ሰላምና መረጋጋት በሌለበት ሀገር የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴና እድገት ፈፅሞ የሚታሰብ አይደለም። የኢንቨስትመንት ሥራ ሰላም ይፈልጋል። ግጭትና ጦርነት ያለባቸው አካባቢዎች አዳዲስ የኢንቨስትመንት እድሎችን ማግኘት ይቅርና፣ በአካባቢዎቹ ያሉ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎችንና ተቋማትን ይዘው መቆየት አይችሉም፤ ባሉበት የመቀጠል እድላቸውም እጅግ ዝቅተኛ ይሆናል። እንኳን በተግባር የሚታይ የሰላም እጦት፣ ተጨባጭ ማስረጃ የሌለው ወሬም ኢንቨስትመንትን ያስደነግጣል። ለዚህም ነው ‹ሰላም የኢንቨስትመንት መተንፈሻ ነው› የሚባለው።
‹‹ዴቨሎፕመንት ኢኒሼቲቭስ›› (Development Initiatives) የተባለ የጥናት ተቋም ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፤ በሰላምና በኢንቨስትመንት መካከል ያለው ግንኙነት የዓለም አቀፍ ልማትና የምጣኔ ሀብት እድገት ወሳኝ የትኩረት ነጥብ እንደሆነ አመላክቷል። በግጭትና ጦርነት ውስጥ የተዘፈቁ ሀገራት የኢንቨስትመንት ዘርፋቸው የተዳከመ መሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተያዙ የልማት እቅዶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እንዳይሳኩ እክል መፍጠሩ እንደማይቀርም ስጋቱን ገልጿል።
ሰላም ከኢንቨስትመንት ጋር ምን ዓይነት ቁርኝት እንዳለው ያለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ ጥሩ ምስክር መሆን ከሚችሉ ሀገራት መካከል እንደምትመደብ አያጠራጥርም። በእነዚሀ ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱ አለመረጋጋቶች፣ በተለይም የሰሜኑ ጦርነት፣ በኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ ጉዳት አድርሰዋል። በእነዚህ አለመረጋጋቶች ምክንያት ውድመትና ዝርፊያ የተፈፀመባቸው የኢንቨስትመንት ተቋማት የደረሰባቸው ጉዳት የሚዘነጋ አይደለም። ይህ ሁኔታም ሠራተኞች ከሥራ እንዲፈናቀሉ፣ ምርትና አገልግሎት እንዲቀንስ እንዲሁም ኢንቨስትመንት እንዲዳከም በማድረግ በሀገራዊ ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል።
ባለፈው ዓመት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከተካሄደው ጦርነት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ክስተቶች ለኢንቨስትመቱ ዘርፍ መሰናክል እንደነበሩ በተደጋጋሚ ተገልጿል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንም በ2104 ዓ.ም የበጀት ዓመት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትንና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው መረጃ፣ ከጦርነቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የኢትዮጵያ ከአጎዋ (AGOA) መታገድ እና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጫና በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ተግዳሮቶች መካከል ተጠቃሽ እንደነበሩ መግለፁ ይታወሳል።
ሰላምና መረጋጋት ከኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ በተለይ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረው የሰላምና ፀጥታ መደፍረስ በኢንቨስትመንት ላይ ተሠማርተው የነበሩ ትልልቅ አምራች ድርጅቶችን ትልቅ ጫና ውስጥ አስገብቷቸዋል። አለመረጋጋቱን ተከትሎ የመጣው የውጭ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘመቻና ጫና አምራች ድርጅቶች ተረጋግተው እንዳይሠሩና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች በቀላሉ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ ተፅዕኖ አሳድረዋል። በተጨማሪም ኤምባሲዎች ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ ስለነበር አምራቾች በጫና ውስጥ ሆነው ለመሥራት የተገደዱበት ዓመት እንደነበር አይዘነጋም።
የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲቀዛቀዝ ምክንያት ለነበረው የሰላም መደፍረስ መፍትሔ ይሆናል የተባለውና ባለፈው ጥቅምት ወር በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት እና በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ለኢንቨስትመንት ዘርፉ መነቃቃትና ማንሰራራት ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል። የሰላም ስምምነቱ በተለያዩ ጫናዎች ሳቢያ የተቋረጡ የማምረት ሥራዎች እንዲጀመሩ፣ የተቀዛቅዙ ምርቶችን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ሥራዎች እንዲያንሰራሩ እና አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ሀገሪቱ እንዲመጡ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። እንደተጠበቀውም የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ወዲህ ተቀዛቅዞ የነበረው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መነቃቃት ታይቶበታል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን፣ የሰሜን ኢትዮጵያው ግጭት በሰላም ስምምነት መቋጨቱን ተከትሎ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃትና መሻሻል እየታየ እንደሚገኝ ይገልፃሉ። ‹‹ጦርነቱ በኢንቨስትመንት ላይ አስከትሎት የነበረው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። በወቅቱ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የነበራቸው ፍላጎት ቀንሶ ነበር። ከሕግ ማሻሻያዎች ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ የነበሩ እድሎች ሰፊ ቢሆኑም በተለይ ትልልቅ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በኢንቨስትመንት ላይ ለመሠማራት ይዘውት የነበረውን ፕሮግራማቸውን በተወሰነ መልኩ አዘግይተውታል። እንደ ሳፋሪኮም ያሉ ድርጅቶች ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በኢንቨስትመንት ላይ እንደተሰማሩ አይዘነጋም›› ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት፣ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ ወደ መረጋጋት ተሸጋግራለች ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ‹‹ከጦርነቱ መቆምና ከሰላም ስምምነቱ መፈረም ጋር ተያይዞ ሁለት ዓይነት እንቅስቃሴዎችን እያየን ነው። ከእኛ ጋር ግንኙነት የነበራቸው አካላት በድጋሚ ከእኛ ጋር ንግግር ጀምረዋል፤ ወደ ኢንቨስትመንት ሥራዎቻቸው ለመመለስና ወደ ተግባር ለመግባት ፍላጎት አሳይተዋል። እኛም በበቂ ሁኔታ በማገዝ ወደ ሥራ እንዲገቡ እያደረግን ነው። በተጨማሪም የአዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ፍሰት እየጨመረ ይገኛል። ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት በየጊዜው እያደገ መጥቷል። በአጠቃላይ የሰላም መስፈን ለኢንቨስትመንት ወሳኝ እንደሆነ በተግባር እያየን ነው›› በማለት የሰላም ስምምነቱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን እያነቃቃው እንደሚገኝ ይናገራሉ።
የፐብሊክ ፖሊሲ ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ የሰላም ስምምነቱ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መነቃቃት በጎ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ጠቁመው፣ የዘርፉን እድገት ዘላቂ ለማድረግ ግን ከሰላም ስምምነቱ የተሻገሩ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። እርሳቸው እንደሚገልፁት፣ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማሳደግ የምጣኔ ሀብት፣ የፖለቲካና የሰብዓዊ ዲፕሎማሲ ጥረቶች ያስፈልጋሉ። እነዚህ የዲፕሎማሲ ሥራዎች የሀገሪቱን ገጽታ ለሌላው ዓለም በበጎ መልኩ በማሳየት ሰብዓዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ድጋፍ ለማግኘት የሚያግዙ ተግባራት ናቸው።
ትልልቅ የውጭ ሀገራት ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በኢንቨስትመንት ተግባራት ላይ እንዲሰማሩ ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የሚያያዘው የንግድና ቢዝነስ ሥራ አመቺነት (Ease of Doing Business) ነው። ተቋማዊ ቢሮክራሲን ቀላልና ፈጣን በማድረግ የንግድና ቢዝነስ ሥራን ምቹ ማድረግና የኢንቨስትመንት ፍሰትን ማሳደግ ይገባል። ለዚህም በታችኛው የአስተዳደር እርከኖች ላይ ከሚገኙ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ብዙ ሥራ ይጠበቃል።
ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹በሀገሪቱ በስፋት ለተንሰራፋው አደገኛ የሙስና ተግባር ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል። ትልቅ አቅም ኖሯቸው በኢትዮጵያ ውስን የሚባል የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ካላቸው ሀገራት ጋር ግንኙነትን የበለጠ ማጠናከር እጅግ አስፈላጊ ነው። የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ በሚደረገው ጥረት ከዲፕሎማቶች ብዙ ሥራ ይጠበቃል›› በማለት ይመክራሉ።
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የተቀዛቀዘው የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲነቃቃ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ የኢንቨስትመንት ማነቃቂያ አሠራር መተግበር እንደሚያስፈልግ ይታመናል። ለዚህም የድህረ ጦርነት ኢንቨስትመንት አስተዳደር ሥርዓትን መቅረፅና መተግበር ያስፈልጋል። ቀደም ሲል የነበረው ሀገራዊ የኢንቨስትመንት አዋጅ መሻሻሉ የድህረ ጦርነት ኢንቨስትመንት ሥራው ውጤታማ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። የኢንቨስትመንት ሕግጋት መሻሻል በድህረ ጦርነቱ ወቅት የሚኖረውን ሀገራዊ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው አቶ ተመስገን ይገልፃሉ።
አቶ ተመስገን እንደሚናገሩት፣ አዲሱ የኢንቨስትመንት አዋጅ (1180/2012) ኢትዮጵያን ተወዳዳሪና ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ሊያደርጋት የሚችል ሕግ ነው። አዋጁ ለግሉ ዘርፍ በተለይም ለውጭ ባለሀብቶች ሰፊ የኢንቨስትመንት እድል የሚፈጥርና ገደብ የማያስቀምጥ አዋጅ በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ የመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ሰፊ እድል ያገኛሉ።
‹‹ባለፉት ዓመታት ከተከናወኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መካከል አንዱ በኢንቨስትመንት ፖሊሲ ላይ የተደረገው ለውጥ ነው። ቀደም ሲል ሀገሪቱ ትጠቀምበት የነበረው ፖሊሲ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው ሊሠማሩባቸው የሚችሉ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን የሚገድብ (Positive Listing Approach) ነበር። ይህ አሠራር ኢንቨስተሮቹ ሊሠማሩባቸው ከሚችሉባቸው ዘርፎች ውጭ ባሉት ሌሎች ዘርፎች ላይ እንዳይሳተፉ ገደብ የሚጥል ነበር።
ይህ የቀደመው አሠራር በኢንቨስትመንት አዋጁ (1180/2012) ተቀይሯል። አዲሱ የኢንቨስትመንት አሠራር ባለሀብቶች ሊሰማሩባቸው የማይችሉባቸውን ዘርፎች የመዘርዘርና የቀሩትን ክፍት የማድረግ አቅጣጫ (Negative Listing Approach) ያለው በመሆኑ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። አሁን ባለው የኢንቨስትመንት አዋጅ መሠረት ሦስት የኢንቨስትመንት ዘርፎች አሉ። እነዚህም የግሉ ዘርፍ ከመንግሥት ጋር በጋራ ሊሰማራባቸው የሚችሉ፣ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ የተከለሉ እና ለውጭ ባለሀብቶች ሁሉ ክፍት የሆኑ ዘርፎች ናቸው›› ይላሉ።
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በልዩ ልዩ ምክንያቶች ሲዳከም ለሀገራዊ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ወሳኝ አቅም የሚሆኑት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ናቸው። የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍና አቅማቸውን ማሳደግ በጊዜ ሂደት በራስ አቅም የተገነባ ሀገራዊ የኢንቨስትመንት ዘርፍን ለመፍጠር አስተማማኝ ግብዓት ይሆናል።
በሌላ በኩል በድህረ ጦርነት ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል አንዱ ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ሊደረግ የሚገባው ድጋፍ እንደሆነ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ዛሬ በምጣኔ ሀብታቸውና በፖለቲካ ተፅዕኗቸው የዓለም ኃያላን የሆኑት ሀገራት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶቻቸውን በመደገፍ ረገድ ትልቅ ተሞክሮ አላቸው። እንዲያውም ለአሁኑ የምጣኔ ሀብት ኃያልነታቸው መሠረት የሆናቸው ከውጭ ጥገኛነት ያላቀቃቸው የአምራችነት አቅማቸው ማደግ እንደሆነ ይታወቃል።
ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማጠናከር መንግሥት በዋናነት የፋይናንስ ድጋፎችን ማድረግ እንዳለበት ይናገራሉ። የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን አቅም ለማሳደግ የሚያስችል የተደራጀ የመንግሥት መዋቅር መገንባት፣ በአጠቃላይ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የኢኮኖሚው ምሰሶ የሆኑ ግብዓቶችን ማሟላት አስፈላጊ እንደሆነ ይገልፃሉ።
ከእነዚህም መካከል አንዱ የሆነው የፋይናንሱ ዘርፍ ትልቅ ሪፎርም ያስፈልገዋል ሲሉም ይገልጻሉ። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ከሰላምና መረጋጋት ባሻገር የፋይናንስ ሁኔታው ምቹ ሊሆን ይገባል። ሕግጋትን ማሻሻል እንዲሁም ወቅቱን የሚመጥኑ ውጤታማ ባለሙያዎች ዘርፉን እንዲመሩት ማድረግ ያስፈልጋል። የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ መግባታቸው እጅግ አስፈላጊ ነው። የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ችግር እየገጠማቸው ይገኛል። የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ለኢንቨስትመንት ሥራዎች የተሻለ የፋይናንስ ምንጭ ይገኛል። ይህም ከኢንቨስትመንት ሥራዎቹ የውጭ ምንዛሪ እንዲገኝና የሀገሪቱ የንግድ ሚዛን እንዲስተካከል ያግዛል። ‹የውጭ ባንኮች ቢገቡ የሀገር ውስጥ ባንኮችን ይጎዳሉ› የሚለው ሃሳብ ትክክል እንዳልሆነ ያስረዳሉ።
የሰላም መስፈን ለኢንቨስትመንት ማደግ የመጀመሪያውና ዋናው ቅድመ ሁኔታ ነው። ያለሰላም የሚታሰብም ሆነ የሚከናወን የኢንቨስትመንት ተግባር የለም። ለኢንቨስትመንት ዘርፉ መነቃቃትና ማንሠራራት ትልቅ ተስፋ የተጣለበት የሰላም ስምምነት የታሰበውን ውጤት እንዲያስገኝ ለስምምነቱ ገቢራዊነት ቁርጠኛ ከመሆን በተጨማሪ፣ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ መነቃቃትና ማንሰራራት ዋስትና ሊሆኑ የሚችሉ የድህረ ጦርነት የኢንቨስትመንት ማነቃቂያ ስትራቴጂዎችን ማዘጋጀትና በብቃት መተግበር ይገባል።
የሰላም ስምምነቱ ሀገሪቱ ለኢንቨስትመንቱ ዘርፍ በሚል የገነባቻቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ይበልጥ እንዲነቃቁ ያስችላል
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2015