ሰዎች በራሳቸው ሲበሳጩ አሊያም በአድራጎታቸው እፍረት ቢጤ ሲሰማቸው ቁጭታቸውን በተለያየ መልክ ይገልጻሉ። ከእኛ ዘንድ ከተለመዱት መካከል «ምነው የሄድኩበትን እግሬን ቄጤማ ባደረገው፣ ያየሁበትን ዓይን በጋረደው፣ ምላሴን በቆረጠው፣…» የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው። ይህን ማለታቸው የተሰማቸውን ቁጭት በጥልቅ ከመግለጽ ባሻገር ግን የእውነት ይሆንባቸዋል ማለት አይደለም። ግን ግን «ቄጤማ ባደረገው» ያሉትን እግር እንዲሄድ ያዘዘው አእምሮ ነው አይደል? እንጂማ እግር ብቻውን መንገድ አይነሳም። ለመናገርም፣ ለማየትም፣ ለመንካትም፣… የአእምሮ ይሁንታ የግድ መሆኑንም እናውቃለን። ታዲያ ከወደ ህንድ የተሰማውና ስህተት እንደሰራ የታመነበት ጣት ላይ መፈረዱ፤ ይህንን ከመዘንጋት የተከሰተ ይሆን? ዜናው በሀገሪቷ ከተሰማ በኋላ ብዙዎችን «ጉድ» ሲያስብል ነበር የቆየው፤ አሁን ደግሞ መላው ዓለም እየተነጋገረበት ያለ ጉዳይ ሆኗል።
አስገራሚውን ነገር ያደረገው ፓዋን ኩማር የተባለው የ25 ዓመት ወጣት ሲሆን፤ ነገሩ የሆነው ደግሞ ከሰሞኑ በሀገሩ እየተካሄደ ባለው ብሄራዊ ምርጫ ድምጹን በሰጠበት አጋጣሚ ነው። ኩማር በምርጫው ድምጹን ሊሰጥ የፈለገው (SP-BSP-RLD) የተባለውን ፓርቲ ለወከሉት ዮገሽ ሻራማ ለተባሉ እጩ ነበር። ነገር ግን የምርጫ ምልክቶቹ ስላደናገሩት ላሰበው ሳይሆን (BSP) ፓርቲን ለወከሉት ባሁጃን ሳማጅ ይሁንታውን ይሰጣል። ይህ ስህተትም የእግር እሳት ሆኖ ቢያንገበግበው በራሱ ፈረደ፤ እናማ ድምጹን የሰጠበትን አመልካች ጣቱን መጥረቢያ በመሰለ መሳሪያ ቆርጦ ጣለው።
ጉዳዩን ሲያስረዳም «መምረጥ የፈለኩት የዝሆንን ምልክት ነበር፤ ግን በስህተት የአበባው የምርጫ ምልክትን ነካሁት። ከዚያማ ወደ ቤቴ ሄጄ ስህተት ፈጻሚውን ጣት አስወገድኩት» ብሏል። ወንድሙ ኬይላሽ ቻንድራም «ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጽ ለመስጠት በመቻሉ እጅግ ደስተኛ ሆኖ ነበር። ስህተት እንደፈጸመ ሲያውቅ ግን በመጨነቁ ጣቱ ሊቆርጥ ችሏል። ሁሌም አመልካች ጣቱን ሲያይ ንዴት ይሰማዋል» ሲል ተጨማሪ አስተያየቱን ሰጥቷል። ችግሩን ያባሰው ደግሞ በምርጫው ላይ መራጮች በድጋሚ ድምጽ እንዳይሰጡ በሚል እሳቤ በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ በመካሄዱ ድምጹ በመቅጽበት ነው የሚመዘገበው። ኦዲቲ ሴንትራል በድረ-ገጹ ባስነበበው በዚህ ታሪክ ላይም ኩማር ጠቋሚ ጣቱን በጨርቅ እንደጠቀለለ የሚያሳየውን ምስልም ለጥፏል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2011
ብርሃን ፈይሳ