በትግራይ ክልል የስፖርት እንቅስቃሴዎችን ወደ ቀድሞው ለመመለስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተጠቁሟል። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የስፖርት ኮሚሽን በክልሉ ስፖርቱን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ በመመለስ ውድድሮችን ዳግም ለማስጀመር ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።
በትግራይ ክልል በጦርነት ምክንያት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ተቋርጠው የቆዩ ሲሆን ክልሉ ከተለያዩ ውድድሮች ርቆ መቆየቱ ይታወቃል። አሁን ግን በተፈጠረው ሰላም ቆሞ የነበረው የስፖርት እንቅስቃሴ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል።
ክልሉ በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ የራሱ የሆነ ድርሻ ያለው መሆኑን ያስታወሱት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የስፖርት ኮሚሽን ኮምሽነር አቶ ተክላይ ፍቃዱ፣ በጦርነቱ ምክንያት በክልሉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ከመቋረጣቸው በፊት በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ሰፊ ተሳትፎ ይደረግ እንደነበር ይናገራሉ።
ክልሉ በስፋት ከሚሳተፍባቸው የስፖርት ዓይነቶች መካከል እግር ኳስ፣ አትሌቲክስና ብስክሌት ዋንኞቹ ናቸው። እነዚህን ወደ ተለመደው እቅስቃሴያቸው ለመመለስም የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ሥራዎች መጀመሩን አቶ ተክላይ ጠቁመዋል።
ከጥቂት አመታት በፊት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማንሳት ከቻለው መቐለ ሰባ እንደርታ ጀምሮ እንደ ሽሬ እንደሥላሴ፣ ውልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና ሌሎች በከፍተኛ ሊግና በክልል ክለቦች ቻምፒዮና የሚሳተፉ ክለቦች በጦርነቱ ሳቢያ ከውድድር ርቀው ቆይተዋል።
በተለይም በትልቁ የፕሪሚየር ሊግ ውድድር በመሳተፍ ላይ የነበሩት ሦስቱ የክልሉ ክለቦች መቐለ ሰባ እንደርታ፣ሽሬ እንደሥላሴና ውልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ2016 ወደ ውድድር እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አቶ ተክላይ አስረድተዋል። ክለቦቹ ወደ ውድድር እንዲመለሱ ውሳኔው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቢሆንም የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ክለቦቹን በቀጣይ ዓመት ወደ ውድድር የመመለስ ሃሳብ እንዳለውም አክለዋል።
ክለቦቹ ከዚህ በፊት የነበሩበትን ደረጃና የደረሰውን ውድመት አጥንተው መጨረሳቸውን የጠቀሱት አቶ ተክላይ፣ ክለቦቹ እንዴት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ይመለሱ የሚለው ጥያቄ መነሳቱንም ጠቅሰዋል። በክልሉ አሁን ባለው ሁኔታ መሠረተ ልማቶች መውደማቸውና ኳስ ተጫዋቾች ከመደበኛ የስፖርት እንቅስቃሴ በመውጣታቸው እንዴት ወደ እንቅስቃሴ ይመለሱ በሚለው ጉዳይ ላይ ከብሔራዊ ስፖርት ፌዴሬሽኖች ጋር ውይይቶች እየተደረጉ እንደሆነም ተጠቁሟል።
በጦርነቱ ከደረሰው ጉዳት አንጻር ክለቦችን ወደ ውድድር ለመመለስ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ስለሆነ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ የገለፁት አቶ ተክላይ፣ በዚህም መሠረት ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ጋር እንዴት እናስጀመር በሚለው ውይይት ለማድረግ እቅድ መኖሩን ይጠቁማሉ።
እንደ አቶ ተክላይ ገለፃ፣ በአትሌቲክሱም ወደ እንቅስቃሴ ለመመለስ ስፖርት ኮሚሽኑ ጥረት በማድረግ ላይ ነው። በክልሉ የሚገኙ የማሰልጠኛ ማዕከላት ላይ ጉዳት ከመድረሱም በተጨማሪ ሰልጣኞች መበታተናቸው እንዲሁም በዕድሜ ምክንያት እንደ አዲስ ምልመላ ማድረግም ያስፈልጋል። ‹‹የማሰልጠኛ ማዕከላትን ዳግም እንቅስቃሴ ለማስጀመር ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ከዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ድጋፍ ያስፈልጋል›› ሲሉም ተናግረዋል።
የክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በመጪው ግንቦት መጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤውን በማድረግ የተጓደሉ የሥራ አስፈጻሚ አባላትን እንዴት መሟላት እንዳለባቸው ለመወሰን እቅድ እንዳለም ታውቋል።
ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ተክላይ፣ አትሌቲክሱን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ለማስገባት ጥረቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በዚህም ክልሉ በ52ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቻምፒዮና የመሳተፍ ፍላጎት እንዳለ ገልፀዋል። ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ያለውን ነገር ተመልክቶ መልስ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
ሌላኛው ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ለመመለስ ጥረት የሚደረግበት የብስክሌት ስፖርት ሲሆን፣ ብስክሌት በክልሉ በርካታ ተሰጦ ያለበትና ስመጥር ስፖርተኞችን ማፍራት የቻለ ነው። የብስክሌት ስፖርትን ዳግም ወደ እንቅስቃሴ ለማስገባት በፊት ያለበት ደረጃና የደረሰውን ጉዳት በኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ጥናቶች ተጠንቶ መጠናቀቃቸው ተጠቁሟል።
በንብረት፣ የሰው ኃይልና ሌሎች ቆጠራና ልየታ መደረጉንና ውጤቱ ወደ ፊት እንደሚገለጽም ኃላፊው አስረድተዋል። ስፖርቱን ባለው ሀብት ወደ እንቅስቃሴ ለማስገባት ከኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ጋር መስማማታቸውንም አክለዋል።
አቶ ተክላይ ከደረሰው ጉዳት አኳያ የተወሰነ ድጋፍን በማድረግ ብቻ ስፖርቱን ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መመለስ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰው፣ የክልሉን ስፖርት ለማነቃቃት ‹‹ከጎናችሁ ነን›› በማለት ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
በተለይም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቀድሞ ክልሉን ስለጎበኘና ጉዳቱን ተመልክቶ ድጋፎችን ስላደረገ ሊመሰገን እንደሚገባው ተናግረዋል። ሁሉም የስፖርት አካላት ቦታው ድረስ በመምጣትም የደረሱ ጉዳቶችን ተመልክቶ ስፖርቱ በቶሎ ወደ እንቅስቃሴ እንዲገባ የድርሻቸውን እንዲወጡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም