በእንስሳት ሀብቷ ከፍተኛ አቅም እንዳላት የሚነገርላት ኢትዮጵያ ሀብቷን በአግባቡ መጠቀም አለመቻሏም እንዲሁ በስፋት ይገለጻል። ከእንስሳት ሀብቷ የምታገኘውን ስጋና የእርድ ተረፈ ምርቶች ወደ ውጭ ገበያ በመላክ በሚሊዮኖች ዶላሮች የሚቆጠር ገቢ እያገኘች ብትሆንም፣ ካላት እምቅ የእንስሳት ሀብት አኳያ ሲታይ ገቢው ዝቅተኛ የሚባል መሆኑ ይገለጻል።
አገሪቱ ቀደም ሲል ለውጭ ገበያ ከሚቀርቡ የግብርና ምርቶች አኳያ ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ታገኝ የነበረው ጥሬ ቆዳ ለውጭ ገበያ በማቅረብ እንደነበረ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህን ገቢ ለማሳደግ በጥሬ ቆዳ ላይ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ማቅረብ ውስጥ ተገብቶም ነበር።
በሁለቱም የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመኖች በቆዳው ላይ በስፋት በመሥራት ከቆዳው ዘርፍ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ቢታቀድም እቅዱ ግን አልተሳካም። ከዚህ ይልቅ የጥሬ ቆዳ ዋጋ እየቀነሰ መጥቶ ቆዳ ገዥ እያጣ እንደ ዋዛ እየተጣለ ይገኛል።
በእሴት ሰንሰለት ውስጥ በተለያየ ዘርፍ ሰፊ ቁጥር ያለውን የሰው ኃይል በማሳተፍ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ የሚነገርለት የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ወቅት ትኩረት እያገኘ መሆኑ ይነገራል።
ሰሞኑን ለ13ኛ ጊዜ የመላው አፍሪካ ዓለም አቀፍ የቆዳ ንግድ ትርዒት በሚሊኒየም አዳራሽ ለሦስት ቀናት ተካሂዷል። በቆዳ ዘርፍ የተሰማሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው አንጋፋና አዳዲስ ድርጅቶችም በንግድ ትርዒቱ የተሳተፉ ሲሆን፤ የንግድ ትርኢቱ ፋይዳ ብዙ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
በአንበሳ ጫማ ፋብሪካ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አጠቃላይ የአንበሳ ጫማ መደብሮች ኃላፊ አቶ ቅዱስ በላይ ፋብሪካው በቆዳ ምርቱ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ጠቅሰው፣ እንዲህ ያሉ የግንድ ትርዒቶች የገበያ ትስስር ለመፍጠርና አገርን ለማስተዋወቅ እንደሚጠቅሙ ይገልጻሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ አንበሳ ጫማ ፋብሪካ ጫማ፣ ቦርሳ፣ ቀበቶ፣ የመከላከያ ጓንትና የተለያዩ የቆዳ ውጤቶችን እያመረተ ለገበያ ያቀርባል። ከዚህ ቀደም ቆዳውን ከተለያዩ ቆዳ አቅራቢ ድርጅቶች በመግዛት የሚያመርተው ፋብሪካው፣ በአሁኑ ወቅት የራሱን ቆዳ ፋብሪካ በባህርዳር አቋቁሟል። ይህም ምርቱን በስፋትና በጥራት ሳይቆራረጥ ለማምረት ያስችለዋል።
የቆዳ ኢንዱስትሪው በአገሪቱ ትልቅ አቅም እንዳለው ኃላፊው ጠቅሰው፣ ገና ብዙ ያልተሠራበትና ብዙ ሊሠራበት የሚገባ ዘርፍ መሆኑን ተናግረዋል። ለዘርፉ እድገት ማነቆ ከሆኑት መካከልም ወጥ የሆነ የገበያ ዋጋ አለመኖር እና ከቆዳ ውጪ የሆኑ የዘርፉ ግብዓቶች ከውጭ የሚመጡ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ቅዱስ፤ ለኢንዱስትሪው በግብአትነት በዋናነት የሚያገለግለው ቆዳ ብቻ በአገር ውስጥ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
ከውጭ የሚመጡትን የተቀሩት ግብዓቶች ማግኘት ፈተና መሆኑን አቶ ቅዱስ ይገልጻሉ። ይህንንም አብነት ጠቅሰው ሲያብራሩ አብዛኛዎቹ የአንበሳ ጫማ ሶሎች እና የተለያዩ ኬሚካሎች ከውጭ አገር የሚመጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህም አገሪቷ ካለባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ የምርቶቹን ዋጋ ከፍ ያደርገዋል ብለዋል። እነዚህና ተያያዥ ምክንያቶች የቆዳ ውጤቶች ወጥ የሆነ ዋጋ እንዳይኖራቸው አድርገዋል ሲሉም ገልጸው፣ ይህም ገበያው እንዲቀዛቀዝ ማድረጉን ነው የተናገሩት።
ያም ቢሆን ግን የአገር ውስጥ ቆዳ በውጭው ዓለም እጅግ ተፈላጊ በመሆኑ ፋብሪካው የተለያዩ የቆዳ ምርቶችን በማምረት ለውጭ ገበያ እያቀረበ እንደሆነ ይገልጻሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ የአንበሳ ጫማ ፋብሪካ አብዛኛው ምርት ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ነው፤ ምርቶቹም ሦስት ዓይነት ሲሆኑ፣ እነሱም ከፍተኛ፣ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ጭምር ተደራሽ መሆን የሚችሉ ናቸው።
የውጭ ገበያ መዳረሻቸውም በስፋት ማዳጋስካር ነው፤ ፋብሪካው ምርቶቹን በቀጥታ ወደ ማዳጋስካር በስፋት ኤክስፖርት ቢያደርግም፣ የማዳጋስካር ገዢዎች ምርቶቹን ወደ አሜሪካና ሌሎች አገራት ይልኳቸዋል። ካናዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቡሩንዲና ሩዋንዳ ምርቶቹ የሚላኩባቸው ሌሎች አገሮች ናቸው።
መድረኩ የገበያ ትስስር መፍጠር ዋና ዓላማው መሆኑን አቶ ቅዱስ ጠቅሰው፣ በዚህም በንግድ ትርዒቱ ተሳታፊ ከሆኑ የውጭ አገር ገዢዎች ጋር የመተዋወቅና የገበያ ትስስር የመፍጠር አጋጣሚ እንደሚፈጥር ገልጸዋል። ቀደም ሲል አንበሳ ጫማ በጥንካሬው እንደሚታወቅና በዲዛይን ግን ክፍተት አለበት ተብሎ እንደሚታሰብ አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ግን እጅግ በተሻሻሉ ዲዛይኖች መምጣቱን ለማስተዋወቅ እንደሚጠቅም ይናገራሉ።
ጥራት፣ ምቾትና ጥንካሬን በመያዝ ከውጭ ገበያ በተጨማሪ በአገር ውስጥም የአንበሳ ጫማን የዲዛይን መሻሻል ተከትሎ ምርቶቹ በስፋት ወደ ገበያው እየገቡ መሆናቸውን በማስተዋወቅ ሰፊ የገበያ ትስስር ለመፍጠር የንግድ ትርኢቱ እንደሚረዳም ተናግረዋል።
አንበሳ ጫማ የዲዛይን መሻሻል ለማምጣትና ገበያው ውስጥ ለመቆየት የተለያዩ የገበያ ጥናቶችን ማድረጉን የተጠቀሱት አቶ ቅዱስ፤ ከዚህ ቀደም ማንኛውንም ዲዛይን በፋብሪካው በማዘጋጀት ጫማውን ሠርቶ ወደ ገበያ ማውጣትና የገበያውን ሁኔታ እየተመለከቱ መልሶ የማምረትና መሸጥ አሠራርን ይከተል እንደነበር ያስታውሳሉ። አሁን የገበያ ጥናት በማድረግና ያለውን ክፍተት በማየት፣ ከደንበኞች አስተያየት በመሰብሰብ በደንበኞች ፍላጎት መሠረት እያመረተ ለገበያ እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል።
አንበሳ ጫማ በውጭ ገበያ እጅግ ተፈላጊ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ቅዱስ፤ ተመራጭ የሚያደርገውም የመጀመሪያው የምርቶቹ ጥራትና ጥንካሬ መሆኑን ይገልጻሉ። አሁን ላይ ደግሞ ምርቶቹ በዲዛይንም ተመራጭ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል። በተለይም ኤክስፖርት የሚደረጉ ምርቶች ገዢዎች በሚሰጡት ዲዛይን መሠረት የሚመረቱ በመሆናቸው ፋብሪካውን ተመራጭና ተወዳጅ እንዲሆን አስችለውታል ይላሉ።
ሌላው ደንበኞች በሚፈልጉት ጊዜ አንዳንዴም ከተቀመጠው ጊዜ ቀደም በማለት ምርቶቹን ማስረከብ መቻሉ በኤክስፖርት ገበያ ውስጥ በስፋት መግባት እንዳስቻለው አመልክተዋል። አንበሳ ጫማ በከፍተኛ ካፒታል የሚንቀሳቀስና በአገሪቱ ከሚገኙ ጫማ ፋብሪካዎች መካከል ትልቁ የጫማ ፋብሪካ መሆኑ ይታወቃል።
አምሳለና ሳምራዊት የቆዳ ውጤቶች አምራች ድርጅትን ወክለው ያገኘናቸው ወይዘሮ አምሳለ ታደሰ የተለያዩ የቆዳ ውጤቶችን ይዘው በንግድ ትርዒቱ ላይ ለማስተዋወቅ ቀርበዋል። የንግድ ትርዒቱ ለዘርፉ መነቃቃት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል፤ ኢንዱስትሪውን ከፍ ማድረግም ያስችላል ሲሉ ወይዘሮ አምሳለ ይናገራሉ። አጠቃላይ የቆዳ ውጤቶችን ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም በማስተዋወቅ ብዙ መሥራት እንደሚቻል ጠቅሰው፣ የንግድ ትርዒቱ ልምድ ከመለዋወጥ ባለፈ የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሚያስችልም ነው የተናገሩት።
የአገሪቱ ቆዳ በውጭው ዓለም እጅግ ተፈላጊ እንደመሆኑ ይህን ተፈጥሮ የሰጠንን ቆዳ በቴክኖሎጂ ደግፎ አገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ውጤት ማግኘት እንድትችል መሥራት ከሚመለከታቸው ሁሉ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል። የዘመን አሞር የቆዳ ውጤቶች ኩባንያ ዲዛይነር፣ መሥራችና ባለቤት ዘመን አሞር እንደምትለው፤ ኩባንያው በዓለም ገበያ እጅግ ተወዳጅና ተመራጭ በሆነው የኢትዮጵያ ‹‹ሃይላንድ ሺፕ ስኪን» ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ትናገራለች።
ዘመን እንዳለችው፤ በደጋማ አካባቢና ከፍታ ቦታ የሚገኙ በጎች ብርዱን ለመከላከል በተፈጥሮ እግዚአብሔር የሰጣቸው ጸጋ አለ። የበጎቹ ቆዳ በተለየ መንገድ ከጨርቅ የሳሳ ሆኖ ነገር ግን እጅግ በጣም ጠንካራ ነው። በዚሁ ተፈጥሯቸው ምክንያትም ቆዳቸው በውጭ ገበያ እጅግ ተፈላጊና ተመራጭ ነው። ነገ ደግሞ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ይበልጥ ከፍ ማድረግ የሚችል የቆዳ ዓይነት ነው ስትል ዘመን አብራርታለች።
የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበርም ይህንን በዓይነቱ የተለየ የቆዳ ዓይነት በተለየ መንገድ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ጊዜ ወስዶ እየሠራበት መሆኑን ተናግራለች። ለአብነትም በአውሮፓ አገራት ይህ ቆዳ እንዲተዋወቅ እየተደረገ መሆኑን ዘመን ጠቅሳ፣ ወደፊት ትልቅ ተስፋ ያለውና ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ የሚችል የቆዳ ዓይነት መሆኑን አስታውቃለች። ኩባንያው ቆዳ መክበድ የለበትም ብሎ እንደሚያምን ትገልጻለች። ከቆዳው ልስላሴ የተነሳ ምርቶቹ ለማምረት እጅግ ፈታኝና አድካሚ ቢሆኑም፣ ውጤቱ ግን እጅግ ውብና ማራኪ ነው ትላለች።
እንዲህ ዓይነት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶች መዘጋጀታቸውም በዋናነት የገበያ ትስስር ለመፍጠር ያስችላል ያለችው ዘመን፤ በተለይም ኢትዮጵያ አሁን ላይ ለጀመረችው ነፃ የንግድ ቀጣና ተወዳዳሪ ሆኖ ዕድሉን ለመጠቀም ትልቅ እገዛ ማድረግ እንደሚችል ነው ያስረዳችው። በነፃ የንግድ ቀጣናው ተሳታፊ ለመሆን እንደ አገር ምን ደረጃ ላይ እንደምንገኝ የማየት አጋጣሚም የሚፈጥር ትልቅ ሁነት መሆኑን ተናግራለች። ከተለያዩ አፍሪካ አገራት የመጡ ገዢዎች በንግድ ትርዒቱ በቀረቡ የቆዳ ውጤቶች እጅግ ሲደሰቱና ሲገረሙ እንደነበር ያስተዋለችው ዘመን፤ ለማሳያ ያቀረበቻቸውን ምርቶችን ለመግዛት ፍላጎት እንዳሳዩ ገልጻለች።
የቆዳ ምርቶቿን ወደ አሜሪካና ካናዳ ኤክስፖርት በማድረግ እንደምትሸጥ ጠቅሳ፣ በቀጣይ ግን በነፃ ንግድ ቀጣናው ለመሳተፍ ከፍተኛ ጉጉት እንዳደረባትም ተናግራለች። በርቀት ከሚገኙት ከአሜሪካና ከካናዳ ገበያ ይልቅ እንደ ኬንያ ባሉ ጎረቤት አገራት መገበያየት መቻልና የንግድ ትስስር መፍጠር ጠቀሜታው የጎላ ነው ብላለች። ከዚህ ቀደም አፍሪካ ውስጥ ያልነበረውን ነፃ የንግድ ቀጣና በመጠቀም ለኢትዮጵያ ቅርብ በሆኑ የአፍሪካ አገራት ተጉዞ የንግድ ትስስር መፍጠር ‹‹ኬንያ ለቁርስ ሄዶ፣ ለእራት ኢትዮጵያ እንደመመለስ›› ነው በማለት በነፃ የንግድ ቀጣናው ያላትን ትልቅ ተስፋ ገልጻለች።
የመላው አፍሪካ ዓለም አቀፍ የቆዳ ንግድ ትርዒት እስከአሁን ለ12 ጊዜ መካሄዱን ያስታወሱት የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ዋና ጸሐፊ አቶ ሰለሞን ጌቱ፣ ዓለም አቀፍ በሆኑ ተግዳሮቶች ከሁለትና ሦስት ዓመታት ወዲህ ዘርፉ የገበያ መረበሽና የመቀዛቀዝ አዝማሚያ ታይቶበታል ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤13ኛው የመላው አፍሪካ የቆዳ ንግድ ትርዒት መዘጋጀቱ በተከታታይ ጊዜ ከታየበት የመቀዛቀዝና የገበያ መረበሽ ለማውጣትና እንዲነቃቃ ለማድረግ ይጠቅማል። ዘርፉ የመልማትና የማደግ ሰፊ ዕድል ያለው ነው። ይህም ማለት ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ሀብት በማፍራት፣ እንዲሁም በአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ተሳታፊ በማድረግ ለአገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችል ዘርፍ ነው።
የንግድ ትርዒቱም ይህን ትልቅ አቅም ያለው፣ ነገር ግን ብዙ ጥቅም ላይ ያልዋለውን ሀብት ለመጠቀምና ለማነቃቃት የተዘጋጀ ነው ያሉት ዋና ጸሐፊው፣ በዘርፉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተዋናዮች ስለመኖራቸው ይናገራሉ። ከእርድ በኋላ ቆዳን ሰብስበው የሚያቀርቡ፣ የተሰበሰበውን ቆዳ አልፍተው የሚያለሰልሱ የቆዳ ፋብሪካዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ ይህን ቆዳ ተረክበው ጫማ፣ ቦርሳ፣ ቀበቶና ሌሎች የቆዳ ውጤቶችን የሚያመርቱ አምራቾች በርካቶች መሆናቸውን አመልክተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በሺዎች የሚቆጠሩ አምራቾችም ወደ ዘርፉ መጥተዋል ነው የሚሉት። ይህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዋጋ እያጣ የመጣው የጥሬ ቆዳ ምርት ፈላጊ አንዲያገኝ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
ይህ ውጤት የመጣውም ኢትዮጵያ የአገር በቀል ኢኮኖሚን መሠረት በማድረግ ባላት ጸጋ መሥራት እንድትችል መደረጉ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሌላው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናን ወደ ተግባር ማስገባት መቻሏ ነው ይላሉ። በመሆኑም ኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪው የኢኮኖሚ ድርሻ እንዲያድግ ትልቅ አቅጣጫ ይዛ እየሠራች መሆኑ ለዘርፉ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም ለዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ እያረከተ መሆኑን አቶ ሰለሞን ጠቅሰዋል። የተማሪዎች ጫማና ቦርሳዎችን በአገር ውስጥ አምራቾች ማምረት መጀመሩ የቆዳ ኢንዱስትሪውን በእጅጉ እያነቃቃ እንደሆነ ተናግረው፣ ለዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሮጀክት ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከስድስት መቶ ሺ በላይ ጫማዎችን ማምረት መቻሉ ተ ጠቃሽ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህ ወቅትም ተዘግተው የነበሩ ትናንሽ የሚባሉ ኢንዱስትሪዎች ሁሉ ተከፍተው ትስስር መፍጠር እንደቻሉና ዘርፉም እንደተነቃቃ ነው አቶ ሰለሞን የተናገሩት። በቀጣይም በተማሪዎች ጫማ ላይ ብቻ የተመሠረተው ዕቅድ ከሰባት መቶ ሰባ ሺ በላይ አዲስ የሥራ ዕድል የሚፈጠር ይሆናል ሲሉም ጠቁመዋል። ስለዚህ ቆዳ ብዙ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ አይጣልም፤ ተኪ ምርትን በማምረት ከውጭ የሚገባውን ማስቀረት ይቻላል። ይህም ለኢኮኖሚው ዕድገት የሚኖረው አበርክቶ የጎላ ነው ብለዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም