የቮሊቦል ስፖርት በኢትዮጵያ ከ1970 ጀምሮ ተወዳጅና ተዘውታሪ መሆኑ ይነገርለታል። ኢትዮጵያ እስከ 1990ዎቹ በአህጉራዊ ውድድሮች በሴቶችና በወንዶች ብሔራዊ ቡድን በዚሁ ስፖርት ተሳታፊ ነበረች። ነገር ግን ባለፉት በርካታ ዓመታት ስፖርቱ ተቀዛቅዞ ይገኛል። ስፖርቱን በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ግን የተቀዛቀዘውን ስፖርት ለማነቃቃት ጥረቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
ለዚህም ከተሰሩት ስራዎች መካከል ከዓለም አቀፉ የቮሊቦል ፌዴሬሽን የሜዳ ንጣፍ በድጋፍ መገኘቱ ተጠቁሟል። የሜዳ ንጣፉ ግምታዊ ዋጋም ከአራት እስከ ስድስት ሚሊዮን ብር እንደሚያወጣ ተገልጿል። የሜዳ ንጣፉ በቮሊቦል ስፖርት በሚታወቀው ወላይታ ሶዶ ክለብ ሜዳ እየተነጠፈ መሆኑንም የኢትዮጵያ ቮሊቮል ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ ገልፀዋል። መሰል መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት በስፍራው ያለውን አቅም ለመጠቀም እንደሚረዳም ኃላፊው አስረድተዋል። ይህም ለስፖርቱ ማደግ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው አክለዋል።
ኢትዮጵያ ከሶስት ዓመት በፊት በታሪክ ለመጀመሪያ በወንዶች ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ቮሊቦል ቻምፒዮና መሳተፍ እንደቻለች ያስታወሱት አቶ ተክሉ፣ ተሳትፎውን ለማስቀጠል በፌዴሬሽኑ አቅም ከባድ ስለሚሆን መንግስት በተገቢው መንገድ መደገፍ እንደሚኖርበት ተናግረዋል። ስፖርቱ እንዲያድግ በርካታ ስራዎች በፌዴሬሽኑ እየተሰሩ እንደሚገኙ የጠቆሙት ኃላፊው፤ ለባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የአሰልጣኝነት ስልጠናዎች መሰጠታቸውን ይናገራሉ። ተከታታይና ወጥነት ያላቸው ውድድሮች እንዲኖሩም ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
እንደ አቶ ተክሉ ገለፃ፣ በዘንድሮ ዓመት የሴቶች እና ወንዶች የቮሊቦል ፕሪሚየርሊግ ውድድሮች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ። የፕሪሚየርሊግ ውድድሩ በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ጅማሮውን ሲያደርግ የ2014 ዓ.ም የሊጉ አሸናፊ ወላይታ ድቻንና የጥሎማለፍ አሸናፊው መደወላቡ ዩኒቨርሲቲን አገናኝቶ መደወላቡ በታሪክ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ቮሊቦል አሸናፊዎች አሸናፊ መሆን ችሏል።
ከዚህ በኋላ ፕሪሚየርሊጉ ቀጥሎ በወንዶች የመጀመሪያ ዙር በመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ባሌሮቤ ከተማና እና በወላይታ ሶዶ ከተማ ማድረጉን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። የሁለተኛው ዙር የመጀመርው ውድድር ደግሞ ከሳምንት በፊት በባህርዳር መደረጉንና የመጨረሻው ዙር ውድድር በግንቦት አጋማሽ በአዲስ አበባ እንደሚጠናቀቅም ተጠቁሟል።
በሴቶችም የመጀመሪያው ዙር በወላይታ ሶዶ ተካሂዶ የተጠናቀቀ ሲሆን ሁለተኛው ዙር በተመሳሳይ በግንቦት አጋማሽ እንደሚካሄድ ተገልጿል። የሁለተኛ ዙር የፕሪሚየር ሊግ ውድድሮች ከመካሄዳቸው አስቀድሞ የጥሎ ማለፍ ውድድሮችን ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅቶችን በማደረግ ላይ እንደሚገኝም ፌዴሬሽኑ ጠቁሟል። ውድድሩን ከሚያዝያ 23 ጀምሮ ለማድረግ እቅድ እንዳለ የተጠቆመ ሲሆን፣ ፌዴሬሽኑ ከአንዳንድ ክለቦች ከዓለም አቀፍ ተሳትፎ ጋር ተያይዞ የይራዘምልን ጥያቄ በመኖሩ በቀጣይ ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚችል ተገልጿል።
በፕሪሚርሊጉ የሚሳተፉ ክለቦች በየዓመቱ አንድ አይነት በመሆናቸውና ተተኪ እየመጣ ባለመሆኑ ጠንካራ እንዳይሆን አድርጎታል። ይህ በአለም አቀፍ ጠንካራና ተፎካካሪ የሆነ ክለብና ብሔራዊ ቡድን እንዳይኖር አንዱ ምክንያት ሆናል።
የቮሊቦልን ስፖርት ጠንካራ ለማድረግ የክልል ክለቦች ቻምፒዮናን በማዘጋጀት እና ጠንካራ ክለቦችን ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለመቀላቀል በእቅድ ደረጃ ተይዞ ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጅት ተደርጓል። በፕሪሚየር ሊጉ በቂ ክለቦች ሲኖሩ የመውጣትና የመውረድ ሁኔታ ይዞ የሚቀጥልም ይሆናል። ወደ ፕሪሚየር ሊግ መውጣትና መውረድ ሲኖር ፉክክርን በመፍጠር ጠንካራ ክለቦችን ለማፍራት እንደሚያስችልም አቶ ተክሉ ያላቸውን እምንት ይገልፃሉ። በዚህም ፌዴሬሽኑ የክልል ክለቦች ቻምፒናንና የጥሎ ማለፍ ውድድሮችን በአንድ ለማካሄድ እንቅስቃሴ እንደጀመረና ከአንዳንድ ክልሎች ተቀባይነት መግኘቱን ይጠቁሟሉ።
በፕሪሚየር ሊጉ ምንም እንኳን አዳዲስ ክለቦች በይኖሩም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ክለቦች በአፍሪካ ክለቦች ቻምፒዮና ተሳታፊ በመሆን ይታወቃሉ። ይህም ጠንካራ ጎን በመሆኑ ከተሳትፎም ባለፈ ውጤት ለማምጣት መሰራት እንደሚኖርበት ባለሙያው ያስረዳሉ።
በዘንድሮው የአፍሪካ የክለቦች ቻምፒዮና ሶስት ክለቦች ይሳተፋሉ። እአአ ከግንቦት 13-26/2023 በቱኒዝያ በሚደረገው ቻምፒዮና በወንዶች መደወላቡ፣ ወላይታ ድቻና ሙገር ሲሚንቶ የሚሳተፉ ይሆናል። በሴቶች ደግሞ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ተሳታፊ ይሆናል። ክለቦቹ ከተሳትፎ ከፍ ብሎ ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ፌዴሬሽኑ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝና ዝግጅታቸውን አጠናክረው እንደቀጠሉም ተጠቁማል።
ስፖርቱን ለማሳደግ በታዳጊዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት አስፈላጊ መሆኑን የገለፁት አቶ ተክሉ፣ ‹‹በታዳጊ ልማት ያልሰራ ሀገር ከተሳትፎ የዘለለ ምንም ማድረግ አይችልም›› ይላሉ። ስለዚህም በቀጣይ የቮሊቦል እምቅ አቅም ባለባቸው አካባቢዎች ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራና በየክልሉ ፕሮጀክቶች በአስገዳጅነት እንደሚቋቋሙ ተናግረዋል። ፌዴሬሽኑ በበኩሉ ሶስት ፕሮጀክቶችን በመያዝ እንዲሰራ ግዴታ እንደተሰጠውም ጠቁመዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20/2015