ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የሚያሳዩት አቋም ሃገርን ከማኩራት አልፎ የሌላውን ዓለም ህዝብም ማስደመሙ ግልጽ ነው።በዚህም ምክንያት በአትሌቶቹ ስም ሃውልት ከማቆምና ስፍራዎችን ከመሰየም ባለፈም በህይወት ታሪካቸው፣ በገድላቸውና የሩጫ ህይወታቸው ላይ ያጠነጠኑ መጽሃፍቶችን ይደርሳሉ፤ ፊልሞችንም ይሰራሉ።በአንጻሩ ይህ ዓይነቱ ልምድ እምብዛም ባልተለመደበት ኢትዮጵያ የጥቂት አትሌቶችን ህይወትና ተሞክሮ የሚዳስሱ መጽሃፍት በሌሎች ጸሃፊዎች ተዘጋጅተዋል።
በዚህም ረገድ ፈር ቀዳጅ ሊባል የሚችልና ለሌሎች አትሌቶችም አርዓያ የሚሆን የአንጋፋው አትሌት የህይወት ታሪክ በመጽሃፍ መልክ ተዘጋጅቶ ለአንባቢያን ቀርቧል።‹‹የተፈተነ ጽናት›› በሚል ርዕስ የታተመውና የ286 ገጽ ብዛት ያለው ይህ መጽሃፍ፤ በተለይ በማራቶን ሩጫ ስኬታማ፣ ለሃገሩም ኩራት መሆን በቻለው አትሌት መቶ አለቃ በላይነህ ዴንሳሞ የተጻፈ ነው።በግራንድ ኃይሌ ሆቴል በነበረው የመጽሃፉ ምረቃ መርሃ ግብር ላይም የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ አትሌቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
አንጋፋው አትሌት በመላው ዓለም የናኘ ዝናውንና በአትሌቲክስ ስፖርት እጅግ ፈታኝና ከፍተኛ ጽናትን በሚጠይቀው ማራቶን ስኬታማ ለመሆን ያሳለፋቸውን ውጣ ውረዶች ጨምሮ ህይወቱ ያለፈባቸውን መንገዶች መጽሃፉ ይተርካል።በዚህም ጀማሪና ወጣት አትሌቶች ልምድ የሚያገኙበትና ብርታትንም ሊሰንቁ የሚችሉበት ይሆናል።መጽሃፉን ያነበቡ የደራሲው አጋሮችና የተለያዩ ባለሙያዎችም ለወጣት አትሌቶች መነሳሳትን የሚፈጥርና ለሃገር የሚከፈልን መስዋዕትነትንም የሚያሳይ ስለመሆኑም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያን ካስጠሩ ጀግና አትሌቶች መካከል ቀዳሚ የሆነው አንጋፋው ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፤ ወደ አትሌቲክስ ስፖርት ከመግባቱ አስቀድሞ እንደ አርዓያ ከሚመለከታቸው አትሌቶች መካከል አንዱ መቶ አለቃ በላይነህ ዴንሳሞ እንደነበር ይገልጻል።ልምምድ በሚያደርግበት ወቅት የሚመለከተው ሲሆን፤ በአንድ ወቅት ከዓለም አቀፍ ውድድር መልስ ይዞለት የመጣው ትጥቅ (የስፖርት ሱሪ እና ጫማ ድጋፍ) ትልቅ መበረታቻ እንደሆነው አስታውሷል።በላይነህ ለሃገሩ ኢትዮጵያ ጽኑ ፍቅር ቢኖረውም በአንዳንድ ሁኔታዎች ለዓመታት ኑሮውን በባህር ማዶ አድርጎ ቆይቷል።ከአሁን በኋላ ግን ባኮራት ሃገሩ መኖር እንደሚገባው በመግለጽም ለዚህ ይረዳ ዘንድ 10 መጽሃፍቶች እያንዳንዳቸውን በ10ሺ ብር ሂሳብ በአጠቃላይ በ100ሺ ብር በመግዛት ቀዳሚ ተግባርም አከናውኗል።
ሌላው የቀድሞ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን አባልና በማራቶን ሃገሩን ከረጅም ዓመታት በኋላ በኦሊምፒክና ዓለም ቻምፒዮና መድረክ ውጤታማ ያደረጋት አንጋፋ አትሌት ገዛኸኝ አበራም ከበላይነህ ባገኘው ስልጠና፣ ልምድና ምክር ታግዞ ውጤታማ እንደሆነ ገልጿል።የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት የሆነው ገዛኸኝ በግሉ የ50ሺ ብር መጽሃፍ ገዝቷል።ስራ አስፈጻሚውም ተወያይቶ አትሌቱን ለማበረታታት እንዲሁም በሁሉም ክልሎች በሚገኙ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ተቋማት ታዳጊዎች መማሪያ እንዲሆናቸው የ200ሺ ብር ግዢ እንደሚፈጽምም ጠቁሟል።
የበላይነህ የቀድሞ ክለብ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን (ኮሜድላን) በመወከል የተገኙት ነብዩ ኢሳያስ፤ አትሌቱ ለአባላቱ አርዓያ እና በስነምግባር የታነጸ አመራር እንደነበረም አስታውሰዋል።የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው፤ መጽሃፉ ሌሎች አትሌቶችም አርዓያነቱን እንዲከተሉ እንደሚያነሳሳ ጠቁመዋል።አትሌቱ በርካታ ስራ ማከናወን የሚችል በመሆኑም ቀጣይ ህይወቱን በሃገሩ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ኤዳሞ፤ አትሌቱ ወደ ክልሉ ተመልሶ ወጣት አትሌቶችን የሚያበቃበትን መንገድ እንዲያመቻች ጠይቀዋል።ለዚህም ይረዳው ዘንድ በሀዋሳ ከተማ ዓይን ቦታ ላይ 1ሺ ካሬ ሜትር ቦታ የክልሉ መንግስት እንዳበረከተለት ገልጸዋል፡፡
ከመጽሃፉ ሽያጭ 20 ከመቶ የሚሆነው ለመቄዶንያ እርዳታ ድርጅት የሚውል ሲሆን፤ ሌሎች የአትሌቱ ወዳጆችና አድናቂዎችም መጽሃፉን በከፍተኛ ዋጋ ገዝተዋል።
ከምርጥ የማራቶን አትሌቶች መካከል አንዱ የሆነው መቶ አለቃ በላይነህ ዴንሳሞ በተለይ በሮተርዳም ማራቶን ባስመዘገበው የዓለም ክብረወሰን ይታወቃል።በፖርቹጋላዊው አትሌት ለሶስት ዓመት ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን 2:06:50 በመሮጥ ያሻሻለ ሲሆን፤ ለ10 ዓመታት ያህል ሳይደፈር መቆየቱም አስደናቂ አድርጎታል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2015