ገና ሳይመሽ ጭጋግ ያጨለመው ግሮሰሪ፤ እነተሰማ መንግሥቴን፤ ዘውዴ መታፈሪያንና ገብረየስ ገብረማሪያምን ጨምሮ የዘወትር ደንበኞች በጊዜ ታጭቀው ስላጨናነቁት በሰዎች ትንፋሽ ታፍኗል። ሁሉም እየጮሁ ያወራሉ። ብዙዎቹ ደምስራቸው በግንባራቸው ላይ ተገታትሯል። የበዓል ድባብ አልጠፋም። ብልጣብልጡ የግሮሰሪው ባለቤት ለጠጪው ዳቦ በትንንሹ ሸንሽኖ በአስተናጋጆቹ በኩል እያከፋፈለ ነው።
ተሰማ የብልጣብልጡን የግሮሰሪ አትራፊ የፈጠረውን አጋጣሚ ተከትሎ ትልቅ ዳቦ ስለመጋገር አሰበ። ‹‹ወገን ከወገን ጋር ተባብሮ ትልቅ ዳቦ መጋገር አለበት። የሚያዋጣው በትንሿ ዳቦ ምክንያት መገዳደል ሳይሆን፤ ትልቅ ዳቦ መጋገር ነው። ትልቅ ዳቦ ለመጋገር ደግሞ ትልቅ ንቅናቄ ያስፈልጋል።›› አለ።
ዘውዴ ከት ብሎ ሳቀ። ‹‹ትልቅ ዳቦ ለመጋገር ብዙ ዱቄት እና በደንብ የታሰሰ ምጣድ ያስፈልጋል፤ የታሰሰ ምጣድ እና ብዙ ዱቄት ከየት እናምጣ?›› በማለት ጥያቄ አቀረበ። ተሰማ፣ ‹‹የሥራ ንቅናቄ መፈጠር አለበት። ዜጎች 24 ሰዓት የሚሠሩበት ሁኔታ ከተመቻቸ ብዙ ዱቄት ማግኘትም ሆነ ትልቅ ዳቦ መጋገር የሚያስችል ትልቅ ምጣድ ማሟሸት አያዳግትም።›› በማለት ምላሽ ሰጠ።
ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹በቅድሚያ መጋደልን ምን አመጣው? የሚለውን ጥያቄ ቀድሞ መመለስ ያስፈልጋል። ሰው ከሠራ ለራሱ አያንስም። ለራሱ ትንሽ ዳቦ መጋገር አያቅተውም። 24 ሰዓት ቀርቶ ለስምንት ሰዓት በትክክል ከሠራ ከራሱ አልፎ ለሰው ይተርፋል። በሽታ የሆነብን ሁላችንም ያልሠራነውን ያህል መፈለጋችን ነው። ችግሩ ሥራ አለመውደድ ነው። ወጣቱ የወደፊት ዕድሉን ለማቃናት ከመሥራት ይልቅ፤ በማይገባው እየገባ ፖለቲካውን ሲያራግብ የመሥሪያ ሰዓቱ ያመልጠዋል። ሌላውም የራሱን ኃላፊነት መወጣት ሲኖርበት በተቃራኒው በወሬ ጊዜውን ሲገፋ የሚበላው ያጣል። በጥቂቶች የተጋገረው ትንሽ ዳቦ ለብዙኃኑ አይበቃም፤ መቧጨቅ ይሆናል። አገር የምታድግበት ዕድል ይጠባል። ድህነት በላይ በላዩ ይደራረባል። ሃብት ሲያንስ ወንድማማችነት ቀርቶ ወደ ጦርነት መግባት ግድ ይሆናል›› አለ።
ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹ፀረ ጦረኛ ወይም ከጦርነት ውጪ ለመሆን አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት እና ትልቁን ዳቦ በመጋገር ሕዝብ ለማጥገብ ያለፈው አልፏል በሚል መንፈስ፤ ይቅር ተባብሎ ወደ ፊት መቀጠል የግድ ነው። ያለበለዚያ በማሸነፍ ሁሉን መቆጣጠር ቢቻል እንኳ ከፊል ሰላም እንጂ ሙሉ ሰላም ማምጣት ያዳግታል።›› አለ። ዘውዴ ግን፤ ‹‹ሰላም አስፈላጊ መሆኑንማ ማንም አያጣውም። ለአንድ አገር ሕዝብ ሰላም አስፈላጊው መሆኑን መናገር ተራ ጉዳይ ነው፤ ሁሉም ያውቀዋል። ሰላም ከሌለ ለሕዝብ ብቻ አይደለም፤ መንግሥት ፖለቲካውን ከላይ ሆኖ ለመምራት ቢሞከርም አይሳካለትም። ምክንያቱም ሰላም ሳይመጣ በጉልበት ላይ ተማምኖ ኃይል መጠቀም ስምምነት ስለማያመጣ፤ አመፅ የሚያጋጥምበትን ጊዜ ለመተንበይ ያስቸግራል። ይህ ደግሞ ለመንግሥትም ትልቅ ስጋት ነው። ዋናው ጉዳይ ግን የተጎዳው ተጎዳ ያለፈው አለፈ ብሎ ለመዝጋት የተጎዱትን መካስ የግድ ነው። ቢያንስ በኑሯቸው መደገፍ ያስፈልጋል›› አለ።
ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹እርሱማ ምን ጥያቄ አለው። ሰላም ስለመጣ ሌሎች ሞተዋል እና አሁንም ሞት ይቀጥል ማለት አይገባም። ለቆመው ‹ሞት አነሰው› ካልን አያዋጣም፤ ሰላም መፍጠር ተንኮለኝነት ወይም ክፉነት አይደለም። አታላይ እና ውለታ ቢስነት ሊሆንም አይችልም፤ የሰውን ደም ደመከልብ ማድረግም አይደለም፤ ደግ ማሰብ እና ለጥሩ ነገር መታገል መልካም ነው። ቂም ይዞ መለያየት እና መጣላት አትራፊ ሆኖ አያውቅም። ለሰው ልብሱ ሰው ነው። ለሰው ጉልበቱ፣ ድምቀቱና ሕልውናው ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት እና በሌሎች ሰዎች ድጋፍ ላይ የተመሰረተ ነው። በመደጋገፍ ትልቅ ዳቦ መጋገር ቢሳነን እንኳ ከምንገዳደል ለየራሳችን የሚበቃ ቢያንስ ትንሽ ዳቦ እንጋግር፤ …›› ብሎ ሊቀጥል ሲል ተሰማ በደስታ በገብረየስ ሃሳብ በመስማማት እርሱም ለማለት የፈለገውን ማተት ቀጠለ።
‹‹ከምንባላ እንስማማ በትንሿ ዳቦ ላይ ከምንጋደል በስምምነት ትልቅ ዳቦ እንጋግር ያልኩት ለዚሁ ነው።›› አለ ተሰማ ዘውዴን እያየ። ዘውዴ ደግሞ ‹‹ለስሟ መጠሪያ ቁና ሰፋች አይነት ነገር እንዳይሆን መጠንቀቅ የግድ ነው። ለመታየት እና ለመታወቅ ሲባል የሚፈፀም ድርጊት ፍፃሜው አያምርም። መታረቅ ከልብ መሆን አለበት። ትልቅ ዳቦ ለመጋገር መስማማትና የሚጋገርበት ምጣድ እንዳይሰበር መጠንቀቅ ይገባል። ምጣድ ከተሰበረ እርቅም ጠብም ቅንጦት ነው። ወጣት ወይም የተማርኩ ንቁ ስለሆንኩ ሁሉን በግድ አስፈፅማለሁ ማለት ብዙ ርቀት አያስጉዝም። ማደግ፣ መወፈር እና መዳበር ቢቻልም፤ ዱላ ካለ ለመከላከል በሚደረግ ያላሰለሰ ጥረት መድከም አይቀርም።
ለእዚህ መፍትሔው ሰላም እና የዜጎችን ነፃነት ማረጋገጥ ነው። ምጣዷ ሳትሰበር እንድትቆይ እና ትልቅ ዳቦ ለመጋገር በነፃነት መነጋገር እና ይቅር መባባል ያስፈልጋል።›› ብሎ ዘውዴ ሊቀጥል ሲል፤ ተሰማ ሳይቀደም ፈጠን ብሎ ‹‹ትልቅ ዳቦ ለመጋገር የሰላም ስምምነት በመፍጠር ሂደት ውስጥ የመናገር፣ የመፃፍ፣ የመሰብሰብ እና ወዘተን የመሳሰሉ ነፃነቶችን ማክበር የግድ ነው። ሰላም ለማምጣት መመሳጠር ጦርነት ለማወጅ በእልህ ከመወጣጠር ጋር በእጅጉ ይቃረናል። ለሰላም ሲባል መተሳሰር ምጣዷ እንዳትሰበር መጠንቀቅ በምንም መልኩ አያስነቅፍም። ነገር ግን ትልቁን ዳቦ ለመጋገር የተወጠነ መደራጀት፣ የተወጠነ እና በደንብ የታሰበበት አመራርነት እና የመመራት ጥበብ ያስፈልጋል።›› አለ።
ተሰማ ቀጠለ፤ ‹‹ የተወጠነ ሰላም መፍጠር በደንብ ከታሰበበት ከተወጠነ አመራርነት ጋር የሚያያዝ ነው። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው በጣም አስገራሚ የመመራትም ሆነ የመምራት ጊዜያትን አሳልፈዋል። ነገር ግን አሁን በሚታየው ደረጃ ላይ ደርሰናል። ኢትዮጵያውያን ለትውልድ የሚተርፍ ዕዳን አከማችተናል፤ በድህነት ስመ-ጥር በኢኮኖሚያዊ ሃብት ደግሞ ጭራ ሆነናል። የዚህ ሁሉ ምክንያት ዘመናችንን በጦርነት ማሳለፋችን ነው። ደርሰን የሚቀናን ጦርነት ነው። ዳቦ ለመጋገር ከመሯሯጥ ይልቅ የሚያለያይ ነገር ፈልጎ መራቆትን ልማድ አድርገነዋል። ሰበብ እየፈለጉ፤ ብሔር እና ሃይማኖት እየጎተቱ አፍንጫ መንፋት፣ በመተባበር የወደፊቱን አስቦ ከመሥራት ይልቅ የመለያያ ቀዳዳ እየፈለጉ ነገር እያወሳሰቡ ልዩነትን ማስፋት በተለይ የተማረው ኅብረተሰብ የብቃት መለኪያ ሆኗል።
ነገር ግን አዋቂነት ነባራዊውን ሁኔታ መረዳት ነው። የሀገርን ነባራዊ ሁኔታ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ አስመልክቶ ማሰብ ብቻ ሳይሆን የግድ ማሰላሰል ያስፈልጋል። ቢያንስ የውጪ ጠላትን አሳፍሮ አገርን በሰላም ለማቆየት የውስጥ ስምምነት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ይህ በፍፁም የሚደገፍ እንጂ የሚነቀፍ አይደለም።›› በማለት ለማሳመን ጥረት አደረገ።
ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹የውጪ ጠላቶች ጉዳይ እንዲህ በእኔና በአንተ ለዛውም በእዚህች ትንሽ ዕይታ እና ጊዜ የሚብራራ አይደለም። እርግጥ ነው፤ ፍላጎታቸው ኢትዮጵያውያንን ማባላት ነው። እኛ ደግሞ ለመባላት ዝግጁ ነን። ያለፉ መንግሥታት ምንም ቢያጠፉ ኢትዮጵያ እንዳታድግ የሆነበት ትልቅ ምክንያት ሰላም ማጣታችን ነው። መንግሥታት ኃይላቸውን የሚጨርሱት በልማትና ኢትዮጵያን በማሳደግ ላይ ሳይሆን ምጣዷ እንዳትሰበር በመጠንቀቅ ለርሷ የኃይል ከለላ በማድረግ ሲታገሉ በውጪ ጠላቶች ግፊት ያልፋሉ። ኢትዮጵያውያን የዳበረው መጥቶ በአዲስ ለተተካው መንግሥትም ከጎን በመቆም አገር እንድታድግ ከመሥራት ይልቅ በተቃራኒው በተቃውሞ ይቆማሉ። መንግሥትም ከመዳበር ይልቅ ይሽመደመዳል። በሂደት ምጣዷ እንድትሰበር ዕድል ይፈጠራል።›› ሲል ተሰማ ዘውዴ በሰጠው ሃሳብ በመደሰት ፊቱ በፈገግታ ተሞላ።
‹‹አሁን እየገባህ ነው።›› አለ ተሰማ፤ ዘውዴ ግን ‹‹እኔ ሰላም አያስልፈልግም አላልኩም። ሰላም እና ዕርቅ እንደሚያስፈልግ አያጠያይቅም። የእኔ ጥያቄ ሌላ ነው። ለሕዝቡ ለምን አይታሰብም የሚል ነው።›› አለ። ተሰማ ጥያቄ አቀረበ። ‹‹ለሕዝብ ማሰብ ማለት ምን ማለት ነው? ከዚህ በላይ ማሰብ እንዴት ይቻላል? ሰላምን እንመርኮዝ እያልን ነው። ይህ ያለምንም ጥያቄ ለሕዝብ ማሰብ ነው። ሰላም ከሆነ ለልማት ሰፊ ጎዳና ለማግኘት አያዳግትም። ግልጹ ጉዳይ ሰላም ከሌለ ልማት የለም። ዘመናት የሚያልፉት በጥፋት ብቻ ይሆናል። ይህ አሁን ላለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድም መከራ እና ፍዳን ማስቀመጥ ነው።›› በማለት በንዴት እና በኃይል ለመናገር ሞከረ።
ዘውዴ ግን ለስለስ ብሎ ‹‹ትልቅ ዳቦ ለመጋገር ዋነኛው ጉዳይ የኑሮ ዋስትና ነው። የኑሮ ዋስትና ከተረጋገጠ ከመሐል ከተማ እስከ ዳር ጠረፍ በነፃነት መንቀሳቀስ፣ በነፃነት መሥራት ከተቻለ ዕዳው ገብስ ነው። ይህ ሳይሆን የዜጎችን የተሟላ ኑሮ ማረጋገጥ ይቻላል ብሎ ማሰብ ቀልድ ነው። የተሟላ ኑሮን ለመምራት ሳይሞከር ትልቅ ዳቦ ስለመጋገር ማውራትም ከተረተረት ያለፈ አይሆንም።›› ሲል በዘውዴ ንግግር ተሰማ ይበልጥ ቆጣ አለ።
‹‹ትልቅ ዳቦ ስለመጋገር ስገልፅ መነሻዬ ሕዝብን መጨቆን ላይ ተመርኩዤ አይደለም። ሰላም፣ ፍትሕ፣ ነፃነትና እኩልነት መኖር እንዳለበት የእኔም እምነት ነው። ያለበለዚያ የሚሠራው ሁሉ ውሎ አድሮ በአሸዋ ላይ እንደተገነባ ቤት ሊናድ እንደሚችል አምናለሁ። ስለዚህ አሁን ውስጣዊ አንድነት ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው። ይህንን ጥረት እንደግፈው፤ እንደጋገፍና ፊታችንን አገርን ወደ ማሳደግ እናዙር፤ ያለበለዚያ ጨቅላ ተስፋዎችን እየቀጨን ካኮላሸን መንግሥት ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ሕልውናም አደጋ ላይ ይወድቃል። እያልን ነው።›› በማለት ተሰማ የሚያምንበትን ለማሳመን በቁጣ አዘል ድምፀት ሃሳቡን ገለፀ።
ዘውዴ በበኩሉ፤ ‹‹ጨቅላ የሰላም ተስፋዎችን የመቅጨት ፍላጎትም ሆነ አላማ የለኝም፡፡ ነገር ግን የመናገር ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ፡፡ ኑ! ትልቅ ዳቦ እንጋግር ብለሃል፡፡ በዚህ ሃሳብ እስማማለሁ፡፡ ነገር ግን ደግሞ ፍትህን ወይም ነፃነትን በሚመለከት ጥያቄ ማቅረቤን እንደሃጢያት ከቆጠርከው ያው ጠላት ሆንን ማለት ነው፡፡ የኔን ሃሳብ ባትቀበል እንኳን ለማዳመጥ ዝግጁ ሁን፡፡ ያለበለዚያ ወጣትነትና ባለሙሉ ሃይልነት ዘላቂ አይደለም፡፡ መድከም ማርጀት ይመጣል፤ የዛን ጊዜ የኔ ልጅ ፈርጥሞ የኔን ሃሳብ በመቃወምህ ዋጋ ያስከፍልሃል፡፡ ስለዚህ ለዚህ መሠረቱ ሰላም፤ ከሰላም ጋር ነፃነት እና ፍትህን ማረጋገጥ ነው፡፡›› ብሎ እንደልማዱ የብርጭቆውን ድራፍት ጨልጦ ቀድሞ ተነሳ፡፡ ‹‹ሳይመሽ ብገባ ይሻለኛል፤›› ብሎ ከግሮሰሪው ወጣ፡፡
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2015