
ሃሳብና ጭንቀት የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ናቸው። ማንኛውም ጤናማ የሆነ ሰው በሚገጥሙት የተለያዩ ችግሮች ምክንያት ያስባል፤ ይጨነቃል። ልዩነቱ ግን ሁሉም ሰው እኩል አያስብም፤ እኩል አይጨነቀም። አንዳንዱ አብዝቶ ይጨነቃል። ሌላው ደግሞ ብዙ አይጨነቅም። አንዱ ከመጠን በላይ ሃሳብ ይገባዋል። ሌላው ብዙ አያስብም። ስለዚህ ሀሳብና ጭንቀት እንደየሰው ባህሪ፣ ችግሮችን የመጋፈጥና ተቀብሎ የማስተናገድ አቅም ይወሰናል። ምንም እንኳን ሃሳብና ጭንቀት የሰዎች ባህሪ ቢሆንም ታዲያ ‹‹ሲበዛ በሽታ ነው›› ይላሉ የአእምሮ ህክምና ባለሞያዎች። ስለሆነም አብዝቶ ማሰብንና መጨነቅን እንዴት ማቆም ይቻላል?
አብዝቶ ማሰብና መጨነቅ የብዙ ሰዎች ችግር ነው። ሰዎች ነብስ ካወቁ ጀምሮ እስከ ህይወታቸው ፍፃሜ ድረስ ማሰብና መጨነቅ እንደጥላ የሚከተላቸው ባህሪ ነው። መጠኑ ይለያይ እንጂ አብዝቶ የማያስብና የማይጨነቅ ሰው የለም። ማሰብ መልካም ነገር ነው፤ ህይወትንም ይቀይራል። ሲበዛ ነው መጥፎነቱ። ማሰብ ከበዛ እንቅልፍ የሚባል ነገር የለም። በዚህ ምክንያት አንዳንዴ ሰዎች የሚችሉትን ሁሉ መስራት አይችሉም። ወይም ብዙ ከማሰባቸው የተነሳ ለመስራት አቅም ያንሳቸዋል። ሲያስቡ ግዜው ይሄድባቸዋል።
ሌላ ግዜ ደግሞ ሰዎች ተመሳሳይ ብዙ ሃሳቦችን አስበው ይደክማቸዋል። ሃሳባቸው ወይ የትናንት ትዝታ ነው፤ አልያም ደግሞ ቁጭትና የሚያጨንቃቸው ጉዳይ ነው። አንዳንዴ ምን እንደሚያስቡ ሁሉ አያውቁትም። ግን ሃሳበቸው ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን እየተሻማባቸው ነው። ከሰው በታችም እያደረጋቸው ነው። ጭንቀታምም እያደረጋቸው ነው። ምን ይሻላል ታዲያ?
በዚህ አለም ከፍተኛ የስኬት ደረጃ ላይ የደረሱ የሃይማኖት ወይ የቢዝነስ ሰዎች ወይም የምናከብራቸው ሰዎች ብዙ ግዜ የሚያስቡት በፕሮግራም ነው። ስራ እየሰሩ ከሆነ መቶ በመቶ ስራው ላይ ብቻ ነው ትኩረታቸው። ከቤተሰባቸው ጋር ከሆኑም መቶ በመቶ እዛ ቦታ ላይ ናቸው። ቅፅበቱ ላይ ነው የሚያተኩሩት። ማሰብ ሲፈልጉ ደግሞ ቁጭ ብለው ነው። እኛ የከበደን እሱ ነው። በምንፈልገው ሰአት አይደለም የምናስበው።
ስራ እየሰራን ሃሳብ አለ። የምንፈልገውን እያደረግን ሃሳብ አለ። ልንተኛ ስንል ሀሳብ አለ። አስቡት እንግዲህ ሃሳባችሁን መቆጣጠር ብትችሉ ተአምር መፍጠር ትችላላችሁ። ብዙ ነገር በህይታችሁ ትቀይራላችሁ። ሀሳባችሁን ተቆጣራችሁ ህይወታችሁን መቀየር የምትችሉባቸው በጣም ቀላል የሆኑ ሳይንሳዊ መፍትሄዎች አሉ።
1ኛ. ራስን ማድመጥ አንዳንዴ ምን እንደምታስብ እንኳን አታውቀውም። እንደውም አንዳንድ ሰው በጣም ሃሳብ ውስጥ ይሰምጥና የሚነቃው ወይ ስልኩ ሲጠራ ነው፤ ወይ ደግሞ ‹‹እንዴ አንተ የት ሄድክ በሀሳብ›› ሲባል ነው። ከዛም ምን እያሰብክ ነው ሲባል ምን እንደሆነ አያውቀውም። ስለዚህ አሁን ራስህን ለማድመጥ ሞክር። ምንድን ነው የምታስበው? ልክ ስታስብ ንቃ። የሆነ ጭንቀትና ሃሳብ ውስጥ ስትገባ ‹‹አሁን እያሰብኩ ነው›› በል። የሆነ ሰው መጥቶ እስኪቀሰቅስህ ድረስ አትጠብቅ።
በመቀጠል ንቃና ምንድን ነው እያሳሳበኝ ያለው ነገር የሚለውን ለይተህ አውጣው። በርግጠኝነት በጣም አብዝተህ የምታስባቸው ነገሮች ከሁለትና ሶስት ጉዳዮች አይበልጡም። ወይ ኖሮ ነው፣ ወይ ትዳር ነው፣ ወይ ስራ ነው፣ ወይ ትምህርት ነው፣ ወይ ቢዝነስ ነው፣ ወይ ገንዘብ ነው፣ ወይ የፍቅር ግንኙነት ነው። ከነዚህ አይዘልም። ስለሆነም ስለምን እንደምታስብ ነቃ ብለህ ለማሰብ ሞክር። እንደዚህ የማድረግ ዓላማው ጫፉን ለመያዝ ነው። ስለምን እያሰብክ እንደሆነ ለማወቅ ነው። ያስጨነቀህን ጉዳይ ለይቶ ለማወቅ ነው። ከጭንቀትና አብዝቶ ከማሰብ መውጣት ከፈለክ ራስህን አድምጠውና ልክ ሀሳብ ውስጥ ስትገባ ነቃ ለማለት ሞክረህ ‹‹ይህን እያሰብኩ ነበር›› በል።
2ኛ. አምስት መፍትሔዎችን ፃፍ
ምን እንደሚያሳስብህ ማወቅ ከጀመርክ አሁን ወረቀት ላይ ማሰብ መጀመር አለብህ። ወረቀት ላይ የሚያስቡ ሰዎች ሃሳባቸውን መቆጣጠር ይችላሉ። ስለዚህ ይሄ ችግር በጣም እያሳሰበኝ ነው ብለህ ትፅፍና ወደአእምሮህ የሚመጡትን መፍትሄዎች መዘርዘር ጀምር። አምስት መፍትሄዎችን ፃፍ። ለምን መሰለህ አእምሮህ ትኩረቱን ከችግሩ ላይ አንስቶ ወደመፍትሄው መምጣት አለበት። ስለመፍትሄው ማሰብ አለብህ። ስለጨለማው አብዝቶ ማሰብ ብርሃን አይሰጥህም። በችግሩ ላይ ግዜ አታጥፋ።
አየህ በዚህ ምድር ሁለት አይነት ሰዎች አሉ። ለምሳሌ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ኑሮ ተወደደ ተብሎ ሲነገራቸው ‹‹አቤት! አቤት! ይሄኔ ዘይቱን ደብቀውት ነው፤ ሊገሉን ነው፤ እንደው ምን አደረግናቸው ሊያስርቡን ነው›› ይላሉ። ችግሩ ላይ ይራቀቁበታል። አብዝተው ስለችግሩ ያስባሉ። ሁለተኞቹ ግን ኑሮ ተወደደ ሲባልና ችግሩን ሲሰሙ ‹‹ምን ይሻላል ይባስ ሳይወደድ እቃውን ቶሎ ልግዛ እንዴ፤ ወይስ ገቢዬን ላሳድግ?›› ይላሉ። ወደ መፍትሄው ይገባሉ። ስለዚህ አንተ የትኛው ላይ ነህ ነው ጥያቄው። ችግሩ ላይ ነው ጊዜህን የምታጠፋው ወይስ መፍትሄው ላይ? የመፍትሄ ሰው መሆን አለብህ።
3ኛ.ጥድፊያውን አቁም
ከጊዜ ጋር አትታገል። ከጊዜ ጋር ስለምትታገል ነው አብዝተህ የምታስበው፤ የምትጨነቀው። ለምሳሌ ፈተና ክፍል ውስጥ አስተማሪው ‹‹አሁን አስር ደቂቃ ነው የቀራችሁ ፈጠን ብላችሁ ሰርታችሁ የፈተና ወረቀታችሁን እየሰጣችሁ ውጡ›› ሲል ትደነግጣለህ። ምክንያቱም ያለህ አስር ደቂቃ ቢሆንም አንተ የቀረህ ብዙ ጥያቄ ስለሆነ ነው። ስለዚህ ትደናበራለህ። ጥድፊያ ውስጥ ትገባለህ። ሁሉንም ለመመለስ ስትል የምታውቀው ሁሉ ይጠፋብሃል።
አንዳንዴ አንተ የምታስበው ነገር በምትፈልገው ፍጥነት አለመሳካቱ አብዝተህ እንድታስብ ያደርግሃል። አንዳንድ ሰው እኔ በሃያ አምስት አመቴ ጥሩ ቢዝነስ ገምብቼ ጥሩ ገቢ ይኖረኛል ይላል። ልክ ሀያ አምስት አመቱን ሲያከብር እንኳን ቢዝነስ ሊገነባ ተቀጥሮ እንኳን እየሰራ አይደለም። እርሱን የሚቀጥረው ሰው እንኳን የለም። ግራ ይገባዋል። በጣም ይጨነቃል።
ሁላችንም የሆነ ነገር እንፈልግና በምንፈልገው ፍጥነት ካልተሳካ አብዝተን እናስባለን፤ እንጨነቃለን። የጭንቀታችን ጉዳይ ጥድፊያ ነው። ህይወት ፎቅ ይመስል ስለሊፍት እናስባለን። አጭር መንገዶችን እንፈልጋለን። ይሄኔ ተረጋግተንና እጃችን ላይ ያለውን ነገር አስተካክለን ብንጓዝ ነገሮች ቶሎ ተስተካክለው በምንፈልገው ፍጥነት ልንደርስ እንችላለን። ግን ሁሌም ጥድፊያ ላይ ነን። ስለዚህ ወዳጄ ከግዜ ጋር አትወዳደር። የፈጀውን ይፍጅ እንጂ እኔ በሂደትም ቢሆን የምፈልግበት ደረጃ እደርሳለሁ በል። አየህ ትእግስት ማለት የምትችለውን ሁሉ እያደረክ የሚሮጠውን ግዜ ማሳለፍ መቻል ነው።
4ኛ.ለማሰቢያ የሚሆን ጊዜ መድብ
በዚህ ሰአት ለሃያና ሰላሳ ደቂቃ አስባለሁ በልና ፕሮግራም ያዝ። ልክ ያ ሰአት ሲደርስ አላርም ሙላ። ከዛ ማሰብ ጀምር። የባጥ የቆጡን የፈለከውን አስብ። ከዛ አላርሙ ሰላሳ ደቂቃ ሞልቶ ሲጮህ ወደስራህ ተመለስ። አሁን ለሀሳብህ ቦታ ሰጥተኸዋል። ስለዚህ በጣም ወሳኝ ስራ እየሰራህ ሃሳብ አይመጣብህም። አንዳንድ ጊዜ እኮ ለማሰቢያ የሚሆን ጊዜ ስላልመደብክ ወሳኝ ሰአት ላይ ሀሳብና ጭንቀት ይመጣል። ልትተኛ ስትል ሃሳቦች ይመጡና እንቅልፍ አይወስድህም። በጣም ወሳኝ ሰዓት ላይ ስራ ልትሰራ ስትል ሃሳብ ይመጣብሃል።
አሁን ግን ለሀሳብህ ጊዜ መድበህለታል። እንደውም የሜታኮግኒቲቭ ቴራፒስቶች ምን ይላሉ የሰው ልጅ ሃሳቡን መቆጣጠር ይችላል። ለምሳሌ ስልክህ ሲጠራ ያንን ጥሪ መቀበል ካልፈለክ እያየኸው ዝም ማለት ትችላለህ። ከዛ ጠርቶ ማቆሙ አይቀርም። አይምሮህ ውስጥም እንደዛ ነው። ሃሳቡ ይመጣል፤ ይጠራል። ስለዚህ ያን ሃሳብ አብዝተህ ማሰብ ከፈለክ እንደስልኩ ታነሳዋለህ። ካልፈለክ ዝም ትልዋለህ፤ታሳልፈዋለህ። ወይ ቀጠሮ ትይዝለታልህ። ስለዚህ ይህ ነው ሃሳብን መቆጣጠር ማለት። ለማሰብ ጊዜ መመደብ በጣም የሚገርም መፍትሄ ነው። ጭንቀትህንና አብዝቶ ማሰብህን ታቆማለህ።
5ኛ.ትንንሽ ሃሳቦችን አስቀይስ
ትንንሽ ሃሳቦች ሁሌም ትንንሽ ናቸው። ነገር ግን የትልቁን ሃሳብ ቦታ ይይዛሉ። አንዳንዴ በጣም ትንንሽ የሆኑ ሃሳቦች አይምሮህን ይቆጣጠሩታል። ምንም ስለማይጠቅምህ ሰው አብዝተህ ትጨነቃለህ። ወይ ደግሞ ከሰዎች ጋር ራስህን እያወዳደርክ እያሰብክ ረጅም ሰአታትን ትፈጃለህ። እንደነዚህ አይነት ሃሳቦች በጣም ትንንሽ ናቸው። ሆኖም አእምሮህ ላይ ትልቅ ቦታ ይይዛሉ። ጊዜህን ይሻማሉ። ጉልበትህን ይመጡታል። እንደነዚህ አይነት ሀሳቦችን ማስቀየስ ነው ያለብህ። መሸሽ ነው ያለብህ። ማለትም በድርጊት/በተግባራዊ ነገር መሸሽ/ አለብህ።
ለምሳሌ እነዚህ ትንንሽ ሃሳቦች ወደአእምሮህ ሲመጡብህ ተንስና ቤትህን አስተካክል።አልጋህን አንጥፍ። ቤትህን አፀዳዳ። ወይ ደግሞ ስፖርት ስራ። የእግር ጉዞ አድርግ። አጠገብህ ያለን ህፃን አንሳና አጫውት። ያን ሃሳብ በአንድ ጊዜ ትረሳዋለህ። ትናንሽ ሃሳቦች ካንተ መራቅ ይጀምራሉ። ነገር ግን ትልልቅ ሃሳቦችን መሸሽ የለብህም። ለትልልቅ ሃሳቦችን ሁልጊዜም ቁጭ ብለህ መፍትሄ ነው የምትፅፈው። ስለዚህ ትንንሽ ሃሳቦች ሲመጡብህ ‹‹አረ እኔ ይህን ማሰብ ለእኔ አይመጥንም፤ በጣም የወረደ ሃሳብ እኮ ነው›› ማለት አለብህ።
አንዳንዴ ስራ ስለፈታህ ይሆናል እንደነዚህ አይነት ትንንሽ ሃሳቦች የአዕይምሮህን ቦታ የሚያጣብቡት። ‹‹ስራ የፈታ ሰው የሴጣን መጫወቻ ይሆናል›› እንደሚባለው ስራ ስትፈታ የማይረቡ ሃሳቦች አእምሮህን ይሞሉታል። ስለዚህ ወደ ስራህ ተመለስ። የሆነ ስራ መስራት ጀምር። ያኔ ትንንሽ ሃሳቦችን ታስቀይሳቸዋለህ።
6ኛ. በእምነትህ ጠንክር
እንዴት ሰው ከፍሎ ይሸከማል በነፃ ማሸከም እየቻለ? አንተ ሃሳብህንና ጭንቀትህን ትልቁ ሸክምህን ለፈጣሪህ መስጠት እየቻልክ ለምን አንተ ትሸከማለህ? አንተ መቆጣጠር የምትችለው ነገር ብቻ ላይ አተኩር። መቆጣጠር የማትችላቸውን፣ የማትጨብጣቸውንና የማትታገላቸውን ነገሮች ለፈጣሪህ አስረክብ። አየህ አንዳንድ ግዜ እኮ አቅምን ማወቅ ጥሩ ነው። ቅልል ይልሃል። እኔ ይህን እቆጣጠራለሁ፤ ይህንን ግን አልቆጣጠርም ለፈጣሪ እሰጠዋለሁ በል።
ሁኔታዎችን አንተ አትቆጣጠራቸውም። የሀገሪቷን ሁኔታ፣ የሰዎችን እንቅስቃሴ፣ ኢኮኖሚውን፣ አንተ አትቆጣጠረውም። የሰዎችን ፀባይ አንተ መቀየር አትችልም። አንተ መቀየር ምትችለው ነገር ላይ ብቻ አተኩር። የማትችለውን ለፈጣሪ አስረክብ። ለባለቤቱ ስጠው። ታዲያ በጣም ያስቸገሩኝን ከባድ ችግሮች ለፈጣሪዬ እንዴት ላስረክበው? ልትል ትችላለህ። ወረቀት አውጣ። ያስጨነቁህንና ከአቅምህ በላይ የሆኑ ችግሮችን ዘርዝራቸው። ፈጣሪ ሆይ እነዚህን ችግሮች ለአንተ አስረክቤያለሁ በል።
የስራ ውል እንደምትገባ ሁሉ ከፈጣሪህ ጋር ውል ግባ። ትልቁ ችግርህን ከፈጣሪህ ጋር ንኡስ ኮንትራት አድርገው። ያኔ ቅልል ይልሃል። የሆነ ስሜት ይሰማሃል። አንበው ከአእምሮህ ወደወረቀቱ፤ ከወረቀቱ ወደፈጣሪህ ያ ችግር እንደሄደ ይሰማሃል። ስለዚህ አንተ የማትቆጣጠራቸውን ነገሮች አሳልፈህ ለፈጣሪህ ሰጥተሃል ማለት ነው። ህይወት ነፃ ታደርግሃለች። መጨነቅና አብዝተህ ማሰብ ታቆማለህ።
አንዳንዴ በጣም ለፍተህ ሰርተህ ውጤቱን መቆጣጠር አትችልም። ስለዚህ ውጤቱን ለፈጣሪህ አስረክበው። አንተ መዝራት ነው ስራህ። የሚያበቅለው ፈጣሪህ ነው። ለባለቤቱ አስረክብ። ነገን አትቆጣጠረውም። ሰዎችን አትቆጣጠርም። ሁኔታን መቆጣጠር አትችልም። አስረክበው ለፈጣሪህ። አይታወቅህም እንጂ ፈጣሪህ እንደሰው በግልፅ ስለማይሰራ ነው እንጂ ያን ችግርህን በስውር፤ በድብቅ እየፈታው ሊሆን ይችላል። አንተ ስለማታይ ነው። ስለዚህ ችግርህን ለፈጣሪህ አሳልፈህ ስጥ።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2015