የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከወጪ ንግድ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ማስታወቁ ይታወሳል:: ይህ ገቢ ከእቅዱ አንፃር በጣም ዝቅተኛ ነው ባይባልም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 312 ሺ ዶላር ቅናሽ አሳይቷል:: ለዚህ ደግሞ በዋናነት ከተጠቀሱ ምክንያቶች መካከል የዓለም ገበያ መቀዛቀዝ፣ የኮንትሮባድ ንግድ እና የፀጥታ ችግሮች ይገኙባቸዋል::
በዘርፉ እየታየ ላለው የገቢ ማሽቆልቆል በምክንያትነት የተጠቀሱት አብዛኞቹ ችግሮች በተለይም ላለፉት አራት ዓመታት በተደጋጋሚ ሲነሱ የነበሩ እንደመሆናቸው መጠን ችግሮቹን ተሻግሮ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ያልተቻለበትን ምክንያት ማወቅ ተገቢ ነው:: በተለይ የወጪ ንግዱን በመሪነት እያንቀሳቀሱ ያሉ ተቋማት አሠራራቸውን ሊፈትሹ እንደሚገባ ያመላከተ ነው::
ለውጪ ንግዱ አፈፃፀም መቀነስ በተደጋጋሚ ከተጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ የሆነውን የኮንትሮባንድ ችግር በመከላከል ሥራ ላይ የተሰማሩ ተቋማት እርስ በርስ ተናበው፤ በተጠያቂነት መንፈስ በመሥራት ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት ባይቻል እንኳን መቀነስ እንደምን ሊያዳግታቸው እንደቻለ መጠየቅም ተገቢ ይመስለኛል::
የኮንትሮባድ ንግድ በተጨባጭ መሬት ላይ እንደሚታየው አይደለም፤ በየጊዜው በዓይነትም ሆነ በመጠን እየጨመረ አጠቃላይ የሆነውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ክፉኛ እየተፈታተነው ነው:: ለዚህም በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙኃን ስለመያዛቸው የምንሰማቸው በሚሊዮኖች ብር የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ሸቀጦች ማሳያ ናቸው።
ችግሩ በተለይ በሕጋዊ መንገድ ግብር ከፍለው እየሠሩ ያሉ የንግዱ ማህበረሰብ አባላትን ቀስ በቀስ ከገበያ እያስወጣ እና ወደዚሁ ብልሹ መንገድ እንዲገቡ እየጋበዘ ስለመሆኑም በአግባቡ ማሰብ የሚጠይቅ ነው::
ለችግሩ መባባስ ተቋማቱ በተጨባጭ የቤት ሥራቸውን ያለመሥራታቸው ብቻ ሳይሆን የዚሁ የጥፋት / የሌብነት መስመር ተዋንያን ብዙ መሆናቸውም ይጠቀሳል። ችግሩን ለማጽዳት የሚሠሩ ሥራዎች ቢኖሩም በአንድ ምሽት ያልተፈጠረ በጊዜ ሂደት የገነገነ ከመሆኑ አንጻር ገና ብዙ እንደሚቀረው ይታመናል።
በተለይ የወጪ ንግዱ ዘርፍ ላይ ተግዳሮት የሆኑ የኮንትሮባንድ ችግሮችን ለመቅረፍ ባለው አቅም ሁሉ ፈጥኖ መንቀሳቀስ ለነገ የሚባል ሥራ አይደለም። እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ቀርቶ በእድገታቸውም ሆነ በሥልጣኔ ጫፍ የደረሱ አገራት የወጪ ንግድ የኢኮኖሚያቸው ምሰሶ በመሆኑ ከምንም ነገር በላይ ትኩረት የሚሰጡት ነው::
እርግጥ ነው፤ በተለይ ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ተከትሎ የመላው ዓለም ገበያ መቀዛቀዙ የማይታበይ ሃቅ ነው። ግን ደግሞ ቫይረሱ ችግር ብቻ ሳይሆን ሌሎች የገበያ አማራጮችንም መፍጠሩን ባለፉት ዓመታት በተግባር ያስመሰከሩ አገራትም አሉ:: ከነዚህ አገራት ኢትዮጵያም አንዷ ተጠቃሽ ነች።
ይህም ሆኖ ግን አሁንም ለዘመናት ከምንመካባቸው የግብርና ውጤቶች ባሻገር እሴት የተጨመረባቸው እና የእኛ መገለጫ የሆኑ አዳዲስ ምርቶችንም ወደዓለም ገበያ ይዘን በመቅረብ ተወዳዳሪ የምንሆንበት ብዙ አማራጮች እንዳሉ ይሰማኛል። ለዚህም አሁን ላይ በስንዴ ሆነ በአቦካዶ ምርቶች ላይ እየታየ ያለው ስኬት እንደ አንድ ማሳያ ሊቀርብ ይችላል። በተጨማሪ በአትክልትና ፍራፍሬ በቅመማቅመም አካባቢ ያለውን አገራዊ አቅምን በአግባቡ ማየት ተገቢነው::
ይህ ደግሞ ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ድጋፍን ጨምሮ አምራች ኢንዱስትሪውን ማበረታታት፤ በተለያዩ አገራትም ተደራሽ ለመሆን ሰፊ የሆነ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራትንም ይጠይቃል:: እርግጥ ከዚህ አኳያ ባለፉት አራት ዓመታት የተሻሉ ሥራዎች ተሠርተዋል የሚል እምነት አለኝ፤ ግን ደግሞ የተፈጠሩ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን ፈጥኖ ወደ ጥቅም መቀየሩ ላይ አሁንም ብዙ የሚቀሩ የቤት ሥራዎች አሉ::
በተለይ ይህ ሰጥቶ በመቀበል ላይ የተመሠረተ መርህ የሚከተለው የዓለም ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችሉ በጥራት ከፍ ያሉና በዓይነታቸውም የተለዩ ምርቶችን ይዞ መቅረቡ ላይ ከፍተኛ ዝግጅትና ርብርብ ማድረግ ይገባል::
ከዚህ ባሻገር ብዙዎች በአንድ ድምፅ የሚስማሙበት ጉዳይ አገሪቱ ከሁለት ዓመታት በላይ ለዘለቀ ጊዜ ጦርነት ውስጥ መክረሟ በወጪ ንግዱም ሆነ አጠቃላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ያሳደረው አሉታዊ ሚና መኖሩን ነው::
አገሪቱ በእነዚህ ጊዜያት ከገቢዋ በላይ ህልውናዋን ለመታደግ ርብርብ ማድረጓ ተገቢ ነው:: ይህም ለገቢው መቀነስ እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀስ ከመሆኑም ባሻገር ጦርነቱ በራሱ ባመጣው ጣጣ የንግድ ትስስሩንም መስመር በማበላሸቱ ከዚያ ሁኔታ ውስጥ ፈጥኖ ለመውጣት አዳጋች አድርጎት ነበር::
አሁን ግን በአገሪቱ የሰላም ጎህ ቀዶ ሕዝቡም ሆነ መንግሥት ወደነባራዊ ሁኔታው ለመመለስ እየተንደረደረ ይገኛል። በመሆኑም ከዚህ ጋር ተያይዞ የተነሱ ችግሮች መፍትሄ ሊያገኙ እንደሚችሉ ተስፋ እያየን በመሆኑ እንዲቀጥልና የወጪ ንግዳችን ዳግሞ እንዲያንሰራራ የሁሉንም ትኩረት እና ርብርብ ከወዲሁ ይሻል።
ሜሎዲ ከኳስ ሜዳ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 27/2015