ቢግ ፋይፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው በግንባታ ዘርፍ ላይ ያተኮረ የንግድ ትርዒት ነው:: ይህ የንግድ ትርኢት በተለያዩ የዓለማችን ሃገራት ላይ መካሄድ ከጀመረ 40 ዓመታትን አስቆጥሯል፤ ከመቶ ሺህ በላይ ዓለም አቀፍ አቅራቢዎችንና ገዢዎችን በማገናኘት ለንግድ ሥራ ትስስር ድልድይ ከመሆኑም በላይ ለዘርፉ ባለሙያዎች ትምህርታዊ መድረኮችን በማዘጋጀት በርካታ ባለሙያዎችን ማሰልጠኑን መረጃዎች ያመለክታሉ:: በዚህም ዓለማችን ካሏት ታላላቅ እና ተፈላጊ የግንባታ ዘርፍ የንግድ ትርዒቶች ውስጥ በመሪነት ደረጃ ለመቀመጥ ችሏል።
ቢግ ፋይፍ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት በዱባይ ከሚያካሂደው የንግድ ትርዒት በተጨማሪ በሳዑዲ ዓረቢያ፣ ካታር፣ ናይጄሪያ፣ ግብፅ፣ ኬንያ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ቢግ ፋይፍ ብራንድ የንግድ ትርዒቶችን በየዓመቱ ያሰናዳል:: ኢትዮጵያም ይህን ዓለም አቀፍ ኩነት ለማዘጋጀት በአፍሪካ አምስተኛ ሀገር ሆና ተመርጣለች። የዚህ ንግድ ትርዒት አዘጋጅ ዲኤምጂ ኢቨንትስ የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም ሲሆን፣ የቢግ ፋይፍ ብራንድን በኢትዮጵያ ለማዘጋጀት ከሀገር በቀሉ ኢትኤል ኢቨንትስ ጋር በመተባበር ከግንቦት 10 እስከ 12 ቀን 2015 ዓ.ም ‹‹አዲስ ቢዩልድ ባይ ዘ ቢግ ፋይፍ ኮንስትራክት ኢትዮጵያ›› በሚል ስያሜ ይህን የንግድ ትርዒት በሚሊንየም አዳራሽ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል::
ኤግዚቢሽኑን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጠበት ወቅት እንደተገለጸው፤ ይህ የንግድ ትርዒት በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ይፋዊ ድጋፍ ያለው ሲሆን በመጀመሪያው ፕሮግራም ላይ ከ17 ሀገራት የሚመጡ ከ100 በላይ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ይሳተፉበታል። በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለውና በግንባታ ዘርፍ በሀገራችን የንግድ ትርዒት ታሪክ የመጀመሪያ የሆኑ ተከታታይ ሙያዊ ስልጠናዎች ፕሮግራሞች ይኖሩታል።
በዚህ የሲፒዲ /CPD/ ፕሮግራም/ የሙያ ስልጠና/፣ በግንባታ ዘርፍ የተሠማሩ የሀገራችን ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀቶችን እንዲያገኙ እንዲሁም የሲፒዲ ነጥቦቻቸውን እንዲጨምሩ የሚያስችሉ ከ20 በላይ የሚሆኑ መድረኮች ተዘጋጅተዋል:: እነዚህ መድረኮች በፕሮጀክት አስተዳደር፣ በቴክኖሎጂ፣ በኪነሕንጻና ሥነቅርጽ፣ በምሕንድስና እንዲሁም በዘላቂነት ዙሪያ የተዘጋጁ ሲሆኑ፣ ታዋቂ ባለሙያዎች የሙያ ልምዳቸውን ያካፍሉባቸዋል:: ከስድስት ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ ገዥዎችም በኤግዚቢሽኑ ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል::
ኤግዚቢሽኑን አስመልከቶ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኢትዮጵያ በደቻ እንደተናገሩት፤ ቢግ ፋይፍ ኢትዮጵያ የተባለው የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽን የተዘጋጀው በፈጣን እድገት ላይ ያለውን የሀገሪቱን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ጉዞን ለመቃኘት እና ያለበትን ሁኔታ ለማየት ነው:: በኤግዚቢሽኑ ከበርካታ ሀገራት የተውጣጡ ትላልቅ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ኤግዚቢሽኑ በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ድጋፍና ሙሉ እውቅና የሚሰጠው ኤግዚቢሽን ነው::
ይህ ኤግዚቢሽን በሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ጠቁመው ከዚህ ቀደም በሌሎች ሀገሮች መሰል ኤግዚቢሽኖች በስፋት ሲካሄዱና ኢትዮጵያም በኤግዚቢሽኖቹ ላይ ስትሳተፍ እንደነበር ጠቁመዋል:: በተለይም ባለፈው ዓመት በዱባይ በተካሄደው ኤግዚቢሽን ላይ ከኢትዮጵያ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ አመራሮች ተሳትፈውበታል::
የንግድ ትርዒቱ ላይ የአገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ማኅበረሰብ መሳተፋቸው ለዘርፉ ተዋናዮች ሙያዊ እድገት የራሱ አስተዋፅዖ ያበረክታል:: በርካታ ሙያተኞች የሚሳተፉበት እንደመሆኑ የሀገራችን የዘርፉ ሙያተኞች ከውጭ ሀገራት ከሚመጡ ሙያተኞች ጋር ተቀራርበው የመነጋገር እና በቀጣይ አብሮ የመሥራት እድል ይፈጥርላቸዋል:: ይህም በቀጣይ ለሀገራችን ሙያተኞች የሙያ እድገት ድርሻው የላቀ ነው ሲሉ አቶ ኢትዮጵያ ተናግረዋል::
እንደ አቶ ኢትዮጵያ ማብራሪያ፤ ኤግዚቢሽኑ ለሀገሪቱ ባለሙያዎች የሙያ እድገት ከሚያበረክተው አስተዋፅዖ ባሻገር የአገሪቱ ባለሙያዎች እና ኩባንያዎች ዓለም አቀፋዊ የኮንስትራክሽን ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ያደርጋል:: በዓለም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ተዋናይ እንዲሆኑም በር የሚከፍት ነው::
እሳቸው እንዳሉት፤ የአገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ተግዳሮት ያለበት ነው የሚሉት አቶ ኢትዮጵያ፤ ተግዳሮቶቹ የግብዓት፣ የቴክኖሎጂ፣ የክህሎት ክፍተቶች መሆናቸውን አንስተዋል:: ከኮንስትራክሽን ግብዓት አንጻር የሲሚንቶ እና ብረት እጥረት እና ዋጋ መናር ዘርፉን እየፈተኑ ካሉ ችግሮች መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው:: የግንባታ ማጠናቀቂያ ግብዓቶች እጥረትም እንዲሁ ተጠቃሽ ነው:: የግንባታ ግብዓት አማራጮችንም ከማየት አኳያ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን ነው የጠቆሙት:: ኤግዚቢሽኑ በተለይም ዘርፉን እያጋጠመ ያለውን የግብዓት እጥረት ችግርን ለመቅረፍ በየአካባቢው ያሉ አማራጮችን ለመጠቀም የሚረዱ አማራጭ መንገዶችን ለማየት በር እንደሚከፍት አስታውቀዋል::
እንደ አቶ ኢትዮጵያ ማብራሪያ፤ ለሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ሌላኛው እንቅፋት የዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም አነስተኛ መሆን ነው:: ኢትዮጵያን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ሲታይ በጣም ኋላ ቀር መሆኑ ይታወቃል:: በዓለም ላይ የኮንስትራክሽን ዘርፍ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በፍጥነት ጥቅም ላይ እያዋለ ነው:: ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን የኮንስትራክሽን ታሪክ ያላት ብትሆንም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ የኮንስትራክሽን ሥራዎችን በማካሄድ ረገድ እምብዛም ነው:: በዚህም ምክንያት ዘርፉ ማደግ ባለበት ልክ ማደግ ሳይችል ቆይቷል::
በቅርቡ በሚካሄደው ኤግዚቢሽን ላይ አንቱታን ያተረፉት ትላልቅ ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂዎች ባለቤት የሆኑ ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ ሲሆን፤ የሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ከእነዚህ ኩባንያዎች ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉ እና ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችል ሥራ እንዲሠሩ እድል የሚፈጥር ነው ተብሏል::
በዘርፉ የዳበረ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል እጥረትም መኖሩን የጠቆሙት አቶ ኢትዮጵያ፤ የክህሎት ክፍተቱ የተለያዩ መንስኤዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፤ የክህሎት ክፍተቶችን ለመሙላት በተለያዩ አካላት የሚደረጉ ጥረቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል:: ኤግዚቢሽኑ የክህሎት ክፍተቱን ለመሙላት ለሚደረገው እንቅስቃሴ የራሱን ሚና እንደሚጫወትም ነው የገለጹት::
እንደ አቶ ኢትዮጵያ ገለጻ ሀገሪቱ ለኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ አመቺ የሆኑ የተለያዩ እድሎችም አላት:: ኤግዚቢሽኑ የዘርፉን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ካለው ፋይዳ ባሻገር፤ በአገሪቱ ያለውን የኮንትራክሽን ኢንዱስትሪ እድሎችንም ለማስተዋወቅ እድል በር የሚከፍት ነው:: ሀገሪቱ ያላትን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪና በዘርፉ ያለውን ሀገር በቀል ሀብት ለማስተዋወቅ ዕድል ከመስጠት ባሻገር ሀገር በቀል ሀብት እንዴት ማስተዋወቅ እንደሚቻል፣ እንዴት ጥቅም ላይ ማዋል ፍንጭ የሚሰጥ ትልቅ ኤግዚቢሽን ነው::
ኤግዚቢሽኑ በርካታ የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ እንዲሰማሩና መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱም መነቃቃትን የሚፈጥር ነው ያሉት አቶ ኢትዮጵያ፤ በተለይም የውጭ ኩባንያዎች ከሀገር በቀል ኩባንያዎች ጋር በቅርበት የሚሰሩበትን እድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል::
ኤግዚቢሽንና ባዛር ሲካሄድ በዋናነት የሀገራችን የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ከሌሎች ሀገራት ከሚመጡ ኩባንያዎች ጋር እንዲሁም እርስ በርሳቸው የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ እድል ይፈጥራል:: በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ የኢንዱስትሪው ተዋናዮች ማለትም ተቋራጮች፣ መሐንዲሶች፣ አማካሪዎች፣ የሙያ ማኅበራት ሁሉ በቀላሉ ልምድ ማግኘት የሚችሉበት፣ የዓለማችን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የደረሰበትን ደረጃ ማየት የሚችሉበት እና በቀጣይም እንዴት አድርገው ተገናኝተው መሥራት የሚችሉበት ቢዝነስ ቱ ቢዝነስ የሚባለውን ፓርትነርሺፕ የሚፈጥሩበት ትልቅ እድል ነው::
እንደ አቶ ኢትዮጵያ ማብራሪያ፤ ለሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዎች የኮንስትራክሽን ማሽነ ሪዎች እጦት አንዱ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል:: በአገሪቱ ያሉ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች አስመጪዎች ማሽነሪዎችን የሚያስገቡት በብዙ ውጣ ውረድ ነው:: በኤግዚቢሽኑ የሚፈጠረው እድል ደግሞ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስመጡ ትላልቅ ሀገር በቀል ተቋማት የግንባታ ማሽነሪዎችን በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበትን እድል ይፈጥራል::
ቢግ ፋይፍ ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲሆን፤ ኩባንያው በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሀገራት ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ኤግዚቢሽኖችን ሲያካሄድ ቆይቷል:: በእስያ፣ በአውሮፓ በሚገኙ በተለያዩ ከተሞች ኤግዚቢሽኖችን ሲያካሂድ ቆይቷል:: በሚሊኒየም አዳራሽ ከግንቦት 10 ጀምሮ የሚካሄደው ኤግዚቢሽን ለኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ እንደ ልዩ አጋጣሚ የሚታይ ነው ብለዋል::
ኤግዚቢሽኑ ለኮንስትራክሽን ዘርፍ ከሚያበረክተው አስተዋፅዖ ባሻገር ለቱሪዝም ዘርፉም የራሱን አስተዋፅዖ ያበረክታል:: በኤግዚቢሽኑ በርካታ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት እንደመሆኑ ኤግዚቢሽኑ በኮንፈረንስ ቱሪዝም በኩል ለሀገሪቱ የሚያስገኘው ከፍተኛ ፋይዳ አለ:: ሀገሪቱ በኤግዚቢሽኑ ለመሳተፍ ከሚመጡት የውጭ ዜጎች ገቢ ታገኛለች ብለዋል::
ኤግዚቢሽኑን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጠበት ወቅት የተገኙት የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው በበኩላቸው የሀገሪቱ የኮንትራት እና የአማካሪ ኩባንያዎች ልምዶቻቸውንና ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት እና የሚያሳዩበት እድል እንደሚፈጠር ጠቁመዋል:: ኮርፖሬሽኑም ድርጅቶቹ ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት እድል ለመፍጠር በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል::
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፤ መንግሥት የኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት እየሠራ መሆኑን ተናግረው፤ በተለይም በአሁኑ ወቅት መንግሥት በኮንስትራክሽን ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት ወሳኝ ሥራዎችን እየሠራ ነው ብለዋል::
በ10 ዓመቱ እቅድም ዘርፉ ማበርከት የሚያስችለውን ሀገራዊ ሚና እንዲወጣ የተለያዩ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎችን በመጠቀም እየተሠራበት መሆኑን ጠቁመው፤ በተጨማሪም የዘርፉ የ30 ዓመት ፍኖተ ካርታ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በቅርቡ የሚካሄደው ኤግዚቢሽንም በኢትዮጵያ መካሄዱ ዘርፈ ብዙ ጠቃሜታዎች እንደሚኖረው ጠቁመዋል:: ኤግዚቢሽኑ በኢትዮጵያ መካሄድ የሀገራችንን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ሁለንተናዊ እድገት የሚያበረክተውን የላቀ ሚና በመገንዘብ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሰሩ ነው::
ዘርፉን ለማዘመን በሀገሪቱ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ባሉበት በዚህ ወቅት መካሄዱ እንደ ሀገር ልንቀስማቸውና ልንማርባቸው የሚገቡ ዓለም አቀፍ ልምዶችን አሠራሮችን፣ ዘርፉ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ በሀገራችን ለማስተዋወቅ እድል የሚፈጥር በመሆኑ ለሀገራችን እንደ ልዩ እድል የሚታይ ነው ብለዋል::
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ኤግዚቢሽኖችን በማዘጋጀት የሚታወቀው የዲ ኤም ጂ ኢቨንትስ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ቤን ግሬኒሽ እንደተናገሩት፤ ኤግዚቢሽኑ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ሰፊ ልምድ ያካበቱ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተዋንያን ከመላው ዓለም በስፋት የሚሳተፉበት ነው:: በኤግዚቢሽኑ ላይ የሚሳተፉ አካላት በግንባታ፣ በግንባታ ዲጂታላይዜሽን እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የረጅም ዘመን ልምድ ያላቸው መሆናቸውን አንስተዋል:: ኤግዚቢሽኑ ለኮንስትራክሽን ዘርፍ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ የመፍትሔ ሀሳቦች የሚቀርቡበት ሲሆን ከዚህ ባለፈም በዘርፉ ያሉ ባለድርሻ አካላት እውቀትንም አንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ነው ብለዋል::
በተጨማሪም ዘመኑ የደረሰበትን የሕንጻ ውስጥ ንድፎች እና የፊኒሽንግ ሥራዎች፣ የግንባታ እቃዎች እና መሣሪያዎች፣ የሶላር እና የከተማ ዲዛይን ላይ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን እንዲሁም ምርቶቻቸውን ለመጎብኘት እና የንግድ ትስስር ለመፍጠር ምቹ እድል የሚፈጥር እንደሆነም አንስተዋል::
ኤግዚቢሽኑ እነዚህ ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ማኅበረሰብ ጋር እንዲገናኙ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመው፤ ባለሙያዎቹ ከኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ማኅበረሰብ ጋር የሚኖራቸው መስተጋብር የሀገሪቱን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አንድ እርምጃ እንደሚያሳድግ ጠቁመዋል::
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28/2015