የዓለም ስፔሻል ኦሊምፒክ ለተገለሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የውድድር እድልን በመፍጠር አካታች ስፖርታዊ ውድድር የሚደረግበት ትልቅ መድረክ ነው። የዘንድሮው ስፔሻል ኦሊምፒክ ውድድር በጀርመን በርሊን ከሰኔ 9-17/2015 ዓ.ም ይካሄዳል። በውድድሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ስፖርተኞች ይሳተፋሉ።
ኢትዮጵያም በውድድሩ እንደምትሳተፍ የስፔሻል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታውቋል። የኢትዮጵያ ስፔሻል ኦሊምፒክ ብሄራዊ ቡድንም በጥር ወር 2015 ዓ.ም በተካሄደው አገር አቀፍ ውድድር መመረጡ ታውቋል። ኢትዮጵያ የምትሳተፈው በአትሌቲክስ ስፖርት ሲሆን ከነዚህም ውስጥ አጭር ርቀት፣ሪሌይ (ዱላ ቅብብል)፣ ርዝመት ዝላይ ዋንኞቹ ናቸው።
ብሄራዊ ቡድኑ ዝግጅቱን ከግንቦት ወር አጋማሽ ጀምሮ ያደርጋል። በተቻለ አቅም ውጤት እንዲመዘገብ የሚያስችል ዝግጅት በመደረግ ላይም ይገኛል። ለዚህም አራት በውድድሩ በቀጥታ የሚሳተፉና አራት ተጠባባቂን ጨምሮ ቡድኑ በአጠቃላይ ስምንት አትሌቶችን አቅፎ ዝግጅቱን የሚያደርግ ይሆናል።
ብሄራዊ ቡድኑ ጠቅልሎ በአንድ ቦታ ስልጠና ያልጀመረው ባለበት የፋይናንስ እጥረት ምክንያት ሲሆን በፊት የሚደግፉት አካላትም በመዳከማቸው ድጋፎች እንዳጠሩ ታውቋል። ስፖርተኞቹ ባሉበት ቦታ በሳምንት ሁለት ጊዜ ልምምዶችን እንዲያደርጉ ስፖርቱን የሚመራው አካል ሁኔታዎችን እያመቻቸ ሲሆን ከደጋፊ አካላት በሚያገኙት ድጋፎች ውድድሩ ቀረብ ሲል ለአስራ አምስት ቀናት በውድድሩ ህጎችና መሰረታዊ ነገሮች ጠንከር ያሉ ስልጠናዎችን በመስጠት ዝግጅት እንደሚያደርግ ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ስፔሻል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ናሽናል ዳይሬክተር አቶ ገበየሁ ሙሉጌታ፤ ኮሚቴው የሚሰራው የአእምሮ እድገት ውስንነት ባለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ እንደሆነ ይናገራሉ። ብዙ ጊዜ በስፖርቱም ይሁን በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ልዩ ድጋፍ የሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደማይሆኑ የጠቆሙት አቶ ገበየሁ፣ በማህበረሰቡ ዘንድ የግንዛቤ እጥረት ስለሚኖር ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ አደባባይ የማያወጡበት ሁኔታዎች እንዳሉ ያስቀምጣሉ።
በዋናነት የኢትዮጵያ ስፔሻል ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ የአፍሪካ እና የዓለም ስፔሻል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ያሉት ተደብቀው ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ አደባባይ ወጥተው እንደማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል እኩል ተጠቃሚና በስፖርቱም እራሳቸውን መዝናናትና አገራቸውን በመወከል ውጤት ማምጣት እንዲችሉ ለማድረግ መሆኑን ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ።
ከዚህ አንጻር ኮሚቴው በርካታ ስራዎችን አቅዶ ወደ ስራ የገባ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም አቡዳቢ ላይ በተደረገ ውድድር ብሄራዊ ቡድኑ ውጤት አስመዝግቦ መመለስ እንደቻለ ይታወሳል። እንደ አቶ ገበየሁ ገለፃ፣ ዘንድሮ በጀርመን በሚደረገው ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክለው ብሄራው ቡድን ካለው ልምድ ጋር ጥሩ ዝግጅት በማድረግ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ ነው። ስፖርተኞቹ ልዩ ትኩረትና እንክብካቤ ስለሚያስፈልጋቸው የሚያሳዩትን ባህሪ ተቋቁሞ የሚያሰለጥን ባለሙያ ግን አስፈላጊ ነው። በዚህ ዘርፍ እንደ አገር የሰለጠነ ባለሙያ እጥረት ቢኖርም፤ ያሉት አሰልጣኞች በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፉና ቤተሰብ በመሆናቸው ልጆቹን በመንከባከብ ከፍተኛ ልምድን ያካበቱ ናቸው። በመሆኑም በሚሰጣቸው እንክብካቤና ስልጠና ረገድ የሚገጥም ችግር ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ኮሚቴው ከተመሰረተ የሶስት ዓመታት እድሜ ብቻ ያለው ሲሆን ትኩረት አድርጎ የሚሰራው የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች ከቤት ወጥተው እንደሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው። ኮሚቴው አሁንም በየቤቱ ብዙ ተደብቀው የሚገኙና ልጆችን ያካተተ የተለያየ ፌስቲቫልና ፎረሞችን ለማድረግ አብሮት የሚሰሩ አካላትን ይፈልጋል። የሚታዩ ስራዎችን እየሰራ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያወጡም ያበረታታል። የህብረተሰቡ ግንዛቤ ሲቀየርና ልጆቹን ሲያወጣ በቂ ባለሙያ ማፍራት ላይ ይሰራል።
በአእምሮ እድገት ውስንነት በዓለም ከ25 በላይ ስፖርቶች ውድድር ይካሄድባቸዋል። ኢትዮጵያም በነዚህ መድረኮች በውስን ስፖርትና ስፖርተኞች ትሳተፋለች። በቀጣይ ግን ቢያንስ በሶስትና አራት የስፖርት አይነቶች ለመሳተፍ በእቅድ እየተሰራ ነው። የተሳትፎ መጠን እና ተሳታፊን ለማብዛት በቂና የሰለጠነ ባለሙያን ማፍራት ግን የግድ ይላል። በባለሙያ ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላትም በሐምሌ 2015 ዓ.ም ከሁሉም ክልል ለተወጣጡ ባለሙያዎች ትልቅ የሆነ የአሰልጣኞች ስልጠናን በአዲስ አበባ ለመስጠት ታቅዷል። ለስልጠናው ከአፍሪካ ዳይሬክተሮች ጋር ግንኙነት በመደረግም ፍቃደኝነት ታይቷል።
አቶ ገበየሁ አሁን ከተመረጡት ስፖርተኞች ውስጥ ልምድ ያላቸው እና ባሉበት ቦታ ጠንካራ ልምምድ በማድረግ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው በጀርመኑ ውድድር ውጤት እንደሚጠብቁ ይናገራሉ። ‹‹አትሌቲክሱ በሌላውም የህብረተሰብ ክፍል ውጤት ስለሚመጣበት ጠንክረን ከሰራን ውጤት የማናመጣበት ነገር አይኖርም›› ሲሉም ተናግረዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 26/2015