በተለያዩ የዓለም ከተሞች ከሚካሄዱ የማራቶን ውድድሮች በሚያስተናግዱት ከፍተኛ ፉክክር የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮናን ያህል ግምት ከሚሰጣቸው መካከል አንዱ የሆነው የለንደን ማራቶን ነው። የፕላቲኒየም ደረጃ ካላቸው ስድስቱ ዋና ዋና ማራቶኖች አንዱ የሆነው የለንደን ማራቶን ከትናንት በስቲያ ሲካሄድ የዓለም ሻምፒዮኖችን ጨምሮ የዓለምን ክብረወሰን የማሻሻል አቅም ያላቸው ምርጥ የርቀቱ አትሌቶች ተፎካክረውበታል። እጅግ ተጠባቂ የሆነው ይህ ውድድር የዘንድሮ አሸናፊዎች ከተጠበቀው ውጪ አዲስ ፊት ይዞ ብቅ ማለቱ አስደናቂ ክስተት ሆኗል።
በውድድሩ ለአሸናፊነት ተጠባቂ ከሆኑት ታዋቂና የማራቶን ልምድ ካላቸው አትሌቶች ይልቅ አዳዲስ አትሌቶች የተሻለ ሆነው መገኘታቸው አስገራሚው ክስተት ነበር። በሁለቱም ጾታዎች ከዚህ ቀደም ማራቶን ላይ ልምድ የሌላቸው አትሌቶች በለንደን ማራቶን ደረጃ ባሉ ሩጫዎች አሸናፊ መሆናቸው በእርግጥም አስገራሚ ነው።
በመም ውድድሮች አድናቆትን ያተረፈችው በትውልድ ኢትዮጵያዊት በዜግነት ደግሞ ሆላንዳዊት የሆነችው ሲፈን ሐሰን በሴቶች በኩል ባለድል ሆናለች። በወንዶች ደግሞ የግማሽ ማራቶን ልምድ ያለውና ማራቶንን ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ዓመት የሮጠው ኬንያዊ አትሌት ኬልቪን ኪፕተም የማራቶንን የዓለም ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ጭምር አሸናፊ ሆኗል።
የዓለም ከዋክብት አትሌቶች በተካፈሉበትና በተለይ በቅርቡ ከመም ወደ ጎዳና ሩጫዎች የተሸጋገሩ ብርቱ አትሌቶች ተሳትፏቸውን ባረጋገጡበት በዚህ ውድድር ተሳታፊ መሆን በእርግጥም አሸናፊ የሚሆነውን አትሌት ለመገመት አዳጋች ያደርገዋል። ሆኖም በወንዶች በኩል እንደነበረው ሩጫ ከሆነ ቀነኒሳ በቀለን የመሰለ ትልቅ አትሌት መሳተፉ ፉክክሩን አስቀድሞ ሊያከረውና የአሸናፊነት ቅድመ ግምቱንም ሊያስገኝለት እንደሚችል አያጠራጥርም። ሆኖም በውድድሩ የታየው እንዲሁም ከሳምንት በፊት በተከናወነው ሌላኛው ትልቁ ውድድር ቦስተን ማራቶን የተስተዋለው ሁኔታ በማራቶን ለዓመታት የዘለቀው የኃያላኑ የበላይነት ወደማብቂያው ደርሶ ይሆን የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል።
በተለይ ከመም እስከ ጎዳና የዘለቀው የሁለቱ አትሌቶች ጠንካራ ፉክክር እንደ ለንደን ያሉ ትልልቅ ማራቶኖችን በየዓመቱ ተናፋቂ ሲያደርጋቸው ቆይቷል። ማራቶንን ከአንድ ሰዓት በታች የመግባት ተደጋጋሚ ጥረት ያደረገው ኬንያዊው አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ እና በመም የረጅም ርቀት ውድድሮች የነገሰው ኢትዮጵያዊው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የሚፋለሙበት መድረክ በእርግጥም በስፖርት ቤተሰቡ አጅግ ተጠባቂ ነው።
በሰከንዶች የሚሰላው ልዩነታቸውም ይበልጥ የሚጠብበት ውድድር ሲናፈቅ የቆየ ቢሆንም፤ የአትሌቶቹ ወቅታዊ አቋም ግን ከዚህ የራቀ ሊሆን እንደሚችል አመላካች ነው። ለማሳያነትም በሳምንት ልዩነት ኪፕቾጌ በቦስተን ማራቶን ስድስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ እንዲሁም ቀነኒሳ የለንደን ማራቶንን አቋርጦ መውጣቱን ማንሳት ይቻላል።
በሴቶች በኩልም ከመምና ከግማሽ ማራቶን ውድድሮች ወጥተው ማራቶንን ከሁለት ዓመት ወዲህ የተቀላቀሉ አትሌቶች የቀደመ ብቃታቸውን ከአዲስ መንፈስ ጋር ይዘው ወደ ውድድር ገብተዋል። የለንደን ማራቶን አሸናፊዋን ሲፈን ሃሰንን ጨምሮ፣ አልማዝ አያና፣ ያለም ዘርፍ የኋላው፣ ገንዘቤ ዲባባ፣… የመሳሰሉ ብርቱ አትሌቶች ከዚህ በኋላም በጠንካራ ፉክክር በረጅሙ ርቀት ሩጫ የሚታዩ አትሌቶች ናቸው። በመም ውድድር ድንቅ አትሌቷ ጥሩነሽ ዲባባም በሳምንቱ መጨረሻ በጃፓን በተካሄደ
ግማሽ ማራቶን ውጤታማ መሆኗም ቀጣይ ማረፊያዋ ይኸው ርቀት ስለመሆኑ ጠቋሚ ነው። እንደ አጠቃላይም ከዚህ በኋላ የሚኖረው የማራቶን ሩጫዎች ድል በእነዚህ አትሌቶች ሊመዘገብ እንደሚችልና ምናልባትም አዲስ የማራቶን ምዕራፍ እየመጣ ስለመሆኑ ማሳያ ይሆናል።
ከጥቂት ወራት በኋላ በቡዳፔስት የሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለዚህ መልስ ሊሆን እንደሚችል እርግጥ ነው። በዚህ ሻምፒዮና ላይ ሃገራቸውን የሚወክሉ አትሌቶችን አሰላለፍም ከወዲሁ ለመገመት ያስችላል። በመም የሚታወቁ አትሌቶች በመሰል ሜጀር የማራቶን ውድድሮች መታየታቸው ምናልባትም በማራቶን ሊወዳደሩ ስለማቀዳቸው ፍንጭ ሊሆን ይችላል።
ባለፉት ሻምፒዮናዎች የተሻሉ የነበሩ የርቀቱ አትሌቶች ደግሞ በአዳዲስ ተፎካካሪዎች የሚፈተኑበት ጊዜ መድረሱን የሚያመላክት ይሆናል። በመልካም ወቅታዊ አቋም ላይ ያሉትና በቅርቡ ኦሊምፒክን የተቀላቀሉት እንደ ሞ ፋራህ ያሉ አትሌቶች መጪው የማራቶን ተሳትፎም በቅርቡ የሚለይም ነው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም