በያኔው አጠራሩ ኦሜድላ የአሁኑ የፌዴራል ፖሊስ ስፖርት ክለብ፤ በ1980 ዓ.ም በቶኪዮ፣ ሮተርዳም እና ሞስኮ ማራቶኖች ድል ላስመዘገቡ አትሌቶቹ የምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግ ሰጠ። ሹመቱን አስመልክቶ በተዘጋጀው ግብዣ ላይም ተሿሚዎቹ ንግግር እንዲያደርጉ ወደ መድረክ ተጠሩ። ከተሿሚ አትሌቶች መካከል አንዱም ‹‹… እኔ ውጪ ሀገር ለውድድር ስሄድ እንደ በፊቱ ለማሸነፍ ብቻ አይደለም። በጀግናው አትሌታችን ሻምበል አበበ ቢቂላ ተይዞ የነበረውን አሁን ግን በነጮች የተወሰደውን ክብረወሰን የማስመለስ ህልም አለኝ። ኢትዮጵያዊው በላይነህ ዴንሳሞ ክብረ ወሰን ሰበረ ተብዬ ነው የምመጣው እንጂ፣ አሸንፌ ብቻ አይደለም›› ሲል በወኔ ተናገረ።
ከኢትዮጵያዊያን የማራቶን ጀግኖች መካከል አንዱ የሆነው ይህ አትሌት ሹመቱን ያገኘበት ወቅት ለኢትዮጵያ የማራቶን ሩጫ ክብረ ወሰን መስበር ብርቅ ነበር። ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ የማራቶን ክብረወሰንን በሮም ኦሊምፒክ ካሸነፈ በኋላ ለ23 ዓመታት ከኢትዮጰያውያን እጅ አምልጦ በሌላ አገር አትሌት ተይዞ ቆይቷል። ከዚያ በኋላ በርካታ አትሌቶች ቢያሸንፉም ክብረ ወሰን የመስበር ነገር ግን ተሰምቶ አይታውቅምና ይህ በላይነህን ይከነክነው ነበር። በዚህና በሹመቱ ደስታ ምክንያት በሰራዊቱ ፊት ያደረገው ንግግር ግን መልሶ ያስጨንቀው ይዟል።
ቃል አንድም የእምነት እዳ ነው፤ አንድም የተናገረውን የማይፈጽም ወታደር ብቁ ወታደር አይደለም ይባላልና እንደተናገረው ባይሆንስ የሚለው ሃሳብ አብሰለሰለው። ነገር ግን ጠንካራ ልምምድ ማድረግ ለውጤት እንደሚያበቃው በማመን ቤተሰቦቹን ትቶ ለአንድ ወር ያህል ሆቴል በመግባት ወደ ልምምድ ገባ። ሌት እና ቀን ሳይልም ለፍጥነት ጃንሜዳ፣ ለጉልበት እንጦጦ ማለዳም በአስፓልት ጠንካራ ዝግጅት ማድረጉን ገፋበት። በመጨረሻም ዝግጅቱ ተጠናቆ የውድድሩም ቀን ደርሶ ጉዞ ወደ አውሮፓዊቷ ሮተርዳም ሆነ።
በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ የተወከለችው በስድስት አትሌቶች ነበር። እንዲህ ዓይነት ብዙ ቁጥር ያለው ተወዳዳሪ አገርን ወክሎ ወደ አንድ ቦታ ሲሄድም የመጀመሪያው ነበር። በላይነህ አስቀድሞ ለሃገሩ ህዝብ ክብረወሰኑን ዳግም ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመልስ ይናገር እንጂ፤ ውድድሩ ከሚካሄድበት ስፍራ ሲደርስ ግን ሙያ በልብ ነው በማለት ዝምታን መረጠ። በአንጻሩ ከሌላ ሀገር የመጣ አንድ አትሌት ክብረ ወሰን እሰብራለሁ ብሎ በመፎከር ሃምሳ ሺ ዶላር እንዲከፈለው አስቀድሞ ተዋውሎ ነበር። ከውድድሩ አስቀድሞ ቃለ ምልልስ ባደረጉለት ጊዜም በላይነህ ‹‹… ጥሩ ዝግጅት አድርጌያለሁ፣ ክብረ ወሰን ደግሞ እርሱ ከሰበረ እኔም የማልሰብርበት ምክንያት የለም። ኢትዮጵያውያን ብዙ ጉራ አይወዱም፤ እኔም ብዙ ጉራና መፎከር አልፈልግም። ሜዳና ፈረሱን እሁድ ዕለት ታዩታላችሁ። ግን እግር ስላለኝ፣ እርሱ ከሰበረ፣ እኔ የማልሰብርበት ምክንያት የለም›› በማለት መለሰላቸው።
ተጠባቂው ዕለት ደርሶም ውድድሩ ተጀመረ። በሩጫው በርካታ ታዋቂና ፈጣን ሰዓት ያላቸው ተወዳዳሪዎች ነበሩና እስከ 30ኛው ኪሎ ሜትር ፉክክሩ የበረታ ነበር። ከ35 ኪሎ ሜትር በኋላ ግን በላይነህና ዝግጅቱን በኢትዮጵያ ሲያደርግ ቆይቶ ክብረወሰኑን እንደሚሰብር ሲፎክር የቆየው አትሌት ብቻ ቀሩ። ይህ አትሌት በትውልድ ጅቡቲያዊ ሲሆን፤ የሚሮጠው ግን ለፈረንሳይ ነበር። ጠንካራ ተፎካካሪ ቢሆንም የኋላ ኋላ ግን ውድድሩ የከበደው መሆኑ ስለገባው በላይነህ ፍጥነቱን ጨመረ። ከአሰልጣኙ ንጉሴ ሮባ ‹‹አሁን እየለቀቀ ነው፣ ቀጥል! ወደ ኋላ አትመልከት፣ ወደ ፊት ሂድ እየለቀቀ ነው›› የሚል ድምጽ መስማቱ አበርትቶች ወደፊት መስፈንጠሩን ጀመረ።
በቀሩት ሶስት ኪሎ ሜትሮችም ፍጥነቱን ይበልጥ በመጨመር ርቀቱን 2 ሰዓት ከ06 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ በመግባት የዓለምን የማራቶን ክብረወሰን ሰበረ። ኢትዮጵያም ዳግም የመሪነት ድሏን ተቀዳጀች። ያለውን ኃይል ሁሉ አንጠፍጥፎ የሮጠው በላይነህ እንደ ቃሉ ክብረወሰኑን መስበሩን ሲያውቅም ‹‹ምንጊዜም ኢትዮጵያ! ምን ጊዜም ኢትዮጵያ!›› እያለ መዝለልና መሮጥ እንደጀመረም ‹‹የተፈተነ ጽናት›› በሚል ርዕስ በፃፈውና በዚህ ሳምንት ባስመረቀው የህይወት ታሪኩ ላይ ያጠነጠነ መፅሐፍ አስፍሮታል።
በላይነህ ለዚህ ማራቶን ውድድር በወታደሩ ፊት የገባውን ቃል ለመፈፀም ለአንድ ወር ቤተሰቡን ተለይቶ በሆቴል በመቀመጥ ሲዘጋጅ ለመውለድ የደረሰች ባለቤቱን ጭምር ርቆ ቆራጥ ውሳኔ ወስኖ ነው። ውሳኔውም አላሳፈረውም ቃሉን በተግባር ቀይሯል። ከድሉ በኋላ ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላም ባለቤቱ የበኩር ልጁን አሳቀፈችው። እሱም ክብረወሰን ሲል ወጣ ያለ ስም ሰጣት።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22/2015