ላይ አገኘዋለው። እኔ እናቴና ታናሽ እህቴ በየፊናችን እንብሰለሰላለን። እናቴ ማዕድ ቤት..እህቴ ከሶፋው ላይ ከነጫማዋ፣ እኔ አንዴ በርጩማው ላይ አንዴ አግዳሚው ላይ።

አባቴ በሚሰማው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት እህህ ይላል። ዝምታ በዋጠው በዚያ ቤት ውስጥ የአባቴ እህህ እዬዬ ነበር።

አይኑን ከቴሌቪዥኑ ላይ ሳይነቀል ‹እኚህን ሰዎች አስታራቂ ጠፋ አይደል?

የአባቴን ድምጽ ተከትዬ ‹ማነው ይሄ..የሩሲያው ጠቅላይ ሚኒስትር?

‹ፑቲን ማለትህ ነው..ደሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አይደለም ፕሬዚዳንት ነው› አባቴ በኔ መሳሳት ውስጥ ጣልቃ ገባ።

‹ግን ጀግና ነው..ሀያላኖቹን እኮ አንቀጠቀጣቸው› አልኩ።

‹የጦርነት ጀግና የለውም። ጀግና ሰላም ውስጥ ነው የሚፈጠረው። ችግራችን ጀብደኝነትን ነውጥ ውስጥ መፈለጋችን ነው። ሀገራችን ለምን ድሀ የሆነች ይመስለሀል? ጀግኖቿ ሁሉ በጦርነት ውስጥ የተፈጠሩ ስለሆነ ነው። ሀገር የሰላም አምባሳደር፣ የሰላም አለቃ ነው የሚያስፈልጋት። ሀገር የይቅርታና የመቻቻል እውቀት ነው የሚያስፈልጋት። አንተም ሆንክ ታሪክህ ጀግንነታችሁን ሰላምና መረጋጋት ውስጥ ፈልጉት።

ምን እንደምል ጠፍቶኝ ዝም አልኩ። ለስሙ እኮ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነኝ፣ ለስሙ እኮ የት ይደርሳል የተባለልኝ ነኝ። አባቴ ልቡን ቀልቡን ለዜናው ሰጥቶ ዝም አለ።

‹እኛ ጋ አይድረሱብን እንጂ እነሱስ እንደ ብጥርጥራቸው› ስትል እናቴን ከወደ ጓዳ ሰማኋት። በእናቴ ንግግር አባቴ ዝም አላለም ዳግመኛ አንደበቱን ፈታ።

‹ምን ትያለሽ? ጦርነቱ እኮ በቆመህ ጠብቀኝ አይደለም..በቫለስቲክ ሚሳኤል ነው›

‹ቢሆንስ ታዲያ! የት አባታቸው ያገኙናል..

‹አሁንስ መች አጡን፣ እያገኙን እኮ ነው..የኑሮ መወደዱ፣ የታሪፍ ጭማሪው በማን የመጣ መሰለሽ በነሱ እኮ ነው›

እናቴ ዝም አለች..አባቴ የጥያቄዎቻችን መልስ ነው። አባቴን ጠይቀነው መልስ አጥቶ አያውቅም። አባቴ መልስ የሚያጣው ከታናሽ እህቴ ጋር ሲነጋገር ነው።

‹በዚሁ ከቀጠሉ እንጃልን..የዓለም ፍጻሜ በነሱ በኩል እንዳይመጣ እፈራለው›

‹ውይ.. በስመአም በወልድ! ምን እያልክ ነው? ስንት ጥሩ የሚወራ እያለ..ምነው ቢራራ?› እናቴ ለማልቀስ በቃጣው ድምጽ ከወደ ጓዳ ምሬቷን ገለጸች። ይሄን የድንጋጤ ድምጽ ያወጣው ፊቷ ምን እንደሚመስል ለማሰብ አልተቸገርኩም፡ እናቴ ሁልጊዜ ስለ መጥፎ ነገር ሲነሳ ፊቷን በፍራቻ የመዘፍዘፍ ልማድ አለባት።

‹እውነቴን እኮ ነው..ጦርነቱ ወደ ኒውክሌር ጦርነት እያዘገመ ነው›

‹ታዲያ የሆነ እንደሆነስ! እንዴት ሆኖ ነው የዓለም ፍጻሜን የሚያመጣው?

‹ኒውክሌር ማለት ዓለምን የሚያጠፋ መሳሪያ ነው..› ብሎ አባቴ ዝም አለ።

‹አበስ ገበርኩ› እያለች እናቴ ከጓዳ ወጣች። ዓለም አሁን የምትጠፋ ይመስል ሳሎኑ መሀል ላይ ቆማ እኔንም አባቴንም ታናሽ እህቴንም በአንድ ጊዜ አስተዋለችን። በእናት ዐይን፣ ሶስት ሰው በአንድ ጊዜ ሲታይ የመጀመሪያዬ ነው። ሶስት ሰው በአንድ ዐይን ማየት እንዴት ቻለችበት? እያልኩ እስከዛሬ ባላስተዋልኩት በእናቴ ብቃት እየተደነኩ ባለበት ሰዐት የታናሽ እህቴን ድምጽ ሰማሁት።

‹ግን ለምንድነው የሚጣሉት?

‹ዩክሬን የናቶ አባል ካልሆንኩ ብላ› አባቴ መለሰ።

‹ብቶን ምን ችግር አለው? እህቴ ጠየቀች።

‹ከሆነች የሩሲያን ደህንነት፣ ሀያልነት ባጠቃላይ ሉአላዊነት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል› ሲል መለሰላት። ይግባት አይግባት እንጃ አፏን ከፍታ ሌላ ጥያቄ ስታምጥ ትታየኛለች።

‹ለምንድነው የሚከተው?

‹ምክንያቱም ዓለም የራስ ወዳዶች ቤት ስለሆነች። ሁሉም ለሌሎች እንድትመች ሳይሆን ለራሱ እንድትመቸው አድርጎ እየጠፈጠፋት ነው። ይሄ የኃይል ሚዛን ደግሞ ድሀውን እየጨቆነው ነው። ዝሆኖች ሲጣሉ ሳሩ ነው የሚጎዳው። የዝሆኖች ጥል ዝሆኖችን ጎድቶ አያውቅም። በእኛም ሀገር እንዲሁ ነው..

‹ዝሆኖቹ እነማናቸው?

አባቴ እህቴን ከዚህ በላይ ሊያስረዳት አልፈለገም። ሁልጊዜ የእህቴ ጥያቄ የአባቴ መቆሚያ ነው። እኛ ቤት ውስጥ አባቴ በእህቴ፣ እህቴም በአባቴ ግራ እንደተጋቡ ነው።

እናቴ ብዙ ቆማ ወደ ጓዳ አዘገመች። ለምን እንደ ምትሰጋ አላውቅም ጦርነት አትወድም፣ ክፉ ነገር መስማት ያስጨንቃታል። ከአባቴ ንግግር በኋላ አላረፈችም። ቀን ሙሉ እዬዬ ስትል ነው የዋለችው። ‹እግዚኦ› ስትል እንኳን ከሀምሳ ጊዜ በላይ ሰምቻታለው። አባቴ የእናቴ የሙሴ ሕግ ነው። የኖረችው እየሰማችውና እያደመጠችው ነው። የዓለም ሁሉ ጌታ እግዜርን እንኳን የአባቴን ያክል አታምነውም።

አባቴ ቻናል እየቀያየረ ዜና ፍለጋ ወዲያ ወዲህ ሲል ጥዬው ወደ ውጪ ወጣሁ። ማታ ለመኝታ ወደ ቤት ስገባ አባቴን እዛው ሶፋ ላይ ስለ ሩሲያና ዩክሬን ዜና እየሰማ አገኘሁት። አስቸኩሎ ያስሮጠኝን የጋሽ ቢራራን መልዕክት ሳልነግረው እንደያዝኩት ተኛሁ። ጠዋት ከእንቅልፌ ነቅቼ ዐይኔን እያሻሸሁ ወደ ሳሎን ስገባ አባቴ የጠዋቱን ዜና ጓጉቶ እየጠበቀ አገኘሁት። ሁላችንም ጸጥ።

አባቴ በእናቴ ንግግር አርጎመጎመ። በዚህ እኔነት ስሜት ውስጥ አለማወቅ ክፉ እንደሆነ ክፉ ሰርቶ ጀግና የሆነ።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You