‹‹ገና የሁለት ዓመት ዕድሜ እያለ ነበር የትኩረት ማጣት ችግር የተስተዋለበት። ትኩረቱን ወደ እኔ እንዲያደርግም ብዙ ጥሬያለሁ። ግን በፍፁም ዓይኔንም፤ ፊቴንም ለማየት አልቻለም›› ይላሉ የኦቲዝም ታማሚ ልጅ ያላቸው ወይዘሮ የሺወርቅ አጥላው።
ዛሬ ላይ ሃያ ዓመቱን የደፈነው የያኔው ጨቅላ ልጃቸው እንደ ሕፃን አልቅሶ እናቱን ጡትም ሆነ ጡጦ ጠይቋቸው አያውቅም። ጭራሽ እናቱ እንደሆኑ ያለመለየቱም ነገር ግራ ሲያጋባቸው ቆይቷል። በተለይ ሁለት ዓመቱ አካባቢ ዓይኖቹ እንደቦዘዙ ከእሳቸው በስተጀርባ ባለ ቀይ ነገር ላይ ተተክለው ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን ያስተውሉ ነበር።
‹‹እውነት ለመናገር ልጄ ቀዩን ነገር ራሱ ለማየቱ እርግጠኛ አልነበርኩም›› ይላሉ ወይዘሮ የሺወርቅ። ቀዩን ነገር ስለማየቱን ለማረጋገጥ ፊቱ ላይ ምንም ስሜት ይታይ እንዳልነበርም ይገልፃሉ። ብዙ ነገሮች ቢያንቃጭሉለት፣ ሲያንኳኩ ቢውሉ እንቅስቃሴው አለመለወጡና ጆሮው መስማቱን ሁሉ ያጠራጥሯቸው እንደነበርም ያስታውሳሉ።
ወይዘሮ የሺወርቅ ስለልጃቸው መግለፅ ሲጀምሩ እንባ አቆርዝዘው የነበሩ ዓይኖቻቸው ዘለላውን ዱብ ዱብ ያደርጋሉ። ሕፃን ልጃቸውን ወደ ሆስፒታል የወሰዱትም እነዚህን ሁሉ ምልክት ካዩበት በኋላ ነበር።
‹‹ይህ የበርካታ በኦቲዝም የተጠቁ ልጆች እናቶች ገጠመኝ ነው›› ይላሉ በአርሲ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአእምሮ ጤና ባለሙያና የኦቲዝም ሀኪም የሆኑት ሲስተር ካሰች ለታ። ሲስተር ካሰች እንደሚሉት፣ ኦቲዝም አንድ በሽታ አይደለም። ይልቁንም ኦቲዝም የሚለው ስያሜ ራሱ ከአእምሮ እድገት መዛባት ብሎም ሰው ከመለየት ጋር የተያያዘ የአእምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች የሚጠሩበት የጋራ ስያሜ ነው። ሰዎች በአብዛኛው ውስጣዊውንና ውጫዊውን ወይም ደግሞ የራሳቸውንና ከሌሎች ጋር ያላቸውን ዓለም አመጣጥነው ይኖራሉ። በኦቲዝም የተጠቁ ሰዎች ግን አኗኗራቸው እንደዚህ አይደለም።
በሕክምናው ሙያ እንደተጠናው የኦቲዝም ህመምተኞች በአብዛኛው በራሳቸው ውስጥ በፈጠሩት ምናባዊ ዓለም ብቻ ይሽከረከራሉ። በእኔነት ወይም በራሳቸው ዛቢያ ውስጥ እየተሽከረከሩም ነው የሚኖሩት። እነርሱ ልክ ባዶ ቤት ወይም ትንሽ ሳጥን ውስጥ ተቆልፎባቸው ለብቻቸው የተቀመጡ ያህል ነው የሚሰማቸው። ሁሌም በራሳቸው ጭንቅላት ውስጥ ብቻ ነው ያሉት። ከዚህም የተነሳ ለሰው ግራ የሚያጋባና ለመረዳት አስቸጋሪ የሆነ የባህርይ፣ የቋንቋና የማህበራዊ ግንኙነት ሁኔታዎች አብዝተው ይስተዋሉባቸዋል።
ከንግግር ውጪ በሆኑ የመግባቢያ ችግሮችም የተጋለጡ ናቸው። በሚያስገርም፤በሚያስደነግጥና በሚያሳስብ ሁኔታ ይወድቃሉ። የገዛ ወላጆቻቸውንም ሆነ የሌሎች የቤተሰቡን አባለት ብሎም እንግዶችን ዓይን በፍፁም ላይመለከቱ ይችላሉ። እርስ በእርስ የመተያየት የግንኙነት መስተጋብር በኦቲዝም ለተጠቁ ልጆች አይሠራም ወይም አይታወቅም።
ሲስተር ካሰች እንደሚሉት ብዙ ወላጆች የኦቲዝም ተጠቂ ልጆቻቸው ፊታቸውን ለማየት እንደማይደፍሩ ሲገልፁ መስማታቸውንና ሆኖም የአባትና እናታቸውን ፊት ገጽታ ለማየት የማይደፍሩት ፈርተው እንዳልሆነ ያስረዳሉ። ፊታቸውን የማያዩት በኦቲዝም የተጎዳው አእምሯቸው ስለወላጆቻቸው በነሱ አጠገብ መኖር ምንም ዓይነት መረጃ ስለማይሰጣቸው እንደሆነም ያብራራሉ። ይሁንና ሁሉም በበሽታው የተጠቁ ልጆች አንድ ዓይነት ባህርይና ምልክት እንደማያሳዩ ይጠቁማሉ።
የተወሰኑት በበሽታው የተጠቁ ልጆች ፍላጎት የሚያሳዩባቸው ውሱን ጉዳዮች ብቻ ይኖራሉ። ለምሳሌ የሆነ ቀለምን ውስጣቸው ስለሚረዳው ለዛ ቀለም ተመሳሳይና ተደጋጋሚ ትኩረት የሚሰጡበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። ቀሪዎቹ ደግሞ ሌላ ዓይነት ነገር ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ወይም ምንም የትኩረት ስሜት ላይኖራቸው ይችላል። አንዳንዶቹ ራሳቸውን መግለጽም ሆነ የሌሎችን ሁኔታ መረዳት ይከብዳቸዋል።
በምልክትም ሆነ በንግግር መግባባትም ያስቸግራቸዋል። ተደጋጋሚ የሆነ ትርጉም የማይሰጥም ሆነ የማይገባ ቃላት ወይም ድምጽ ወይም እንቅስቃሴ ይደጋግማሉ። ውስን ቢሆንም ስሜታዊነትም ሊታይባቸው ይችላል። በጥቅሉ በኦቲዝም የተጠቁ ልጆች (ሰዎች) ለምንም ዓይነት ነገር ምንም ዓይነት መረዳትና ምላሽ ላይሰጡ ወይም ከሚገባው በላይ ምላሽ ሊሰጡ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለም ነው ሲስተር ካሰች የሚገልፁት።
ኦቲዝም አንድ ዓይነት ብቻ አይደለም የሚባለውም ከዚሁ ተጠቂዎቹ ከሚያሳዩት ባህርይ ወይም ምልክት በመነሳት እንደሆነ ሲሰተር ካሰች ያስረዳሉ። ኦቲዝም አምስት የተለያዩ መጠሪያ ዓይነቶች እንደነበሩትም ገልፀው፤ ነገር ግን ከጊዜ በኋላ አምስቱም በአንድነት ‹‹ኦቲዝም ስፔክትረም ዲስኦርደር›› ተብሎ መጠራት እንደጀመረ ይጠቅሳሉ።
ከነዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው ‹‹ሪት ሲንድሮም›› በሴቶች ላይ ብቻ የሚታይ ሲሆን በጣም ታዋቂው ምልክት ከወሊድ በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ አምስት ወሮች ውስጥ መደበኛ እድገት በኋላ የሕፃኑ ጭንቅላት ከጊዜ ወደ ጊዜ ስፋቱ (ዲያሜትር) መቀነስ ነው።
ስለምልክቶቹም ሲሰተር ካሰች ሲያብራሩ እነዚህ ሕፃናት እጆቻቸውን ለተወሰነ ዓላማ መጠቀም ያቆማሉ። እንዲሁም የተለመደውን የእጅ እንቅስቃሴዎችን ይተዋሉ። የንግግርና በእግር መጓዝ ችግሮችም ይስተዋልባቸዋል።
በመሆኑም ሁሉም ዓይነት ችግር ያለባቸውን የኦቲዝም ተጠቂዎችን የማገዙ ተግባር የዘርፉ ሞያተኞች ተግባር ብቻ ሳይሆን የእያንዳንዱ ኅብረተሰብ ክፍል ኃላፊነትም ጭምር እንደሆነና ስለ ኦቲዝም ሁሌም መወራት እንዳለበትና ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበት ሲሰተር ካሰች ያሳስባሉ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 26/2015