በዛምቢያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተካፋይ የሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዛሬ አመሻሽ ላይ ወደ አገሩ ሲመለስ አቀባበል ይደረግለታል:: ቡድኑ በተሰጠው አደራ መሰረት ውጤታማ ሆኖ በመመለሱ የዕውቅና መድረክ የተዘጋጀለት መሆኑንም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል::
የአፍሪካ አትሌቲክስክ ኮንፌዴሬሽን ከሚያካሂ ዳቸው ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው ከ18 ዓመት እና ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ውድድሮች በዛምቢያዋ ንዶላ ከተማ ለአምስት ቀናት ያህል ሲከናወን መቆየቱ የሚታወስ ነው:: ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ ከሆኑ 50 ቡድኖች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ወጣት ብሄራዊ ቡድን አንዱ ሲሆን፤ ዛሬ ምሽት 1 ሰዓት ከ50 ደቂቃ ላይ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ የሚደርስ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል::
ወደ ውድድሩ ከማቅናቱ አስቀድሞ ኢትዮጵያ በምትታወቅበት የአትሌቲክስ ስፖርት የተለመደ ውጤታማነቱን እንዲያስመሰክር አደራ ተጥሎበት ነበር:: አደራውን በተግባር የለወጠው ልኡኩ 6 የወርቅ፣ 11 የብር እና 6 የነሃስ በድምሩ 23 ሜዳሊያዎችን ያስመዘገበ ሲሆን፤ 13 ዲፕሎማዎችንም አሳክቷል:: በመሆኑም ይህ ቡድን ነገ ሚያዚያ 28/2015 ዓ.ም ረፋድ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበልና የማበረታቻ ዕውቅና መስጠት መርሃ ግብር የተዘጋጀለት መሆኑን ከፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል::
በየፊናቸው ይካሄዱ የነበሩት እነዚህ ውድድሮች ከ20 ዓመት በታች ቻምፒዮናው ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ፣ ከ18 ዓመት በታች ቻምፒዮናው ደግሞ ለ4ኛ ጊዜም ሲከናወን፤ በጥምረት መካሄድ ከጀመሩ 2ኛ ጊዜያቸው ነው:: በሩጫ፣ የሜዳ ተግባራትና እርምጃ በሚካሄደው ውድድር ኢትዮጵያ በምትታወቅበት የመካከለኛና ረጅም ርቀት ሩጫ (ከ800 ሜትር እስከ 10 ሺህ ሜትር) እንዲሁም በእርምጃ አትሌቶቿን አሳትፋለች:: በሁለቱም ጾታ እና የዕድሜ እርከኖች ከ30 ያላነሱ አትሌቶች ተካፋይ በመሆንም በጠቅላላው 23 ሜዳሊያዎችን በማስገኘት ቡድኑ ውጤታማነቱን ማረጋገጥ ችሏል::
ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ጸጋዋ በተለይ ከምትታወቅባቸው ነገሮች አንዱ አትሌቶቿ ተከታትለው በመግባት ሜዳሊያዎችን ጠራርገው ወደ አገራቸው በመውሰዳቸው ነው:: በዚህም ምክንያት ‹‹አረንጓዴው ጎርፍ›› የሚል ቅጽል የተሰጣቸው ሲሆን፤ በዚህ ውድድርም በሶስት ርቀቶች ይኸው ድል ተመዝግቧል:: በመጀመሪያው ዕለት በ3ሺ ሜትር አስማረች አንለይ፣ የኔዋ ንብረት እና አይናዲስ መብራቱ ከወርቅ እስከ ነሃስ ያለውን ሜዳሊያ ጠቅልለው በመውሰድ ነበር ድሉን ያስጀመሩት:: በሁለተኛው ቀን ደግሞ 1ሺ500 ሜትርም በተመሳሳይ ውብርስት አስቻለ፣ ሳምራዊት ሙሉጌታ እና ምጥን እውነቴ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ መያዝ ድሉን ማስቀጠል ችለዋል:: በአምስተኛውና የመጨረሻው ዕለት ውድድርም በ5ሺ ሜትር ውድድር አትሌት ውብርስት አስቻለ፣ አይናዲስ መብራቴ እና አስማረች አንለይ ተከታትለው በመግባት ድሉን በመካከላቸው አስቀርተዋል:: አስገራሚ በሆነ ሁኔታ እነዚህን ድሎች ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው ደግሞ ሁሉም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች የተመዘገቡ በመሆናቸው ነው::
በተለያዩ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት እንዲሁም አካዳሚዎች የሚሰለጥኑ ወጣት አትሌቶች የስልጠናውን ውጤታማ ለመለካት እንዲሁም የዓለም አቀፍ ውድድር ልምድ እንዲያገኙ በሚል መሰል ውድድሮች በእድሜ እርከን ይዘጋጃሉ:: በርካታ ታዋቂ አትሌቶች በእነዚህ ውድድሮች ውስጥ አልፈው አገራቸውን በትልልቅ የውድድር መድረኮች ማስጠራት ችለዋል:: በዚህ ውድድር ውጤታማነታቸውን ያስመሰከሩ ወጣት አትሌቶችም ተተኪ በመሆን በሌሎች ውድድሮች ላይ አገራቸውን የመወከል ዕድል የሚያገኙ ይሆናል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27/2015