/ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ « ጦርነት ይብቃ ሰላምን እናጽና» በሚል የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በሂደቱ አስተዋጽዖ ላደረጉ ሁሉ የእውቅና እና ምስጋና መርሐ ግብር ላይ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል/
የተከበሩ ሙሳ ፋኪ መሃመት የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር፤ የተከበሩ ኦባሳንጆ የዚህ የሰላም ሂደት ሰብሳቢና ልዩ ሚና የተጫወቱ አባት፤ የተከበሩ ኡሁሩ ኬኒያታ የቀድሞ የኬኒያ ፕሬዚዳንት፤ የተከበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ኡማላንቦ፤ የተከበሩ የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ፓንዶር፣ የተከበሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፤ የተከበሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ የተከበሩ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት፤ የተከበሩ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፤ የተከበሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በኢፌዴሪ ወገን ይህን የሰላም ቡድን የመሩ ሽልማታቸውን በጓዳ የተቀበሉ አቶ ደመቀ መኮንን፤ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፤ የተከበራችሁ የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች፤ በተለየ መንገድ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳና ከትግራይ የመጣችሁ ልዑካን፤ የሀገር ሽማግሌዎች፤ የእምነት አባቶች፤ በዚህ ስፍራ የተገኛችሁ ታዳሚዎች፤ ፈጣሪ እንኳን ይህቺን ቀን በጋራ አሳየን፡ እንኳን ደስ አላችሁ ልላችሁ እወዳለሁ። እንደዚህ ያለውን ድንቅ ቀን እንዲሁ አቅልሎ መቀበሉ ተገቢ አይደለም። ካለፍንበት መከራ አንጻር ይህንን ቀን የሰጠን፤ ይህንን ቀን እንድናይ ያደረገንን ፈጣሪ መላው ኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያመሰግን ከአደራ ጭምር ላሳስብ እወዳለሁ።
ጠብ አቁሞ ሰላም ለመፍጠር ፤በቂ ያልሆነ ምክንያት፤ ትክክለኛ ያልሆነ ጊዜ የለም። ሰላም ምክንያት አይፈልግም። ሰላም የተለየ ጊዜም አይፈልግም። በዚህም ምክንያት ዛሬ እየሆነ ያለው የሰላም መቋጫ የምስጋናና የአዲስ ምዕራፍ መጀመሪያ ማብሰሪያ ዕለት ምክንያትም የተገደበ ጊዜ ሳይሆን ዛሬውኑ መሆን ያለበት እንደሆነ ይሰማኛል።
ጥላቻ ያፈርሳል፣ ያናቁራል፣ ያገፋፋል። ፍቅር ይገነባል፣ ያሳስባል፣ ያስቃል። ጦርነት ያወድማል፣ ይገላል፣ ያፈርሳል። ሰላም ያለማል፣ ያበለጽጋል፣ ወጥቶ መግባትን በቀለለ መንገድ እንዲቻል ያደርጋል። ጦርነት ጨለማ ነው። ጦርነት ክፉ ነው፡፡
ከአፍ የሚወጣው፤ ከአፈሙዝ የሚወጣው ውስጥንና ሥጋን የሚገድል ነው። ሰላም ብርሃን ነው። ሰላም የነገር ሁሉ መጀመሪያ ነው። ስለሆነም ለዚህ ሰላም ቀን እንድንበቃ ያደረጋችሁ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ወዳጅ ሀገራት፣ ኢትዮጵያ ከነበረችበት ጨለማ ወደሚገባት ብርሃን ለመሸጋገር ፈቅዳ የጀመረችበት ዕለት ስለሆነ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን በቂ የጦርነት ታሪክ አለን። የበቃና የሚነገር የሰላም ታሪክ ግን የለንም። ጦርነት በሁለት ሰላሞች መካከል የሚፈጠር ሁኔታ መሆን ሲገባው፤ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ግን ሰላም በሁለት ጦርነቶች መካከል የሚገኝ እፎይታ ብቻ ሆኗል። የረዘመ ሰላም አልፎ አልፎ ግጭት የተለመደ ቢሆንም ለእኛ ኢትዮጵያውያን ግን የበዛ የማይፈለግ ጎጂ ጦርነትና አልፎ አልፎ የሚገኝ የሰላም እፎይታ ብቻ ሆኗል ።
የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያንና ታዳሚዎች፤ ሁለት ዓመት ከመዋጋት ሃያ ዓመት መወያየት ይሻላል። ሁለት ዓመት ስንዋጋ ብዙ እናወድማለን። ብዙ እንገድላለን፤ ውስጣችን ይሞታል የመፍጠር አቅማችን ይዳከማል።ሃያ ዓመት ስንወያይ የፈለግነው የተመኘነው በአጭር ያልተከወነ ይሆን ይሆናል ነገር ግን በሂደቱ ሰው ሳንጎዳ ንብረት ሳናወድም ለመማር እድል የሚሰጥ ስለሆነ ኢትዮጵያውያን እንንቃ፡፡
በውይይት፣በምክክር ችግሮቻችንን መፍታት የሥልጣኔ ሀሁ እንደሆነ እንገንዘብ። ከምክር ይልቅ መከራ የሚመክረው ሕዝብ አንሁን። እኛ ኢትዮጵያውያን በምክክር በውይይት ችግርን መፍታት ተስኖን መከራ፣ በሚያስከፋ ሁኔታ የሚያስተምረን ሞኝ ሕዝቦች አንሁን። በዚህም ብዙ እናጣለንና።
ትናንት ብዙ አምልጦናል፤ ብዙ የተበላሹ ነገሮች አሉ። ነገር ግን ከተበላሸው ትናንት የተሻለ ነገ፤ ያማረ ነገ፤የተዋበ ነገ፤ ተስፋን፤ ለትውልድ የሚሰጥ ነገን መፍጠር እንችላለን። ትናንትናን እያሰብን ቁስል እያከክን የምንቆም ሳይሆን፤ ትናንትናን ተሻግረን የተሻለ ነገር ለመፍጠር የምንተጋ የምንሥራ እንድንሆን አደራ ልላችሁ እፈልጋለሁ፡፡
ጦርነት ማስቀረት፣ ስድብ ማስቀረት፣ መገፈፋትን ማስቀረት፤ የይቅርታ ዋንኛ ተልዕኮ ነው። እርቅ ግን ማረም ነው። ዛሬ ይቅርታና እርቅ ስለሆነ ማስቆም ብቻ ሳይሆን ወደኋላ የተበላሸውንም ማረም ይጠበቅብናል። የተሰበረን መጠገን፣ የቆሰለን ማከም፣ መብል የተቸገረን ማብላት፣ ትናንትናን የተሻለ ፍቅር ማደስና ማስቀጠል የሚያስችል መሠረት መጣል ይኖርብናል።
የተከበራችሁ ታዳሚያንና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በውጊያ የላቁ፣ በጀብዱ የደመቁ በሀገር ፍቅር ያሸበረቁ፣ ለሀገር የሚበቁ ዘወትር የነቁ ፣ኢትዮጵያን በልባቸው ያነገሱ፣ አይተኬ ሕይወታቸውን እንኳን በኢትዮጵያ የማይደራደሩ፣የበቁ የፀጥታ ኃይሎች አሉን።
በሙያቸው፣ በእውቀታቸው፣ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን እንዲጠብቁ ከአፈሙዝ ጋር የሚያያዘውን ሥራ ለእነሱ እንተውላቸው። ለነቁ፣ ለበቁ ፣ሀገር ለሚወዱ የፀጥታ ኃይሎች ዲሞፍቶር ትተን እኛ ሞፈር እናንሳ። ሁሉም ዲሞፍቶር አንሺ ከሆነ ሞፈር የሚጨብጠው እጅ ያጣል።
ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ሞፈር ነው። በርግጥ የሚጠብቋት የተማሩ የነቁ ዲሞፍቶር የጨበጡ የሚያስፈልጓት ቢሆንም ብዙዎቻችን ግን ሞፈር የምንጨብጥና ሞፈር የሚጨብጡት የምንደግፈ ብንሆን ከልመና ነጻ እንወጣለን።
ማንዴላ ”በሕይወቴ ተሸንፌ አላውቅም” ይላሉ።” በገጠሙኝ ፈተናዎች ባለፍኩባቸው ተግዳሮቶች አንዳንዴ አሸንፌለሁ ፤ብዙ ጊዜ ግን ተምሬለሁ” ይላሉ። የገጠመን ፈተና ያሸንፍንበት ብለን የምንኩራራበት ባይሆንም እንደ ኢትዮጵያውያን የተማርነበት፣ የምንማርበት የምንሻገርበት ሊሆን ይገባል ።
እጅግ በቂ የሆነ ትምህርት ያገኘንበትን የጥፋት ጊዜ ስላሳለፍን ከእንደዚህ አይነት ተግባር ተቆጥበን፣ ተምረን ልጆቻችንና የሚቀጥለው ትውልድ ያማረች ያሸበረቀች ኢትዮጵያን መውረስ እንዲችል፤ ከጥላቻ ከመገፈፋት ከመዋጋት ራቅ እንድንል በታላቅ ትህትና አደራ ልላችሁ እፈልጋለሁ፡፡
ኢትዮጵያውያን አንድ አባባል አላቸው፤ ”ሲታረቁ ከሆድ፣ ሲታጠቡ ከክንድ” ይላሉ። እኛ ስንዋጋ ከልባችን ነበር የተዋጋ ነው፤ ከዛሬ ጀምሮ ግን ከልባችን መታረቅ ይኖርብናል። ኢትዮጵያውያን በጦርነት ጀግኖች መሆናችንን ዓለም ይመሰክራል። በሰላም ጀግኖች መሆናችንን ግን ከልብ መታረቅ ብቻ ሳይሆን የተጎዳው ሁሉ ወገኔ ነው ብለን በሙሉ ልብ በአንድነት እንድንሠራ ያጎደልነውን፣ ያበላሸነውን፣ በአጠረ ጊዜ እንድንሞላ ሁላችሁንም በታላቅ ትሕትና ልጠይቃችሁ እፈልጋለሁ።
ዛሬ የመረጃ ምንጭ ብዙ ነው። ብዙ ሰዎች መረጃ ማመንጨት ይችላሉ፤ በዚህም የተነሳ ጠዋት ተገናኝታችሁ ከተስማማችሁ በኋላ ከሰዓት ሰዎች ሀሳባቸውን ይቀይራሉ።ውሳኔ መነሻው መረጃ ነው። ኢንፎርሜሽን ነው ፤ ኢንፎርሜሽን በጣም በስፋት በሚሰራጭበት በዚህ ዓለም ጠዋት ያገኛችሁት ወንድማችሁ ማታ ሌላ አቋም ሊይዝ ይችላል።
በዚህ ዓውድ ውስጥ የምንኖር ትውልዶች ልንማር የሚገባው ጉዳይ ዛሬ የሚያዋጣው መቻቻል ብቻ ነው። ምክንያቱም በየቀኑ የሚቀያየር ባሕሪ ስላለ፤ በመቻቻል፣ በመደማመጥ በመወያየት የበለጠውን የላቀውን በመመኘትና ለዚህ በመትጋት መሥራት ይኖርብናል። በተለዋዋጭ ዓለም እና በበዛ ኢንፎርሜሽን የአቋም ልዩነት ሲፈጠር ሰክኖ መወያየት ፣ መነጋገር ያስፈልጋል።
አቶ ጌታቸው ሰላሙን ያመጣነው ጀግነን ነው ብሏል። ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት አቶ ጌታቸውን የምጠይቀው ጀግኖ ወደ ባሕር ዳር እንዲሄድና ወንድሞቹን ማቀፍ እንዲችል ነው፡፡ ዶክተር ይልቃልን የምጠይቀው ጀግኖ ወደ መቀሌ እንዲሄድና ወንድሞቹን እንዲያቅፍ ነው። ሰላም እንዲሁ በቀላል የሚገኝ አይደለም። መሥራት፣ መትጋት፣ መጀገን ይፈልጋል።
የተከበረው የትግራይ ሕዝብ ከተከበረውና ከወንድሙ የአማራ ሕዝብ ጋር ጠንካራ የደም ትስስር ያለው ቢሆንም፤ በፖለቲካ ብልሽት ምክንያት የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት አቶ ጌታቸው፣ ዶክተር ይልቃል መጀገን ይጠበቅባቸዋል። አቶ አወል በዚህ አይጠረጠሩም ብዬ ነው።
ዛሬ ለኢትዮጵያ እጅግ አስደሳች ቀን ነው። ከዛ የጦርነት ነጋሪት ፉከራ፣ጥፋት ወጥተን፣ሰላም መልሶ ግንባታን የምንነጋገርበት ቀን ነው። ይህ ለእኛ ደስታ የሆነው ቀን እጅግ ለምንወደው ለደጉ፤ በቸገረን ጊዜ ሁሉ መጠጊያችን ለሆነው ኢትዮጵያን አብዝቶ ለሚወደው ለሱዳን ሕዝብ ይህችን ቀን ማየት እንዲችል ያለንን ከፍተኛ ምኞት እየገለፅኩ ወንድሜ ጄኔራል ቡርሃን እና ወንድሜ ጄኔራል አህሚቲ ከኢትዮጵያውያን ተምረው ሰክነው፣ ተነጋግረው፣ በሱዳን ያጋጠመውን ያልተገባ መገዳደል እንዲያስቆሙ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ ላቀርብላቸው እፈልጋለሁ።
ኢትዮጵያ ለወንድም ሕዝቦች ሰላም የምትመኝ ሰላም አስከባሪ የምትልክ ብቻ ሳትሆን፤ ለሱዳን 50ሺ ኩንታል ስንዴና በርከት ያሉ መድኃኒቶች ለመላክ ኢትዮጵያን ኤይድ ወደ ካርቱም ለመሄድ የተዘጋጀ መሆኑን ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ በደስታ ማብሰር እፈልጋለሁ።
የሱዳን ሕዝብ ከወንድም የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ ይፈልጋል። ኢትዮጵያውያን እንደ ድሮው ማንነታችን ተርፎን ሳይሆን ከጎደለ ማንነታችን በማካፈል ወንድም ሕዝብን ለማጽናናት ጊዜው አሁን ስለሆነ እኛ ኢትዮጵያውያን ለማስታረቅ፤ ለመርዳት፤ ከፍተኛ ዝግጁነት እንዳለን አውቀው የሱዳን አመራሮች ይሄን መሰል ፕሮግራም በካርቱም ለማዘጋጀት እንዲታደሉ ያለኝን ታላቅ ተስፋና ምኞት ልገልፅላቸው እወድዳለሁ።
በሚቀጥለው ሳምንት ሁለት ኩነቶች ይከወናሉ። አንደኛው የሁሉም ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች በፓርቲያችን ምክትል ፕሬዚዳንት እየተመሩ ወደ መቐሌ ይሄዳሉ። የሁሉም ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች መቐሌ የሚሄዱት ያነቡ ዓይኖችን ለማበስ፤ የተበላሹ፣ የፈረሱ ቦታዎችን ለመጠገን፤ ክልሎች እንደ ወንድም ሕዝቦች ካላቸው ለማጋራትና ይሄን የሰላም ጅማሮ በተግባር ለማስቀጠል ነው፡፡ በሚቀጥሉት ቀናት ወደ መቐሌ የሚደረገው ጉዞ ዛሬ የምናደርገው ንግግር የተግባር ማስጀመሪያና ወንድም የትግራይን ሕዝብ ከጎኑ መሆናችንን፤ መሆናቸውን ሁሉም ክልሎች የሚያሳዩበት ዕለት ስለሆነ ልክ እንደ ዛሬው ቀን በከፍተኛ ጉጉት የምንጠብቀው ይሆናል።
ሁለተኛው ከሸኔ ጋር የሚደረገው ድርድር ከነገ ወዲያ በታንዛንያ ይጀመራል። ይሄን ድርድር የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ አብዝቶ ይፈልገዋል። በዚህ ድርድር የሚሳተፉ ወገኖች ሁሉ የዛሬዋን ቀን እያሰቡ፤ከግጭት፤ ከጦርነት እንደማናተርፍ አውቀው ሕግና ሥርዓት ተከትለን፣ ይቅር ተባብለን ሀገራችንን በጋራ ማነፅና መገንባት እንድንችል፤ የወለጋ ሕዝብ አሁን ካለበት ስቃይ እፎይ ማለት እንዲችል ሁሉም ወገን የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ከወዲሁ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
በመጨረሻም የኛ የሰላም ሂደት እንዲሳካ ከፍተኛ እገዛ ያደረጉ የወዳጅ ሀገራት፤ የአፍሪካ ኅብረት፣ ኢጋድ እንዲሁም አንዳንድ ግለሰቦች ከሁሉ በላይ የቲፒኤልኤፍ አመራሮች፣ የብልጽግና አመራሮች መላው የትግራይ ሕዝብ፣ የአማራ ሕዝብ፣ የአፋር ሕዝብ፣ የሶማሌ ሕዝብ፣ የኦሮሚያ ሕዝብ፣ የሲዳማ ሕዝብ፣ የደቡብ፣ ሁሉም ብሔሮች፣ (ጉራጌ ስልጤ፣ወላይታ፣ ሃድያ፣ ከንባታ፣ ዳሰነች፣ ዳውሮ፣ ኮንታ) የተቀሩትን በሙሉ የጋምቤላ ሕዝብ፣ የደቡብ ምዕራብ ሕዝብ፣ የቤኒሻንጉል ሕዝብ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ላደረጋችሁት ድጋፍና ጸሎት፤ ምኞት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥትና በራሴ ስም በተለይም የኢትዮጵያ እናቶች ለነበራችሁ ጭንቀትና ጸሎት ያለኝን ከፍተኛ ምስጋናና አክብሮት በዚህ ታሪካዊ ቀን ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ።
ውድ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች፣ ኢትዮጵያ ትፀናለች፣ ኢትዮጵያ ትቀጥላለች፤ ኢትዮጵያን የሚያስቆማት ምንም ኃይል የለም፤ ኢትዮጵያን የሚያስቆማት ኃይል የኛ መጠላላት ብቻ ነው። ከዛሬው ቀን እንማር የማይወደድ ፣የማይፈለግ የኢትዮጵያ ክፍል የለም፡፡ አንዳንዶች ኢትዮጵያ ትገነጣጠላለች ወይም አንዳንዶች ይገነጠላሉ ይላሉ ፤ኢትዮጵያ አትገነጠልም ጸንታ ትቀጥላለች። ይልቁንም ለልማቷ፣ ለመጽናቷ ለአንድነቷ የሚያስፈልጋትን ፤የቀራትን ለማግኘት አብዝታ ትሠራለች።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
አመሰግናለሁ!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም