ለሁለት ዓመታት ያህል የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ይብቃ ተብሎ፣ ሰላማዊ ድርድር ተደርጎ፣ የሰላም እንቅስቃሴዎች ከተጀመሩ እነሆ ከስድስት ወራት በላይ ተጉዘናል። ባለፈው እሁድ ሚያዚያ 15 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ በወዳጅነት አደባባይ ‹‹ጦርነት ይብቃ፤ ሰላምን እናጽና›› በሚል መሪ ሀሳብ በሰሜኑ ጦርነት የነበረውን ደም አፋሳሽ ግጭት በሰላም ለመቋጨት ሚናቸውን ለተወጡ ግለሰቦች የዕውቅና መስጠት መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩም የፌዴራሉ መንግሥትና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት በማያሻማ ቋንቋ አስታወቀዋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ከሳምንታት በፊት ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ አድርገው ነበር። በጦርነቱ ወቅት ስለተሰነዘሩት ሃሳቦች ተጠይቀው የመለሱት መልስ፤ ‹‹የሚታረቀው የተጣላ ባልና ሚስት ነው›› በማለት አብራርተዋል። በርግጥም ያልተጣሉ ባልና ሚስቶችን ለማስታረቅ የሚሄድ ሽማግሌ አይኖርም!።
አዎ! ደቡብ አፍሪካ ድረስ የተካሄደው ጦርነት ስለነበር ነው፤ በጦርነት ወቅት ተገቢ ያልሆኑ ነገሮች ተፈጽመው ስለነበረ ነው። እርቅና ድርድር ያስፈለገው አለመግባባት ተፈጥሮ ስለነበርና ጦርነት ስለተካሄደ ነው። ዛሬ ላይ እነዚያን በጦርነት ወቅት የነበሩ ድርጊቶችን እያመጡ ማሳየት ምን የሚሉት የአገር ፍቅር ነው? በጦርነቱ ወቅት የነበረውን ‹‹እገሌ እንዲህ ብሎ ነበር!›› እያሉ ንግግሮችን ማምጣት እንደገና ወደ ጦርነት እንግባ ለማለት ይሆን?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደግሞ በዕውቅና መድረኩ ላይ እንዲህ ብለው ነበር። ‹‹…ሲታረቁ ከሆድ፣ ሲታጠቡ ከክንድ…፤ እኛ ስንዋጋ ከልባችን ነበር የተዋጋነው፤ ከዛሬ ጀምሮ ግን ከልባችን መታረቅ ይኖርብናል›› ብለዋል።
በጦርነቱ ወቅት ጦርነት ነበርና ብዙ ነገር ተብሏል፤ ብዙ ነገር ተደርጓል። በዚያን ወቅት ሲባል የነበረው ወደ ሰላምና ድርድር መምጣት አለበት ነበር። እነዚያ ወደ ሰላምና ድርድር መምጣት አለበት ይሉ የነበሩት አካላት ግን ዛሬ ላይ ለምን ወደ ሰላምና ድርድር ተመጣ እያሉ ነው። የሰላም እንቅስቃሴዎችን በመቃወም ‹‹እንዲህ ተብሎ ነበር›› ይላሉ። አዎ! ተብሎ እና ተደርጎ ስለነበር ነው አሁን የሰላም መድረኮች እየተዘጋጁ ያሉት!
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አሁንም በዚያው መድረክ ላይ ‹‹ከሸኔ ጋር የሚደረገው ድርድር ከነገ ወዲያ ይጀምራል››ብለው ነበር። በተባለው መሰረት በታንዛኒያ ድርድሩ እንደተጀመረ ከወጡ መረጃዎች ማወቅ ተችሏል። ለጊዜው ስለሁኔታው ዝርዝር መረጃ ባይኖርም ሂደቱ መጀመሩ ግን አሁንም መንግሥት ለሰላም ያለውን ቆራጥነት ያሳያል።
ሰላም ከጦርነት ያላነሰ ድፍረትና ቆራጥነት ይፈልጋል፤ ጀግንነት ይፈልጋል። እንዲያውም ከጦርነት በላይ ሰላም ነው ጀግንነት የሚጠይቅ። ሰላም አርቆ አስተዋይነትን፣ ቆራጥነትን፣ ለትውልድ ማሰብን፣ ከራስ ይልቅ ዜጋን ማስቀደምን ይጠይቃል። ሰላም የሚመጣው የግል በደልን በመተው ለሌሎች በማሰብ ነው። ሰላም የሚመጣው ቂመኝነትን በመተው ለቀጣዩ ትውልድ የተረጋጋች አገር በማስረከብ ነው።
አቶ ጌታቸው ረዳ ለሰላም ጀግና መሆን ይኖርብናል ብለዋል። ለሰላም ጀግና መሆን ማለት ከራስ በላይ ለሌሎች አስቦ ለዜጎች ምቾት መፍጠር ማለት ነው። አንድ ሰው የግል ቂሙን ለመወጣት ብሎ ጥቃት ቢመኝ እያሰበ ያለው ለዜጋው ሳይሆን ለራሱ ብቻ ነው ማለት ነው። እሱ ላለማፈር ሲል ለጊዜያዊ ስሜት በግትር አቋሙ ይቀጥላል ማለት ነው። እንዲህ አይነት ሰው የንፁሃን ዜጎች ሕይወት መተራመስ ደንታ አይሰጠውም፤ የሕጻናትና እናቶች ጎዳና ላይ መውደቅ ደንታ አይሰጠውም። ለእሱ ጀግንነት የሚመስለው የግል በቀሉን መወጣት ብቻ ነው።
ከወታደሮች እንደምንሰማው ጀግንነት ማለት ራስን በድሎ ሌሎችን ማዳን ነው። ለሰላም ዘብ መቆም ደግሞ ማንም ሳይበደል ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበት ነው። ስለዚህ ለሰላም የሚያስብ ሰው እንኳን ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበትን ራሱ ቢበደል እንኳን ለቀጣይ ትውልድ ሲል ዋጋ ከፍሎ ሰላምን ነው የሚያሰፍን።
ልብ እንበል! የሚነታረኩት እና የሚጨቃጨቁት ‹‹አንቂ›› የሚባሉት እና ‹‹ልሂቅ›› የሚባሉት ናቸው። እነዚህ አካላት በሕዝብ ስም ነው የሚነግዱ። የእገሌ ሕዝብ እንዲህ ተበድሏልና ከበደለው አካል ጋር መታረቅ የለበትም ነው የሚሉት። በእነርሱ አስተሳሰብና አመላካከት በደሉ የሚሻረው እንደገና ሲዋጉ ይሆን? የልጅ ልጆቻቸው በሰላም የሚኖሩት የሰው ሕይወትና ንብረት በማውደም ነው?
ልብ ብለን ካስተዋልን እነዚህ አካላት ሰላማዊ እንቅስቃሴን የሚቃወሙት ፈሪ ስለሆኑ ነው። ፈሪ ማለት የግድ ጥይትን ብቻ አይደለም። እንዲህ አደርጋለሁ ብለህ ነበር እየተባሉ የሚቀለድባቸው ስለሚመስላቸው ነው። ከሕዝቡ ይልቅ የራሳቸው ግላዊ የክብርና የቅሌት ነገር ስለሚያሳስባቸው ነው።
አፍ አዳልጦት ‹‹እገሌን እናጠፋለን›› ብሎ የነበረ አንድ የማህበረሰብ አንቂ ወይም ምሁር ወይም ፖለቲከኛ፤ እሱ የተናገረው ከሸፈ እንዳይባል ብቻ ጦርነት ቢቀጥል ይመርጣል። የወደመው ወድሞ ያ አጠፋዋለሁ ያለው አካል ቢጠፋና የልቡ ቢደርስ ይሻለዋል፤ የዜጎች ዘላቂ ትርምስ ውስጥ መግባት ደንታው አይደለም። ለእርሱ ስኬት ማለት በግሉ የተናገረው ነገር ሰምሮ ማየት ብቻ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ሥራው ጠንክሮ መቆስቆስ ነው።
መላው ህዝባችን ይህንን እውነታ በአግባቡ ሊያስተውለው ይገባል ። ለሰላም የሚያደርገውን የትኛውንም እንቅስቃሴ ተቃዋሚና ደጋፊ በመሆን ሳይሆን ሰው በመሆን ብቻ ሊያደርገው ይገባል። እንደ አገር የምንመኛቸው ነገሮች ሁሉ ሊሳኩ የሚችሉት ሰላም ሲኖር ብቻ ነው፤ ለምንም ነገር ዋናው ሰላም መሆኑን መረዳት የፖለቲካ ‹‹ሀ ሁ›› ነው።
የዓለም አገራት መሳለቂያ መሆን ይብቃን! ከጦርነት ጋር በተያያዘም የከፈልናቸው ያልተገቡ ዋጋዎች ከአቅማችን በላይ ናቸው። ይህንን እውነታ በመቀልበስ መንግሥት የጀመረው የሰላም ሂደት ውጤታማ ሆኖ የተረጋጋች እና የበለጸገች ሀገር ለመፍጠር ዜጎች ሁሉ ሰው በመሆናቸው ብቻ የሰላም ሂደቶችን ሊደግፉ ይገባል!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 20/2015