
ብርቱ ናቸው። አካል ጉዳታቸው ቤት ያላስቀራቸው፣ በቤተሰብ ላይ ጥገኛ ያልሆኑ፣ ዘጠኝ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ደፋ ቀና የሚሉ ጠንካራ አባወራ። እግራቸው እንደ ልብ የመረጡትን ለመስራትና ሕይወታቸውን ለመለወጥ አያስችላቸውም። እሳቸው ግን ‹‹እችላለሁ›› ባሉት ሥራ ተሰማርተው ለቤተሰቡ የአባወራነት ሚናቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ያምናሉ። እንደማንኛውም ሙሉ አካል እንዳለው ሰው ተሸክመው፣ የቀን ስራዎችን አከናውነው የተሻለ ገቢ በማምጣት ቤተሰቡን ለማስተዳደር አይሆንላቸውምና ሌሎች ሊያሰሯቸው የሚችሉ ምርጫዎችን ማፈላለግ ጀመሩ።
ለእግር ጉዳታቸው የሚመጥን ሥራ ነው ያሉትን መርጠው በወር የተወሰነ ብር እያገኙ ከእጅ ወደአፍ የሆነ ኑሯቸውን መግፋት ያዙ። የመረጡት ሥራ አትክልተኝነት ነበር። ቦታው አዲስ አበባ ከተማ በመሆኑ በቀላሉ ብዙ ቦታ ለመስራት አያስችላቸውም። እንዲያም ሆኖ ዝም አላሉም። ‹‹ግለሰብም ቢሆን የቤተሰቤን ሕይወት ይታደግልን እንጂ ምን ገዶኝ›› ሲሉ በከተማ ግብርና ከተሰማራ አንድ ግለሰብ ዘንድ ተቀጠሩ።
አቶ ነስሩ አህመድ የተቀጠሩበት የወር ደምወዝ አይደለም ለዘጠኝ ቤተሰብ ባልና ሚስትን እንኳን ለማኖር በቂ አይደለም። እናም እዚያው እየሰሩ ወጪያቸውን የሚቀንሱበት መላ ዘየዱ። ሥራው የግብርና በመሆኑ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ወደ ቤታቸው የሚወስዱበትን ሁኔታ ከአሰሪዎቻቸው እንዲፈቀድ አደረጉ። ይህ ደግሞ ከቤት ኪራይ ቀጥሎ ያለውን ወጪያቸውን በእጅጉ ቀንሶላቸዋል። አትክልትና ፍራፍሬውን ወደቤታቸው ሲወስዱ ለራሳቸው ብቻ አልነበረም።
ለጎረቤት ጭምር በመሸጥ ዘይትና ስኳር የመሳሰሉ ወጪዎቻቸውን የሚሸፍኑበት ገንዘብ ያገኛሉ። በዚህም ቤተሰቡን አሳርፈው ለራሳቸውም ደስታን ፈጥረው እንዲኖሩ እድል ሰጥቷቸዋል። ይህንን ያደረጉላቸውን ሰዎች ደግሞ በእጅጉ ያመሰግኗቸዋል። በእርግጥ ከምስጋናው በተጨማሪ እርሳቸው ለቀጠሯቸው ሰዎች መልካም የሆነ አገልግሎቶችን ይሰጧቸው ነበር። አንዱ ለእርሳቸው የተሰጠው ተግባር መኮትኮትና እጽዋቱን መንከባከብ ብቻ ቢሆንም አዳደስ ችግኞች ሲመጡ እነርሱን የሚተክል ሌላ ሰው ሳያስፈልግ ራሳቸው ብቻ ይከውኗቸዋል። አልፎ ተርፎም የጥበቃውን ሥራ ይሰሩላቸዋል።
መቅጠፉ፣ ማጨዱና ከመሸከም ውጪ ያሉ ሌሎች ተግባራትንም ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ ያከናውናሉ። ይህ ግን እስመጨረሻው የዘለቀ አልነበረም። ድንገት ሥራው በመቆሙና መሬቱ ለሌላ ተግባር በመፈለጉ ቀጣሪዎቻቸውም ሆኑ እርሳቸው ሌሎች አማራጮችን እንዲፈልጉ ግድ ሆነባቸው ።
አቶ ነስሩ ይህንን ጊዜ ሲያስታውሱት ‹‹የጨለማ ወቅት ነበር›› ይሉታል። ምክንያቱም ጊዜው እንደልብ ተቀምጠው ሥራን የሚሰሩበትን አጋጣሚን ነጥቋቸዋልና። ለእርሳቸው አካል ጉዳታቸውን ያገናዘበ ሥራ ያገኙበትን እድልም አጨናግፎታል። ከሁሉም የሚብሰው ደግሞ ትናንት ላይ እንደ ልብ ተቀምጠው አትክልቶቹን የሚንከባከቡበት እግራቸው ተጨማሪ ችግር ያገኘው መሆኑ ነው። የእግር ጉዳታቸው መነሻ በመውደቃቸው የተፈጠረ አደጋ ነበር። አሁን ደግሞ ከሰዎች ጋር ተጣልተው ስለገፈተሯቸው ሕመማቸው የባሰ ሆኗል። በዚህ ሁኔታ ደግሞ በምንም መልኩ ቤተሰባቸውን ማገዝ አይቻላቸውም። እናም በባለቤታቸው ጫንቃ ላይ መውደቃቸው የግድ ሆኗል።
አቶ ነስሩ ስለ ባለቤታቸው ሲያነሱ እንባ ይቀድማቸዋል። እርሷ ባትኖር ሕይወት ኑሯቸው አደጋ ውስጥ እንደሚገባ ያምናሉ። ዛሬም ቢሆን ተስፋን ሰንቀው የሚኖሩት በእርሷ ድጋፍና እንክብካቤ ነው ። ሰባቱን ልጆቻቸው ትምህርታቸው እንዳቋረጥ በጥንካሬ እያስተማረች፣ የፈለጋቸውን እያደረገች፣ ቤቱን የምትደጉመው እርሷ መሆኗን ያስረዳሉ።
‹‹ እኔ አባወራነቴን መወጣት ሲሳነኝ እርሷ አባወራ ሆና ቤቱን ታስተዳድራለች። ማልዳ ወጥታም ምሽት በመግባት የቤቱን ጎደሎ ትሞላለች። በቀን ሥራዋ ልብስ ታጥባለች። አሻሮ ትቆላለች። የሰው ቤት እንጀራ ትጋግራለች። ያም ሳይበቃት ቤት ገብታ ለልጆቿና ለእኔ ምግብ ታበስላለች። አሁን በእርሷ ጥረት ነው እየኖርን ያለነው›› የሚሉት ባለታሪካችን፣ አሁን በትንሹም ቢሆን ሻል ስላለኝ እርሷን ማገዝ እፈልጋለሁ። ለዚህም ከሆነ እንደ ቀደመው ሥራዬ ቀጥሮ የሚያሰራኝ ሰው ባገኝ ደስ ይለኛል። ይህ ካልተሳካ ደግሞ ከሸክም ውጪ ለአካል ጉዳቴ የሚመጥን ሥራ ባገኝ እሻለሁ። ይህንን ሊያደርግልኝ የሚችል አካል ካለም መልዕክቴ ይድረስ›› ይላሉ።
ኑሯቸውን አዲስ አበባ ኮልፌ አካባቢ ያደረጉት አቶ ነስሩ አሁን ባሉበት የአኗኗር ሁኔታ እጅጉን ፈርተዋል። በተለይም የቤታቸው ጉዳይ አሳሳቢ ሆኖባቸዋል። መኖሪያ ቤታቸው ጣሪያው ያፈሳል። ግርግዳውም ቢሆን አብዝቶ ውሽንፍርና ንፋስ ያሳልፋል። በዚህም ገና ከአሁኑ የክረምቱ አገባብ ስጋት ውስጥ ጥሏቸዋል፤ ብርዱንም ቢሆን የሚችሉት አይመስልም ። በተለይ የሀምሌ ዝናብ ማየል በቀላሉ ግዜውን እንዳያልፉት አስግቷቸዋል ። እናም ይህ የበጎ ፈቃድ የሁለት ወር ጤና አገልግሎት ለጤናችን ብርቱ ድጋፍ እንዳደረገ ሁሉ ለቤታችንም የሚደርስበት ሁኔታ ካለ ቢነገርልን መልካም ነው ሲሉም ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
እርሳቸው ከአካል ጉዳታቸው ጋር ተያይዞ ወደ ልመና አልያም ወደ ጎዳና መውጣትን አይሹም። ሰርተው ቤታቸውን ሙሉ ባያደርጉም በአቅም ሰርተው የእለት ጉርሳቸውን መድፈን ብቻ ይፈልጋሉ። ለዚህም የመጀመሪያ ጥያቄያቸው ‹‹ሥራ ስጡኝ›› ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ‹‹ቤቴን ጠግኑልኝ›› ነው። እነዚህን ሁለት ነገሮች ካገኙ ራሳቸውን፣ ሀገራቸውንና እንደእርሳቸው በእንዲህ መሰሉ ችግር ውስጥ ያሉ አካልጉዳተኞችን እንደሚያግዙ ያነሳሉ።
አቶ ነስሩ ‹‹ድንጋይ አናቱን ሲመታ አንድም ለመረገጥ አንድም ለማይጠቅም ነገር መሙያነት ይሆናል። ደረቱ ላይ እየተመታ ሲስተካከል ግን በንግስና ለመቀመጥ የሚችልበትን እድል ያገኛል። ግልጋሎቱም ለቤት ግንባታ ጡብ ይሆናል። የሰው ልጅም ለችግር አናቱን ከሰጠ ውድቀቱን፣ አለያም ሞቱን ያፋጥናል። ደረቱን ከሰጠ ግን መሻሻሉን ያጎላል። የተሻለውን አግኝቶም ነገውን ያበራል። ስለዚህም ሰዎች ምንም አይነት አካል ጉዳት ቢገጥማቸው ሊቋቋሙበት የሚችሉትን ደረታቸውን እንጂ አናታቸውን መስጠት የለባቸውም›› ይላሉ አባወራው በመልዕክታቸው።
በጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም