የአመለካከትና ሃሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት የዜጎች ዴሞክራሲዊ መብት አንዱ መገለጫ ነው።በኢፌዴሪ ህገመግሥት አንቀፅ 29 እንደተደነገገውም ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃገብነት ሃሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው። ይህ ነፃነት በሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጪ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በህትመት፣ በስነጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፣ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሃሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነፃነቶችን እንደሚካተትም በዚሁ አንቀፅ ላይ በዝርዝር ሰፍሯል።
ከዚህም ባሻገር በተለይ ፕሬስን በተመለከተ የቅድመ ምርመራ በማንኛውም መልኩ የተከለከለ መሆኑን እንዲሁም የህዝብን ጥቅም የሚመለከት መረጃ የማግኘት መብት እንዳለም በህገመንግሥቱ ሰፍሯል።ለዚህም የህግ ጥበቃ እንደሚደረግለት ተቀምጧል። በሌላ በኩል ሐሳብን በነፃ የመግለጽ መብት በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ነፃ የሆነና የተጠናከረ ፕሬስ ሲኖር፣ ሲጎለብትና ሲስፋፋ በመሆኑ፣ ነፃ ፕሬስ ዜጎች ሐሳባቸውን በነፃ የሚገልጹበት መድረክ ከመሆኑም በላይ የግለሰብና የህዝብ መብት እንዲከበር፣ ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲዳብር፣ እንዲሁም ዜጎች በተለያዩ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ሚዛናዊ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና በመንግሥት አመራርና አሠራር ላይ ሐሳብ እንዲያቀርቡ በማስቻል ጉልህ የሆነ ሚና እንዲጫወቱ የፕሬስ ነፃነትን ያለገደብ ተግባራዊ ማድረግ ታምኖበት ሲሠራበት ቆይቷል።
መገናኛ ብዙሃንም ይህንን ተግባራቸውን ሊያከናውኑ የሚችሉት የቅድመ ምርመራ (ሴንሰርሺፕ) እና ሌላም ተመሳሳይ ገደብ ሳይደረግባቸው በነፃና በኃላፊነት ስሜት ሊንቀሳቀሱ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ ሲፈጠርላቸው እንደሆነ በመታመኑ የፕሬስ አዋጅ ቁጥር 34/1985 ሥራ ላይ ውሏል። ከዚህ በኋላም በሃገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት በህገመንግሥቱ ለተረጋገጡ መሰረታዊ ነፃነቶችና መብቶች መከበር ዜጎች በነፃ መረጃና አስተያየትን ለመሰብሰብ፣ ለመቀበልና ለማስተላለፍ ያላቸውን መብት ሙሉ ለሙሉ ለማረጋገጥ፣ ማንኛውም ግለሰብ በመንግሥት አካላት እጅ የሚገኝ መረጃዎችን የማግኘት መብቱ እንዲከበር እና በህገመንግሥቱ የተረጋገጡት ግልጽ የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነት እሴቶች እንዲዳብሩ ለማስቻል ቀደም ሲል በሥራ ላይ የነበረው የፕሬስ አዋጅ በመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ተተክቷል።
እነዚህ የህግ ድጋፎች ሁሉ በአገሪቱ የፕሬስ ነፃነትን ለማረጋገጥና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመፍጠር ዋነኛ የዴሞክራሲ መሳሪያዎች ናቸው።ይሁን እንጂ የአገራችን መገናኛ ብዙሃን በሚጠበቀው ልክ በነፃነት ተንቀሳቅሰው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት አልቻሉም።ለዚህም በአንድ በኩል ህጉ ቢኖርም ህጉን ተግባራዊ በማድረጉ ረገድ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት ቁርጠኝነት ማነስ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የባለሙያው ከህሎት አለመዳበርና ከቀደመው ፍራቻ ባለመላቀቅ ራስን መገደብ ናቸው። በርግጥ የፕሬስ ህጉ ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ ከ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በአገራችን በርካታ የግል ፕሬሶች የተስፋፉ ቢሆንም ገበያው ላይ መቆየት አልቻሉም።በተለይ በ1997 የተደረገውን ምርጫ ተከትሎ አብዛኞቹ የግል ጋዜጦችና መፅሔቶች ከገበያ ወጥተዋል።ይህንን ተከትሎ ለብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ፈቃድ ተሰጥቶ ጥቂት የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቢቋቋሙም በሚፈለገው ደረጃ ውጤት ማምጣት አልቻሉም። አብዛኞቹ የመገናኛ ብዙሃንም ሙያዊ ስነምግባርን ጠብቆ ከመሥራት አንጻር ከተለያዩ አካላት የሙያ ትችት ይቀርብባቸዋል።
ከዚህ አንጻር በመንግሥት የሚደጎሙት የህዝብ ሚዲያዎች የመንግሥት የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ሆነዋል የሚል ትችት ሲቀርብባቸው የግሎቹ ደግሞ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንደበት ሆነዋል በሚል ሁሉም ለህዝብ ተገቢውን አገልግሎት አለመስጠታቸው ይተቻል። በሌላ በኩል በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም ዘንድ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ስትብጠለጠል ቆይታለች።ለምሳሌ መቀመጫውን ፈረንሳይ ያደረገው የዓለም አቀፉ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ከለውጡ በፊት አውጥቶ በነበረው መረጃ ኢትዮጵያ በመረጃ ነፃነት ከ180 አገራት 150ኛ ደረጃ ላይ በማስቀመጥ የሚዲያ ነፃነት ከሌላቸው አገራት አንዷ እንደሆነች አስፍሮ ነበር።ይህ መረጃ ግን ለውጡን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻል ማሳየቱን ዘግቧል።በዚህም መሰረት በዘንድሮ ዓመት ኢትዮጵያ 40 ደረጃዎችን ማሻሻሏን ይፋ አድርጓል።
በዚህ ዓመት የሚከበረው የዓለም የሚዲያ ነፃነት ቀን ጉባኤም ሚያዝያ ከ23 እስከ 25 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል። ኢትዮጵያ ይህንን ጉባኤ እንድታዘጋጅ መመረጧም አገራችን የሚዲያ ነፃነትን ለማረጋገጥ የሔደችበት ርቀት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ምን ያህል ትልቅ ዕውቅና እንደተሰጠው ማሳያ ነው። በአገራችን ለውጡን ተከትሎ በማረሚያ ቤት የነበሩ በርካታ ጋዜጠኞችና ጦማርያን ከእስር እንዲለቀቁ ተደርጓል።ከዚህም ባሻገር በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩ የሚዲያ ተቋማት ጭምር ፍረጃው ተነስቶላቸው በነፃነት ወደ አገር ገብተው በነፃነት እንዲንቀሳቀሱና እንዲሠሩ ተደርጓል።ቀደም ሲል ተዘግተው የነበሩ ጋዜጦችና መፅሔቶችም ተከፍተው ሥራ ጀምረዋል።ይህ ታላቅ ድልና የለውጡ ትሩፋት ነው። ስለሆነም ሀገራችን የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ማዘጋጀቷ ተገቢ ነው።ይገባታልም።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 21/2011