ረዳት ኮሚሽነር ጄነራል ደራርቱ ቱሉ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዘዳንት ሆና ተመረጠች። የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በፕሬዚዳንትነት እየመራች የምትገኘው የቀድሞዋ የረጅም ርቀት ኮከብ አትሌት ደራርቱ በዛምቢያ ሉሳካ ከትናንት በስቲያ በተካሄደው የኮንፌዴሬሽን ኦፍ አፍሪካ አትሌቲክስ ኮንግረስ የአፍሪካ አትሌቲክስን በምክትል ፕሬዚዳንትነት እንድትመራ ካውንስሉ በሙሉ ድምፅ እንደመረጣት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ካሜሮናዊው ሃማድ ካልካባ የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፤ አራት ምክትሎች አሏቸው። ከነዚህ መካከል ሶስቱ ወንዶች ሲሆኑ ደራርቱ ብቸኛዋ እንስት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆናለች። ለቀጣዩ አራት አመታትም በዚህ ማዕረግ የአህጉሪቱን አትሌቲክስ ታገለግላለች።
“ሀገሬን ወክዬ በመመረጤ ደስ ብሎኛል፤ ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ አመራርነት በአፍሪካም ሆነ በአለም ከዚህ የበለጠ መወከል ይገባታል፤ አመራሮቻችንና ባለሙያዎቻችን ከፌዴሬሽናችን ባለፈ በአህጉራችንና በአለም የአትሌቲክስ ተቋማት ላይ ገብተው እንዲሰሩ ጠንክረን መስራት አለብን፤ በዚህ ኮንፌዴሬሽን የኬኒያው ጃክሰን ቲዊ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሲሆኑ እኔ ምክትል ነኝ፤ ከምስራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያና ኬኒያ በአመራርነት አለን፤ የተጣለብኝን ሀላፊነትና አደራ ለመወጣት ዝግጁ ነኝ” በማለት ደራርቱ ከሹመቱ በኋላ ለጋዜጠኛ ታምሩ አለሙ አስተያየቷን ሰጥታለች።
በአፍሪካ የመጀመሪያውን የአስር ሺ ሜትር የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ እኤአ 1992 ባርሴሎና ላይ በማስመዝገብ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ የሰራችው ደራርቱ ከኢትዮጵያ ባለፈ የአትሌቲክሱ ዘርፍ ላይ በትልቅ የአመራርነት ቦታ ስትሾም ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም።ደራርቱ ከዓመታት በፊት የምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ዞን አምስት ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ተመርጣ እያገለገለች እንደምትገኝ ይታወቃል።
30ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ኮንግረስ እና ካውንስል ስብሰባ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በዛምቢያ ዋና ከተማ ሉሳካ የተካሄደ ሲሆን፤ በዚህ ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እንዲሁም የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅን ምክትል ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ካውንስል አባል በመሆን ተሳታፊ ሆናለች።በተጨማሪም ዶክተር ተስፋዬ አስግዶም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የአፍሪካ ከ18 እና አ20 አመት አትሌቲክስ ቻምፒዮና የኢትዮጵያ ቡድን መሪ፣ አቶ ዮሐንስ እንግዳው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ተወካይ በስፍራው ተገኝተው ስብሰባውን ተካፍለዋል።
ከኮንግረስ ስብሰባው አስቀድሞ የካውንስል ስብሰባ የተካሄደ ሲሆን፤ ኮንግረሱ ሲጀመር የዛምቢያ ስፖርት፣ ባህልና አርት ሚኒስትር፣ የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንት ሎርድ ሳባስቲያን ኮይን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።ጉባኤው ያለፈውን አመት ስብሰባ ቃለ ጉባዔን፣ የስራ አፈጻጸምን፣ የቴክኒካዊና ልማት ሪፖርቶችን አቅርቦ በመመርመር ያጸደቀ ሲሆን የአፍሪካ አትሌቲክስ ልማት ማእከልን (AADC) የስራ እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬንን የውድድር መርሀ ግብር ለጉባኤው አቅርቦ አፈጻጸሙን ተመልክቷል።በማያያዝም የአየር ንብረትና ብክለት ጉዳይን እንዲሁም የሴቶች ኮሚቴ የጾታ ፖሊስን አስመልክቶ ገለፃ ያደረገ ሲሆን በቀጣይ አመት ኮንግረሱ የሚካሄድበትን አገር ምርጫም በማቅረብ አቅጣጫ ሰጥቷል።
ዛምቢያ ጉባዔውን ያስተናገደችው የአፍሪካ የታዳጊና ወጣት አትሌቲክስ ቻምፒዮናን ከማስተናገዳ ማግስት ሲሆን በቻምፒዮናው ኢትዮጵያን የሚወክለው ቡድን ትናንት ማለዳ ወደ ዛምቢያ ተጉዛል።ከ18 እና ከ20 አመት በታች የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ከዛሬ ሚያዝያ 21 – 25/2015 ዓ.ም ጀምሮ ለ5 ተከታታይ ቀናት በዛምቢያ – ኒዶላ ከተማ ለ2ኛ ጊዜ ይካሄዳል።
በዚህ የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን የሚወክለው የታዳጊና የወጣት ብሄራዊ ቡድን ውስጥ 15 ሴቶችና 15 ወንዶች በድምሩ 30 አትሌቶች እና 7 አሰልጣኞች፣ 1 ሐኪምና 1 ማሳጅ ባለሙያ ተካትተዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ እና የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ግርማ ለማ ቡድኑ ሲሸኝ በስፍራው ተገኝተው መልካም እድል በመመኘት አሸኛኘት አድርገዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21 ቀን 2015 ኣ.ም