አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ከውጭ አገራት ጋር ያላትን የንግድ ትስስር ለማጎልበት እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ውቤ መንግሥቱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የውጭ የንግድ ትስስሯን ለማጎልበት ከ52 አገራት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርማ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ከእነዚህ አገራት ጋር የዋጋ መረጃ በመለዋወጥ፣ የንግድ ትርኢቶች ላይ በመገኘትና በመጋበዝ፣ ችግሮችን በጋራ በመፍታትና የልምድ ልውውጦችን በማድረግ የአገሪቱን የውጭ ንግድ ለማሳደግ እየተሠራ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ከውጭ አገራት ጋር ያላትን የንግድ ትስስር ለማጠናከርና ለማስፋት እየሠራች ትገኛለች ያሉት አቶ ውቤ፤ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በየዓመቱ በአሜሪካ የንግድ አውደ ርዕይ የሚያዘጋጅ ሲሆን ይህም አሜሪካ ላሉ ኢትዮጵያውያን ምርት ለሚያቀርቡ ኩባንያዎች የንግድ ትስስር እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ውቤ ገለጻ፤ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ስምምነት ከፈረመችባቸው ከግማሽ በላይ ከሚሆኑት አገራት ጋር የተሻለና ውጤታማ የንግድ ትስስርን ፈጥራለች፡፡
የውጭ ገበያ ለማግኘት ብዙ ሙከራዎች ተደርገው የሚሳኩ ቢሆንም ትልቁ ችግር ግን በሚፈለገው ልክ ቋሚ ሆኖ ምርት ማቅረብ አለመቻሉ ትስስሩን የሚያላላ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ለዚህም የአቅርቦቱን ችግር ለመፍታት የግል ዘርፉን ማበረታታትና ወደ ሥራ ማስገባት አስፈላጊ ነው ያሉት አቶ ውቤ በአሁኑ ጊዜ ያለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና ንግድ ለመጀመር የሚኖረው የመሬት አቅርቦት ችግር ጀማሪ ኩባንያዎችን የማያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው ምርቶች አብዛኛዎቹ ከግብርናው ዘርፍ የሚገኙ ቢሆንም የግሉ ዘርፍ ሰፋፊ እርሻ ወይም ሰፋፊ የእንስሳት ልማት በማካሄድ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያበረታታ የአሠራር ሥርዓት አለመዘረጋቱን ነው የተናገሩት፡፡
የአቅርቦት እጥረት ባለባቸው ምርቶች ላይ የግሉ ዘርፍ ትኩረት እንዲሰጥ መንግሥት እያበረታታ መሆኑ የሚያስመሰግነው ቢሆንም አሁን በስፋት ትኩረት ከተሰጠው ከስንዴ ምርት በተጨማሪ ሌሎች ምርቶች ተጠንተው ትኩረት ሊያገኙ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ከውጭ አገራት በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን ምርት መግዛት በመለማመድ ሁሉም የራሱን ኃላፊነት እየተወጣ ለትውልድ የሚተላለፍ ነገር መሥራት እንደሚገባ አቶ ውቤ አሳስበዋል፡፡
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 24/2015