የወደፊት ከተሞች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በዳታ ወይም መረጃ ትንተና ላይ ተመስርቶ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆን ለማድረግ ስልጡን ከተማ ወይም “ስማርት ሲቲ” የተሰኘ ከተሞችን የማዘመን ሀሳብ በተለያዩ ሀገራት በተግባር እየተሞከረ ይገኛል፡፡ የስልጡን ከተማ ወይም ስማርት ሲቲ ሀሳብ የሰው ልጆችን ሀሳቦች በማሽን በመተግበር ሰዎች ያለባቸውን ውስንነት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ የማበጀቱ አንዱ አካል ነው፡፡
በዓለማችን ከሚኖረው ህዝብ ግማሽ የሚሆነው በከተማ እንደሚኖር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የከተማ ነዋሪ ህዝብ ቁጥር እያደገ ስለመምጣቱም ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የከተማ ህይወት በራሱ በርካታ ውስብስብ ሂደቶች ያሉት በመሆኑ እንዲሁም በነዋሪው ቁጥር መጨመር ሳቢያ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይስተዋላሉ፡፡ የነዋሪው ጥግግት እና የትራፊክ መጨናነቅ፣ የአየር ብክለት እየጨመረ መምጣት፤ የውሃና የሀይል ፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም፣ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱት ናቸው፡፡ ስልጡን ከተማም እነዚህን ፈተናዎች ቀላል የማድረግ ጽንሰ ሀሳብ ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ለምሳሌ በስልጡን ከተማ ጽንሰ ሀሳብ የከተማ መብራት ያለ ምሰሶ አገልግሎት እንዲሰጥ ማስቻል፣ የብሮድ ባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት፣ ሹፌር አልባ ተሽከርካሪዎች በመጠቀም የትራፊክ አደጋን መቀነስ፣ ድሮን እና ሮቦቶችን የህዝብ አገልጋይ እንዲሆኑ ማድረግ፣ የእሳት አደጋ መከላከል ስራን በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ የታገዘ እንዲሆን ማድረግ ባደጉት ሀገራት በስልጡን ከተማ ትግበራ ሙከራ ላይ ካሉ ሀሳቦች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
አንድ ከተማ ስልጡን ከተማ (ስማርት ሲቲ) ይሁን ከተባለ በከተማው ውስጥ ያሉ እንቅስቃሴዎችን የሚገነዘቡና ዳታ የሚሰበስቡ የኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂዎችን በየቦታው ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ስለትራፊክ ቁጥጥሩ፣ ስለአየር ብክለት እና ስለሌሎች ጉዳዮች የተፈለገውን መረጃ ለመሰብሰብ ያስችላል፡፡ ስለዚህ ግዙፍ መረጃዎችን መሰብሰቡ ብቻ ግብ አይደለም፡፡ ይህንን ዳታ በመሰብሰብና በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመተንተን መፍትሄ ማፍለቅ ይጀመራል፡፡ ያኔ የስልጡን ከተማ ጽንሰ ሀሳብ ተግባር ላይ ዋለ ማለት ነው፡፡
በዚህ መንገድ በዓለማችን በርካታ ከተሞች ለችግሮቻቸው መፍትሄ እየተበጀላቸው ነው፡፡ ባደጉት ሀገራት በሚገኙ በአንዳንድ ከተሞች አረንጓዴ ስፍራዎች በተገጠመላቸው ሴንሰሮች ውሃ እንዲጠጡ ይደረጋል፤ የቆሻሻ ገንዳዎችም ገና ከመሙላታቸው ይነሳሉ፡፡ በአንዳንድ ከተሞች የተሸከርካሪዎች እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ክትትል የሚደረግላቸው በሰው ሰራሽ አስተውሎት ነው፡፡ በአንዳንድ ከተሞች ደግሞ የሮቦት ፖሊሶች የከተማ ጥበቃ ስራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡ ከተሞች ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ተጠቅመው የአገልግሎት አሰጣጥ ግልፅነትን በማስፈን ሙስናን መከላከል እየቻሉ ስለመሆናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ጁኒፐር የተሰኘ በዘርፉ ጥናት የሚያደርግ ተቋም እንዳሳወቀው፤ በስልጡን ከተማ መረጃ መሰብሰብ የሁልጊዜም ስራ ነው፡፡ የሚሰበሰቡ መረጃዎችን ሰንዶና ተንትኖ መፍትሄ ለማምጣት ለሚሰሩ ኩባንያዎች በሀብት ፈጠራና በስራ እድል ፈጠራ አይነተኛ ሚና እየተጨወተ ይገኛል፡፡ እንደ ጥናት ተቋሙ ትንበያ ወደፊት ገበያ ይደራላቸዋል ተብለው የሚጠበቁት በአብዛኛው ግዙፍ ዳታ በመሰነድና በመተንተን ትልቅ ሚና የሚጫወቱት ስልተቀመር / አልጎሪዝም/ ባለቤት የሆኑ ተቋማት ናቸው፡፡
በሀገራችን ከተሞች ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት አለመዘርጋቱ፣ ከተሞቹ በፕላን እንዲመሩ ምቹ ሁኔታዎች አለመፈጠራቸውና በከተሞች ዕድገት ዙሪያ ወጥ ግንዛቤ አለመኖር በዜጎች ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር እየፈጠረ ስለመሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እንደ መፍትሔም በሀገሪቱ በተመረጡ ከተሞች ከየሀገራቱ ስልጡንና ተመራጭ ከተሞች ልምድን በመቀመር የስልጡን ከተማ የ“ስማርት ሲቲ” ጽንስ ሃሳብን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራበት ይገኛል፡፡
በከተማና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኢትዮጵያ በዴቻ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያም ከተሞችን ስልጡን ለማድረግ ስትራቴጂ ተነድፏል፡፡ ይህ ስትራቴጂ በቅድሚያ ስለ ስልጡን ከተማ ጽንሰ ሀሳብ በአግባቡ ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ አስቀምጧል፡፡ በተለይም ለከተሞች አመራሮች ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ ያስቀመጠ ነው፡፡ የማስተዋወቅ እና ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ ከተሰራ በኋላ የሚመራበትን ስትራቴጂ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግም በግልጽ አስፍሯል፡፡
ይህንን ስራ ለመስራት ስትራቴጂውን በተለያዩ አካላት የማስተቸት እና ግብዓት የማሰባሰብ ስራ የተሰራበት አውደ ጥናት በቅርቡ በአዳማ ከተማ መካሄዱን የጠቆሙት አቶ ኢትዮጵያ፤ መድረኩም በሚኒስቴር መ/ቤቱ የከተማ ፕላንና አከታተም መሪ ስራ አስፈጻሚ እና በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ስራ አስፈጻሚ በትብብር የተዘጋጀ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በመድረኩ ላይም የክልል አመራሮች፣ የከተማ ስራ አስኪያጆችና የፌዴራል ተቋማት ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በርካታ የከተማ አመራሮች ከሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች፣ የከተማ አመራሮች፣ ከክልሎች ቢሮ ሀላፊዎች ጀምሮ እስከ ከተማ ከንቲባና፣ ከተማ ስራ አስኪያጅ ድረስ ያሉ አካላት በተገኙበት ስትራቴጂው ተተችቷል፡፡ ስትራቴጂው ከተተቸ በኋላ፣ የተለያዩ ግብዓቶችን በማሰባሰብና እንዲዳብር በማድረግ ከተሞቹ ላይ በቀጣይ መሰራት የሚገባቸው ነገሮችን አመላክቶ ወደ ስራ ይገባል ብለዋል፡፡
ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር የሀገራችን የክትመት ምጣኔ ዝቅተኛ ቢሆንም፤ የክትመቱ ፍጥነት ግን ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ ኢትዮጵያ፣ የክትመት ፍጥነት ከፍተኛ መሆን ማለት ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረገው የሰዎች ፍልሰት የታጀበ ፈጣን የከተሞች መስፋፋት አለ ማለት ነው ይላሉ፡፡ ይህንን ሁኔታ በስልጡን ከተማ ጽንሰ የከተሜነት ምጣኔ ማስተካከል ካልተቻለ ከፍተኛ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን ሊፈጥር ይችላል፡፡ ከተሞች የሀይል አቅርቦት ችግር፣ የትራፊክ መጨናነቅ፣ ከቆሻሻ አያያዝ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ችግሮች እንዲሁም የደህንነት ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን ማስተካከል ትልቅ የከተማ ተግዳሮቶች ናቸው ብለዋል፡፡
የከተማ ህዝብ ቁጥር መብዛት ከተጠቀሙበት ዕድል ካልተጠቀሙበት ደግሞ ስጋት መሆኑን ገልጸው፣ የከተማ ህዝብ ምጣኔ ዕድገትን ስልጡን ከተሞችን በመፍጠርና ምቹ የመኖሪያ አካባቢ እንዲሆኑ በማድረግ የከተማ ነዋሪውን የኑሮ ደረጃ ማሻሻልና ፍላጎቱን ማርካት ይቻላል ብለዋል፡፡
ስልጡን ከተማን ለመገንባት የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ የፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ አቅምን የሚጠይቅ መሆኑንም ጠቅሰው፣ በአንድ ጊዜ ተሰርቶ የሚያልቅ እንዳልሆነና የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ብዙ መስራት እንዳለበት እንዲሁም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በማያያዝ የስልጡን ከተማ ምሰሶዎች ናቸው በማለት የገለጿቸው ስልጡን ኢኮኖሚ፣ አስተዳደር፣ ሞቢሊቲ፣ አካባቢ፣ ነዋሪ እና ኑሮ ወሳኝ መሆናቸውን አመልክተው፣ ከተሞችን ጽዱ፣ ውብና ማራኪ እንዲሁም ለኑሮና ለስራ ምቹ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሠራር ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነና የሁሉንም ተቋማት የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ኢትዮጵያ ማብራሪያ፤ እነዚህን ችግሮች ስልጡን በሆነው መንገድ ማስተካከል ሲቻል ብቻ ነው የከተሜነትን ምጣኔና የከተማን ህብረተሰብ ከችግር መታደግ የሚቻለው፡፡ ይህንን ደግሞ የተለያዩ ሀገሮች ተግባራዊ አድርገውት ውጤታማ ስራዎችን እየሰሩ ናቸው፡፡ ሀገራችን ዘመናዊ ስልጡን ከተማን ለመፍጠር ከዓለም ወደኋላ የቀረች መሆኗን ጠቅሰው፣ ሌሎች ሀገራት የፈጸሙትን ስህተት ባለመድገም ፈጥኖ የሰለጠነ ከተማን ለመፍጠር ዕድል የሚሰጥ ሁኔታ እንዳለም አመላክተዋል፡፡
ይህም ማለት ከተሞችን በፕላን ከመምራት ጀምሮ ዘመናዊ የኢንፎርሜሸን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶችን መዘርጋት፣ ከተሞች ስልጡን አገልግሎቶችን በማቅረብ ለኑሮና ለስራ ምቹ እንዲሆኑ ማድረግ ስልጡን ከተማ ተግባራዊ ማድረግ የሚቻልበት አንዱ ትልቁ እሳቤ ነው፡፡
አንድ ስልጡን ከተማ ከተማውን የሚመራበት፣ የሚያስተዳድርበት፣ ነዋሪዎች የሚፈልጉትን አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ የሚያደርግበት በቂ የሆነ የራሱ እቅድ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ የከተማ ነዋሪን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን፤ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች እና የአገልግሎት አቅራቢ ተቋማትን ያደራጃል፡፡ በዚህ ረገድ እንደ ሀገራችን ከተሞችም ብዙም የተሰሩ ስራዎች የሉም ብለዋል፡፡
የሀገራችንን ከተሞች ወደ ስልጡን ከተማነት ለማሸጋገር የሚደረገው ጥረት በተለያዩ ተግዳሮቶች የተከበበ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ አንደኛው ተግዳሮት የግንዛቤ እጥረት ነው ይላሉ፡፡ ስልጡን ከተማ ሲባል ቴክኖሎጂ የተሟላለት ከተማ ብቻ ተደርጎ የማየት ሁኔታ አለ፤ ይህ ግን ትክክለኛ ግንዛቤ አይደለም ምክንያቱም ስማርት ወይም ስልጡን ቴክኖሎጂ ብቻ አይደለም ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ኢትዮጵያ ማብራሪያ፤ አገልግሎት አሰጣጥ፣ አጠቃላይ በከተሞች ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን የመምራት፣ የመግራት እና የማስተካከል ሂደቶችን ያካተተ ነው፡፡ ስለሆነም እነዚህ ነገሮች እውን እንዲሆኑ እንቅፋት እየሆኑ ያሉ ተግዳሮቶች ይፈታሉ ተብሎ የታሰበው ከዘርፉ ተቋማት ባሻገር ባለድርሻ ተቋማት አሉ፡፡ እነዚህ ባለድርሻ ተቋማት በዋናነት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አጀንሲ፣ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ማዕከል፣ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንን ጨምሮ ሁሉም የስልጡን ከተማ ስትራቴጂ ትግበራ ባለድርሻ አካላት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ስራው የሚመለከታቸው ናቸው፡፡
የከተሞችን አገልግሎት ስልጡን ሲደረግ ከላይ የተጠቀሱ ተቋማት ሁሉ የጉዳዩ ባለቤት ሆነው የሚሰሩ መሆናቸውን በመጠቆም፤ በመሆኑም እነዚህ አካላት ባለድርሻ በመሆናቸው ዙሪያ በቂ ግንዛቤ አልነበረም፡፡ በመሆኑም የጋራ የሆነ አረዳድ ይዞ ወደ ስራ ለመግባት ታስቧል፡፡ የግንዛቤ ክፍተት የማጥራት ስራ ይሰራል፡፡ ግንዛቤ በአንድ ጀንበር አይፈጠርም፡፡ ግንዛቤ የማስጨበጥ እና ስትራቴጂውን ወደ ስራ የማስገባት ስራ እየተሰራ ይቀጥላል፡፡
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚያብራሩት፤ ስልጡን ከተማን እውን ለማድረግ የነቃ አመራር መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ስለ ቴክኖሎጂ በቂ እውቀት ያለው አመራር ስልጡን ከተሞችን እውን ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት ሚናው የላቀ ነው፡፡
በቅርቡ በአዳማ በተካሄደው አውደ ጥናት የመድረኩ ተሳታፊዎች ከተሞችን ወደ ስልጡን ከተማ ለማሸጋገር በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ውይይቶችን ከማከሄዳቸው ባሻገር የአዳማ ከተማን የስልጡን ከተማ አተገባበር በአካል ተገኝተው መጎብኘታቸውን የጠቆሙት አቶ ኢትዮጵያ፤ የቀረበውን ሰነድ እና የተደረገውን የአካል ምልከታ መነሻ በማድረግ በውይይት መድረኩ ላይ የስትራቴጂ ጥናት ሰነዱን ለማዳበር የሚያስችሉ ግብአቶች ተገኝተውበታል ብለዋል፡፡ የስልጡን ከተማ ትግበራን በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለማስጀመር የሚያስችል መነቃቃትም የተፈጠረበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የስልጡን ከተማ ጽንሰ ሀሳብ የከተሞች አገልግሎትን በማቀላጠፍ ረገድ ያለው ትልቅ ድርሻ ቢሆንም የመረጃ ምንተፋ ትልቁ ተጋዳሮቱ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ስልጡን ከተማ ግንባታ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሀገራት ይህንን ችግር ለመቅረፍ በሚያችሉ መፍትሄዎች ላይ ጭምር ትኩረት አድርገው ይሰራሉ፡፡ ሀገራችንም በስልጡን ከተማ ግንባታ ላይ ከምታደርገው ርብርብ ጎን ለጎን ስልጡን ከተማ ሲተገበር ሊፈጸም የሚችለውን የመረጃ ምንተፋ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል አሰራርን ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ልታደርግ ይገባል፡፡
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2015