በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው ጦርነት በርካታ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችን አስከትሎ አልፏል። የኢትዮጵያ መንግሥት ፊቱንም ቢሆን ለሰላም ካለው ጽኑ አቋም በመነጨ ጦርነቱ የበለጠ ቀውስ ሳያስከትል ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲቋጭ በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል።
ጦርነቱ እንዲቆም አንዳንድ ምዕራባውያን አገሮች ሞካክረው ነበር፤ ይሁንና መንግስት ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚል ጽኑ አቋም በመያዝ በአፍሪካውያን አወያይነት መንግስትና ሕወሓት ከሰላም ስምምነት ደርሰዋል።
በስምምነቱ መሰረትም በርካታ ተግባሮች ተከናውነዋል። በክልሉም ሆነ ክልሉ ከፌዴራል መንግስቱ ጋር የሚያደርጋቸው አገልግሎቶች በስፋት ተጀምረዋል። የአየር ትራንስፖርት፣ የቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ፣ የባንክ አገልግሎቶች በፍጥነት የተጀመሩ ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ የየብስ የትራንስፖርት አገልግሎትና ሌሎችም አገልግሎቶች ተጀምረዋል፤ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።
ቀደም ሲል የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች በትግራይ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ በቅርቡም የክልል መስተዳድሮች በትግራይ ጉብኝት አርገዋል። መንግሥት በሰላም ስምምነቱ ማግስት በጦርነቱ የተጎዳውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማከም የሚያደርገውን ርብርብ ተያይዞታል።
ከእነዚህ ጥረቶች መካከል በጦርነቱ ምክንያት እጅግ የተጎዳው የትግራይ ክልል የንግድ እንቅስቃሴ አንዲያንሰራራ ማድረግ አንዱ ነው። ለዚህም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ወደ ክልሉ ተጉዞ በንግዱ ዘርፍ ከተሰማሩ የተለያዩ አካላት ጋር ውይይቶችን በማድረግ የንግድ እንቅስቃሴው ወደ ቀድሞው የተነቃቃ እንቅስቃሴው እንዲመለስና ህብረተሰቡ ከንግድ ዘርፉ ማግኘት የሚገባውን አገልግሎት ማግኘት እንዲችል አስቻይ ሁኔታዎችን የመፍጠር እንቅስቃሴውን በይፋ ጀምሯል።
ሚኒስቴሩ ደጋፊና ዋነኛ አስተባባሪ በመሆን ከትግራይ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር ‹‹የትግራይ የንግድ እንቅስቃሴ ለቀጠናዊ ሰላም›› በሚል የትግራይ ተጓዥ ባዛር ከሚያዝያ 21 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚካሄድ ሰሞኑን የትግራይ ክልል ንግድ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አታኽልቲ ስዩም አስታውቀዋል።
አቶ አታኽልቲ እንዳሉት፤ የንግድ ባዛሩ በክልሉ የንግድ እንቅሰቃሴና አጠቃላይ ቀጠናዊ ትስስርን ለማጠናከር ዓላማ አድርጎ የተዘጋጀና በሁለት ዙር የሚካሄድ ይሆናል፤ የመጀመሪያው ዙር በመቀሌ፣ ውቅሮ አዲግራትና ማይጨው የሚደረግ ሲሆን፣ ለአንድ ወር የሚቆይ ነው። ሁለተኛው ዙር ደግሞ በዓብይ ዓዲ፣ ዓድዋ፣ አክሱምና ሽረ ይቀጥላል።
ባዛሩ ከመከፈቱ አስቀድሞ ሚያዝያ 21 ቀን 2015 ዓ.ም ባለድርሻ አካላት በዋናነት ከፌዴራል የንግድና ፋይናንስ ተቋማት ጋር ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ የፓናል ውይይት ተደርጓል። ጥናታዊ ጽሑፉም የትግራይ የፋይናንስ ተቋማት ከየት እንደተነሱና አሁን ያሉበት ሁኔታ ተዳሷል። የትግራይ ክልል ቀጠናዊ የንግድ ትስስር አቅጣጫም ለውይይት ይቀርባል ነው ያሉት።
ባዛሩ በጦርነት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ክልሉ ከክልሎችና ማእከል ጋር የሚያደርገው የንግድ ትስስር በጥሩ ሁኔታ መልሶ እንዲቀጥል ለማድረግና የኮንትሮባንድ ንግድን ለማስቆም እንዲሁም ነጋዴዎች ከአጋር ድርጅቶች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፣ በክልሉ ያጋጠመውን የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ለመፍታት ከባንኮች ጋር ለመስራት የሚያስችል ሁኔታ የሚፈጠርበት እንደሆነም ጠቁመዋል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ስርዓትና ፈቃድ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ተሻለ በልሁ እንዳሉት፤ ‹‹የትግራይ የንግድ እንቅስቃሴ ለቀጠናዊ ሰላም›› በሚል መሪ ሃሳብ መካሄድ የጀመረው የትግራይ ተጓዥ ባዛር እስከ ግንቦት 26 ቀን 2015 ዓ.ም ለአንድ ወር ይካሄዳል። ባዛሩ በመንግስትና በሕወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የመጣውን ሰላም ይበልጥ ለማጽናት ያስችላል። በክልሉ ተፋዞ የቆየውን የንግድ እንቅስቃሴ ያነቃቃል።
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ የትግራይ ተጓዥ ባዛር ዋነኛ ዓላማ በእነዚህ አካባቢዎች መሰረታዊ የሆኑ የምግብ ሸቀጦችና ሌሎች ምርቶች እንደ ልብ ለማህበረሰቡ መድረስ እንዲችሉና ህዝቡ አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል ነው። በዚህም የተለያዩ የመንግሥት አካላትና የግሉ ባለሃብቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ወገን ለወገን በሚል መድረስ የሚችሉ ማንኛውንም ምርቶችንና ሸቀጣ ሸቀጦችን በትግራይ ክልል ተደራሽ ለማድረግ በተለይም አምራቾች ጉልህ ሚና አላቸው።
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተካሄደው ጦርነት በሰላም ስምምነት መቋጨቱን ያስታወሱት አቶ ተሻለ፤ ሰላሙ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና የንግድ ሂደትን በአግባቡ መምራት መቻል የግድ እንደሆነም አመልክተዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የትግራይ ክልል በአሁኑ ወቅት ጊዜያዊ አስተዳዳር አቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል። ይህን ተከትሎም ቢሮዎች ተቋቁመዋል። ከተቋቋሙ ቢሮዎች መካከል አንዱ የንግዱን ዘርፍ የሚመራው ኤጀንሲ ሲሆን፤ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከዚህ ኤጀንሲ ጋር በመቀሌ ተገኝቶ ውይይት አድርጓል። ባዛሩ የመጣው ሰላም ዘላቂነት እንዲኖረው የማድረግ እንዲሁም ተፋዞና ተቀዛቅዞ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ ማስቀጠል የሚያስችል ትልቅ አቅም ይኖረዋል።
በተለይም የተቀዛቀዘውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ከመሀል አገር ወይም ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መሰረታዊ ሸቀጦች ወደ ትግራይ ክልል መዘዋወር እንደሚኖርባቸውም አስታውቀዋል። በተመሳሳይ ከትግራይ ክልል ወደ ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች መሰረታዊ የሆኑ ሸቀጦችን ማንቀሳቀስም ይጠበቃል ሲሉ አቶ ተሻለ አስገንዝበዋል። በተለይ ንግድ በባህሪው ነጻ የሸቀጦች ዝውውርን እንደሚፈልግ ጠቅሰው፣ ለተግባራዊነቱም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል።
የክልሉን የንግድ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ወደ ትግራይ የሚደረገው ጉዞ በአማራ ክልል እና በአፋር በኩል እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ተሻለ፤ እነዚህን ሁለት አማራጭ መንገዶች በመጠቀም ከመሀል አገር ወደ ትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሚደረግ እንቅስቃሴ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተገቢውን ማስረጃ ለመስጠት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ያም ሆኖ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ምርቶች ካልሆኑ በስተቀር ማንኛውም ሸቀጥ በአገር ውስጥ በነጻነት ይንቀሳቀሳል ሲሉ አቶ ተሻለ ገልጸዋል። ኤክስፖርት የሚደረጉ ምርቶች ከሆኑ ለኤክስፖርት ንግድ የተዘጋጀ የአሰራር ስርዓት እንዳለም አስታውቀዋል፤ ይህም ስርዓቱን ተከትሎ እንደሚፈጸም ተናግረዋል። ከዚህ ውጭ የሆኑ ለአብነትም የምግብ ዘይት፣ ስኳርና ሌሎች መሰረታዊ ሸቀጦችን በየትኛውም የአገሪቱ ጫፍ በነጻነት ማንቀሳቀስ እንደሚቻል አስረድተዋል።
ምርቶቹ በአካባቢው ተደራሽ ሆነው ማህበረሰቡ የሚፈልጋቸውን የምግብ ሸቀጦችና ሌሎችንም አገልግሎቶች ማግኘት እንዲችል ብዙ ሥራ ይጠበቃል ሲሉም አመልክተው፣ ይህም የተነቃቃ ንግድ ለማምጣት እንደሚያስችል ነው ያስታወቁት። ንግዱ ሲነቃቃ ሰላሙን በበለጠ መንገድ ማጠናከር እንደሚችልም ጠቅሰው፣ የተጠናከረ ሰላም ደግሞ ትግራይን ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት እንደሚያስችል ተናግረዋል። ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን በማጠናከር ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ነው አቶ ተሻለ ያብራሩት።
የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ተወካይ አቶ ካህሳይ ላዕከ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የትግራይ ተጓዥ ባዛር ክልሉ ያጋጠመውን የንግድ እንቅስቃሴ ችግር በጊዚያዊነትና በቋሚነት መፍታት ያስችላል።
የክልሉ የንግድ እንቅስቃሴ ውስብስብና ከፍተኛ ችግር የገጠመው መሆኑን አቶ ካህሳይ ጠቅሰው፣ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት እንዲቻል የባዘር ዝግጅቱ አስፈላጊና ወሳኝ ነው ይላሉ። ከዝግጅቱ አንዱ በሆነው በፓናል ውይይት የቢዝነስና የፋይንንስ ተቋማት እንደሚሳተፉ አስታውቀው፣ በውይይቱም ክልሉ ከገጠመው ችግር ተላቆ ወደ ቀድሞ ሰላማዊ የንግድ እንቅስቃሴው መመለስ የሚችልበትን መንገድ ለማምጣት እንደሚጠቅም አስረድተዋል።
እንደ አቶ ካህሳይ ገለጻ፤ በክልሉ ከፍተኛ የሸቀጦች እጥረት ይታያል። ችግሩን በጊዚያዊነት ለመፍታት አምራቾች፣ አስመጪዎችና አከፋፋዮች ከፍተኛ ሚና አላቸው። አምራቾች፣ አስመጪዎችና አከፋፋዮች በባዛር መልክ ወደ ክልሉ ተጉዘው የህብረተሰቡን ችግር በአቅርቦት፣ በጥራትና በዋጋም ጭምር በመፍታት ማህበረሰቡን ማገዝና መደገፍ ይችላሉ። በተመሳሳይ ራሳቸውም ሸቀጦችንና አገልግሎታቸውን በመሸጥ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ። በመሆኑም ሁሉም አምራቾች፣ አስመጪዎችና ገበያ የሚፈልጉ በሙሉ በባዛሩ መሳተፍ ይችላሉ፤ ለዚህም እንደ ክልል ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጓል።
የትግራይ ተጓዥ ባዛር ባለፉት ሶስት ዓመታት ተዳክሞ የቆየውን የትግራይ ክልል የንግድ እንቅስቃሴ ማነቃቃት እንደሚያስችልና የንግድ እንቅስቃሴውን ወደ ቦታው የመመለስ አቅም እንዳለው አቶ ካህሳይ አስታውቀዋል። ለዚህም ሰላም መምጣቱ ዋናው ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ነው ያስታወቁት። ለተግባራዊነቱም የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የክልሉ የንግድና የቢዝነስ እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ጠቅሰው፣ ለዚህም ድጋፍ እንደሚያደርግ እምነቱ እንዳላቸው ገልጸዋል።
አቶ ካህሳይ የንግዱ ዘርፍ በፓናል ውይይትና በባዛር መልክ የሚያደርገው የንግድ እንቅስቃሴ ሁለት ተልዕኮ እንዳለው አስታውቀዋል፤ አንደኛው በክልሉ ሰላማዊ የንግድ እንቅስቃሴ መካሄድ መጀመሩን ለማሳየት፣ ሁለተኛው ደግሞ የክልሉ ህዝብ የገጠመውን የሸቀጦችና የመሳሰሉት አቅርቦቶች ጉድለት ቀረብ ብሎ በመረዳት ክፍተቱን መሙላት መሆኑን አመልክተዋል። በክልሉ ከተሞች የተፈጠረውን ጉድለት ለመሙላትና የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ጥረት እንደሚደረግም አስረድተዋል።
የትግራይ ተጓዥ ባዛር፤ በዋናነት የትርፋማነት አጀንዳ ሳይሆን ለማህበረሰቡ አግልግሎት መስጠትና እሴት መጨመር እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ካህሳይ፤ የንግድ ባዛሩ በተለይም ሰላምን የማጽናትና የእርስ በእርስ ግንኙነትን ማጠናከር አንዱና ዋነኛው ተልዕኮው እንደሆነ ነው የተናገሩት።
ሌላው በአካባቢው የተፈጠረውን የአቅርቦት ክፍተት የመሸፈን እንዲሁም አገልግሎት መስጠትን ዋና ዓላማው አድርጎ በሚካሄደው የትግራይ ተጓዥ ባዛር ላይ የሸቀጣ ሸቀጦች ዝውውር ባልተገደበ ሁኔታ እንዲፈጸም ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግም እሳቸውም አመላክተዋል።
በጦርነቱ ክፉኛ የተጎዳውን የንግድ እንቅስቃሴ ለማነቃቀት አሁን የተፈጠረው ሰላም እጅግ ወሳኝና ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ይታመናል። በመሆኑም ለአንድ ወር የሚካሄደው የትግራይ ተጓዥ ባዛር የመጣውን ሰላም ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ እንዲሁም የህዝቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነት በማጠናከር ጤናማ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲፈጠር እንደሚያስችል ታምኖበታል።
በባዛሩ በተለይም የንግዱ ዘርፍ በሁሉም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ በክልሉ የተፈጠረውን የአቅርቦት እጥረት በዋጋና በጥራት በመሙላት የክልሉን የንግድ እንቅስቃሴ ወደ ቀድሞ ቦታው ለመመለስ የሚጠበቅበትን ጥረት ማድረግ ይኖርበታል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25/2015