እንደ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ያላደጉ ከሚመስሉና ብዙዎች ውጤታማነታቸውን ካልተረዷቸው ስፖርቶች መካከል ጠረጴዛ ቴኒስ አንዱ ነው:: በዚህ ስፖርት ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ጥሩ እንቅስቃሴ አላት:: ባለፈው ዓመት በተካሄደው የቀጣናው ውድድርም በሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋንጫ መገኘቱ ማሳያ ነው:: ይሁንና ስፖርቱን ይበልጥ ውጤታማና አገርም በትልልቅ የውድድር መድረኮች የምትወከልበት እንዲሆን ድጋፍ ያስፈልገዋል::
ፈጣን እንቅስቃሴ በሚፈልገውና የተመልካችን ቀልብ በመስቀል የሚታወቀው ይህ ስፖርት ተዘውታሪ ይሁን እንጂ በሚፈለገው ልክ ተወዳዳሪዎችን በማፍራት ረገድ ጥረቶችን ማድረግ ይጠበቅበታል:: በዚህም ታዳጊዎች ላይ መሠረት አድርጎ መሥራት፣ ክለቦችን ማቋቋም፣ ማህበራትን ማደራጀት እና ባለሙያዎችን አሰልጥኖና አብቅቶ ጠንካራና ተፎካካሪና ስፖርተኞችን እንዲያፈሩ ለማስቻል መትጋት እንዳለበት ባለሙያዎች ይናገራሉ:: በተጨማሪም ስፖርቱን ለመደገፍ ከሌሎች ደጋፊ አካላት ጋር ሀብት የማፈላልግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ባለሙያ ብሩክታዊት ተገኝ ገልጸዋል::
በስፖርቱ ተተኪዎችን ለማፍራት በሚደረገው ተግባርም በየክልሉ 78 የሚሆኑ የታዳጊ ወጣት ፕሮጀክቶችን ስልጠና ጣቢያዎችን በማቋቋም ወደ ሥራ ገብተዋል:: በእነዚህ የስልጠና ጣቢያዎች የሚገኙትን አሰልጣኞችም በማሰልጠን በክህሎትና በተግባር የማብቃት ሥራ መሥራት ተችሏል:: ከፕሮጀክት የሚያድጉ ወጣቶችን የሚቀበሉ ከስድስት በላይ ክለቦች በኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን ስር ይገኛሉ:: በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም የክለቦች ቻምፒዮና የተከናወነ ቢሆንም፤ የክለቦቹ ቁጥር ግን በቂ አለመሆኑ ታይቷል::
ከውድድሩ ብሔራዊ ቡድንን የሚወክሉ ስፖርተኞች ተመርጠው ጅቡቲ ላይ በተደረገ ውድድር በመካፈል ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ መመለሳቸውንም ባለሙያዋ ይጠቁማሉ:: በቅርቡ በሚካሄድ ሌላ ውድድር ላይም ይህንኑ ውጤታማነት አስጠብቆ ለመመለስ ታቅዷል:: ከመጪው ግንቦት 23- 25/2015 ዓ.ም የሚካሄደው ውድድሩ የአፍሪካ ጠረጴዛ ቴኒስ ክለቦች ቻምፒዮና ሲሆን፤ አዘጋጇም ኬንያ ናት:: በኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ የክለቦች ቻምፒዮና የውድድሩ አሸናፊ የሆነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም አገሩን በመወከል በቻምፒዮናው የሚሳተፍ ክለብ ይሆናል:: በስፖርቱ የተሻለ የውጤታማነት ታሪክ ያለው ክለቡ በውድድሩ በሚኖረው ቆይታ ውጤት እንደሚያስመዘግብም ይጠበቃል::
በመጪው ዓመት መስከረም ወር 2016 ዓ.ም የአፍሪካ ቻምፒዮና በቱኒዝያ አዘጋጅነት ይካሄዳል:: በዚህም ኢትዮጵያ በወንድ፣ በሴት፣ በነጠላ እና በቡድን መሳተፏን አረጋግጣለች:: ለተሳትፎውም ከሌሎች አካላትና ከመንግሥት ድጋፍ ይጠበቃል:: እስከ አሁን ባለው ሂደት መንግሥት የሚያደርገው ድጋፍ እንደሌሎች የስፖርት ዓይነቶች አጥጋቢ አይደለም:: በተለይ ለቤት ውስጥ ስፖርቶች የሚሰጠው ትኩረትና ድጋፍ በቂ የሚባል አለመሆኑን ባለሙያዋ ያነሳሉ:: በተገቢው መንገድ እንቅስቃሴ ቢደረግ ተወዳዳሪዎች በዓለም አቀፍ ውድድሮች መሳተፍ ቢችሉ ውጤታማ መሆናቸው ግልጽ ነው::
በእርግጥ በጠረጴዛ ቴኒስ ብሔራዊ ቡድኑን የሚወክሉ ተጫዋቾች በቁጥር አናሳ ቢሆኑም ጠንካራና ተፎካካሪ ናቸው:: ነገር ግን እንደ ሌሎች ስፖርቶች ባለማደጉና ትኩረትን መሳብ ባለመቻሉ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ለመሳተፍ አዳጋች እየሆነ መጥቷል:: ስፖርተኞች ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተው፤ ጊዜ፣ ጉልበት፣ ገንዘብ ባክኖ በመጨረሻ ድጋፍ ባለመገኘቱ ተሳትፎን ማድረግ ሳይቻል ይቀራል:: በመሆኑም በዓለም አቀፍ ውድድሮች ለመሳተፍ ተገቢው ድጋፍ መደረግ እንደሚኖርበት ባለሙያዋ ያሳስባሉ::
በኢትዮጵያ የጠረጴዛ ቴኒስ ተጫዋቾች በቴክኒክ ጥሩ ደረጃ እንደሚገኙ ባለሙያዋ ያስረዳሉ:: በአውሮፓ አገራት ከሚጫወቱ አፍሪካውያን ተጫዋቾች ጋር ጥሩ ተፎካካሪ መሆን የሚችሉ ናቸው:: ይሁንና ፌዴሬሽኑ የስፖርት ቁሳቁስ ችግሮች አሉበት:: ተጫዋቾች የሚጠቀሙባቸው ጠረጴዛ፣ ኳስ እና ራኬት ከሌሎች አንጻር ኋላ ቀር የሚባል ነው:: ደረጃቸውን የጠበቁ ባለመሆናቸውም በስልጠና ሂደቱ ተጽዕኖ ማሳረፍ ችለዋል:: እንደ አገር ዘመናዊ የስልጠናና ውድድር መሣሪያዎችን ማሟላት ቢቻል ከዚህም የበለጠ ውጤትን ማስመዝገብ ይቻላል:: ሌላው ተጫዋቾች በቴክኒክ የተሻሉ ቢሆኑም በአካል ብቃት ረገድ ግን ደከም ስለሚሉ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል:: በቀጣይም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ በታክቲክና ቴክኒክ ከሚያሰለጥን ባለሙያ በተጨማሪ በአካል ብቃት የሚያሰለጥን ባለሙያ ለመቅጠር እቅድ መያዙንም አብራርተዋል:: ስፖርቱን ለማሳደግና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በሚደረገው ጥረትም ፌዴሬሽኑ የባለድርሻ እና የደጋፊ አካላትን እገዛ ይፈልጋል::
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 23/2015