የባቡር ትራንስፖርትንና ሎጂስቲክስ አገልግሎትን ለማዘመን ያለመው ሪፎርም

ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ለመሸጋገር ለምታደርገው ጉዞ የባቡር መሠረተ ልማት ወሳኝ የልማት አንቀሳቃሽ እንደሆነ ታምኖበታል። በመሆኑም ዘርፉን ለማሳደግ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወን ላይ ትገኛለች። በሀገር ውስጥ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲሳለጡና ከዓለም ጋር ያላትን የንግድ ትስስር የሚያቀላጥፍና የሚያሳድግ እንደመሆኑም አሁን ያለውን የባቡር መሠረተ ልማት በእጅጉ ለማዘመን ቆርጣ ተነስታለች። ለዚህም እንዲረዳ ስትራቴጂካዊ የሆኑ የአሠራር ሂደቶችን፣ ሕግና መመሪያዎችን በማሻሻል ጭምር እየተንቀሳቀሰች ነው።

በሌላ በኩልም በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል የባቡር መሠረተ ልማቱን ከማዘመን ጎን ለጎን የሎጂስቲክ አገልግሎቱንም አቅም በእጅጉ ማጎልበትና አሁን ከሚታይበት የተንዛዛ አሠራር ማላቀቅ ወሳኝ መሆኑም እንዲሁ ታምኖበታል። ለዚህ ደግሞ በተለይም በዘርፉ የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው ሃገራት ልምድ መውሰድ ተገቢ እንደሆነ እሙን ነው።

የኢትዮጵያ የባቡር ትራንስፖርት ከሕግ ማዕቀፍ፣ ከመዋቅርና ከአሠራር ሥርዓት እንዲሁም ከፋይናንስ እጥረት ጋር በተያያዙ ችግሮች ምክንያት ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት የሚገባውን ሚና መጫወት አለመቻሉን የዘርፉ ተዋናዮች ይናገራሉ።

በተለይም እየመጣ ካለው ፈጣን እድገትና ፍላጎት ጋር የሚመጥን አገልግሎት በመስጠት ረገድ በዘርፉ ከፍተኛ የሆነ የአቅም ውስንነት መኖሩን፣ ደረጃውን የሚጠብቅ መሠረተ ልማት ያለመዘርጋቱ፣ የተርሚናል ግንባታ በሚፈለገው መጠን ያለመከናወኑ፣ ዘመኑ በሚጠይቀው ልክ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሚመራ አለመሆኑ እንዲሁም የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓቱ ጠንካራ ያለመሆኑ ዘርፉን ወደኋላ የጎተተው መሆኑ ይጠቀሳል። በተጨማሪም ተቋማዊ የሆነ የቴክኒካል አደረጃጀት፣ ግልፅና ተጠያቂነት የታከለበት የአሠራር ሥርዓት ያለመዘርጋቱና ገለልተኛ ተቆጣጣሪ አካል ያለመኖሩም ለዘርፉ ያለማደግ በምክንያትነት የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው።

መንግሥት በዘርፉ የሚስተዋሉትን ውስብስብ ችግሮች መፍታት ያስችለው ዘንድ በተለያዩ ጊዜያት የአሠራር ማሻሻያዎችን አድርጓል። አሁንም ይህንኑ ቀጥሎበታል። ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በባቡር ትራንስፖርቱም ሆነ በሎጂስቲክ አገልግሎቱ ላይ የሚስተዋሉትን ክፍተቶች ነቅሶ የለየና የመፍትሔ አቅጣጫንም ጭምር ያስቀመጠ የሪፎርም ሰነድ አዘጋጅቶ ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል።

ይህም በባቡር መሠረተ ልማት ላይ የሚደረገው ሪፎርም ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ ሃገራት ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት በእጅጉ የሚያጠናክር፤ በዓለም ገበያም ተወዳዳሪ ሆና እንደትቀጥል የሚያግዛት እንዲሁም አጠቃላይ የትራንስፖርት ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ የሚያዘምን ይሆናል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ሪፎርሙን አስመልክቶ በቅርቡ በተካሄደ መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤ በባቡር ትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የሚደረገው ሪፎርም የንግድ ሥርዓቱን ለማዘመን፣ አቅም ለማጎልበት፣ ከሃገራት ጋር ያለውን የትራንስፖርት ትስስር ለማጠናከር እንዲሁም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ልማት በምሥራቅ አፍሪካ ሃገራት እንዲመጣ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ኢትዮጵያ እንደሃገር በዘርፉ ሪፎርሙን ማካሄዷ ፈጣን እድገቷን በማስቀጠል ብልፅግናዋን እውን ለማድረግ ያስችላታል ተብሎም ይጠበቃል።

በዘርፉ የሚስተዋሉት ውስብስብ ችግሮች ኢትዮጵያ በሃገር በቀል ኢኮኖሚ መርሐ ግብሯ ዜጎቿን ከድህነት ለማላቀቅ ለምታደርገው ብርቱ ጥረት በተለይም ደግሞ በገቢና ወጪ ንግዱ ስኬታማነት ላይ ተግዳሮት ሆነው መቆየታቸውን ዓለሙ (ዶ/ር) ያመለክታሉ። በባቡርና በመንገድ ዘርፉ ላይ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ጥናት መደረጉንና በዚያ ጥናት መሠረት ለሃገሪቱ ወሳኝ የሚባል ሪፎርም ለማድረግ መታሰቡን አስታውቀዋል።

‹‹ሎጂስቲክስ የአንድ ሃገር የደም ስር ነው፤ ሎጂስቲክስ ከሌለ ኢኮኖሚው ሕይወት ሊኖረው አይችልም›› የሚሉት ሚኒስትሩ፤ በተለይ የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት ለማድረግ ከሚያይዋቸው ወሳኝ ጉዳዮች አንዱ የሎጂስቲክስ ዋጋ መሆኑን ያመለክታሉ። በዚህ ረገድ በተለያዩ ምክንያቶች በኢትዮጵያ ያለው የሎጂስቲክስ ግንዛቤ ደካማ መሆኑ፤ አሠራሩም የዘመነ ባለመሆኑ ኢንቨስትመንቱን በሚፈለገው ልክ መሳብ አለመቻሉን ያስረዳሉ።

በተለያዩ ጊዜያት ዘርፉን ለማዘመን በርካታ ማሻሻያዎች ቢደረጉም ውስብስብና በርካታ ችግሮች ያሉባቸው በመሆናቸው ውጤት ማምጣት አልተቻለም ሲሉም ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ዘርፉን ለማሻሻል ባቡርና መንገድ ጭነት አገልግሎት ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናት መደረጉን፤ ጥናቱም አዳዲስ የመፍትሔ ሃሳቦችን መያዙን ያመለክታሉ።

በጥናቱ ከተለዩ ችግሮች መካከል በተለይ አሁን ያለው የባቡር መስመር በሙሉ አቅሙ መሥራት አለመቻሉ ዋነኛው ችግር መሆኑን ጠቅሰው፤ ‹‹ካሉን ባቡሮች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት እየሠሩ አይደሉም›› ይላሉ። ይህም የሆነው ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ አነስተኛ መለዋወጪያዎች አምጥቶ መጠገን ባለመቻሉ እንደሆነ ያብራራሉ።

ከዚህም ባሻገር በአገልግሎት ላይ ያሉትም ባቡሮች በተፈቀደላቸውና መሄድ ባለባቸው ፍጥነት ልክ እንደማይንቀሳቀሱ ይናገራሉ። ‹‹መንገዱ አጥር ወይም መከለያ ስለሌለው ባቡሩ የሚያልፈው በአብዛኛው በአርብቶ አደርና በአርሶ አደር አካባቢዎች በመሆኑ ሰውና እንስሳ እየገባበት አንዳንድ አደጋዎች እየደረሱ የሚቆምበት ሁኔታ አለ›› ሲሉ አብራርተዋል። አደጋውን ተከትሎም የሚነሳው የካሣ ጥያቄ የባቡሩን እንቅስቃሴ እያስተጓጎለው መሆኑን አመልክተው፣ የባቡር ኦፕሬተሮች ቀስ ብለው ለመሄድ መገደዳቸውን ያስረዳሉ። ‹‹በሰዓት 120 ኪሎ ሜትር መሄድ የሚገባው ባቡር 40 ኪሎ ሜትርና ከዚያ በታች ለመሄድ ይገደዳል፤ ይህም የአገልግሎቱን ቅልጥፍና ገድቦታል›› በማለትም አስታውቀዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ የባቡር ትራንስፖርቱ ችግር የቅልጥፍና ብቻ ሳይሆን በመጠንም በቂ አይደለም። የባቡር መስመሩ ሲገነባ የሎጂስቲኩን አብዛኛውን ሸክም ይይዛል ተብሎ ቢታሰብም፣ አሁን ላይ ድርሻው ከ14 በመቶ አይበልጥም። አሁንም 86 በመቶ የሚሆነው እቃ በተሽከርካሪ እየተጫነ ነው ያለው። በመሆኑም የዘርፉን ቅልጥፍና በመጨመር ውጤታማ ለማድረግ ለዚህ ደግሞ ተጨማሪ ተዋናዮችን መጨመር በሚያስችል መልኩ ጥናቱ እንዲካሄድ ተደርጓል።

‹‹ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ በፍጥነት እያደገ ያለች ሃገር ናት፤ በዚሁ ልክ የወጪና ገቢ ምርት መጠን እየጨመረ ነው፤ አሁን ባለው ሁኔታ ይህንን ሊያስተናግድ የሚችል የሎጅስቲክ ሥርዓት የለንም›› የሚሉት ዓለሙ (ዶ/ር)፤ በተለይም ጅቡቲ እቃዎች ደርሰው በጭነት አገልግሎት ችግር ቶሎ ያለመጫን፤ የተጫነውም በታሰበበት ቦታ ያለመድረስ ሁኔታዎች ዘርፉ እንዳይዘምን ተግዳሮት እንደሆነ ያስረዳሉ።

በተመሳሳይ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በተለይም የቡና እና አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በከፍተኛ ደረጃ መጨመራቸውን ጠቅሰው፣ ሎጂስቲክሱ በሚያድገው ኢኮኖሚ ልክ ማደግ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፤ ኢኮኖሚውን መምራት በሚችልበት አቅም ላይ ሊደርስ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ። ሪፎርሙ ያስፈለገውም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ነው የጠቆሙት።

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ በሃገሪቱ የጭነት ተሽከርካሪዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑም ሌላው አጠቃላይ የሎጂስቲክ አገልግሎቱ ቅልጥፍና እንዳይኖረው ያደረገ ምክንያት ነው። የሎጂስቲክስ የአሠራር ሥርዓቱ ያለመዘመኑና ዲጂታላይዝ ያለመደረጉም አገልግሎቱ የተንዛዛ እንደሆን አድርጎታል።

‹‹ዘርፉ የኦፕሬሽን ብቻ ሳይሆን የሕግ ማዕቀፍ፣ የአደረጃጀትና የፋይናንስም ችግር አለበት›› የሚሉት ሚኒስትሩ፤ በመሆኑም ሚኒስቴሩ ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ባካሄደው ጥናት እነዚህንና ሌሎች በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በዝርዝር ለመዳሰሰ ጥረት መደረጉን ያመለክታሉ። በጥናቱ ላይ ከመንግሥት ተቋማት ባሻገር ከግሉ ዘርፍ ተዋናዮች ጋር ውይይት የሚደረግበትና ግብዓት የሚሰበሰብበት መሆኑን ጠቅሰው፣ እንደ ዓለም ባንክ ያሉ የልማት አጋሮችም መፍትሔ እንዲመጣ እገዛ ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ይሁንና ችግሩ በዋናነት ሊፈታ የሚችለው የግል ባለሃብቱ በስፋት ዘርፉን ሲቀላቀል እንደሆነ ዓለሙ (ዶ/ር) ይናገራሉ። ‹‹የባቡር መስመሩም አሁን ባለው የኢትዮ-ጅቡቲ ኮርፖሬሽን ብቻ ኢትዮጵያ ያለመችውን እድገት ማምጣትም ሆነ በባቡር ዘርፍ ልታገኘው የሚገባትን የሎጂስቲክና ትራንስፖርት አገልግሎት ሊያሟላ አይችልም፤ ተጨማሪ ኦፕሬተር ከሃገር ውስጥም ከውጭም እንዲገባ የማበረታታት ሥራ እንሠራለን›› ሲሉም ጠቁመዋል። በተባበረና በተቀናጀ መልኩ ካልተሠራ ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል ተናግረው፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በሚደረገው ሪፎርም ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በዓለም ባንከ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ማርያም ሳሊም በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ባቡር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ዘርፉ የሚስተዋለው ችግር በወጪና ገቢ ላይ እያሳደረ ካለው ጫና ባሻገር በወደፊቱም የሃገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳርፍ ነው። ኢትዮጵያ ከጠቅላላ የሃገር ውስጥ ምርቷ 30 በመቶ የሚሆነውን ለሎጂስቲክስ ታወጣለች። ይህ የሎጂስቲክስ ወጪ በኢኮኖሚያቸው ካደጉት ሃገራት በላይ ሲሆን፣ ይህም በሃገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል። የተንዛዛውና ያልዘመነው የሎጂስቲክስ አሠራር በተለይም የግብርና እና ኢንዱስትሪው ዘርፎች ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ተጨማሪ ወጪ በየዓመቱ እንዲያወጡ ያደርጋል።

‹‹በዘርፉ የሚታየው ችግር ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ምርት ወጪዋ ውድ እንዲሆንና በውጭ ባለሃብቶች ተመራጭ እንዳይሆን አድርጎታል›› የሚሉት ዳይሬክተሯ፤ ለዚህም የአሠራር ሥርዓቱ ያለመዘመን ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ አስታውቀዋል። በተለይም ግልፅነትና ተጠያቂነት የተላበሰ ተቋማዊ አሠራር ያለመፈጠሩ ሃገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያሳጣት ስለመሆኑ ይጠቁማሉ። በመሆኑም ሪፎርሙ አጠቃላይ የሎጂስቲክስ ዘርፉንም ሆነ የባቡር መሠረተ ልማቱን ዘመኑና ዓለም በደረሰችበት ሥልጡን ደረጃ ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።

መብራቱ ደለለኝ (ዶ/ር) የኢትዮ-ጅቡቲ አክሲዮን ማኅበር የኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ አክሲዮን ማኅበሩ ባለፉት ስድስት ዓመታት ሲገነባ ከታለመለት ዓላማ አንፃር የሚጠበቅበትን ያህል መሥራት አልቻለም። በእነዚህ ዓመታት በቻይና ኮንትራክተር ሲተዳደር የነበረ ነው፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያውያን እየሠራ ሲሆን ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ ደግሞ የሪፎርም ሥራዎች እየሠራን ነው። ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት አክሲዮን ማኅበሩ የሚጠበቅበትን ዓላማ እንዲያሳካና ትርፋማ እንዲሆን ለማድረግ የሦስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።

የመጀመሪያው የሪፎርሙ ሥራ ተቋማዊ መዋቅር መሥራት እንደሆነ ጠቁመው፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት ተቋሙን መሸከም የሚችል የሰው ኃይል የማደራጀት ሥራ እየተሠራ ነው። በተጨማሪም የአጭር ጊዜ ስትራቴጂክ እቅድ የተዘጋጀ ሲሆን በዚህም ከትራንስፖርት አገልግሎቱ ባሻገር በአጭር ጊዜ ኢንቨስት የሚደረጉ ፕሮጀክቶችን ቀርፀናል›› በማለትም ይናገራሉ።

ለባቡር ከተገዙ የኤሌክትሪክ ሎኮሞቲቮች ውስጥ በአሁኑ ወቅት እየሠሩ ያሉት ከግማሽ በታች በመሆናቸው እነዚህን መለዋወጪያዎች ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ ማስገባት አንዱ የአጭር ጊዜ ፕሮጀክት እንደሆነ ያስረዳሉ። በተመሳሳይ በናፍጣ የሚሠሩትንም ወደ ሥራ ማስገባትና ለዚያ የሚያገለግሉ ግብዓቶች ከውጭ እንዲመጡ የማድረግ ሥራ እንደሚሠራ አብራርተዋል።

በተጨማሪም ቢዝነሱን ከማስፋት አንፃር አዳዲስ ፕሮጀክቶች መጀመራቸውን ጠቅሰው.‹‹ አሁን ላይ እየሰጠን ያለነው የትራንስፖርት አገልግሎት ነው፤ ነገር ግን በሪፎርሙ ባቡሩን በመጠቀም ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶችን ቀርፀን እንዲካተቱ አድርገናል›› በማለት ይናገራሉ። ከዚሁ ጎን ለጎን የሎጂስቲክ አገልግሎቱን በተቀናጀና በተሳለጠ መልኩ ለመሥራት የሚያስችሉ የአሠራር ማዕቀፎች መዘጋጀታቸውን ይጠቁማሉ። እስከአሁን በሃገሪቱ የመልቲ ሞዳል ኦፕሬተር ለሌሎች ኩባንያዎች ዝግ ነበር፤ አሁን መንግሥት ባመቻቸው ዕድል በመጠቀም መልቲ ሞዳል ኦፕሬተር ለመሆን አቅደን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን›› ሲሉም አመልከተዋል።

‹‹እስከአሁን ድረስ በዘርፉ ከነበሩ ተግዳሮቶች መካከል ዲጂታላይዝ ያለመሆኑ አንዱ ነው፤ ይህንንም ለመቀየር የሚያስችሉ ሥራዎች ተጀምረዋል። በተለይም ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለን ግንኙነት ዲጂታላይዝድ ባለመሆኑ ወደብ አካባቢ ከፍተኛ መጨናነቅና በተገልጋዮች ላይ የሚፈጠር ጫና አለ›› ይላሉ። በመሆኑም የአሠራር ሥርዓቱ ዲጂታላይዝ መደረጉ በደንበኞች የሚቀርበውን ቅሬታ ለመፍታት የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል። በባቡር መስመሮች ላይ ያሉትን መሠረተ ልማቶች በሦስት ዓመት ውስጥ በማሻሻል አገልግሎቱን የማዘመን ሥራ እንደሚከናወን ይጠቁማሉ።

እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ባቡር ወደብ አልባ ለሆነች ሃገር እንደወደብ ይቆጠራል። በዚህ ረገድም ሃገሪቱ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ግብዓት የሚመጣው በጅቡቲ ኮሪደር ነው፤ ለዚህ ደግሞ ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ ያለው የአዲስ ጅቡቲ መስመር ነው። ይህ ኮሪደር የሃገሪቱ ገቢና ወጪ የሚንቀሳቀስበት መስመር እንደመሆኑ ሎጂስቲክሱን የማዘመን ሥራ መሠራቱ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። በመሆኑም የተሳለጠ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ለመስጠት በተለይም እንደማዳበሪያና ዘይት ያሉ ወሳኝ ግብዓቶች በሚፈለገው ፍጥነትና ሁኔታ እንዲገቡ ለማድረግ የተቋሙን አቅም የማሳደግ ሥራ ይሠራል። ለዚህም አዲስ የከባድ ካርጎ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቋል፤ በቅርቡ ይጀምራል። ይህም ከዚህ በፊት ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በ50 በመቶ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላ በኩል ሃገሪቱ ከአጠቃላይ ዓመታዊ ገቢዋ 30 በመቶ ለሎጂስቲክስ ዘርፉ ወጪ ታደርጋለች ሲባል አንደኛው ምክንያት ከጊዜ አጠቃቀም አኳያ እንደሆነ ያስረዳሉ። በመሆኑ በሪፎርሙ ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ከውጭ የሚገቡትም ሆነ የሚላኩ እቃዎች በወደቦች ላይ ያላቸውን ቆይታ ማሳጠር ዋነኛው እንደሆነ ያመለክታሉ። ይህም የሎጂስቲክስ አገልግሎት ወጪን እንደሚቀንስ ይጠቁማሉ። ‹‹ለባቡር ፍጥነት መቀነስ ተግዳሮት የሚሆኑትን የሠላምና ፀጥታ ጉዳይ፤ የኃይል አቅርቦትና ከካሣ ጋር ተያይዞ የሚነሱ አለመግባባቶችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሠራን ነው›› በማለት ተናግረዋል።

ማሕሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You