ሁቲዎች ሁለተኛውን የጭነት መርከብ አሰጠሙ

የየመን ሁቲዎች በጉዞ ላይ የነበረ የጭነት መርከብ ላይ ጥቃት ከፈጸሙ እና መርከቡ ቀይ ባሕር ውስጥ ከሰጠመ በኋላ ስድስት መርከበኞች መትረፋቸውን እና ቢያንስ ሦስት ሌሎች ሰዎች መሞታቸውን የአውሮፓ የባሕር ኃይል ተልዕኮ አስታወቀ። የላይቤሪያን ባንዲራ የሚያውለበልበው እና በግሪክ የሚንቀሳቀሰው ‘ኤተርኒቲ ሲ’ የተባለው የጭነት መርከብ 25 ሠራተኞችን ይዞ እየተጓዘ ነበር። መርከቡ ሰኞ ዕለት ከትንሽ ጀልባዎች በተተኮሱ የሮኬት ቦምቦች ከተመታ በኋላ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን በዚህም የመንቀሳቀስ አቅሙን እንዳጣ የእንግሊዝ የባሕር ንግድ ሥራዎች ኤጀንሲ (UKMTO) ገልጿል።

ጥቃቱ ማክሰኞ ዕለትም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን መርከበኞቹን የማዳን ሥራ የተጀመረው ሌሊት ላይ ነው። በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች፤ ኤተርኒቲ ሲ ላይ ጥቃት የፈጸሙት ወደ እስራኤል እየተጓዘ ስለነበረ እንደሆነ አስታውቀዋል። ቁጥራቸው ያልታወቁ ሠራተኞችንም “ደህንነቱ ወደ ተጠበቀ ቦታ” እንደወሰዱ ተናግረዋል።

በየመን የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሁቲዎች “በሕይወት የተረፉ የቡድን አባላትን አፍነው መውሰዳቸውን” ገልጾ፤ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጥሪ አቅርቧል። የፊሊፒንስ ባለስልጣናት ከቡድኑ አባላት ውስጥ 21 ያህሉ ዜጎቻቸው እንደሆኑ ተናግረዋል። ከቀሪዎቹ መካከል አንዱ የሩስያ ዜግነት ያለው እንደሆነ እና በጥቃቱ በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት እግሩን እንዳጣም ተገልጿል።

ሁቲዎች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይህንን ዓይነቱን ጥቃት ሲፈጽሙ ይህ ሁለተኛቸው ነው። አማጺ ቡድኑ እሁድ ዕለት ‘ማሲክ ሲስ’ በተባለ ሌላ የላይቤሪያን ባንዲራ የሚያውለበልብ የግሪክ የጭነት መርከብ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል። የእሁዱን ጥቃት የፈጸሙት መርከቡ፤ “በተወረረው የፍልስጤም ግዛት ውስጥ በሚገኙ ወደቦች ላይ የተጣለውን የጉዞ ክልከላ የጣሰ ኩባንያ ንብረት በመሆኑ” ነው ብለዋል።

ሁቲዎች ማክሰኞ ዕለት የለቀቁት ቪድዮ፤ የታጠቁ ሰዎች መርከቡን ሲሳፈሩ እና መርከቡ እንሰጥም ያደረጉትን ተከታታይ ፍንዳታዎች ሲፈጽሙ አሳይቷል። በማጂክ ሲስ ላይ የነበሩት 22ቱ መርከበኞች በአካባቢው ሲያልፍ በነበረ የንግድ መርከብ አማካኝነት ተርፈዋል። እ.አ.አ ከኅዳር 2023 ጀምሮ ሁቲዎች በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ሲጓዙ የነበሩ 70 ገደማ የንግድ መርከቦችን፤ በሚሳኤል፣ በድሮኖች እና በትንሽ ጀልባዎች የተሰነዘሩ ጥቃቶች ዒላማ አድርገዋል።

አሁን ደግሞ አራት መርከቦችን አሰጥመዋል፣ አምስተኛውን መርከብ አግተዋል፣ ቢያንስ ሰባት መርከበኞችን ገድለዋል። ቡድኑ እነዚህ ድርጊቶች የሚፈጽመው ጋዛ ውስጥ በእስራኤል እና በሐማስ መካከል በሚደረገው ጦርነት ውስጥ ለፍልስጤማውያንን ያለውን ድጋፍ ለማሳየት እንደሆነ ይገልጻል። ቡድኑ ዒላማ የሚያደርገው ከእስራኤል፣ ከአሜሪካ ወይም ከእንግሊዝ ጋር ግንኙነት ያላቸውን መርከቦች እንደሆነ ብዙ ጊዜ ይናገራል።

እነዚህን የሁቲ ጥቃቶች ተከትሎ አገራቱ የመን ላይ የአየር ድብደባዎችን ፈጽመዋል። ረቡዕ ዕለት በቀይ ባሕር የሚገኘው እና ‘ኦፕሬሽን አስፓይድስ’ የተባለው የአውሮፓ ሕብረት የባሕር ኃይል ተልዕኮ፤ በኤተርኒቲ ሲ ላይ ለተፈፀመው ጥቃት እየተሰጠ ባለው ዓለም አቀፍ የነፍስ አድን ሥራ ላይ እየተሳተፈ መሆኑን ገልጿል።

ተልዕኮው፤ “በአሁኑ ሰዓት ባሕር ውስጥ ሲንሳፈፉ የነበሩ ስድስት መርከበኞችን መታደግ እንደተቻለ” ጠቅሷል። አንድ የአስፓይድስ ባለስልጣን፤ ከተረፉት መርከበኞች ውስጥ አምስቱ ፊሊፒናውያን፤ አንዱ ደግሞ ሕንዳዊ እንደሆኑ፤ እንዲሁም ሌሎች 19 ሰዎች አሁንም እንዳልተገኙ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

በግሪክ የሚገኝ ዲያፕሎስ የተባለ የባሕር ላይ ደህንነት ድርጅት ረቡዕ ዕለት የለቀቀው አንድ ቪድዮ ቢያንስ አምስት ሰዎችን ለማዳን የተደረገውን ጥረት ያሳየ ሲሆን ለነፍስ አድን ሥራው ከ24 ሰዓት በላይ በውሃ ላይ ማሳለፉን እንደገለጸ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ዲያፕሎስ፤ “የቀሩትን መርከበኞች ለማግኘት የምናደርገውን ፍለጋ እስከመጨረሻዋ ብርሃን ድረስ እንቀጥላለን” ብሏል። በተጨማሪም ሮይተርስ፤ የባሕር ላይ ደህንነት ኩባንያዎችን በመጥቀስ የሟቾች ቁጥር አራት መሆኑን ዘግቧል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማጂክ ሲስ እና በኤተርኒቲ ሲ መርከቦች ላይ የተፈፀሙትን ጥቃቶች አውግዟል።

ጥቃቶቹ “በኢራን የሚደገፉ የሁቲ አማጽያን በመርከብ ነጻነት እንዲሁም በቀጣናው ኢኮኖሚያዊ እና የባሕር ደህንነት ላይ የደቀኑትን ቀጣይነት ያለው አደጋ ያሳያል” ብሏል። ሁቲዎች በዓለም አቀፍ መርከብ ላይ የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ አሜሪካ ለሰባት ሳምንታት በየመን ላይ ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ግንቦት ላይ ከዋሽንግተን ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ፈጽመው ነበር። ይሁን እንጂ ስምምነቱ፤ በየመን ላይ በርካታ የመልሶ ማጥቃት ጥቃቶችን በፈጸመችው በእስራኤል ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ማቆምን እንደማይጨምር ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ የባሕር ድርጅት ዋና ፀሀፊ፤ ሰሞነኛዎቹን ተከታታይ ጥቃቶች ተከትሎ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን እንዲያጠናከሩ ጥሪ አቅርበዋል። ዋና ፀሀፊው አርሴኒዮ ዶሚንጌ፤ “ከበርካታ ወራት መረጋጋት በኋላ በቀይ ባሕር ላይ የሚፈፀሙ አሳዛኝ ጥቃቶች ዳግም መጀመራቸው የዓለም አቀፍ ሕግ እና የመርከብ ነጻነትን በድጋሚ የጣሰ ተግባር ነው” መለታቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You