ዘመን፡- ከአሀዳዊና ፌደራላዊ አወቃቀር ለሀገራችን የትኛው ይበጃል ይላሉ?
ዶክተር ብርሀኑ፡- ይህ ጥያቄ በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ በተደጋጋሚ ከሚነሡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በትክክል ጽንሰ ሐሳቦቹን በመረዳት ተነሥቶ ከመነጋገር ይልቅም በሚፈልጉት መንገድ በመሔድ ወደ አላስፈላጊ መናቆር እየከተተ ያለ ጥያቄም ነው፡፡ ጥያቄው በተወሰነ ደረጃ የዲሴንትራላይዜሽን ጥያቄ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላለ ትልቅና ሰፊ የቆዳ ስፋት ያለው አገር ለማስተዳደር የሚሻሉትን አማራጮች በትክክል መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ በአንድ በኩል ሁሉም ነገር ከአንድ ማዕከል የሚሔድበትን መንገድ መከተል አስተዳደር የቀለጠፈ እንዲሆን ይረዳል፡፡ በየአካባቢው ያሉ ሰዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ቶሎ መልስ ለመስጠት ያስችላል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን የአስተዳደር ሥርዓት በየአካባቢው እንዲበተን በማድረግ ‹የሕብረተሰቡን ፍላጎት እያደመጠ እዚያው የሚመልስ ያልተማከለ አስተዳደር ይሻል ይሆን?› የሚል ጥያቄም ሊነሣ ይችላል፡፡ በተለይ ይህኛው ጥያቄ የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ፍላጎት መመለስን መሠረት አድርጎ የሚቀርብ ነው፡፡
እስካሁን ሁሉ ነገር ከማዕከል ብቻ ሆኖ፣ ትእዛዝ ከማዕከል እየወረደ አስተዳደር የሚፈጸምበት ሁኔታ ይኑር የሚል አመለካከት አልሰማሁም፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን የአስተዳደር እርከኖች ወደ ታች ወርደው፣ ሕዝቡን ሊሰሙ የሚችሉ፣ ሕዝቡ በቅርበት የሚያገኛቸው፣ እዚያው አጠገቡ ሆነው የሕዝቡን የልብ ትርታ እያዳመጡ ለመመልስ የሚሞክሩ አስተዳዳሪዎች ያሉበት፣ ያልተማከለ መሆን አለበት፡፡ በእርግጥ ከማዕከል ሊወሰዱ የሚገባቸው አንዳንድ ጉዳዮች አሉ፤ ከነዚያ በቀር ሌላውን ያልተማከለ ማድረግ ይበጃል በሚለው ላይ በእኔ ግምት ሰፊ ስምምነት ያለ ይመስለኛል፡፡
ዘመን፡- ፌደራላዊ ማለትዎ ነው ወይስ ..?
ዶክተር ብርሀኑ፡- የግድ ፌደራላዊ መሆን የለበትም፡፡ የየአካባቢው አስተዳደር ያልተማከለ ሊሆን ይችላል፤ ፌደራላዊ ላይሆን ግን ይችላል፡፡ ፌደራሊዝም አንድ ያልተማከለ ሥርዓት መገለጫ ነው፡፡ ፌደራሊዝም ያልተማከለ ሥርዓት የሚሆነው ለአካባቢያዊ አስተዳደሮች የሚሰጠው መብትና ሥልጣን ሰፋ ስለሚል ነው፡፡ ከሞላ ጎደል በጋራ ስምምነት ከሚወሰድባቸው ነገሮች በቀር ለምሳሌ መከላከያ፣ ውጭ ጉዳይ፣ ከክልል ክልል የሚደረጉ ንግዶች፣ አገራዊ በሚባሉ ሀብቶች ባጠቃላይ የጋራ በሆኑ ወይም ምን እንደሆኑ አስቀድመው በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ካልሆነ በቀር ለሌሎቹ ያልተማከለ የአስተዳደር ሥርዓት ልታመጣ ትችላለህ፡፡
ስለዚህ በመጀመሪያ ደረጃ ያልተማከለ የአስተዳደር ሥርዓት በሚለው ብዙም ልዩነት የለም፡፡ ያልተማከለው አስተዳደር ደግሞ በተቻለ መጠን ብዙ መብቶችን ለክልሎች የሚሰጥ ፌደራላዊ አወቃቀር ይኑረው በሚለውም ላይ ብዙ ክርክር አልሰማም፡፡ ጥያቄ የሚነሣው ‹በፌደራል አስተዳደር ውስጥ ክልሎች በምን መሥፈርት ነው የሚከለሉት?› በሚለው ነው፡፡ ስለዚህ ፌደራሊዝሙን ተቀብለህ በምን ላይ ይመሥረት በሚለው ላይ ግን ልትለያይ ትችላለህ፡፡ ወይም ያልተማከለ ሥርዓት የሚለውን ተቀብለህ ያ ሥርዓት ፌደራላዊ ይሁን የሚለውን ደግሞ ላትቀበል ትችላለህ፡፡
ቁም ነገሩ የጥያቄውን ዋና ይዘት በጥልቀት ፈትሾ፣ በውይይት መፍትሔ መስጠት እንጂ ሐሳቦችን ጥግ እየወሰዱ ጊዜያዊ የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር መሆን የለበትም፡፡ ነገሮችን ጥግ ለማስያዝ መሞከር ከፖለቲካ ባህላችንም ጋር የተያያዘ ይመስለኛል፡፡
ዘመን፡- በሀገራችን ያሉ የማንነትና የብሔር ጥያቄዎች እንዴት ቢመለሱ ጥሩ ነው ይላሉ?
ዶክተር ብርሀኑ፡- አሁን ያለው አስተዳደር ቋንቋንና ዘርን መሠረት አድርጎ የተሠራ ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የተሻለና የተረጋጋ ማሕበረሰብ ይፈጥራል ወይስ አይፈጥርም? የተሻለ ሥርዓት ይፈጥራል ወይስ አይፈጥርም? ዜጎች እንዲሟሉላቸው ከሚፈልጉት መሠረታዊ ፍላጎቶች ጀምሮ አስተዳደራዊ ፍትሕ ሊያገኙ የሚችሉባቸው፣ መብታቸው ተከብሮ ሊኖሩበት የሚችሉበትና የሰዎች ፍላጎት የሆነውን የተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ ለማግኘት የሚያስችል ነው ወይስ አይደለም? ተብሎ ቢጠየቅ ለመልሱ ሩቅ ሳንሄድ ያለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት ታሪካችንን መመልከት ብቻ ይበቃል፡፡
መመለስ ያለበት ጥያቄ አሁን ያለንበት አወቃቀር ሰላም ሰጥቶናል ወይ? አወቃቀሩ በእርግጥ እውነተኛ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አጎናጽፎናል ወይ? አስተዳደሩ የዜጎችን ሰብአዊ መብት የሚያከብር ሆኗል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን ጠይቀህ የምታገኘው መልስ ነው፡፡ በተለይ ዋናው ጥያቄ የሰላምና ጸጥታ ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ሰላም መፍጠር ችሏል ወይ? ክልሎች ከክልሎች ጋር በሰላም መኖር የሚችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል ወይ? በክልሎች ውስጥስ ሰላም ተፈጠሯል ወይ? ይህን ጥያቄ ማንም ኢትዮጵያዊ አይቶ በቀላሉ ሊመልሰው የሚችል ነው፡፡ መልሱ አይደለም የሚል ነው፡፡ አሁን ያለው የፌደራል አወቃቀር ቋንቋንና ዘርን ብቻ መሠረት አድርጎ የተዘረጋ የአስተዳደር ሥርዓት ስለሆነ በጣም ብዙ ችግሮችና እንከኖች እንዳሉበት ለማወቅ ጠንቋይ መቀለብ አያስፈልግም፡፡
በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በማንኛውም አገር ቢሆን ፖለቲካ በቋንቋና በዘር ከተቃኘ ምን ችግር ሊፈጠር እንደሚችል በአካባቢያችንና ከአካባቢያችን ውጪ ባሉ በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ውስጥ ማየት ትችላለህ፡፡ ይህ መንገድ የሚያዋጣ ነው ብሎ የሚያስብ ብዙ ሰው ያለም አይመስለኝም፡፡ ችግሩ ታውቆ ተስማማህ ማለት ግን ‹የመፍትሔ አማራጩ ምን ይሁን?› በሚለው ላይም ስምምነት አለ ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ አማራጭ መፍትሄው ላይ ቁጭ ብሎ፣ ከስሜታዊነት ነጻ በሆነና በሰከነ መንፈስ ለአብዛኛው ማሕበረሰብና ለአገሪቱ ሰላም የሚበጀው የቱ ነው? ብሎ መወያየት አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ነገሩ በጣም ስሱ ስሜቶች ያሉበት (ሴንሲቲቭ) እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ውይይቱን በታቃራኒ ጎን የሚመጣን ሐሳብ ከልብ ለማዳመጥ የማያስችል መንፈስ ባጠላበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ማካሄድም አስቸጋሪ ነው፡፡
ይበልጥ አስቸጋሪ የሚያደርገው ደግሞ አሁን እንዳለንበት የሽግግር ጊዜ ስሱ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ዘልዬ ልግባ ስትል የሚፈጠረው ችግር ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ትልልቅ ጉዳዮች ለመፍታት ከመሞከር በፊት መጀመሪያ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን፤ እንዲሁም መብቶች ግዴታዎችን ከመወጣት የሚመነጩ መሆናቸውን ተገንዝበን በተለይ የፖለቲካ ኃይሎች ይህን መንፈስ ይዘው የሚጓዙበትን ነገር ከፈጠርን በኋላ ወደ ቀጣዮቹ ትልልቅ ጉዳዮች መሔድ ያለብን ይመስለኛል፡፡
ዘመን፡- አሁን ያለው ፌደራላዊ ሥርዓት ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ የተነሡ የብሔርና የማንነት ጥያቄዎችን ለመመስ ተብሎ የተፈጠረ ሥርዓት አይመስሎትም?
ዶክተር ብርሀኑ፡- ነው እንጂ፡፡ በተለይ ግራ ዘመሙ እንቅስቃሴ ‹ሶቭየት ሕብረት ንጉሣዊውን አስተዳደር አስወግዳ የተለያዩ ማንነቶችን በማስታረቅ በአንድ ሶሻሊስታዊ አስተዳደር ሥር የሚተዳደር ማኅበረሰብ የፈጠረችው እንዴት ነው?› የሚለውን በመውሰድ ወደ ራሳቸው አገር ለማዛመት የሞከሩበት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ስታሊን “ስለብሔሮች እኩልነት” በሚል የጻፈውን፣ ሌኒንም እንደዚሁ የጻፈውን በግርድፉ የወሰደና በአግባቡ ያላላመጠ ነው፡፡ ሐሳቡ አገራችን ውስጥ በርግጥ ይሠራል አይሠራም የሚለውን ያገናዘበም አልነበረም፡፡
የብሔር ጭቆና አለ ተብሎ ዋለልኝ አቀረበ የተባለው ባለአምስት ገጽ መጽሐፍ ነው፡፡ ይዘቱም በጥቃቅን ባህላዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሆኖ ኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ የፈጠረው የሰሜኑ ባህል ነው ለሚል ድምዳሜው እንደማስረጃ የሚለበሰው ነጭ ልብስ፣ የሚበላው ዶሮ ወጥ ነው ወዘተ አድርጎ የሚያቀርብ ነው፡፡ ትልቅ ግምት ሊሰጠው የሚገባው የዋለልኝ ሐሳብ ያን ያህል የበሰለ ጥናት ተደርጎበት የተዘጋጀ ዝርዝር ነገር ሳይሆን ግልብ ይዘት ያለው አምስት ገጽ ጽሑፍ መሆኑ ላይ ነው፡፡ ጥናታዊ መፍትሔ የተጠቆመበት ሥራ ሳይሆን ርዕዮተ ዓለማዊ ብቻ ነው፡፡ መጨረሻ ላይ የሰጠው ድምዳሜም ቢሆን የብሔር ጥያቄን በጊዜው ሥልጣን ላይ ያለውን ኀይል ለማዳከም ይጠቅመናል፤ ሥርዓቱን ካፈረስንበት በኋላ ግን የላብ አደሩ የበላይነት ዓለም አቀፋዊ ይሆንና የብሔር ስሜቶች ይጠፋሉ የሚል ነው፡፡ አሁን በተግባር ሲፈተሸ ግን የዋለልኝ ሐሳብ ምን ያህል በቅጡ ያልተላመጠ መሆኑን እንረዳለን፡፡ በርግጥም ሐሳቡ በተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን የመጣ ነው፤ በዘመኑ እንደተነሡት ሌሎች ጉዳዮች ይህም የብሔር ጥያቄ በበሰለ መልኩ ያልተጠናና ያልተላመጠ ነበረ፡፡
ዘመን፡- በርግጥ ከሕዝብ የመነጩ የብሔርና የማንነት ጥያቄዎች አልነበሩም ነው የሚሉት?
ዶክተር ብርሀኑ፡- በደሎች በርግጥ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ጥያቄው ግን አንድ በደል የተፈጸመበት አካል የደረሰበትን በደል እንዴት አድርጎ ያየዋል? ለበደሉስ ምን ዓይነት መልስ ነው የሚያስፈልገው? ተብሎ ነገሩ በዝርዝር ካልታየ ችግር ይሆናል፡፡ ማለትም ተመሳሳይ ችግር ሌላ አገር ተፈጥሮ ‹የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል› በሚል ስለተፈታ እኛም አገር በተመሳሳይ መንገድ ይፈታል ስትል እውነታውና አንተ ከውጭ ያመጣኸው ነገር ይጋጩና አደገኛ የሆኑ ችግሮች ውስጥ ይከትሀል፡፡
ሰዎች ተበድለናል ካሉ፤ አዎ ተበድለዋል፤ እሱ አይደለም ችግሩ፡፡ እርግጥ ነው ቋንቋዎች እኩል ደረጃ አልነበራቸውም፡፡ አንድ ብሔራዊ ቋንቋ ብቻ የበላይ ነበር፡፡ ስለዚህ የተለያዩ ማኅበረሰቦች ቋንቋችንን ባህላችንን ማዳበር አለብን የሚል ጥያቄ ማንሳታቸው ተገቢ ነው፡፡ እዚህ ላይ ማንም ጥያቄ አይኖረውም፡፡ ይህ ግን በፖለቲካ ሲመነዘር ምን ይሆናል? በፖለቲካ ደረጃ ማንነት ማለት ራሱ ምንድነው? እነዚህ እኮ ብዙ ውይይቶችን የሚጠይቁና ብዙ መልሶች ያሏቸው ነገሮች ናቸው፡፡
እያንዳንዳችን ብዙ ማንነቶች አሉን፡፡ አንድ ሰው በብሔሩ ትግራዋይ ሊሆን ይችላል፤ በሙያውም ኢኮኖሚስት በሃይማኖቱም ሌላ እያለ ብዙ ድርብርብ ማንነቶች በአንድ ጊዜ ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ እነዚህ ማንነቶች በተለያየ ጊዜ የበላይነትን ይይዛሉ፡፡ ለምሳሌ የአርሴናል ደጋፊ ስሆን በጨዋታው ወቅት ሁላችንም የአርሴናል ደጋፊዎች በአንድነት እንጮኸለን፡፡ ሁሉም ደጋፊ አንድ ሆኖ ሲያብድ ታየዋለህ፡፡ በሌላ ጊዜ ግን ሙሉ በሙሉ የተለያየን ልንሆን እንችላለን፡፡
በማንነት ምክንያት የተነሡ ግጭቶችን በዓለም ላይ ብትመለከትም ሁሉም አንድ ወጥ ምክንያት የላቸውም፡፡ በሩዋንዳ የተነሣውን ብትመለከት ቋንቋን መሠረት ያደረገ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቋንቋቸው አንድ ነው፡፡ ከሃይማኖትም የተያያዘ አይደለም፤ ሁሉም የአንድ ሃይማኖት ተከታይ ነው፡፡ ሶማሌ ብትሄድና እዚያ ያለውን ግጭት ብታይ ደግሞ በማንነት ግጭታቸው ውስጥ ቋንቋና ሃይማኖት ምንም ሚና እንደሌላቸው ታያለህ፡፡ ቦሲንያ ደግሞ ከቋንቋ በላይ ሃማኖታዊ ማንነት ትልቅ ሚና ይዞ ታገኘዋለህ፡፡ ስለዚህ ማንነት እንደዘመኑ ሁኔታ የሚወሰን እንጂ አጠቃለህ አንዱን በመነጠል ወሳኙ ይህኛው ነው ልትል አትችልም፡፡
ለእኔ ለምሳሌ ወሳኙ ማንነት ኢትዮጵያዊነት ሊሆን ይችላል፡፡ ከሁለት ብሔር የተወለደውስ ምን ሊባል ነው? ማንነት የለውም ሊባል ነው? ስለዚህ ለማንነት ጥያቄው መልስ ለመስጠት ጉዳዩን የምታይበትና የምትተረጉምበት ሁኔታ እንጂ የሚያጠያይቀው ችግር ነበረ አልነበረም የሚለው አይደለም፡፡ እዚህ አገር ያሉ የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ባህሎችና ሌሎች ማንነቶች ሊከበሩ ይገባል፤ ሊበለጽጉም ይገባል በሚለው ላይ ልዩነት ያለው አካል የሚኖር አይመስለኝም፡፡ በዚህ ዘመን ልዩነቶችን ጨፍልቄ አንድ ዶሚናንት ማንነት አስቀራለሁ ብሎ የሚያስብ ካለ እሱ ጽንፈኛ ነው፤ ከዚያም አልፎ ያበደ መሆን አለበት፡፡ ልዩነቱ የሚከሰተው እንደ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ እንዚህ ጥያቄዎች በምን መልኩ ይነሡ? እንዴትስ መፍትሔ ያግኙ? ስንል ነው፡፡
ፖለቲካ ማለት የአንድን ማኅበረሰብ አጠቃላይ ችግር የሚፈታ ማለት እንጂ የወል ስብስቦችን እየነጠለ ችግራቸውን የሚፈታ አይደለም፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ለዚህ ብሔር፣ ለዚያ ብሔር ተብሎ የተለየ ፖለቲካ የለም፡፡ ሕግ የሚወጣው ለሁሉም ነው፡፡ ለሙስሊም የሚሠራ ለክርስቲያን የማይሠራ ተብሎ የሚወጣ ሕግ የለም፡፡ ሕግ አውጪው ሕጉን ለዜጎች ብሎ ነው የሚያወጣው፡፡ ምንም ዓይነት ማንነት ቢኖር ሁሉንም እንደዜጋ ነው የሚያያቸው፡፡
የወል ስብስቦች የሚመሩባቸው የየራሳቸው ነገሮች ይኖሯቸዋል፡፡ ሌሎችን ሊያስገድዱና የግል ፍላጎታቸውን ሊጭኑባቸው አይችሉም፡፡ ሕግ ግን ሁሉም እንዲያከብረው ግዴታ ሆኖ ነው የሚወጣው፡፡ ለሁሉ ሲወጣም እያንዳንዱን እንደ ዜጋ አይቶ ነው፡፡ ለዚህም ነው የአገር ፖለቲካ በዜግነት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል የሚለው ሐሳብ የሚመጣው፡፡ ፖለቲካ የሕዝብ ሁሉ ወይም የዜጎች ሁሉ መሆኑ ቀርቶ የወል ማንነቶች ጋር ሲያያዝ የግድ ችግር ውስጥ መክተቱ አይቀርም፡፡
ዘመን፡- የጥምር መንግሥትና የሽግግር መንግሥት ፍላጎቶች ከምን ይመነጫሉ? አስፈላጊነታቸውና ተገቢነታቸውስ ምን ያሀል ነው?
ዶክተር ብርሀኑ፡- በአንድ አገር ውስጥ በሕዝብ ፍላጎት የተመረጠና ሕዝብ የኔ ነው የሚለው መንግሥት እስከሌለ ድረስ በዚያ መንግሥት የሚወጡ ነገሮች ሁሉ ጥያቄ ውስጥ ይገባሉ፡፡ እኛ አገርም እስካሁን በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት አልነበረም፡፡ በጉልበት ሥልጣን ላይ የወጣ መንግሥት፣ በጉልበት ተጠቅሞ ሥልጣኑን የሚያስጠብቅ ሥርዓት ነበር፡፡ ይህ ነገር እንደማያዋጣ፣ ወደ ባሰ ግጭት እንደሚከተን ታየ፤ ስለዚህም መቀየር አለበት ተባለ፡፡ በመንግሥትም ውስጥ ከመንግሥትም ውጪ ይህንን ለውጥ የሚፈልጉ አንድ ላይ ሆነው ይህንን ለውጥ አመጡ፡፡
እዚህ ከደረስን በኋላ ቀጣዩ የሚሆነው ‹እንዴት ነው ወደ ፊት የምንሔደው?› የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ የሚቀጥለው ሥርዓት ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል የሚወክል እንዲሆን ለማድረግ እንድንችል ምን እናድርግ? ይህ በአንድ ጊዜ የምትመልሰው ጥያቄ አይደለም፡፡ ደረጃ በደረጃ የምታነሣቸው ብዙ ጥያቄዎች በውስጡ የያዘ ነው፡፡ ስለዚህ እኔ እንደሚመስለኝ መጀመሪያ ማድረግ ያለብን በሰከነ ሁኔታ የምንወያይበትን ዕድል መፍጠር ነው፡፡ ይህንን ደረጃ በድርጅታችን “የመስከን ደረጃ” ብለን ነው የምንጠራው፡፡ በጣም ብዙ ጥያቄዎች ያለፋታ የሚቀርቡበት ሁኔታ መስከን አለበት፡፡ የማንነት ጥያቄዎች ብቻ አይደሉም፡፡ ደሞዝ አልበቃንም ብለው ኡኡ የሚሉ አሉ፡፡ ሥራ የማቆም አድማ ሁሉ የሚያደርጉ አሉ፡፡ ይህ በሽግግር ጊዜ የተለመደና የሚጠበቅም ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ በአንድ ጊዜ መመለስ አትችልም፡፡ ለዚህ ነው መጀመሪያ የተወሰነ የመረጋጊያና የመስከኛ ጊዜ ያስፈልጋል የምንለው፡፡
መጀመሪያ እንዴት እንደምንቀጥል፣ የሚነሡ ጥያቄዎችን መልስ የምንሰጥበት ዘዴ፣ ግጭት ሳንፈጥር የምንወያይበት አግባብ ላይ መስማማት ያስፈልጋል፡፡ በሕዝቡ ውስጥ እየፈላ ያለው ስሜት የባሰ ገንፍሎ ችግር ሳይፈጥር የፖለቲካ ኃይሎች ሊኖራቸው ስለሚገባው ሚና በመጀመሪያ ዙር ተወያይተን ልንስማማ ይገባል፡፡ በዚህ መልኩ የሰከነ ሁኔታ ከፈጠርን በኋላ የምንፈጥረው የፖለቲካ ሥርዓት ምን መምሰል አለበት በሚለው ላይ ደግሞ መወያየት እንቀጥላለን፡፡
ሁሉም የሚስማማበት ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት በሚለው ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ደግሞ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ መካሔድ አለበት፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ አስቀድሞ ሊሠሩ የሚገባቸው ሥራዎች አሉ፡፡ የምርጫ ማስፈጸሚያ ተቋማት ነጻና ገለልተኛ ሆነው ሊደራጁ ይገባል፡፡ በዚህ ዙሪያ ብዙ ውይይቶች መደረግ አለባቸው፡፡ ይህም አይበቃም፡፡ ሪፎርም የሚያስፈልጋቸውን ተቋማት ከለየን በኋላ ዋና ዋናዎቹን ጥያቄዎች ወደማንሣት እንሔዳለን፡፡ አሁን ቢነሡ ግን ያልሰከነው ፖለቲካ ወደባሱ ቀውሶች ይከተናል፡፡
አሁን ባለንበት ሁኔታ የመንግሥት ሥልጣን መጋራት ያን ያህል ጠቃሚ ነው ብዬ አላምንም፡፡ አሁን መስከንና ለእውነተኛ ሽግግር መነጋገር ነው ያለብን፡፡ በውይይቱም የምንፈልገው ሁሉ ላይፈጸምልን ይችላል፡፡ ሆኖም መቀየርና መሻሻል ያለባቸው ሕጎች የትኞቹ ናቸው? በሚለው ላይ ተወያይቶ መስማማት ይቻላል፡፡ በተረፈ የመንግሥት ሥልጣን መጋራት የሚያሳስብ ነገር አይደለም፡፡ ሲጀመርም ከምርጫ ውጪ የሚገኝ ሥልጣን ጊዜያዊ ነው፡፡
ሥልጣን እንጋራ የሚሉ ወገኖች ይህን የሚሉት አንድ ስጋት ስላለባቸው ነው፡፡ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው አካል ቀጣዩን ምርጫ እንደሚፈልገው ሊጠቀምበት ይችላል በሚል ስጋት ተነሣሥተው ያ እንዳይሆን ለመከላከል ፈልገው ይመስላል፡፡ ስጋቱ እንዳይደርስ ለማድረግ ግን አማራጩ የግድ ጥምር መንግሥት መሆን የለበትም፡፡ በዋናነት ቁጭ ብሎ ለመወያት የሚያስችለው ዕድል ከተፈጠረ ምርጫውን ነጻ ማድረግ ይቻላል፡፡
ዘመን፡- የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ እንዴት እልባት ሊያገኝ ይችላል ብለው ያስባሉ?
ዶክተር ብርሀኑ፡- አዲስ አበባ የአዲስ አበቤዎች ናት፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚኖሩ ሰዎች ወጪ ስለ አዲስ አበባ ማውራት እኮ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሌሎች ከዚህች የአገሪቱ ማዕከል ከሆነች ቦታ የሚያገኟቸው ጥቅሞች ይኖራሉ፡፡ እሱን ደግሞ በሰከነ መንገድ ‹ምንድነው መሆን ያለበት?› ብለህ ልትወያይበት ትችላለህ፡፡ አስቀድመን ከተነጋገርንበት የተለየ አይደለም፡፡ ችግሩ ማንነትን በአንድ መልኩ ብቻ ለመረዳት መሞከርና ሁሉንም ነገር በዚሁ መስፈርት እየመነዘርክ ስትሔድ የሚፈጠር ችግር ነው፡፡
እስኪ አስበው! አሁን ፖለቲካው በዜግነት ላይ የተቃኘ ነው እንበል፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባን በተመለከተ የኢትዮጵያ ዜጎች ፍላጎት ምን ሊሆን ይችላል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ መኖር የሚፈልግና አቅሙም ያለው እንዲኖር፣ ሲኖርም መምረጥና የመመረጥ መብቱ እንዲከበርለት፣ የከተማው አስተዳደር ለነዋሪው ሊሰጥ የሚገባውን አገልግሎት ያለ ሌላ አድሏዊ የማንነት ክፍፍል ውስጥ ሳይገባ እንዲያሟላ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ቅድም እንደተነጋገርነው የሰከነ ውይይት አካሒደን የጠራ አመለካከት ከያዝን ሁሉም ነገር ቀላል ነው፡፡ የጠራ አመለካከት ለመያዝ ደግሞ ንጹሕ፣ ቀና፣ ምክንያታዊ ውይይት ማካሔድ ያስፈልጋል፡፡
ዘመን፡- ራስን በራስ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መርሆ ለአዲስ አበባ ተከብሮላታል ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ብርሀኑ፡- እስካሁን ያለውንማ … ምን የምታውቀው እኮ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ምርጫ ላይ መንግሥት ጣልቃ በመግባት እንዴት ሕዝብ በመረጠው መንግሥት እንዳይተዳደር እንዳደረገ እኮ ታውቃለህ፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ ብቻም ሳይሆን ሌላውም ራስን በራስ ማስተዳደር ስላልቻለ እኮ ነው ይህ ለውጥ የመጣው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ መሪ ሆኖ ሊመረጥ የሚገባው የከተማዋ ነዋሪና በነዋሪዎችም የተመረጠ መሆን አለበት፡፡ በሥራም ይሁን በሌላ ምክንያት ከየትኛውም የአገሪቱ ክፍል መጥቶ የሚኖረው ሁሉ የአዲስ አበባ ባለቤት ነው፡፡ አዲስ አበባ የአንድ ብሔር ወይም ዘር ብቻ አይደለችም፡፡ ለረጅም ዘመናት የአገሪቱ መዲና የሆነች፣ ዜጎች ከሁሉም አቅጣጫ መጥተው የሚኖሩባት፣ ማንም የተሻለ ኑሮ እኖርባታለሁ ብሎ እስካመነ ድረስ የሚኖርባት ቦታ ነች፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር ሥራ የከተማዋ ነዋሪዎች ከተማ ውሰጥ ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ ውክልናውም ለነዋሪዎቹ ነው፡፡ የትም አገር ያለ ከንቲባ ሥራው ይኸው ነው፡፡ የትም አገር!
ዘመን፡- ከፓርላሜንታዊና ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት ለኢትዮጵያ የትኛው ይሻላል ብለው ያስባሉ?
ዶክተር ብርሀኑ፡- የግል አመለካከቴን ከሆነ በተደጋጋሚ ተናግሬዋለሁ፣ ጽሑፍም ጽፌበታለሁ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላለ፣ የማንነት ጥያቄዎች ግልጽ ውይይት ሳይካሔባቸው ተመሰቃቅለው ባሉበት ሁኔታ አሁን ያለው ፓርላሜንታዊ የሚባለው ሥርዓት ሥልጣንን የሚሰጠው ፓርቲ ውስጥ ከመጋረጃ ጀርባ በሚደረግ ድርድር ነው፡፡ ሕብረተሰቡ በግልጽ በማያውቀውና ባልተሳተፈበት አካሔድ ባልመረጠው መሪ ሲተዳደር ችግር መፈጠሩ አይቀርም፡፡ ስለዚህ እንደኛ የማንነት ጥያቄዎች ተፈትተው ባልሰከኑበት አገር ውስጥ ሕዝቡን እንደ አንድ የፖለቲካ ማሕበረሰብ የሚያስተዳድርና አገሪቱን አንድ የሚያደርግ ግለሰብ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ያ አገሪቱን አንድ የሚያደርግ ሰው በሁሉም የአገሪቱ ክፍል በእኩል ድምጽ የተመረጠ መሆን አለበት፡፡ ይህ ደግሞ ሊሆን የሚችለው ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓቶች መካከል በፕሬዝዳንታዊው ሥርዓት ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ የአገር መሪ ለመሆን በሁሉም አካባቢዎች መመረጥ ግዴታ ይሆንበታል፡፡ አንድ አካባቢ ብቻ መርጦት መሪ ሊሆን አይችልም፡፡ የሁሉንም ፍላጎትም የማስጠበቅ ግዴታ ውስጥም ይገባል፡፡ ራሱ መዋቅሩ እንዲያ እንዲሆን ያስገድደዋልና፡፡
ዘመን፡- እዚህ ላይ ግን ፓርላሜንታዊው ሥርዓት ለልሂቃን ድርድር ይበልጥ ዕድል ይሠጣል ብለው የሚሞግቱ አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
ዶክተር ብርሀኑ፡- ፕሬዝዳንታዊው ሥርዓት ለልሒቃን ድርድር ይበልጥ ምቹ ነው፡፡ አብዛኛው ሕዝብ እንዲመርጥህ በአገሪቱ ውስጥ ካሉ የተለያዩ ልሂቃን ጋር በፖሊሲዎች ዙሪያ መደራደር አለብህ፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶች ከሏቸው ኃይሎች ጋር መደራደር ይኖርብሀል፡፡ እንደዚያ ሲሆን ነው በአገሪቱ ያሉ የተለያዩ ማኅበረሰቦች ሊመርጡህ የሚችሉት፡፡ ማሕበረሰቦች ስልህ በዘር አይደለም፡፡ በጥቅም ነው፡፡ ሠራተኛው ምን ይፈልጋል? ባለሀብቱስ ምንድነው የሚፈልገው? ወዘተ እየተባለ እነዚህን ኃይሎች ከሚወክሉ ልሒቃን ጋር መደራደር ግዴታ ነው፡፡
ፕሬዚዳንታዊ ሥርዓት የምንለውም እንደ አሜሪካ ዓይነት አይደለም፡፡ አሜሪካውያን በየስቴቱ ኢሌክቶራል ኮሌጅ የሚባሉ አሏቸው፡፡ እነሱን ሕዝቡ ይመርጣቸውና በተራቸው ደግሞ ለፕሬዚዳንቱ ድምጽ የሚሰጡት እነዚህ ተወካዮች ናቸው፡፡ አሜሪካውያኑ በታሪክ አጋጣሚ ብዙኃኑን ሕዝብ በመፍራት ይህንን ዓይነት ዘዴ ፈጥረዋል፡፡ አሁን ግን ሥርዓቱን ለማሻሻል ብዙ ይከራከራሉ፡፡ እኛ ግን ገና ከጅምሩ በሕዝብ የተመረጠ ሥርዓት ይኑር ነው የምንለው፡፡
ዘመን፡- ወቅታዊውን የአገራችንን ፖለቲካዊ ሥርዓት ምን ያሰጋዋል? መፍትሄውስ ምን ቢሆን ይሻላል ብለው ያስባሉ?
ዶክተር ብርሀኑ፡- እኔ ትልቁ ሥጋት የሚመስለኝ የሰከነ ውይይት የምናካሒድበት ሁኔታ መፍጠር ካልቻልን ነው፡፡ ለሕዝበኞች (ፖፑሊስቶች)፣ በአቋራጭ ሥልጣን እንይዛለን ብለው ለሚያስቡ ክፍት የሆነ፣ እውነትና ውሸት የማይጣራበት፣ የአንድ ድርጅት አቋም በትክክል የማይታወቅበት፣ ሚድያው የመርማሪነት (ኢንቨስቲጌቲቭ) ሥራውን ለመሥራት የሚያስችል አቅምና ሙያዊ ብቃት በሌለበት ሁሉም የፈለገውን እያደረገ የሚፈጠረው የጨረባ ተዝካር ማኅበረሰባችንን ችግር ውስጥ ሊከተው ይችላል፡፡ ስለዚህ ጥያቄዎቹ ሁሉ እንዳሉ ሆነው አስቀድመን ግን የአገሪቱን ጥቅም ያስቀደሙና በእውነት ላይ የተመሠረቱ ውይይቶችን ማድረግ አለብን፡፡
ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሁሉም የፈለገውን እየተናገረ ሕዝብ በማነሣሣት፣ እንደልቡ የሚሔድ ከሆነ ግን ትልቅ ችግር ውስጥ እንገባለን፡፡ይሁንና ብዙ መከራና ስቃይ እንዳሳለፍን የአንድ አገር ልጆች፣ እንዲሁም ማሰብ እንደሚችሉ የሰው ልጅች በእውነት ላይ የተመሠረተ ውይይት በሕዝብ ፊት የምናደርግ ከሆነና እውነትና ሐሰቱን አጣርቶ ማረጋገጥ የሚችሉ የሚድያ ተቋማት እየገነባን ከሔድን ስጋቶቻችን ይቀረፋሉ፡፡ ወደድንም ጠላንም፣ ቢመረንም ቢጥመንም የሕዝብን ውሳኔ እንቀበላለን፡፡ ሕዝብ ደግሞ የሚበጀውን እንዲመርጥ አማራጮች በትክክል ሊቀርቡለት ይገባል፡፡ ይህ እንዳይሆንና ወደተሳከረ ሁኔታ እንዳንገባ ልንወስዳቸው የሚገቡንን ጥንቃቄዎች እስካደረግን ድረስ አሁን ያንዣበቡብንን ስጋቶች አሸንፈን ወደ ተደላደለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መግባት እንችላለን፡፡ ሁሉንም ግን ደረጃ በደረጃና በየተራ ነው ልንፈጸማቸው የሚገባው፡፡
ዘመን፡- ስጋት ውስጥ የከተቱን ችግሮች መነሻቸው ምንድነው ይላሉ?
ዶክተር ብርሀኑ፡- አሁን ጥቅል በሆነው ጉዳይ ላይ ነው የምናወራው፡፡ እነእገሌ ብለን በዝርዝር ለመነጋገር አሁን ጊዜው አይደለም፡፡ ግጭት የሚያስነሱ … ይህ ነገር እንዳይሳካ የሚፈልጉ፣ ጥቅማቸው የተነካባቸው አካሎች አሉ፡፡ እሱን ሁሉም ሰው ያውቀዋል፡፡ ስለዚህ በግጭት እንጠቀማለን ብለው የሚያስቡ ኀይሎች ይኖራሉ፡፡ ለዚህ ሐሳባቸው መንገድ የምትከፍትላቸው ግን የተደላደለ የውይይት መንፈስ መፍጠር ካልቻልክ ነው፡፡ የጋራ ዕጣ ፈንታ እንዳለን አንድ ማኅበረሰብ መነጋገር ካልቻልን ይህን አገር ለማጥፋት ግጭቱ እንዲቀጥልና ሰላም እንዳይኖር ለሚፈልጉ ኃይሎች በር ትከፍታለህ፡፡ ስለዚህ ጥቅማቸው የሚነካባቸውና የለውጥ ሒደቱ እንዳይሳካ የሚፈልጉ ኃይሎች መኖራቸውን ከግምት ማስገባት ይኖርብናል፡፡ እነዚህ ኃይሎች እንዳይሳካ የሚፈልጉትን ማሳካት የሚችሉት በራሳቸው አይደለም፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ስሜቶችን በመኮርኮርና ግጭት በመፍጠር ነው፡፡ ያ እንዳይሆን ነው የፖለቲካ ኃይሎች የሚወያዩበት ምኅዳር መፍጠር አስፈላጊ ነው የምንለው፡፡ እንደዚያ ማድረግ ከቻልን ለውጡን የማይፈልጉትን አካላት ለይተን ማግለል እንችላለን፡፡
ዘመን፡- ለሰጡን ምላሽ እናመሰግናለን።
ዶክተር ብርሀኑ፡- ዕድሉን ስለሰጣችሁኝ እኔም አመሰግናለሁ!
ዘመን መፅሄት ጥቅምት 2011
በዳዊት አብርሃም