አማራጭ የኢነርጂ ልማትና ቴክኖሎጂ አቅርቦት – በአማራና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች

ሀገሪቱ እየጨመረ የመጣውን የሕዝቡንና የልማቱን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ለመመለስ በውሃ፣ በንፋስና በፀሐይ ኃይል ልማት ላይ በስፋት እየሰራች ትገኛለች። ከአምስት ሺ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ የሚጠበቀውና በተወሰኑ ተርባይኖቹም ኃይል ወደ ማመንጨት የተሸጋገረውን የዓባይ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ የኃይል ምንጮችን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ሥራዋን አጠናክራ ቀጥላለች።

በዚህም ለዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል ማዳረስ እንዲሁም ኢንዱስትሪዎቿና የተለያዩ አገልግሎቶቿ የሚፈልጉትን የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ላይ ትገኛለች። የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመመለስ በተጨማሪም ለጎረቤት ሀገሮች በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እየተቻለም ነው።

የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ላይም በስፋት እየተሰራ ሲሆን፣ የገጠሩንም ሕዝብ የኤሌክትሪክ ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ተግባሮች እየተከናወኑ ናቸው። ዋናው የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር /ግሪድ/ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ የገጠር ቀበሌዎችን ከዚህ መስመር የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

በሌሎች እንደ ፀሐይ ኃይልና ባዮ ጋዝ ባሉት የኢነርጂ አማራጮች ደግሞ ከዋናው ማስተላለፊያ መስመር በርቀት የሚገኘውን የገጠሩን ሕዝብ የኢነርጂ ፍላጎት ለማሟላት ርብርቡ ቀጥሏል። በዚህም ከ200 የማያንሱ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ቴክኖሎጂዎችን ለገጠሩ ሕዝብ ለማድረስ የተለያዩ ተግባሮች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተከትሎ በርካቶችን የኢነርጂው ተደራሽ ማድረግ ስለመቻሉ፣ ሌሎች በግንባታ ላይ ስለመሆናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እንዲያም ሆኖ እስከ አሁን በኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ማድረግ የተቻለው ከሀገሪቱ ሕዝብ 54 በመቶውን ብቻ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከገጠሩ ሕዝብ ከ90 በመቶው በላይ የሚሆነው ማገዶ መሆኑንም ያመለክታሉ።

ይህን ገጽታ በመቀየር የገጠሩን ሕዝብ የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በፀሐይ እና የባዮ ጋዝ ኃይል ልማት ላይ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል። መንግሥት በሶላር ኃይል ልማት ላይ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች በተጨማሪ እንደ ትምህርት፣ ጤናና የመሳሰሉት ተቋማትና ግለሰቦች የሶላር ኃይል ማመንጫ ቴክኖሎጂዎችን በመትከል የኤሌክትሪክ ኃይል እያገኙ ናቸው።

ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይልን ከብክነት ለመታደግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ለገጠሩ ሕዝብ ለማድረሱ ሥራም ትኩረት ተሰጥቷል። ለእዚህም ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን ማውጣት እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ አምጥቶ ማላመድ ላይ በስፋት እየተሰራ ይገኛል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ በዚህ ሥራ እስከ አሁን ወደ 20 ነጥብ 5 ሚሊየን የተሻሻሉ የምድጃ ቴክኖሎጂዎች ተሰራጭተዋል። ይህንን አሃዝ እስከ 2030 ድረስ ወደ 31 ነጥብ አምስት ሚሊየን ለማሳደግ ይሰራል። ዘንድሮ ወደ ሁለት ሚሊየን የተሻሻሉና ንጹህ የኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን ለማሰራጨት ታቅዷል።

ክልሎችም ይህንኑ በማድረግ ላይ ስለመሆናቸው ያነጋገርናቸው የኢነርጂውን ዘርፍ የሚመሩ ኃላፊዎች ገልጸውልናል። የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ሽመልስ ክልሉ ከዚህ አኳያ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ መንግሥት አማራጭ የኢነርጂ ምርቶችን ለማምረትም ሆነ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ሁሉንም ቴክኖሎጂዎች ማምረት አይጠበቅበትም፤ የመንግሥት ድርሻ አምራቾችን ማደራጀትና ለእነሱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው። እነሱ ላይ የአቅም ግንባታ ሥራ ሰርቶ አምራቾቹ በቂ መረጃና እውቀት ካገኙ በኋላ ቴክኖሎጂውን ወደ ህብረተሰቡ ለማድረስ ማስተዋወቅ ላይ መሥራት ያስፈልጋል። ይህን የሚሰራ ተቋም በየደረጃው በማቋቋም እየሰራ ይገኛል።

ለእዚህ ሥራ ፋይናንስ ያስፈልጋል፤ መንግሥት የፋይናንስ ምንጮችን ያፈላልጋል ሲሉ ጠቅሰው፣ ለእዚህም ከአጋሮች ጋር በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችል ሁኔታ ይፈጥራል። ሁለተኛው ድርሻ ደግሞ የታችኛው መዋቅር /ህብረተሰቡ/ ነው ይላሉ።

አቶ ጥላሁን እንዳስታወቁት፤ በእዚህም በቴክኖሎጂ የህብረተሰቡን ጫና የሚቀነሱ ፣ ጤናውን የሚጠብቁ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት በሚያስችል መንገድ ኢነርጂን መጠቀም በሚያስችሉ ሥራዎች ላይ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል። በዚህ ላይ ከዘርፍ ዘርፍ ያለው ቅንጅት እንዲኖር ለማድረግም ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

እየተከናወኑ ያሉት ሥራዎች በቂ ናቸው ማለት አይደለም፤ አሁን ካለው የህብረተሰቡ ብዛትና የኢነርጂ ፍላጎት አኳያ የሚሰራጩት ቴክኖሎጂዎች አቅም ሊሻሻል ይገባል ሲሉም አቶ ጥላሁን አስገንዝበው፣ ይህን የሚሰሩ ባለሙያዎችና አመራሮች እውቀቱ ሊኖራቸው እንደሚገባም አስታውቀዋል።

ሥራው ከፍተኛ መጠን ያለው ፋይናንስ ይፈልጋል። በመንግሥት አቅም የሚሸፈኑት እንዳሉ ሆነው በውጭ ፋይናንስ የሚሸፈኑበትን ሁኔታ ለመፍጠር ከፍተኛ ሥራ መሥራትንም ይጠይቃል በማለት ለፋይናንስ ጉዳይ አጽንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል።

እንደ አማራ ክልል የጸጥታ ችግሮች ቢኖሩም በዚህ ላይ ብዙ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ጥላሁን፣ የክልሉ የውሃና ኢነርጂ ቢሮ የኢነርጂው ዘርፍ እስከ ታች ድረስ መዋቅር እንዲሁም ባለሙያዎች እንዳሉት አስታውቀዋል። በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ አምራቾች እና የሶላር ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፤ ቴክኖሎጂውን ወደ ህብረተሰቡ የሚያደርሱ ባለሀብቶች እንዲኖሩ ለማድረግም እንዲሁ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። ይህ ሥራ በሙሉ በመንግሥት አቅም የሚሰራ አይደለም። የግሉ ዘርፍ ከፍተኛውን ሚና እንዲወጣ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉም ያመለክታሉ።

ምክትል የቢሮ ኃላፊው እንዳብራሩት፤ በክልሉ በሶላር ቴክኖሎጂዎች፣ በማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችና በተለይ በባዮ ጋዝ በኩል ብዙ ሥራዎች ተሰርተዋል። እነዚህ ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆነው በዚህ በጀት ዓመት በክልሉ ወደ 290 ሺ ምድጃዎችን/ ስቶቮችን/ ለማሰራጨት ታቅዷል። እቅዱ የተዘጋጀው የሰላም ሁኔታ ይሻሻላል በሚል ታሳቢ ተደርጎም ነው።

‹‹የ2016 በጀት አፈጻጻም 116 ሺ አካባቢ ነበር። ይህን ያህል አሰራጨን ማለት 116 ሺ አባወራዎችን ደርሰናል ማለት ነው፡፡›› ሲሉ ጠቅሰው፣ በዚህ ሥራ የቤተሰቡ አባላት በሙሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይታወቃል ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ቴክኖሎጂውን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ አቅርቦቶች ያስፈልጋሉ ያሉት አቶ ጥላሁን፣ ምድጃዎቹ የተለያዩ ዓይነቶች እንደመሆናቸው የተለያዩ ሞልዶችም ያስፈልጋሉ ብለዋል። እነዚህንም ከባለሙያዎች ወይም በዞንና በወረዳዎች በኩል ማግኘት እንደሚቻል ጠቅሰው፣ በክልሉ በጣም የተጠናከሩ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ አምራች ሴት አምራቾች እንዳሉም ጠቁመዋል። የአምራቾቹ የማምረት አቅም እንዲያድግና ገበያም እንዲያገኙ በማድረግ በኩል የተቀናጀ ሥራ እንዲሰራ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

በክልሉ ከጸጥታ ችግሩ ጋር በተያያዘ የተቀዘቀዘ ነገር ቢታይም በዚህ ሥራ ግን የተሻለ ተሞክሮ ይታያል ሲሉ ጠቅሰው፣ በዚህ ሂደት ውስጥ የጀርመኑ አጋር ጂአይዜድ ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል። ሌሎች አጋሮች በኢነርጂ ዘርፍ ላይ ብዙም አይታዩም። ይህ ድርጅት ግን ከመጀመሪያው አነስቶ በሶላር ቴክኖሎጂ ሥርጭትና ስልጠና በመስጠት የቴክኖሎጂው አቅራቢዎች በማህበር እንዲደራጁ በማድረግ በኩል እየደገፈን ነው ሲሉ አብራርተዋል። የግሉ ዘርፍ ይህን ሥራ ቢዝነስ አድርጎት እንዲቀጥልና መንግሥት ከዘርፉ እጁን እንዲያወጣ በማድረግ በኩል ድጋፉ ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀው፣ ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።

እንደ ምክትል የቢሮ ኃላፊው አቶ ጥላሁን ገለጻ፤ በአማራ ክልል በ2017 በጀት ዓመት 190 ሺ የሚሆኑ የተለያዩ ምድጃዎችን /ስቶቮችን/ ለማሰራጨት እንዲሁም 90 ሺ የሚደርሱ የሶላር ቴክኖሎጂዎችን ወደ ህብረተሰቡ ለማድረስ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል። በቅርቡ ያገኘነውን ስልጠና በመጠቀም ንቅናቄዎችን በማድረግ ያቀድነውን እናሳካለን ብለን እናስባለን ብለዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም በአማራጭ የኢነርጂ ልማትና ቴክኖሎጂ ላይ በስፋት እየተሰራ ነው። የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ አማራጭ ኢነርጂ ልማትና ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተከተል ማቲዎስ ከሀገሪቱ የገጠር ሕዝብ ከ90 በመቶው በላይ የሚሆነው የሚጠቀው ኢነርጂ ማገዶና የመሳሰሉትን /ባዮ ማስ/ መሆኑን ይገልጻሉ። የዚህን ኢነርጂ አጠቃቀም ማሻሻል ብዙ ለውጥ ማምጣት ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል። ለዚህም ቀደም ሲል ተሞክረው ሥራ ላይ የዋሉ ጥቂት የምድጃ ዓይነቶች ብቻ እንደነበሩ አስታውሰው፣ አሁን የተሞከሩት ምዳጃዎች ወደ 26 መድረሳቸውንም ይናገራሉ። ጠጣር /ሶሊድ/ የባዮ ማስ ኢነርጂ ገጠር ብቻ ሳይሆን በከተማም እንደሚሰራበት አመልክተው፣ የዚህን አጠቃቀም ማሻሻል ማለት ፋይዳው ብዙ ነው ይላሉ።

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ከቴክኖሎጂው ፋይዳዎች መካከልም ደንን ከመጨፍጨፍ ማዳን፣ ቤት ውስጥ የሕፃናትንና የእናቶችን ጤንነት መጠበቅ፣ የማገዶ ወጪን መቆጠብ፣ የካርቦን ፋይናንስ ማግኘት ማስቻል የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው። ምድጃዎችን ከሚያመርቱት አኳያ ሲታይ ደግሞ ገቢም ያስገኛል። ይህ ሥራ ይበልጥ እየተጠናከረ መሄድ ይኖርበታል ተብሎ ይታሰባል።

በሀገሪቱ በትልቅ ግሪድ ላይ /በውሃ ኃይል/ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል። ትላልቅ ፕሮጀክቶች ተሰሩ ማለት በየቤቱ ይደርሳሉ ማለት አይደለም። የኛ ሕዝብ በጣም የተበታተነ ስለሆነ በቤተሰብ ደረጃ የምንጠቀማቸውን ቴክኖሎጂዎችን ጎን ለጎን ማስኬድ ይኖርብናል ሲሉም ያብራራሉ።

እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በክልሉ በሶላር ላይም በስፋት እየተሰራ ነው። በዚህ ላይ ጂአይዜድነን ጨምሮ ከሌሎች አጋሮች ጋር ይሰራል። በገጠር በጤናና በትምህርት ተቋማት በኩል የሚሰራም አለ። በቀላሉ ኃይል በማይደርስባቸው የገጠር አካባቢዎች ደግሞ በሶላር ሚኒ ግሪድ አማካይነት ኃይል ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ክልሎችም በጀት በመያዝ ለዚህ ተግባር ትኩረት ሰጥተዋል።

በአነስተኛ ወንዞች ላይም እንዲሁ ኃይል የማልማቱ ሥራ ቀጥሏል። በዚህ ላይ በፌዴራል መንግሥትም በክልል መንግሥታትም በኩል እየተሰራ ይገኛል። በቤተሰብ ደረጃ እንደ ሶላር ሩም ሲስተም ያሉ ሥራዎች በስፋት ይሰራባቸዋል። እነዚህ በግለሰብ ደረጃ የሚሰራበቸው ናቸው። ሌሎች ሶላር የሚያሰራጩ አካላትን አቅም የማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራዎች ይከናወናሉ።

ሶላር በገጠር በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ቴክኖሎጂውን ለመስኖ ሥራ የማዋል፣ እንደ ጸጉር አስተካካዮች ያሉት ደግሞ ለገቢ ምንጭ ማግኛነት እየተጠቀሙበት መሆናቸውን ተናግረዋል። በጣም ንጹህ ቴክኖሎጂ እንደመሆኑ ዘመኑም ወቅቱም ነው ብለዋል፡፡

ባዮ ጋዝን መጠቀምም ላይም እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፣ በክልል ደረጃ አዋጭ በሆኑ አካባቢዎች የባዮ ጋዝ ልማት እየተካሄደ እንደሚገኝም አመልክተዋል። ሶሊድ ባዮ ጋዝ ጥቅም ላይ የሚውል ከሆነ ቁጠባ የግድ መሆን አለበት በሚል እሳቤ እየተሰራበት ነው ይላሉ፡፡

በሀገር ደረጃ ወደ 48 ሺ የሚደርሱ ባዮ ጋዞች መገንባታቸውን አመልክተው፣ ‹‹የኛ መዋቅር እስከ ወረዳ አለ። የኛ መዋቅሮች በዋናነት ባዮ ጋዝ ላይ ይሰራሉ። በኛ ክልል እሰከ አሁን ሁለት ሺ 300 አካባቢ የቤተሰብ ባዮ ጋዞች ተገንብተዋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ዳይሬክተር እንዳስታወቁት፤ በክልሉ በየዓመቱ ብዙ ቴክኖሎጂዎች ይሰራጫሉ። ለምሳሌ በ2016 ወደ 40 ሺ አካባቢ ሶላር ላንትሪን እንዲሁም ወደ 60 ሺ ሆም ሲስተም አሰራጭተናል።

በህብረተሰቡ ዘንድ የሶላር ፍላጎት ሰፊ ነው። ሰዎች ከኩራዝ ጨርሶ መውጣት ይፈልጋል። ከሶስት ጉልቻ መውጣት ይፈልጋል። ለእዚህ ደግሞ ቆጣቢ ምድጃዎችን ማሰራጨት ያስፈልጋል።

ሶላር ላይ ትልቁ ችግር አስመጪዎች አካባቢ ያለው ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ቴክኖሎጂ ማላመድ ላይ ብዙ ትኩረት እየተሰጠ እንዳልሆነ ነው ያመለከቱት። ሥራ ላይ ያሉት ምርጥ ምድጃዎች የቆዩ ናቸው። ስለዚሀ ይህን ማሻሻል፣ ሶላር አስመጪዎች በሰፊው የሚያመጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ባዮ ጋዝን ዝም ብለን ብንጥለው አካባቢን ይበክላል፤ ስናቃጥለው ሜቴን ይቀንሳል፤ ስለዚህ የአየር ብክለትን እንቀንሳለን የሚሉት አቶ ተከተል፣ ካርቦን ከሜቴን አንጻር ሲታይ በካይነቱ ወስን ነው ሲሉ ያብራራሉ።

መጸዳጃ ቤቶች ጭምር ለባዮ ጋዝነት ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆናቸውን አስታውቀው፣ ይህ ሲሆን ከመጸዳጃ ቤት ጋር በተያያዘ የሚመጡ ተላላፊ በሽታዎች የሚቀንሱበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ገልጸዋል። የባዮ ጋዝ ልማት ከአካባቢ ጋር ተያይዞ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚያስችል አስታውቀዋል፡፡

የቆጣቢ ምድጃ ፋይዳም ተወርቶ እንደማያልቅ ተናግረዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ደን ጭፍጨፋ መቆሙ በራሱ አካባቢን መጠበቅ ነው፤ ደኖች ካርቦንን እየተጠቀሙ ምግባቸውን ያመርታሉ። 50 በመቶ ኃይል ቆጣቢ ምድጃ ተጠቀምን ማለት 50 በመቶ ደን ቆጠብን ማለት ነው ሲሉም ፋይዳውን አብራርተዋል። ደኑን ከማዳን በተጨማሪ ማገዶው ሲቀጣጠል የሚለቀቀውን ካርቦን መቀነስ ያስችላል ብለዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የአማራጭ ኢነርጂ ልማት ከሰው ጤና ከአካባቢ ጥበቃ ከቤተሰብ ጋር ተይይዞ የሚሰራ ነው። ትልልቆቹ ዘንድ ስንሄድ ደግሞ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ያለ ኢነርጂ የሚሰራ የለም፤ በዚህ ላይ በየቦታው ይሰራበታል። ከዚህም በላይ ሊሰራበት ይገባል። የሌሎች ልማቶች አስቻይ ሁኔታ ነው፤ ፋብሪካ ቢባል የቤት ጉዳይ ቢባል ያለ ኢነርጂ የሚሆን የለም፡፡

ኃይሉ ሣህለድንግል

 አዲስ ዘመን መስከረም 25/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You