ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ከፍተኛ እድገት ካስመዘገቡ አገራት መካከል ተጠቃሽ ሆና ቆይታለች። በአገሪቱ ሰፍኖ የቆየው ሰላምና መረጋጋት፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ መፋጠን፣ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች፣ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት እና ሰፊ የገበያ እድል አገሪቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በአፍሪካ ደረጃ ቀዳሚ ከሚባሉ አገራት መካከል አንዷ እንድትሆን አስችለዋታል። ይህም ለኢንቨስትመንት ዘርፍ ማደግ ዓይነተኛ ሚና የተጫወተ ሲሆን፣ ለአገሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገትም ትልቅ ድርሻ አበርክቷል።
ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩት የፀጥታ ችግሮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተፈጠረው የኮቪድ ወረርሽኝ፣ የምጣኔ ሀብት ቀውስና ጦርነቶች ጋር ተዳምረው በአገሪቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድረዋል።
ከጦርነት በኋላ በሚኖር የኢንቨስትመንት አስተዳደርና አመራር ብቻም ሳይሆን በሰላም ጊዜም ቢሆን የኢንቨስትመንት አቅሞችንና አማራጮችን በማስተዋወቅ ባለሀብቶችን መሳብና ዘርፉን ማሳደግ ይገባል። ይህን ጥረት እውን ለማድረግ ደግሞ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ባለድርሻ አካላትን የሚያገናኙ፣ የኢንቨስትመንት አቅሞችንና አማራጮችን የሚያስተዋውቁ መድረኮች ከፍተኛ ሚና አላቸው። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አቅም ለባለሀብቶች ማስተዋወቅን ዓላማ ያደረጉ ልዩ ልዩ መድረኮች መካሄዳቸው ይታወሳል። እነዚህ መድረኮችም ቀላል የማይባሉ ውጤቶችን አስገኝተዋል።
የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ በሕግ ስልጣን የተሰጠው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከሌሎች አጋር የመንግሥት አካላት ጋር፣ በተለይም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በውጭ ከሚገኙ የዲፕሎማቲክ ሚሽኖች ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ‹‹ኢንቨስት ኢትዮጵያ›› (Invest Ethiopia 2023) የተሰኘው የኢንቨስትመንት ፎረም ባለፈው ሳምንት፣ /ከሚያዝያ 18 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2015 ዓ.ም/ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። ፎረሙ የአገሪቱን የኢንቨስትመንት አቅሞችና በዘርፉ ያሉ መልካም እድሎችን ለማስተዋወቅ አልሞ የተካሄደ ሲሆን ባለሀብቶች፣ የመንግሥትና የተቋማት የሥራ ኃላፊዎች፣ የፖሊሲ ባለሙያዎችና ሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተከናወኑ የአሰራር ማሻሻያዎች በኮቪድ ወረርሽኝ እና በግጭቶች ምክንያት በስፋት ሳይተዋወቁ ቆይተዋል። ከአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችና መወዳደሪያ ነጥቦች አሉ። ባለፉት ዓመታት ከ80 በላይ ለቢዝነስና ኢንቨስትመንት ስራ ማነቆ የነበሩ ህግጋት ተሻሽለዋል። ከእነዚህም መካከል ወደ ስራ የገቡት አዳዲሶቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲና የኢንቨስትመንት አዋጅ (1180/2012) ተጠቃሽ ናቸው።
አዳዲሶቹ ህግጋት ለኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢ የሚፈጥሩ ቢሆኑም ለግል ባለሀብቶች በሚፈለገው ልክ ማስተዋወቅ ሳይቻል ቆይቷል። ፎረሙ እነዚህን ማሻሻያዎች ለማስተዋወቅም እድል ፈጥሯል። በአጠቃላይ ፎረሙ በኢኮኖሚ ማሻሻያው ይፋ የተደረጉ ለውጦችን እንዲሁም ባለፉት ዓመታት የተተገበሩት የኢንቨስትመንት ከባቢ ማስተካከያ ስራዎች ያመጧቸው መሰረታዊ የህግና የአሰራር ለውጦች የተዋወቁበት መድረክ ሆኗል።
ፎረሙ ቀደም ሲል በኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተው የቆዩ ባለሀብቶች ስራቸውን በማስፋት አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮችን እንዲመለከቱ የሚያስችል ከመሆኑም ባሻገር ባለሀብቶቹ ከፖሊሲ አውጪዎችና ውሳኔ ሰጪ የመንግሥት አካላት ጋር በነበሯቸው ግንኙነቶች ስለሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች በቅርበት ለመወያየትም እድል ፈጥሯል።
በፎረሙ ሚኒስትሮችና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት የተካሄዱ ከፍተኛ የፓናል ውይይቶችን (High Level Panel Discussions) ጨምሮ፣ የቢዝነስ ተቋማት እርስ በእርሳቸውና ከመንግሥት አካላት ጋር የተገናኙባቸው የኢንቨስትመንት አማራጭ ማስተዋወቂያ እና የልምድ ልውውጥ መድረኮች፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጉብኝቶች፣ ኤግዚቢሽኖችና ተዛማጅ መርሃ ግብሮች ተካሂደዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመጥር የሆኑ የቢዝነስ ተቋማት ስራ አስፈፃሚዎችም ልምዳቸውን አካፍለዋል።
ከወሳኝ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ከዚህ ቀደም ከኮሚሽኑ ጋር ግንኙነት ከነበራቸው አካላት ጋር የመግባቢያ ስምምነቶችና የኢንቨስትመንት ውሎች ተፈርመዋል። ለአብነትም ኮሚሽኑ ከአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ስምምነት ከአምስት ኩባንያዎች ጋር ተፈራርሟል። የ‹‹ቱሉ ካፒ›› የወርቅ ልማት ፕሮጀክትን የሚያከናውነው ‹‹ከፊ ሚኒራልስ›› (KEFI Gold and Copper) ኩባንያ ‹‹ፒ ደብሊው ማይኒንግ›› (PW Mining) ከተባለው ድርጅት ጋር በጋራ ለመስራት የተፈራረመው ስምምነትም የዚሁ ማሳያ ነው።
የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ፎረሙ አገራዊ ምጣኔ ሀብቱ ካጋጠሙት ውጫዊና ውስጣዊ ተግዳሮቶች እየወጣ ባለበት ወቅት መዘጋጀቱ ፋይዳውን የጎላ እንደሚያደርገው ተናግረዋል። እርሳቸው እንዳሉት፣ ባለፉት አራት ዓመታት መንግሥት ዘርፈ ብዙ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ አድርጓል። ከእነዚህ መርሃ ግብሮች መካከል አንዱ አምራች የሆነውን የሠው ኃይል የሚሸከም የሥራ እድል እና የተረጋጋ የማክሮ-ኢኮኖሚ ከባቢ በመፍጠር እንዲሁም የግል ዘርፍ መር (Private Sector-Led) የሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በመገንባት ዘላቂና ፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገት ማስመዝገብን ዓላማው ያደረገው አገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብር (Homegrown Economic Reform Program) ነው።
ከዚህ በተጨማሪም የኢንቨስትመንት አዋጅና የንግድ ሕግ ማሻሻያዎች፣ ብሔራዊ የንግድና ቢዝነስ ስራ አመቺነት ማሻሻያ መርሃ ግብር (National Ease of Doing Business Initiative) እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የግብይት ስርዓት ጋር ዘመናዊ ትስስር ለመፍጠር የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆን የተላለፈውን ውሳኔ ለመተግበር እየተደረጉ ያሉ ዝግጅቶች የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ መርሃ ግብሩ አካል ናቸው።
‹‹ኢትዮጵያ ፈጣን እድገት እያስመዘገበች ነው። በአፍሪካ ለኢንቨስትመንት ምቹ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ ሆናለች። በአገሪቱ በርካታ የኢንቨስትመንት እድሎች አሉ። የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቿ አሳታፊና አካታች እንዲሆኑ መንግሥት ጠንካራ ሥራ እየሠራ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደረጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ጨምሯል። ኢትዮጵያ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ማለት በአፍሪካ ኢንቨስት ማድረግ ነው›› ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ለግሉ ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት በአግባቡ በመጠቀም ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በስፋት በኢንቨስት ስራዎች ላይ ቢሰማሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑና መንግሥትም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ሌሊሴ ነሜ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለችው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት መንግሥት ለኢንቨስትመንት ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ውጤት መሆኑን ገልፀዋል። ኮሚሽነሯ እንደተናገሩት፣ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማሳደግ መንግሥት በርካታ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን አድርጓል፤ ዘርፉ በአገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ ቀዳሚ ትኩረት የተሰጣቸውን ዘርፎች ለይቷል። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በመንግሥት የተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለኢንቨስተሮች የተሟሉ መሰረተ ልማቶችንና ማበረታቻዎችን በማቅረብ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከቱ ይገኛሉ። የምርቶችን የእሴት ሰንሰለት በማጠንከር የምርት መጠንን ለማሳደግና በወሳኝ የምጣኔ ሀብት ዘርፎች ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት ፓርኮቹን የማስፋፋትና የማዘመን ተግባራት ይከናወናል።
አገሪቱ በታዳሽ የኃይል ምንጭ ዘርፍ ልማት እያከናወነች ያለችው ተግባር ለኢንቨስትመንት ተግባራት አስተማማኝ የኃይል ምንጭ ለማቅረብ የሚያሥችል ነው። በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተደረጉ የሕግ ማሻሻያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ባለሀብቶች ቁጥር እንዲጨምር ያስችላሉ። የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ ከተከናወኑ የሕግና መዋቅራዊ ማሻሻያዎች በተጨማሪ ኮሚሽኑ አሰራሩን ማዘመኑንም ወይዘሮ ሌሊሴ ገልፀዋል።
በፎረሙ ላይ ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የየአካባቢዎቻቸውን የኢንቨስትመንት አቅሞችና እድሎች አስተዋውቀዋል። ለወቅቱ የሚመጥን ዘመናዊ የኢንቨስትመንት አመራርና አስተዳደር በማስፈን የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ፈጣንና ቀልጣፋ ለማድረግ እያከናወኗቸው ስለሚገኙ ተግባራትም ገለፃ አድርገዋል።
በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የኢንቨስትመንት ፈቃድ፣ ፕሮሞሽን፣ መረጃና ዳያስፖራ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ዘለቀ ፎረሙ የክልሉን የኢንቨስትመንት አቅም ለባለሀብቶች ለማስተዋወቅ እድል የፈጠረ እንደነበር ሲናገሩ፤ ‹‹የክልሉን የኢንቨስትመንት እድሎች ለባለሀብቶች አስተዋውቀናል። ክልሉ ለግብርና፣ ለማምረቻና ለአገልግሎት ዘርፎች ምቹ እንደሆነ ገለፃ አድርገናል። ከግብርናና ማምረቻ ዘርፎች በተጨማሪ ክልሉ አስደናቂ የሆኑ የተፈጥሮ ሀብቶችና የብዝኃነት ባለቤት በመሆኑ ለቱሪዝም ኢንቨስትመንት የተመቸ እንደሆነ ማብራሪያ ሰጥተናል ሲሉ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት ወደ ክልሉ ሲመጡ ማሟላት የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶችና ግብዓቶች ምን እንደሆኑ እንዲሁም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ይዘው እንዲመጡ ነግረናቸዋል›› ብለዋል። ‹‹ያለግል ባለሀብቶች ተሳትፎ ዘላቂ ልማትን ማሳካት አይቻልም›› የሚሉት አቶ ፀጋዬ፣ ኢንቨስትመንት የብዙ ተቋማትን ትብብርና ቅንጅት የሚጠይቅ በመሆኑ የክልሉ የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ እያንዳንዱ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመተባበር ለባለሀብቶች ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመሬትና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አመንቴ ገሺ ፎረሙ የኢንቨስትመንት ባለድርሻ አካላትን ያገናኘ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኢንቨስትመንት አቅሞችን ለማስተዋወቅ እድል የሚፈጥር ከመሆኑም በተጨማሪ የዘርፉን ችግሮች በትብብር ለመፍታት የሚያግዝ እንደሆነም ገልፀዋል።
እርሳቸው እንዳሉት፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እምቅ ሀብትና ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያሉት በመሆኑ ፎረሙ የክልሉን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማሳደግ አወንታዊ ሚና ይኖረዋል። ክልሉ በግብርና፣ በማምረቻ፣ በማዕድናት (የድንጋይ ከሰል፣ ወርቅ፣ እምነበረድ፣ ግራናይት) እና በሆቴልና ቱሪዝም መስኮች በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች አሉት።
አቶ አመንቱ በክልሉ ለኢንቨስትመንት ሊተላለፍ የሚችል ከ69ሺ ሄክታር በላይ ለም መሬት እንዳለ ጠቅሰው፣ የዓባይ ግድብ ለክልሉ ተጨማሪ የኢንቨስትመንት እድሎችን እንደሚያመጣ ይጠበቃል ሲሉም ገልጸዋል። ‹‹የክልሉ መንግሥት በሀብት አጠቃቀም ላይ ጠንካራ የሪፎርም ስራዎችን ሰርቷል። መሬት ወስደው ወደ ስራ ካልገቡ ባለሀብቶች መሬቱ ተወስዶ ማልማት ለሚችሉ ባለሀብቶች ተሰጥቷል። ቢሮክራሲው በሚፈለገው ልክ አጥጋቢና የተሳለጠ ነው ባይባልም ብዙ መሻሻሎች አሉ›› በማለት ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪም ‹‹የፀጥታ ችግር ተቀርፏል። በአሁኑ ወቅት የፀጥታ ጉዳይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ችግር አይደለም›› በማለት በክልሉ ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስ ተወግዶ መረጋጋት መስፈኑንም አቶ አመንቴ ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል መኮንን በበኩላቸው ፎረሙ በሰሜኑ ጦርነት የተጎዳውን የትግራይ ክልል የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማነቃቃት አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል። እርሳቸው እንዳሉት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት የክልሉን ኢንቨስትመንት ስለጎዳው ዘርፉን ማነቃቃትና መልሶ መገንባት ይገባል። የወደመውን ሀብት መልሶ ለመገንባት ባለሀብቱ ትልቅ ሚና አለው። ኮሚሽነሩ፣ ‹‹ኢንቨስትመንት ሰላም፣ መሰረተ ልማት፣ ፋይናንስና የገበያ ትስስር ይፈልጋል። ትግራይ ክልል በበርካታ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ከፍተኛ አቅም ያለው ክልል ነው። መሰል ፎረሞችን በክልሉ በማዘጋጀት የተጎዳውን ኢንቨስትመንት ማነቃቃት ይገባል ብለዋል።
ለወቅታዊው ሁኔታ የሚመጥን የኢንቨስትመንት አስተዳደር እውን ለማድረግ የሕግ ማሻሻያ ስራዎችን እየሰራን እንገኛለን ሲሉም ጠቅሰው፣ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማነቃቃት ለሰራተኞቻችን ስልጠናዎችን እየሰጠን ነው›› ይላሉ።
አቶ ዳንኤል ከጦርነቱ በፊት በክልሉ ከ13ሺ በላይ ፈቃድ የወሰዱና የተመዘገቡ ኢንቨስተሮች እንደነበሩ አስታውሰው፣ እነዚህ ባለሀብቶች ከሰላም ስምምነቱ ወዲህ ተመልሰው ለመምጣት ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፤ ሌሎች ባለሀብቶችም ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ልዩ እገዛ ሊደረግላቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 26/2015