ቱሪዝምን ከቴክኖሎጂ ጋር የማጣመር ጥረት

ቴክኖሎጂ ፈጣን እና ቀልጣፋ ከመሆኑ ጋር በተገናኘ ከተለመደው ወጣ ባለ ሁኔታ ለዘርፉ እገዛ እንደሚያደርግ ይታመናል። ቱሪዝም እና ቴክኖሎጂ ተለያይተው የማይታዩ የዘመናዊነት ዓለም እጅግ ወሳኝ ጥምረት መሆናቸው አጠያያቂ አይሆንም።ይህንን ተከትሎ እያደገ የመጣው የኢትዮጵያ የቱሪዝም መነቃቃት ዓውዱን በማስፋት ከቴክኖሎጂ ጋር በማበር እምርታ እያመጣ ይገኛል።

ይሄን በማስመልከት የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ቢሮ ሰሞኑን ‹‹ቱሪዝም እና ቴክኖሎጂ›› በሚል መሪ ሃሳብ፤ በስካይ ላይት ሆቴል ዝግጅቱን አድርጓል። ዝግጅቱን እና ቱሪዝምን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ዙሪያ በተሠሩ ሥራዎች ላይ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ነጋ ወዳጆ ሃሳብ አጋርተውናል። የዝግጅቱ ዋና ዓላማ ቱሪዝምን ከቴክኖሎጂ ጋር በማዋሓድ የተሠሩ ዲጂታል እሴቶችን ማስተዋወቅ፣ የተለያዩ የኦሮሚያን የቱሪዝም መዳረሻዎች ማሳየት፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ መስኅቦችን በዲጂታል ኤግዚቢሽን ማመልከት እና ማስተዋወቅ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከዚህ በፊት አዳራሽ እና ሌሎች ነገሮችን ተከራይተው ያደረጉትን ዝግጅት ወደ ኦን ላይን ዲጂታል በመቀየር ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ሰው መስኅቡ ያለበት ቦታ ድረስ ሄዶ ማየት እና መጎብኘት እንዲችል ተመቻችቶለታል ብለዋል። ይህ የመጀመሪያቸው አለመሆኑን ጠቁመው፤ በተጨማሪ ጎግል አርት እና ካልቸር ላይ መገኘት እንዲችል እንዳደረጉ አንስተዋል።

እንደዚሁም የተሻሉ አማራጮችን በመፈለግ እና ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ በቀጣይ ሰፊ ሥራዎች እንደሚሠሩ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ሃሳብ ቢሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለመደው የሚከራዩ ዲጂታል አዳራሾችን በመከራየት ዓለም ዲጂታል ኤግዚቢሽኑን እንዲያይ የማድረግ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል።

በተጨማሪ ቨርቹዋል ሪያሊቲ በመጠቀም መስኅብ ስፍራው ላይ ያሉ ያህል ስሜት እንዲሰማ በማድረግ ከተፈጥሮ ጋር ቁርኝት የሚፈጥርበት የስሜት መስተጋብር መኖሩን አንስተው፤ ለአብነት የወንጪ ገበታ ለሀገር መስኅብ በቨርቹአል ሪያሊቲ መቅረቡን ገልጸዋል።

ሌሎች ተመሳሳይ ውብ ሳይት አፖች መኖራቸውን አንስተው፤ መድረኩ ላይ ለእይታ ቀርበው ለተያዘው ዓላማ የወሳኝነት ሚናቸው የላቀ እንደሆነ አንስተዋል። አያይዘውም እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ቱሪዝም እና ቴክኖሎጂን በማቆራኘት ረገድ ድርሻቸው ከፍ ያለ በመሆኑ ጠቀሜታቸው የዛኑ ያህል ነው ብለዋል።

ቱሪዝሙን በቴክኖሎጂ እያገዙ ያሉ ተቋማት መኖራቸውን የጠቀሱት ኮሚሽነር አቶ ነጋ፤ በቀጣይ በትብብር የበለጠ አዋጭ ሥራዎች እንደሚሠሩ አንስተዋል። እንደአጠቃላይ መድረኩ እየተሠሩ ያሉ የቴክኖሎጂ ሥራዎችን ለማስተዋወቅ የተዘጋጀ እንደሆነ ጠቁመው፤ በየሁለት ዓመቱ መሰል ዝግጅቶች እንደሚደረጉ አንስተዋል። የቱሪዝም ቴክኖሎጂ ፎረም ለኢትዮጵያ ብዙ በረከቶች እንዳለው ያነሱት አቶ ነጋ፤ ሀገሪቱ ባላት የተፈጥሮ ሀብት ልክ ተጠቃሚ እንዳይደለች ገልጸዋል።እየሄዱበት ያለው መንገድ ደግሞ ችግሮችን በመለየት እና በመቅረፍ ሀገራቸው ከዘርፉ ተጠቃሚ እና አልፎ ተርፎም የዓለም የቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን መሆኑን ነግረውናል።

ቱሪዝም ከግብርና፣ ከቴክኖሎጂ፣ ከማኑፋክቸሪንግ እና ከቴክኖሎጂ ከአምስት ትላልቅ የሀገር የኢኮኖሚ ዋልታ እንደአንደኛው ተቆጥሮ ወደሥራ መገባቱ ለዘርፉ ያለው ሚና ትልቅ አድርጎታል ይላሉ። መንግሥት ለሀገር እድገት ቱሪዝምን እንደ አንድ ወሳኝ ዘርፍ ሲመርጥ በሀገራችን ያለውን ተጨባጭ የቱሪዝም ሀብት በማየት እና ቢሠራበት አትራፊ እንደሚሆን በማመን በመሆኑ ዘርፉ ሰፊ እና በይበልጥ ለኢኮኖሚ ፍጆታነት ሊውል የሚገባ ዘርፍ እንደሆነ ገልጸዋል።

ቱሪዝም በባሕሪው ከብዙ ዘርፎች ጋር የሚገናኝ ቢሆንም፤ ከቴክኖሎጂ ጋር የበለጠ ቅርብ ነው። ይሄ ዕድል የቴክኖሎጂ ትሩፋቶቹን ለቱሪዝም ሀብት በመጠቀም የሀገር ሀብቶችን ለማስተዋወቅ፣ ለመጠበቅ ለመንከባከብ እንደረዳቸው አንስተዋል። ቴክኖሎጂ በባሕሪው ሕይወት አቅላይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተፈጥሮ ሀብቶችን በዘመናዊ መንገድ ለእይታም ሆነ ለገበያ ማቅረብ አሁን ላይ የተሻለ አማራጭ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ቱሪዝምን በቴክኖሎጂ የመደገፉ ሃሳብ ከፈረንጆቹ 2022 ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ የመጣ ሃሳብ መሆኑን አንስተው፤ በቀጣይም በበለፀጉ አፖች እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች የማስተዋወቅ እና የመጠበቅ ሥራዎችን እንደሚሠሩ አንስተዋል። ያሉትን ሰው ሠራሽ ሆኑም የተፈጥሮ ፀጋዎችን ለዓለም በማሳየት ትርፋማ መሆን እንዲቻል የቴክኖሎጂ እገዛ ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል።

አሁን ካለው የሀገሪቱ የቱሪዝም መነቃቃት ጋር ተያይዞ፤ የኦሮሚያ ቱሪዝም ቢሮ እንደክልል ኃላፊነት እንዳለበት አስታውሰው፤ ኃላፊነቱን በተለያየ መንገድ በመወጣት ላይ ይገኛል ብለዋል። የጀመራቸውም ሆኑ ሊጀምራቸው በእቅድ ደረጃ ያሉ የትግበራ እቅዶቹን ወደ መሬት አውርዶ ከነበረው የተሻለ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።እንደክልል የሚጠበቀውን በማድረግ በሀገር ደረጃ በቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ ለመሆን የአቅማቸውን በመሥራት ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል።

ቱሪዝም የኅብረት ሥራ ነው። መንግሥት የኢኮኖሚ ምሰሶ ብሎ ለኢኮኖሚ ፍጆታ ሲያውለው፤ ተጋግዞ እና ተያይዞ ማልማት እንደሚገባም ተናግረዋል።በየክልሉ ያሉ የቱሪዝም መስኅቦች የሀገር ሀብቶች ናቸው።በኢትዮጵያ ስም የሚጠሩ፣ ኢትዮጵያን የሚያስጠሩ በመሆናቸው ትስስር አስፈላጊ እንደሆነ አንስተዋል።

ከዚህ በፊት ከነበረው የቱሪዝም እንቅስቃሴ ዘመናዊነትን ተላብሶ ለየት ብሎ ለማምጣት የተቻለው ሁሉ እንደሚደረግ አመልክተዋል።ቱሪዝምን እና ቴክኖሎጂን በማስተሳሰር በዲጂታል ኤግዚቢሽን፣ በጎግል ካልቸር፣ በአፕ እና ዌብ ሳይቶች በመምጣት ጥሩ ውጤቶች መምጣታቸውን አስታውሰው፤ ለቱሪዝም አገልግሎት የሚውሉ አራት ዌብ ሳይቶች አሉ ብለዋል።

የቱሪዝም እና ቴክኖሎጂ ሳምንት በሚል በየዓመቱ የሚከበር ሁነት መኖሩን በማስታወስ፤ በዓይነቱ የተለየ መሆኑን አመላክተዋል። እንደሩዋንዳ፣ ኬኒያ፣ ዑጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ኔፓል ያሉ የውጪ ሀገራትን ሰዎች በመጋበዝ እና በማሳተፍ የሚሠራውን ሥራ ጨምሮ በሌሎች ዝግጅቶችም ለየት ማለት መቻሉንም አብራርተዋል። እንደዚሁም በመሰል የቴክኖሎጂ እንቅስቃሴም ሙከራ አድርገው ለየት ማለት የተሳካላቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

‹‹በሥራችን የአፍሪካ ሀገራት ከእኛ ልምድ እየወሰዱ ነው።ጥሩ የቱሪዝም ተሞክሮ እንዳለን የሚነግሩን ሀገራት ጥቂቶች አይደሉም።›› የሚሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በአምስት ዓመታት ውስጥ በዚህ ልክ ተፅዕኖ መፍጠር መቻል ጥሩ ጅማሮ መኖሩን የሚያሳይ ነው ብለዋል። እንደ አጠቃላይ ቱሪዝምን ከቴክኖሎጂ ጋር አስተሳስረው አዲስ ነገር ለመፍጠር ያደረጉት እንቅስቃሴ እንደጥሩ የሚነሳ መሆኑን ተናግረዋል።

በየክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለሀገር ሀብት ከመጠቀም እና ወደ ገንዘብ ከመቀየር አኳያ ምን ሊሠራ ይገባል የሚል ጥያቄ አንስተንላቸው፤ እንደሀገር በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከዚህ በፊት ያልታየ የቱሪዝም መነቃቃት መኖሩን ገልጸው፤ በሂደት ችግሮችን በመቅረፍ የተሻለ እመርታ ለማምጣት ሁሉም በየፊናው ጠንክሮ መሥራት እንዳለበት ጠቁመዋል። አያይዘውም ያልተነካ ድንግል የተፈጥሮ ውበትን በማስተዋወቅ፣ በመጠበቅ ተጠቃሚነትን መረጋገጥ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

መንግስት እየሠራቸው ያሉ እንደ ገበታ ለሀገር ያሉ በየክልሉ የሚገኙ ትልልቅ ፕሮጀክቶች የቱሪዝም ውጤት በመሆናቸው ተጨማሪ ዕድሎችን እየፈጠሩ መሆኑን አስታውሰው፤ እንደዚሁም እየተሠሩ ያሉ መሠረተ ልማቶች እና የኢንቨስትመንት ውጤቶች ከሌላው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ መሆን እንዲቻል ከማድረግ ባለፈ ንቃትን የሚፈጥሩ ናቸው ሲሉ አመላክተዋል። አክለውም እነዚህ መሠረተ ልማቶች ዓለም አቀፍ ፕሮሞሽን የሚፈልጉ፣ በዲጂታል መደገፍ የሚሹ እንደዚሁም ብቃት ባለው የሰው ኃይል በመታገዝ አገልግሎታቸውን ከፍ ማድረግ ይቻላል ሲሉ ጠቁመዋል።

‹‹ከቴክኖሎጂ ጋር ውሕደት ፈጥረን የምንሠራቸው የቱሪዝም ሥራዎች ሁሉም ሊሳተፍባቸው የሚገቡ በመሆናቸው ሚዲያው የበኩሉን በመወጣት የማስተዋወቅ ሚናውን ቢወጣ ሌላውም እንደዚሁ ዐሻራውን ማሳረፍ ቢቻል በጋራ ጥሩ ውጤት ማምጣት የሚቻልበት ዕድል ሰፊ ነው።›› ሲሉ የተናገሩት ኮሚሽነሩ፤ አዲስ ነገርን ወደሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ ፕሮሞሽን ወሳኝ ነገር ነው። ሀገሩን የማስተዋወቅ ኃላፊነት ደግሞ የሁሉም ግዴታ ነው ብለዋል። ለዚች ሀገር ሁሉም በሙያው ጠጠር ቢያዋጣ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ተናግረዋል።

‹‹ስለሀገራችን ሁላችንም በተናገርን ቁጥር ሌሎች ይሰሙናል። አንዱ ተናጋሪ ሌላው አድማጭ በሆነበት ሁኔታ ለውጥ አይመጣም። ለውጥ ጽንሰ ሃሳቡ ትስስር ነው።እዚህ እኛ ቱሪዝም እና ቴክኖሎጂ ፎረምን አዘጋጅተናል። ሌላው አካልም በመጎብኘት፣ በመጠበቅ እንዲሁም በመሰል ሁኔታዎች አስተዋፅዖውን በማድረግ ዘርፉ ላይ እመርታ ማምጣት ይቻላል።›› ሲሉ ሃሳብ አጋርነት የሚያስፈልግ መሆኑን አመላክተዋል።

እንደምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ እንደሀገር የተያዘው ዓላማ በቱሪዝሙ ዘርፍ ኢትዮጵያን መግለጥ ነው። ለዚህ ደግሞ ከሀገር ቤት ባለፈ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን በመጠቀም የማስተዋወቅ ሥራዎች ይሠራሉ። በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግሬኛ፣ በጉራጌኛ ብቻ ተወስኖ የቆየው የማስተዋወቅ ልምምድ፤ ዓለም አቀፍ ዓውድ ይዞ እንደእንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ እና ዓረብኛ ባሉ ቋንቋዎች ጭምር የሚሠራበት ሁኔታዎች አሉ።ይህም ዓለም ስለኢትዮጵያ የተሳሳተውን እንዲያጠራ፣ እውነታውን ተረድቶ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ ሁሉም በሚችለው ቋንቋ ሁሉ ስለኢትዮጵያ መናገር አለበት።

ቱሪዝም የቀጣዩ ጊዜ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑ አጠያያቂ አይሆንም ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ በተለይ ያሉትን ሀብቶች በተገቢው መንገድ መጠቀም ከተቻለ በቴክኖሎጂ በመደገፍ ለዓለም ገበያ ማቅረብ እና ዘርፉ የሚጠይቀውን መስፈርት አሟልቶ በዝግጁነት መነሳት ከተቻለ አዋጪ የኢኮኖሚ ዘርፍ እንደሚሆን ጥርጣሬ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

‹‹በአፍሪካ ኬንያ በቱሪዝም በእጅጉ የተጠቀመች ሀገር ናት።አብዛኛው የኢኮኖሚ ምንጭዋ የቱሪዝም መዳረሻዎቿን ታኮ የቆመ ነው። የኬኒያን የሀብት መጠን ከኢትዮጵያ ጋር ሲነፃፀር ያነሰ ነው›› ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ነገር ግን ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም በውስን የተፈጥሮ ሀብት ብዙ ጥቅም በማግኘት ላይ ትገኛለች ብለዋል።

በርካታ ሀገራት ከኢትዮጵያ ባነሰ ተፈጥሮ በእጅጉ ሲጠቀሙ ይታያሉ። ቱሪዝም አጠቃቀም ይወስናል። ወደኢትዮጵያ ሲመጣ ግን ይሄ ነገር እምብዛም አይታይም። አሉ ብሎ ስም ጠርቶ ከመቁጠር ባለፈ ወደ ገንዘብ ሲቀየሩ አይታዩም። በእርግጥ እየታዩ ያሉ ጅምሮች ተስፋ ሰጪ መሆናቸው ባይካድም ገና ብዙ ቀሪ የቤት ሥራዎች እንዳሉ አመላካች ሁኔታዎች አሉ ብለዋል።

ቴክኖሎጂን ለቱሪዝም ቱሪዝምን ለቴክኖሎጂ እሳቤ መልካም ውጤት ያለው እንደሆነ ከባለሙያዎች ሰምተናል። የበለጠ ጎምርቶ እና ሰፍቶ የላቀ ውጤት እንዲመጣ የሁሉም ዐሻራ አስፈላጊነቱ ወሳኝ ነው። መስኅቦች በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች እንደመገኘታቸው ተባብሮ እና ተዋሕዶ መሥራት ለእድገቱ ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑ መደምደሚያ ላይ ተደርሷል።

በዝግጅቱ የፓናል ውይይት፣ በቱሪዝም ቴክኖሎጂ ኮንሰርቬሽን፣ በቱሪዝም ፋይናንሲንግ ዙሪያ፣ በዲጂታ ላይዜሽን እና ሰርቪስ ጥራት ዙሪያ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ መድረኩ የተለያዩ ሃሳቦች ተንሸራሽረውበታል። በቱሪዝም ዘርፉ ላይ አስተዋፅዖ ያደረጉ ተቋማት፣ ግለሰቦች እንዲሁም አካላት ምስጋና የተቸሩበትም ነበር።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ሰላማዊት ካሣን ጨምሮ፤ የተለያዩ እንግዶች የተገኙ ሲሆን፤ ለዘርፉ እድገት እና መሻሻል አስተዋፅዖ ያላቸው ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበውበታል።ሁለት ቀን ያህል ቆይታ የነበረው ዝግጅቱ ዘርፉ ላይ የነበሩ ተግዳሮቶችን በመመልከት በቀጣይ ለሚከናወኑ ሥራዎች አቅጣጫ ተቀምጦበታል።

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You