ለሥራ ጉዳይ ወደጅማ እያቀኑ ባሉበት በአንድ ዕለት አንድ የስልክ ጥሪ ይደርሳቸዋል።የስልክ ጥሪው ለጊዜው ስሙን መጥቀስ ከማይፈልጉት ድርጅት ውስጥ ከሚሠራ የሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር የመጣ ነው።የማኅበሩ ሊቀመንበር መረር ባለ ድምጸት በሚሠራበት ድርጅት ውስጥ ባለ አንድ ማሽን ላይ የሚሠራ የአንድ ልጅ እጅ በማሽኑ መቆረጡን ይነግራቸዋል።ልጁም የአካል ጉዳት ስለደረሰበት ሥራውን ለቆ ይሄዳል።
እዚያው ማሽን ላይ ምንም ዓይነት ጥንቃቄ ሳይደረግ ሌላ ሠራተኛ እንዲሠራ መደረጉንና የዚያም ሠራተኛ እጅ መቆረጡን ይገልጽላቸዋል።በዚህ ሳያበቃ ያለምንም ጥንቃቄ ሦስተኛ ሠራተኛ እዚያው ማሽን ላይ እንዲሠራ ይደረግና አሁንም የዚያ የሦስተኛው ሠራተኛ እጅ ልክ እንደቀደሙት ሁሉ ተቆረጠ ይላቸዋል።በዚህ መሃል ሌላ ሠራተኛ እስከሚገኝ በሚል ራሱ የማኅበሩ ሊቀመንበር ገብቶ እንዲሠራ መደረጉን ቅር እያለው ያወጋቸዋል።ጉዳዩን ከጅማ ሥራ መልስ እንደሚያዩት ያወጉትና የመረጃ ልውውጡ ያበቃል፡፡
እርሳቸውም ወደጅማ የሔዱበትን ጉዳይ ፈጽመው ከመመለሳቸው በፊት የዚሁ የሠራተኛ ማኅበሩ ሊቀመንበር እጅ ለአራተኛ ጊዜ መቆረጡን ይሰማሉ።በዚህም በጣም ያዝናሉ።ይህ የጥንቃቄ ጉድለት ያመጣው መከራ ነው እንጂ መቼም በድርጅቱ የተገጠመው የሰው እጅ ብቻ እየመረጠ የሚበላ ማሽን አይደለም ሲሉ ኀዘናቸውን ይገልጻሉ፤ የዛሬው የዘመን እንግዳችን የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ።
አቶ ካሳሁን ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል ነው።በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ በዓለም አቀፍ ሕግ አግኝተዋል።እኚህ የዛሬ እንግዳችን በመጀመሪያ የኦሮሚያ መንገዶች ድርጅት ተቀጥረው ሕግ ክፍል ውስጥ ሠርተዋል።እዚያ እያሉ የድርጅቱ ሠራተኞች የማህበራቸው ፕሬዚዳንት አድርገው ይመርጧቸዋል። በኋላም የኢሰማኮ ፕሬዚዳንት ሆነው ወደ 13 ዓመት ያህል ሠርተዋል፤ በመሠራት ላይም ይገኛሉ።እኛም ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ134ኛ እንዲሁም በአገራችን ለ48ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ እንግዳችን አድርገናቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- አሰሪዎች ሠራተኛው እንዲደራጅ ፍላጎት እንደሌላቸው ይነገራል፤ ለመሆኑ የሠራተኞች በማኅበር መደራጀት እንደ ስጋት የሚቆጥሩት ለምን ይሆን ከሚለው ጭውውታችንን ብንጀምር?
አቶ ካሳሁን፡- መልካም ነው፤ የሠራተኛው መደራጀት ስጋት የሚሆነው ከሁለት ነገር በመነጨ ምክንያት ነው፤ የመጀመሪያው ሠራተኛው ሲደራጅ ስለመብቱ ይጠይቃል ከሚል ስጋት ነው።ከአሰሪው ጋር የመደራደር አቅም ይፈጥራል።ሌላው ቀርቶ በደመወዝ ጭማሪ ጉዳይ መደራደር ይችላል በሚል ነው። ይህ ደግሞ የሠራተኛው ጥቅም ስለሚሆን አሰሪዎች መደራጀቱን እንደ ስጋት ሊቆጥሩት ይችላሉ። ሁለተኛው ስጋት ደግሞ የሙያ ደህንነትና ጤንነት ጉዳይ ነው።የሙያ ደህንነትና ጤንነት ሲባል በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ላይ በግልጽ የተቀመጠ ነው፤ ይህ ስለማይከበር ለሙያ ደህንነትና ጤንነት ወጪ ያወጣሉ።
ያለመረዳት ካልሆነ በስተቀር ለሙያ ደህንነትና ጤንነት ሲባል የሚወጣው ወጪ ጠቀሜታው ለሠራተኛ ብቻ ሳይሆን ለአሰሪውም ጭምር ነው። አንድ ድርጅት ሲቋቋም ለሠራተኛው የሚያስፈልገው ሁሉ ተሟልቶ መሆን ሲገባው አሰሪዎች ያንን አያደርጉም፤ ሠራተኛው ከተደራጀ ደግሞ ይህንንም ጨምሮ ሌሎች መብቶቹን ስለሚጠይቅ መደራጀቱን እንደስጋት ሊያዩት ይችላሉ።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ አሰሪዎች ሠራተኛው ከተደራጀ የሥራ አድማ ለማድረግ ቅርብ ነው የሚል ፍራቻ አላቸው፤ እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ካሳሁን፡- በነገራችን ላይ የሠራተኛ ማኅበር ከተቋቋመበት ድርጅትና ካልተቋቋመበት ድርጅት የሥራ አድማው የሚበረታው ማኅበሩ በሌለው ድርጅት ነው። ሠራተኛ ማኅበር ሲቋቋም ሕጋዊ ሰውነት አለው። ሠራተኛው ሕገ ወጥ ነገር ከሠራ ይከሰሳል። ነገር ግን ሠራተኛ ማኅበሩ በሌለበት ሠራተኛው ሥራ ሲያቆም ወደሥራ የመመለሱ ጉዳይ በራሱ አስቸጋሪ ይሆናል።
ለአብነት የማነሳልሽ አንድ ገጠመኝ አለኝ፤ ወደአራት ሺ ሠራተኞች ያሉት አንድ ኢንዱስትሪ ሠራተኞቹ ሥራቸውን በአድማ አቆመው ወደየቤታቸው ሔዱ። በወቅቱ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተደወለልኝና ምን ማድረግ እንችላለን አሉኝ፤ የእኔም ምላሽ የነበረው ማኅበር ስለሌላቸውና ሠራተኛውንም ማግኘት ስለማይቻል ምንም ማድረግ አይቻልም የሚል ነበር።ነገር ግን ሠራተኛው መጠራት አለበት ወደሚል ቢመጣም ማኅበር ስላልነበራቸው በምን አግባብ ይቻላል የሚለው በወቅቱ አነታራኪ ነበር፡፡
የሠራተኛው መደራጀት ለዚህ ሁሉ ችግር መድኃኒት ነው፤ ምክንያቱም ማኅበር ሲኖር ሠራተኛው ሥራ ለማቆም ቢፈልግ እንኳ የራሱ የሆነ ቅደም ተከተል አለው፤ የትኛውም ሠራተኛ ስላልተመቸው ብቻ ከእንቅልፉ ብንን ብሎ ሥራ ማቆም አይችልም፤ መደራደር አለ። ልምድ ያለውን ሠራተኛ ማጣት ደግሞ ለአሰሪውም ለአገርም ጭምር ጉዳት ነው።ስለዚህ የማኅበሩ መኖሩ ጥቅሙ ከፍ ያለ ነው።
በነገራችን ላይ የሠራተኛውን መደራጀት አሰሪው ብቻ ሳይሆን መንግሥትም ይፈራል።እንዲያውም በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ሠራተኞች በብዛት ያለመደራጀታቸው ጉዳይ መንግሥት ስለሚፈራ ጭምር ነው።የመንግሥት ሠራተኞች እንደማንኛውም የኢንዱስትሪ ሠራተኞች በማኅበር የመደራጀት መብት አላቸው። የኢንዱስትሪውም አሰሪ ሆነ የመንግሥትም ስጋት አንድ ነው፤ ሠራተኛው በማኅበር ከተደራጀ የደመወዝ ጭማሪ ይጠይቃል የሚል ነው።
በመጀመሪያ ደረጃ ሠራተኛው ከአገሪቱ አቅም በላይ የሆነ የደመወዝ ጭማሪ ይደረግልኝ የሚል ጥያቄ ያነሳል ብሎ ማሰብ ሲቪል ሠራተኛው አያስብም እንደማለት የሚቆጠር ነው። ነገር ግን ሠራተኛው አገሩ ያለችበትን ሒደት ስለሚያውቅ ያስባል። ስለሆነም ከአገሪቱ አቅም በላይ ጥያቄ አያቀርብም።የግል ድርጅት አሰሪዎች ዘንድም ቢሆን የሚፈሩት የሥራ ማቆም አድማ ማኅበር ባይኖርም አይቀርም።
በመሆኑም በዚህ በሰለጠነ ዘመን መደራጀት ማለት ሕጋዊ መሆን ማለት ነው። በተለይ በማኅበራዊ ትስስር ገጽ አንድ ሚሊዮን አባላትን ማንቀሳቀስ በሚቻልበት በዚህ ዘመን በማኅበር እንዳይደራጁ መከልከል ወይም እንደ ስጋት መቁጠር ተገቢነቱ አይታየኝም። ስለዚህ አደረጃጀት ለተጠያቂነትም የሚያመች በመሆኑም ይከሳል፤ ይከሰሳል፤ ይደራደራልም ባይ ነኝ።
በመሠረቱ ሲቪል ሠራተኛው እንዳይደራጅ የመከልከሉ ምስጢር ሙሰኞች በየመስሪያ ቤቱ የሚፈጽሙት ሙስና እንዳይጋለጥም ስለሚፈለግ ይመስለኛል። እንዲያውም አንዳንድ ቦታ ከመጀመሪያው ጀምሮ ሠራተኛው እንዳይደራጅ ያደርጋሉ፤ አሻፈረኝ ብሎ ሠራተኛው እንዲደራጅ የሚያስተባብሩ ካሉ ወይ ቀድመው ያዘዋውሯቸዋል፤ አሊያም ሰበብ ፈልገው ከሥራ ያሰናብቷቸዋል።
አንዳንድ ተቋማት ደግሞ ልክ ሠራተኛው ተደራጅቶ ኮሚቴው ሲመረጥ የኮሚቴ አባላትን ወደማኔጅመንት ያሳድጓቸዋል። ወደእዛ ካደገ ደግሞ ማኅበር ሊሆን አይችልም። ስለመብትም ሊከራከር አይችልም። እነርሱም ለሁሉም ሠራተኛ ጥቅም ከሚሰጡ ጥቂት የኮሚቴ አባላትን መጥቀምን ይመርጣሉ። በዚህ አካሄድ ማኅበሩ ከጨዋታ ውጪ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡
አንዳንድ ቦታ ደግሞ እስርም አለ፤ በተለይ የኮሚቴ አባላት ሁሉ ይታሠራሉ። ለምሳሌ በቅርቡ በአዳማ አካባቢ በአንድ ኢንዱስትሪ ያሉ ሠራተኞችን አደራጅተን ነበር። ይሁንና አምስቱንም የኮሚቴ አባላት አሰሯቸው። አሰሪዎቹ ምክንያት ሲባሉ የተደራጁት ለአመጽ ነው የሚል ምላሽ ሰጡ።ነገር ግን ለአመጽ በሕጋዊ መንገድ መደራጀት አያስፈልግም፤ ሠራተኛው ሥራ ማቆም ካስፈለገው እንኳ ሕጋዊ መስመርን ተከትሎ እንጂ እንዳሻው አይሆንም። ምክንያቱም ሥራ ለማቆም በማኅበር የተደራጀ ሠራተኛ ለአሰሪው ቢያንስ የአስር ቀን ጊዜ ይሰጠዋልና ነው።
አዲስ ዘመን፡- የሙያ ደህንነትና ጤንነት እንዲጠበቅ የወጡ መመሪያዎችና ሕጎችን አሰሪዎች ምን ያህል ተግባራዊ እያደረጉ ነው? ተግባራዊ እየተደረገ ካልሆነ ደግሞ መፍትሔው ምንድን ነው?
አቶ ካሳሁን፡- የሙያ ደህንነትና ጤንነት በተመለከተ አስቀድሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩ አስፈጻሚ አካል ዘንድ የግንዛቤ ችግር ይታያል። ሌላው የሥራውን ሁኔታ በማየት በሚቆጣጠረው ላይ የባለሙያ እጥረት አለ።ዘርፉን የሚቆጣጠር የሰው ኃይል ማነሱ ብቻ ሳይሆን በጀትም የሌለው ነው።ስለዚህ ይህ በራሱ በመንግሥት መሟላት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
ለምሳሌ በርከት ያሉ ኢንዱስትሪዎች ባሉባት በእኛ አገር ያለው የሙያ ደህንነትና ጤንነት ባለሙያ 500 ያህል ብቻ ነው። ይህ ለአዲስ አበባ ብቻ እንኳ ቢወሰድ የሚችል አይሆንም። ቢያንስ አንድ ድርጅት አንዴ እንኳ መታየት መቻል አለበት ባይ ነኝ።የሙያ ደህንነትና ጤንነት ባልተጠበቀበት ድርጅት ከሚፈጠረው ጉዳት የተነሳ ድርጅቱ ተከሶ እስከመዘጋት ሊደርስ የሚችል ቢሆንም ይህን መብት በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የለም። ይህ ችግር ደግሞ በየቦታው ጉዳት ሲያመጣ ተስተውሏል።በየቦታው ያሉ ማሽኖች ከጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ በሠራተኛው አካል ላይ ጉዳት ሲያደርሱ ይስተዋላል።
በኮንስትራክሽን ዘርፉ ደግሞ በጥንቃቄ ጉድለት የሚፈጠረውን ሞትና የአካል ጉዳት በየቀኑ የሚሰማ ጉዳይ ሆኗል።በግንባታ ላይ ያለ ሕንፃ ላይ ሠራተኛው የሚወጣጣበት ስካፎል (መወጣጫ) በብረት መሠራት ሲገባው እየተሠራ ያለው በእንጨት ነው። ያውም የሚሠራው በበሰበሰ እንጨት በመሆኑ ሠራተኛው ለአደጋዎች ተጋላጭ ይሆናል።ለምሳሌ በእኛ መስሪያ ቤት አካባቢ አንድ እየተገነባ ያለ ሕንፃ አለ፤ ይህ ሕንፃ ግንባታው ሳይጠናቀቅ በመሃል ቆሞ ነበር። እስካሁን ሕንፃው ሳይጠናቀቅ በጥንቃቄ ጉድለት ስምንት ሰው ሕይወቱን አጥቶበታል። ይህ በየቦታው የሚጠፋው የሰው ልጅ ሕይወት ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ማሳያ ነው።
ይህ በዓይን የሚታይ ነው፤ የማይታይ የውስጥ የሆነ ጉዳት ደግሞ አለ፤ የኬሚካል ተጠቂ ሆነው የሚሠሩ ሰዎች ለምሳሌ የሙያ ደህንነትና ጤንነት በማይጠብቁ የአበባ አምራች ድርጅቶች ላይ የሚሠሩትን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ሠራተኞች የሚያጋጥማቸው የጤና እክል የአጭር አሊያም የረጅም ጊዜ ጉዳት ሊሆን ይችላል። የዚህ ሠራተኛ ሕይወት ያልፋል፤ ግን አይቆጠርም።
በረጅም ጊዜ ጉዳት ሕይወቱ ሊያልፍ ይችላል።በዚህ ዓይነት የአካል ጉዳት የደረሰበት ሠራተኛ ‹ካሳ› ተብሎ እንደዋዛ ጥቂት ነገር ተሰጥቶት ድርጅቱን ለቆ ይሄዳል፤ በተከታታይ ለሚያጋጥመው መከራ ምንም ዋስትና አይኖረውም፤ መጨረሻ ላይ የሚበላውን ሲያጣ ወጥቶ መለመን ዕጣ ፈንታው ይሆናል።
መንግሥት በእንዲህ ዓይነት ግዴለሽነት በሠራተኛው ላይ በሚፈጠረው ጉዳት መሥራት የማይችለውን ሠራተኛ ሁሉ መቀለብ አይችልም፤ ምክንያቱም ከአቅሙ በላይ ይሆናልና ነው። ይህ እንዳይሆን ግን በጋራ መከላከል ይቻላል። በሌላ አገር ያለ ልማድ ሠራተኛ ከመቀጠሩ በፊት አንድ ድርጅት ምን ያህል ሠራተኛ እንደሚቀጥርና ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አስቀድሞ የሚያውቅና ሕግ ሲተላለፍም የሚቀጣ ይሆናል።
በእኛ አገር ለምሳሌ አንዳንድ ድርጅቶች ብየዳ ላይ ለሚሠሩ ሠራተኞች ወተት ያቀርቡላቸዋል፤ ለዚያ ሠራተኛ ደህንነት የሚያስፈልገው በመጀመሪያ ዓይኑ እንዳይጎዳ የሚያግዝ መሣሪያ ነው ሊሰጥ የሚገባው።በእርግጥ ወተት የሚያስፈልግበት ቦታ ሊኖር ይችላል።ስ ለዚህ የሙያ ደህንነትና ጤንነት መጠበቅ አማራጭ ሊሰጠው የሚገባ ሳይሆን ግዴታ ነው፤ ያንን ሳናደርግ ስንቀር ግለሰብ፣ ቤተሰብ ብሎም አገር ተጎጂ ይሆናልና ሊታሰብበት የግድ ይላል፡፡
በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ምናልባት ሥራ ሊኖረው የሚችለው አንድ ሰው ብቻ ሊሆን ይችላል፤ ያም ሰው የአካል ጉዳት ከደረሰበት ጎሮሮው የሚዘጋው የቤተሰቡ ሁሉ ነውና ይህ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ ትኩረት ቢሰጠው መልካም ነው፤ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራም ቢሠራ ጉዳቱን ለመቀነስ አጋዥ ነው። አሰሪውም ቢሆን ተጎጂ ነው፤
ለምሳሌ የአስር ዓመት ልምድ ያለውን ሠራተኛ ከጥንቃቄ ጉድለት አጥቶት ከሆነ ሌላ እስከሚያላምድ ድረስ ብዙ ዋጋ ይከፍላል። ለተጎዳውም አካል ካሳ ከመክፈልና እስከሚድንም ድረስ ከማሳከምም ይድናል።
አዲስ ዘመን፡-የተረጋጋ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍንና ምርታማነት እንዲያድግ ከመንግሥትም ሆነ ከሠራተኛው ምን ይጠበቃል?
አቶ ካሳሁን፡- የተረጋጋ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲፈጠር እንዲሁም ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ከተፈለገ የሁሉም ወገን መብት መከበር አለበት። ምክንያቱም መብት ከተጓደለ መብት ጠያቂ አካል ይኖራል።ስለዚህ ሥራው ይቀርና አሰሪውም ሠራተኛውም ወረቀት ይዞ ፍርድ ቤት መመላለስ ይሆናል።ይህ በመሆኑ ጊዜና ገንዘብ ይጠፋል።ይህ ከሚሆን ሠራተኛውም ተደራጅቶ አሰሪውና መንግሥትም በጋራ ተወያይተው መፍትሔ ማምጣት ይኖርባቸዋል።
ማህበራዊ ምክክር ለምርት ማደግ ፋይዳው ከፍተኛ ነው።ማህበራዊ ምክክር ለሁሉም ችግር መፍቻ ቁልፍ ነው ብለን እንደተቋም እናምናለን። በመሆኑም እስከ ታች ድረስ ለጉዳዩ ትክረት ቢሰጠው መልካም ነው። እኛ ደግሞ ሠራተኛው የኢንዱስትሪ ዲሲፒሊን እንዲያውቅ በጋራ እንሠራ እያልናቸው ነው። ሠራተኛው ሲያጠፋ ብቻ አይደለም መጠየቅ ያለበት፤ ለሥራ ቅጥር ሲመጣም ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሊሰጠው ይገባል። የሥራ ባህሉን እንዲያሻሽል ግንዛቤ መስጠት ያስፈልጋል።ሌሎች አገሮች ያደጉት ሠራተኛን አክብረውና ከእርሱም ጋር ተወያይተው በሚገኘው ጠቀሜታ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለተመጣጣኝ ሥራ ተመጣጣኝ ክፍያ በመከፈሉ ረገድ እንደ አገር የት ላይ ነን? የሠራተኛውን ዝቅተኛ የደመወዝ መነሻ ለመወሰን የወጣው አዋጅ ከምን ደረሰ?
አቶ ካሳሁን፡– ለተመጣጣኝ ሥራ ተመጣጣኝ ክፍያ በእኛ አገር የለም፤ እንዲያውም አይታወቅም።ምክንያቱም ሁሉም የሚከፍለው በራሱ መዋቅር እያጠና ነው።ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ይወሰን ቢባልም እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም፡፡
በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በ2011 ዓ.ም የደመወዝ ወለል እንዲወሰን የሚጠይቅ የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ወጥቷል።አዋጁን መተግበር የሚያስችል ደንብ ባለመውጣቱ፤ አዋጁ አራት ዓመት ቢያስቆጥርም እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም።
በአሁኑ ወቅት ሠራተኛው እየተጋፈጠ ያለው የኑሮ ውድነት ግልጽ ከመሆኑ የተነሳ ማስረዳት አይጠበቅም።በዚህ የኑሮ ውድነት ውስጥ አንድ ሰው በወር 800 ብር ደመወዝ ተቀብሎ በእውነት እንነጋገር ከተባለ መኖር ያስችለዋልን? ምክንያቱም የሠራተኛው የወር ደመወዝ ዝቅተኛው 800፤ ከፍተኛው ደግሞ አንድ ሺ 200 ብር ነው።
አንድ ሺ 200 ቢሆን እንኳ ይህ ብር ከወር እስከ ወር ማድረስ ይችላል? ተብሎ ሲጠየቅ በዘርፉ ሰዎች የሚሰጠው ምላሽ ‹ይህ ሁሉ ሥራ አጥ ባለበት አገር ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል አይወሰንም› የሚል ነው። የወጣውን ሕግ አሰሪው በተቀበለበት ሁኔታ ተግባራዊ አለመደረጉ መልካም አይደለም።
አንዳንዶች የሚሉት ነገር ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ከተቀመጠ ባለሀብቶች ብዙ ሰው አይቀጥሩም ይላሉ፤ እንዲያ ከሆነ ታድያ ኢንቨስትመንቱን ከመቀላቀሉ በፊት ያጠናው ነገር የለም እንደማለት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሥራ አጥ ስላለ ብቻ ብዙ ሠራተኛ በትንሽ ብር እቀጥራለሁ የሚባል ነገር የለም። ሥራው ራሱ በጥናት እና በእቅድ የሚመራ እንጂ በዘፈቀደ የሚካሄድ ባለመሆኑ ባስጠናው ጥናት መሠረት ነው መሠራት ያለበት።
አዲስ ዘመን፡- የዝቅተኛ ደመወዝ ወለል መቀመጥ ጥቅሙ ምንድን ነው?
አቶ ካሳሁን፡- የዝቅተኛ ደመወዝ ወለል መቀመጥ ምርታማነትን ይጨምራል።አንዳንዶች ‹የኢትዮጵያ ሠራተኛ ምርታማ አይደለም› ሲሉ ይደመጣሉ።እንዴ! በልቶ ከማያድር ሰው ነው እንዴ ምርታማነት የሚጠበቀው? በቅጡ በልቶ ከማያድር ሠራተኛ እንዴት ምርታማነት ይጠበቃል።በወር አንድ ሺ ብር ተከፋይ ሆኖ ይህን እየበላህ ምርታማ መሆን ይጠበቅብሃል ማለት ምን ማለት ነው?
መኖር የማይችል፤ መንቀሳቀስ የማይችል ሰው እንዴት ሆኖ ነው ምርታማ የሚሆነው። ስለቤት ኪራይና ስለሚበላ እያሰበ እንዴት ሆኖ ውጤታማ መሆን ይቻላል።በአሁኑ ወቅት ሠራተኛ በሚያገኘው የወር ገቢ መተዳደር እያቃተው ነው። እንዲያውም አሁን የተጀመረ ነገር ቢኖር አንዳንድ ሠራተኛ ቀን ቀን ሥራ ውሎ ወደማታ መለመን ጀምሯል። ከሆቴል ፍርፋሪ እየለመኑ የሚሠሩ እንዳሉም እናውቃለን።
አንዳንድ ሠራተኛ ደግሞ ምሳ ይዞ ወደሥራ ቦታው መሄድ ስለማይችል በምሳ ሰዓት ጥላ ስር ተቀምጦ ያሳልፋል። ወደሥራው የሚመለሰው ባዶ ሆዱን ነው።ይህ ሁኔታ ቢስተካከል ተብሎ ጥያቄ ሲነሳ ስንት ሥራ አጥ ባለበት አገር የሚል ምላሽ የሚሰጡ አካላት አሉ።ሰብዓዊነት ሊሰማቸው ግን ይገባል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሌላው ቀርቶ የመንግሥት ሠራተኛው ራሱ መኖር አቅቶታል። እሱ ግን አብቃቅቶ በቀን አንድ ዳቦ ሊበላ ይችል ይሆናል። አሁንም መንግሥትን የምንጠይቀው ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲቀመጥ እንወያይ ብለን ነው፤ ችግር ካለም በውይይት መፍታት ይቻላል እንላለን።
አዲስ ዘመን፡- የሥራ ግብሩን በአግባቡ እየከፈለ ያለው ሠራተኛ ብዙ ጊዜ የሥራ ግብሩ እንደበዛበት ሲናገር ይደመጣል፤ በዚህ ላይ ምን እየሠራችሁ ነው?
አቶ ካሳሁን፡- የኑሮ ውድነቱ መናሩን ተከትሎ መንግሥትን ደመወዝ ጨምር ማለት አንችልም፤ ምክንያቱም የድሃ አገር ስለሆነ ከየትም እንደማያመጣ መረዳት አያዳግትም። ነገር ግን ከሚሰበስበው ግብር አስተያየት እንዲያደርግልን ነው የምንጠይቀው። ይህን ጥያቄ አቅርበን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ድረስ አስገብተናል፤ ምላሽ ግን እስካሁን አልተሰጠበትም።
ለሚመለከተው ለገንዘብ ሚኒስቴርም ደብዳቤ ጽፈናል።ነገር ግን ደብዳቤያችሁ ደርሶናል አሊያም አልደረሰንም የሚባል መልስ የለም።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይዩት አይዩትም እስካሁን አላወቅንም። ጥያቄያችሁ ትክክል ነው ወይም አይደለምም መልስ ነበር፤ ግን ምንም የለም።ይህ አንድ ዓመት ሊሞላው ነው። ስለዚህ ከመጠበቅ ወደየለም ስለሄድን ተስፋ ቆርጠናል።እኛ የሥራ ግብር ይቀር ሳይሆን ማሻሻያ ይደረግበት ነበር።
ለምሳሌ 35 በመቶ የሥራ ግብር ከሚከፍሉት ላይ ቢያንስ ትንሽ ዝቅ ይበል ነው እያልን ያለነው።የኑሮ ውድነት አይሏል። እኛ በቻልን ጊዜ መንግሥትን እንደየአቅማችን ደግፈናል። ለምሳሌ የህዳሴ ግድብ ላይ እንደ ሠራተኛው ያዋጣ የለም። መንግሥትን ረዳን ማለት አገርን ረዳን ማለት ነው።መንግሥትን የሚረዳው ሠራተኛው ተርፎት ሳይሆን ለአገሬ በሚል ነው።
ገበታ ለአገር በሚለው ፕሮግራም ላይ ከእኛ ሴክተር ካሉ ድርጅቶች አንዱ ድርጅት ብቻ እንኳን የከፈለው አንድ ቢሊዮን ብር ነው።ይህም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኛ ነው። አሁን የኑሮ ጫና ሠራተኛውን እያስጎነበሰው ነውና ቀና ይል ዘንድ ልጅ ለአባቱ እንደሚናገረው ሁሉ እኛ ለመንግሥት እየተናገርን ነው፡፡
ለምሳሌ ከ500 ብር በላይ የሚከፈል ውሎ አበል ላይ ታክስ ይደረጋል። ይህ ግን የማደሪያ አልጋ ብሎም ምግብ ይችላል የሚለው በራሱ አጠያያቂ ነው። ስለዚህ ሰኞ በሰላማዊ ሰልፍ በምናከብረው የዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን ላይ አንዱ ጥያቄ የሚሆነው ይህ ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በማኅበሩ የሥራ ቆይታዎ ያዘኑበት ጊዜ አሊያም አሳካቸዋለሁ ብለው የተደሰቱበት ጉዳይ ይኖር ይሆን?
አቶ ካሳሁን፡- ያዘንኩበት ጊዜ ብዙ ነው፤ በተለይ ሠራተኛ በሚሠራበት ቦታ ከጥንቃቄ ጉድለት በሠራተኛው ላይ የሚደርሰው የሕይወት ኅልፈትና የአካል ጉዳት ውስጤን ያሳምመዋል። ከዚህ ውስጥ አንዱን ልጠቀስልሽ፤ በአንድ አጋጣሚ ለሥራ ጉዳይ ወደጅማ እየተጓዝኩ ለጊዜው ስሙን መጥቀስ ከማልፈልገው በአንድ ድርጅት ውስጥ ከሚሠራ የሠራተኞች ማኅበር ሊቀመንበር ስልክ ተደወለልኝ። የደወለልኝ የማኅበሩ ሊቀመንበር በጣም በማዘን ከዚህ ቀደም በድርጅቱ በአንድ ማሽን ላይ ተመድቦ የሚሠራ ልጅ እጅ በመቆረጡ መሥራት ስለማይችል ከሥራ መሰናበቱን አሳወቀኝ።በዚያው ቦታ ሌላ ሠራተኛ መመደብ የግድ ስለነበር ሌላ ሠራተኛ ቢመደብም በተመሳሳይ እርሱም እጁ በማሽን መቆረጡንና ከሥራ መልቀቁን ነገረኝ። ያው ስህተት ተደግሞ የሦስተኛ ሠራተኛ እጅ መቆረጡንና ከሥራ ውጪ መሆኑን አሳውቆኝ ለጊዜው በዚያ ቦታ እርሱ እየሠራ ስለመሆኑ ነገረኝ።በዚህ በጣም እያዘንኩ ወደጅማ አቀናሁ።ጅማ የነበረኝን ሥራ አጠናቅቄ ከመመለሴ በፊት ግን የዚያ የሠራተኞች ማኅበር ሊቀመንበር እጅ መቆረጡን ሰማሁ።ይህ በእውነት በጣም የሚያሳዝን ክስተት ሆኖብኛል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ብቻ ሳይሆን በሥራ ዘመኔ ባይሳካ አዝን የነበረው የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ማጣታቸው ነው። እኔ ወደዚህ ኃላፊነት ከመምጣቴ በፊት በግል ድርጅት ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች አገልግለው ያለጡረታ ይሰናበቱ እንደነበር አስታውሳለሁ። እነዚህ ሠራተኞች መሠረታዊ የሆነ ጡረታ እንዲያገኙ እመኝ ስለነበረ ወደኃላፊነቱ ስመጣ የተሳካልኝ ነገር ቢኖር ይህ ነው ብዬ እላለሁ። ይህም የተሳካው በእግዚአብሔር ኃይል ነው፡፡
ሌላው ደስተኛ የሆንኩበት በ2008 እና 2009 ዓ.ም ጸድቆ ቢሆን ኖሮ ሠራተኛውን መጉዳት ብቻ ሳይሆን ባሪያ ያደርግ የነበረ የአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ በመጀመሪያ እኛ ተወያይተንበት ወደሚኒስትሮች ምክር ቤት የተላከው ረቂቅ አንዳንዶች አስተካክለናል ባሉት መንገድ ጸድቆ ቢሆን ኖሮ ከባድ ነበር። በወቅቱ በረቂቁ ላይ ውይይት ከሚያደርጉት መካከል ‹‹ይህ አዋጅ ሠራተኛ ሠራተኛ ይሸታል፤ መልሱና ሌላ አዋጅ አምጡ›› ተብሎ ነበር።
ይሁንና አሰሪዎች፣ ሠራተኞችና የመንግሥት ተወካዮች በጋራ ተወያይተን የላክነው ረቂቅ ነው።ነገር ግን ይህ አይሆንም ተብሎ ሌሎች ረቂቁን እንዲያዘጋጁ ተደርጎ ወደእኛ ተላከ፤ በዚያ ረቂቅ ውስጥ የሰፈረው ነጥብ ሲታይ እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ሁሉም ሠራተኛ ተባራሪ እንደሚሆን ነበር።
ምክንያቱም በረቂቁ መሠረት የኢንዱስትሪ ሠራተኛው አንድ ቀን ከሥራ ከቀረ ይሰናበታል።በሌላ በኩል ደግሞ 14 ቀን የነበረው የዓመት እረፍት ወደ ሰባት ቀን ዝቅ እንዲል የተደረገበትም ረቂቅ ነበር። ሰባቱም ቀን ፈቃድ የሚሰጠው ደግሞ አሰሪው ከፈቀደለት ነው።ሌላው ቀርቶ ሁለት ቀን አንድ ሠራተኛ ካረፈደ ከሥራ ይባረራል የሚልም የተካተተበት ነበር።
የላኩልንን ረቂቅ በተመለከተ ለውይይት በጠሩን ጊዜ መቀበል አለባችሁ ብንባልም፤ አንቀበልም የሚል አቋም ያዝን።በወቅቱ ይህን ረቂቅ አስመልክተን መግለጫ እንኳ መስጠት የማይቻልበት የኢህአዴግ ሥርዓት ስለነበር እሱ ደግሞ ‹ቁረጠው› ነው መርሁ በሚል መግለጫውን ትተን በአገሪቱ ያሉትን ሠራተኞች ተከፋፍለን ለማወያየት ትግል ጀመርን።
ኢትዮጵያውያኑ ሠራተኞችም ለመብታቸው ለመታገል የሚታሙ አልነበሩምና ወደዚያው አቀናን፤ ይህን ስናደርግ ረቂቁ ከመጽደቁ በፊት መስተካከል እንዳለበት የሚገልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስገብተን ስለነበር የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጉዳዩ ለውይይት እንደሚቀርብ መልዕክት አስተላለፉልኝ። ጉዳዩም እርሳቸው እንዳሉት ወደውይይት ተመልሶ ባለበት ግማሽ ላይ እንደተደረሰ የለውጡ መንግሥት መጣ። ይሁንና ከቆምንበት በመጀመራችን የጥያቄያችን 95 በመቶ ምላሽ አግኝቷልና በዚህ ደስተኛ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ዘንድሮው የዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረው በምን ዓይነት መርሃግብር ነው?
አቶ ካሳሁን፡– የዘንድሮውን በዓል ለየት የሚያደርገው በዓሉ የሚከበረው በአደባባይ መሆኑ ነው። አስቀድሜ ያነሳኋቸው የሠራተኛው ችግር እንዲቀረፍ በሰላማዊ መንገድ ለመንግሥት የሚቀርብበትም ይሆናል።ከዚህ ጎን ለጎን መንግሥት ለውይይት በሩን እንዲከፍትም የምንጠይቅበት ዕለት ነው።በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የኑሮ ውድነቱ ላይ ትኩረት እናደርጋለን እንጂ የፖለቲካ አሊያም የተለየ የኃይማኖት ጥያቄ አናነግብም።
ጉዳዩን ለመንግሥት ከማሳወቅ ጎን ለጎን ከከንቲባ ጽሕፈት ቤትም ተፈቅዶልን ወደፖሊስ ደብዳቤ ተጽፎልናል።በመሆኑም አስፈላጊው ጥበቃ ይደረግልናል ማለት ነው።እኛም ጨዋነት የተሞላበት ሰልፍ እናካሂዳለን የሚል እምነት አለኝ።እንዲያውም በሰላማዊ ሰልፍ ሐሳብን ሥነ ምግባር በተሞላበት ሁኔታ እንዴት መግለጽ እንደሚቻል ሌላውም ከእኛ ይማራል ብለንም እናስባለን።የሰላማዊ ሰልፍ መሪ ሐሳብ ‹‹ለሠራተኛው ጥያቄ ምላሽ፤ ውይይት መፍትሔ›› ነው የሚል ነው።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ እጅግ አመሰግናለሁ።
አቶ ካሳሁን፡- እኔም አመሰግናለሁ።የኢትዮጵያ ሠራተኞችን ለዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን እንኳን አደረሳችሁ ማለት እወዳለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 21/2015